በአማን ነጸረ
‹‹አፍታ›› የሚለውን የጊዜ ቅጽል ለሦስት መጻሕፍቶቻቸው ተዛራፊ እንዲሆን ለምን እንደፈለጉ እንጃ! ‹‹ ከግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ጋር አንዳፍታ ቆይታ(2010)››፣ ‹‹ከግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ጋር ብዙ አፍታ ቆይታ (2012)›› እና ለዛሬ ወጋችን መነሻ የሆነው ‹‹ አንዳፍታ ላውጋችሁ›› ማዕከላቸውን ‹‹አንዳፍታ›› ያደረጉ ግሩማን መጻሕፍቶቻቸው ናቸው፡፡ በርእሶቻቸው የጊዜ ፍልስፍናቸውን ሊያሠርፁበን ፈልገው ይሆን?! አንዳፍታ እናስላስል! የሆነልንን ከቀረብን ስንለይ የ፹ ቀን መታሰቢያቸውን በሰፊ አዳራሽ ተሰባስቦ ለመዘከር ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም፡፡ ነገር ግን፡-
…ዘመድሰ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፡፡
ኢተፈልጠ ምስለ እሙ እስከ መቃብር ይወርድ፡፡
እንደተባለለት ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ ለዝክረ ፕሮፌሰር ውስጥ እግሩ እስኪላጥ በውጣ ውረድ ከደከመው አማረ በቀር ሌሎቻችን የተጠበቀብንን ያህል ሁነን ስላልተገኘን የአዳራሹ ዝክር በቀጠሮ ተላልፏል፡፡ ከአቅም በላይ ሆነ! አንድ በሬ ብቻ የሚስበው አልሆነማ ነገሩ! የታላላቆቹ ብሔራውያን ምሁራን የፕ/ር ሽብሩ ተድላ እና ፕ/ር ሺፈራው በቀለ እንዲሁም ቅንነት ባለበት ሁሉ በዚያ የማይታጣው ብሬ (ብርህኑ አድማስ) ተአምኖቸውን አላጎደሉም! ከቶ መጽናኛችን ምንድ ነው?! ፹ያቸውን ስናወጣ ከጻፏቸው መጻሕፍት አምስቱ ለዳግመ ኅትመት በቅተዋልና አደራ በል፣ ዘረ ቆርጥም ባለመሆናቸውን እንጽናናለን!
(1) ባሕረ ሐሳብ፣
(2) ከግእዝ ሥነ ጽሑፍ ጋር ብዙ አፍታ ቆይታ፣
(3) ግእዝበቀላሉ፣
(4) Ethiopian_Studies_in_Honour_ of_Amha_Asfaw፣ እና ዛሬ ለአንባብያን የቀረበው (5) በቁም ላልተዘከሩት በሀገራቸው ላይ የአዳራሽ ዝክር ለተነፈጉት ብሔራዊ ሊቅ ቀዋምያን ዝክሮቻቸው ሆነው በመቆማቸው ፈጣሪያችንን እናመሰግነዋለን!
በመጽሐፍ ላይ መጽሐፍ፡ የብርሃኑ ቀዳሚ ቃል
ብርሃኑ አድማስ ኃያል ሰው ነው! ባልተገራ የልጅ አንደበቴ በቀሊል የቀናዒነት መንፈስ ልነደቀደቅባቸው የተነሣሁባቸው ሊቅ አንደርድሮ መንበራቸው ስር ወስዶ ደፋኝ! ከፕ/ር ጌታቸው ጋር በዘለፋ ጀምሬ ምርቃት በመቀበል ቋጨሁ! ‹ምርኮ ለበረከት› እንዳለ ያ የወለጋው ሰው ‹ዘለፋ ለበረከት› ሆነልኝ! ብርሃኑ አድማስ ድልድይ ነው፡፡ ድልድዩን ስንሥለው፡- ፕ/ር ጌታቸው-ብርሃኑ-በአማን-አማረ ( #ብራና_መጻሕፍት) የሚል ሥዕል ይመጣ ይመስለኛል፡፡ መጻሕፍቶቻቸው ተቋማዊ በሆነ መልኩ እንዲታተሙ ምኞት ነበረን፡፡ ተሳካ፡፡ የፕ/ር ሽብሩ ሸከም ወረደ! አማረ እስኪመጣ የፕ/ር ጌታቸውን መጻሕፍት ተሸክመው በየሱቁ በማካፋፈል የሚላላኳቸው ፕ/ር ሽብሩ ነበሩ! ኦ ትሕትና ዘመጠነዝ ትሕትና! አትልም አንተ! ከእነዚያ መጻሕፍት ሽያጭ ፕ/ር ጌታቸው እጅ ተመልሶ የሚገባ የለም! ጻማ ድካሙን እንኳ ያልበላ ሊቅ ነበረ ጌታቸው! ብሬ ‹‹ምስኪን!›› ይላቸዋል! ከልቡ ነው! ብሬ መቅረዝ ነው! ፕ/ር ጌታቸውን ወገግ አድርጎ ያሳየን እርሱ ነው! በዚህ ኅትመት አንደኛው ፈርጥ የእርሱ ቀዳሚ ቃል ነው፡፡ የብሬን ቀዳሚ ቃል ‹‹በመጽሐፍ ላይ መጽሐፍ›› ነው የምለው፡፡ አንዳንዴ ያናድደኛል፡፡ እናም … አንዳፍታ ስናደድ፤- መጽሐፉን የታከከ ግን ደግሞ ለብቻ ተለይቶ መቆም የሚችል ጭብጥ ያነሣና ሙሽራውን የሚያስረሳ ዘናጭ ሚዜ የመሰለ ጽሑፍ -በመጽሐፍ ላይ መጽሐፍ- ያቀርባል እላለሁ፡፡ በፕ/ር ጌታቸው ላይ ይኸን ሊያደርግ ከሞከረ ወደ መስተባርር ድግምታችን መሄዳቸውን ነው! ይባረራል!
አንዳፍታን በአንዳፍታ
ሲጽፉ ለአርትዖት የሚመች ቅጂ ስለማይዙ እነ ወንደሰን ውቤ፣ እነ አማረ ላይ የነበረውን ጫና የምናውቅ እናውቀዋለን፡፡ ልጆቹ ደክመውበታል! ያም ሆኖ የግድ ስለሆኑ በወንዴ ከተጨመሩ የሁለት እጅ ጣቶችን ከማይሞሉ የኅዳግ ማስታወሻዎች በቀር የነበረው አልተቀነሰም፡፡ (1)ብሬ ‹‹ ዘመንን ያስቈጠሩበት ሊቅ›› ሲል በቀዳሚ ቃል በአዋጅ ነጋሪነት መንገዱን ከፍቶት ሊቁ ይገባሉ፡፡ (2) ትረካቸውን አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊት እኔም አስቀድሜ ‹‹ ቅኔያት ለሕያው ተቋም ጌታቸው ኃይሌ›› ስል በ2010 ዓ.ም. የቈጣጠርኩላቸው ቅኔያት (ሙሉ ቤት ነው ቅኔው) በቅኔ መምህራን ታርመው በኑዛዜያቸው መሠረት ይሸኙባቸዋል፡፡ (3) በማሳረጊያው በብሬ ጉትጎታ፣ በእኔና በመሳሰሉ የትውልዳችን አባላት ‹‹ደቂቀ እስጢፋኖስ›› መጽሐፋቸው ላይ የተካሄደውን ዐውድ የሳተ ቁንፀላ (ቁንፀላውን ብሬም በቀዳሚ ቃል ነካክቶታል) በማስመልከት ለተነሣው ጥያቄ ምላሽ እንዲሆን ያዘጋጁት ‹‹የደቂቀ እስጢፋኖስ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን›› የሚል አቋምና ንባባቸውን ገላጭ ማስታወሻ የመጽሐፉ መዝጊያ ይሆናል፡፡ (4) አዳዲስ ፎቶዎች ታክለዋል፡፡ ከለር ያልሆኑት ግን ከምንጫቸውም በብዛት ከለሩ ስላልተገኘ ነው፡፡ በኅትመት ጥራቱ ኮርቻለሁ፡፡ መጽሐፉ በቁም ሳሉ በዚህ ደረጃ ወጥቶ ቢያዩት ከቁም ተዝካር ይቈጠር ነበረ፡፡ ቢሆንም ወጋገኑን የነገ መጠሪያ ዝክራቸውን በትውልዳችን በኩል ዐይተውታልና ደስ ይለናል፤ እንጽናናለን፡፡
የመጽሐፉ አስኳል
የአንድ ከሸንኮራ በባዶ እግሩ መጥቶ በአዲስ አበባ መቃብር ቤት ይኖር የነበረ ጉብል በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ በግብጽ ከፕቲክ ቸርችር፣ በጀርመን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በቤተ ክህነት የመማክርት ጉባኤ፣ በሀገረ እንግሊዝ አድርጎ የኋይት ሐውስ ፕሬዝዳንታዊ ሽልማት ድርስ የደረሰበት በአነጋገር ቀለል ብሎ የቀረበ የተጋድሎ ጎዳና ነው፡፡ በዚያ ጎዳና፤- ቤተ ክርስቲያን፣ ሀገር፣ መንግሥታት፣ ቤተሰብ፣ እጅግ የምትወደድ ሚስት፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ፖለቲካ፣ ድርሳናት፣ ነገረ ሃይማኖት፣ ነገረ ተቋማት፣ … መንገዱ ሲያስቡት የሚከብድ ግን ደግሞ ሲያነቡት ሳይጎረብጥ ቀለል ሰተት አድርጎ የሚወስድ ነው፡፡ በእርግጥ መጽሐፉ የተቋም መጽሐፍ ነው! ጌታቸው ተቋም ነበረ! ስንል አንደበታችንን አያደናቅፍንም! የገባነውን ቃል አላጠፍንምና የሙታንን ከሕያዋን የተሰናሰለ ኅብረተ ምዕመናን (communion of saints) የምናምን ልጆቹ ዛሬ እርሱም በዐፀደ ነፍስ ደስ እንደሚለው እናምናለን!
—
ጸሎታ ለማርያም ወስእለታለነፍሰ ሣህለ ማርያም ያድኅ እመዐተ ወልዳ፡፡