>

እ ን ዳ ይ ደ ገ ም....!!!  (አሳፍ ሀይሉ)

እ ን ዳ ይ ደ ገ ም….!!! 

አሳፍ ሀይሉ


በአዲስ አበባ ከተማ፡፡ ትንሽ ይቀረኛል፡፡ ለመስቀል (ለአብዮት) አደባባይ፡፡ የድሮው ኢ.ሠ.ማ.ኮ. ህንጻ ከአስፋልቱ ማዶ ይታየኛል፡፡ የእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያንን ተሳለምኩ፡፡ የባምቢስን መስመር ትቼ፣ የቦሌውንም መስመር ትቼ፣ ወደ አንድ ጎን ዘንበል ወዳለ ህንፃ አመራሁ፡፡ ደረስኩ።

ዶ/ር ፋሲል ወልደጊዮርጊስ የሚባል የሃገርቤት ባህላዊ የህንፃ አሰራር ንድፎችን ያጠና ኢትዮጵያዊ አርኪቴክት ነው ያነፀው – ያን ያዘነበለ ህንፃ፡፡ ምናልባት ያዘነበሉ የገጠር የደሃ ጎጆዎች በሃሳቡ እየመጡበት ይሆን ህንፃውን ያለዕድሜው ያዘመመው? አልኩ፡፡

እና ደቂቁን እስጢፋኖስ በጀርባዬ ትቼ.. ፊትለፊት ወደሚታየኝ የተንሻፈፈ የሙታን ታዛ ገባሁ፡፡ ወደ “የቀይሽብር ሠማዕታት ሙዚየም”፡፡

“ቀይሽብር”፡፡ ሥሙ ራሱ ሽብር ይለቅብሃል፡፡ ‹‹ነጭሽብር በቀይሽብር ይመታል!›› የሚሉ የ60ዎቹ መፈክሮች፡፡ ‹‹ቀይ ሽብር ይፋፋምብኝ!›› የሚል ወረቀት በላያቸው የለጠፉ ወጣቶች፡፡ ጎመንማ ከለር ያላቸው የፖሊስ ዋዞች፡፡ ኩምቢ ቮልሶች፡፡ የሞተር ጎርምርምታዎች፡፡ ጩኸቶች፡፡

የ”ወ.ፖ.” (ወታደራዊ ፖሊስ) ብረት-ቆብ ያጠለቁ..፡፡ ኡዚ እና ክላሽንኮቭ ያነገቡ..፡፡ የአብዮታዊ ሠራዊት ወታደሮች፡፡ ህዝባዊ ሚላሻዎች። አብዮት ጠባቂዎች..፡፡ መሳሪያዎቻቸውን ደግነው..፡፡ መስቀል አደባባይና እስጢፋኖስ ላይ። አቧራ እያጨሱ፡፡ በህዝቡ ላይ ሲተምሙ፡፡

ይህን የመሠሉ።.. እና ሌሎችም አጫጭር የሙታንና ሌዋታን ድምጾች። እና ትዕይንቶች፡፡ ያቃጭሉብሃል በጆሮህ፡፡ ይህ ሁሉ ይታሰብሃል – ወደ አንድ ወገን ወዳዘመመው ቤት – ወደ ቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም – ስትገባ፡፡

ልክ ስትገባ.. በግራህ በኩል ዕይታህ ውስጥ ሰተት የሚልብህ የመጀመሪያው “ዲስፕሌይ”.. በመስታወት ውስጥ በክብር (እና ለጉድ) የተቀመጠ ጥንድ የወታደር ከስክስ ጫማ ነው፡፡ ከስክሱ በደንብ የሠራ፣ ያገለገለ ከስክስ ነው፡፡ <ስንቱን ሲከሰክስ የነበረ፤ ግን ጊዜ የከሰከሰው ከስክስ>፡፡ ሁለመናዬን ኮሰኮሰኝ፡፡

ቤተመዘክር ውስጥ የሚገቡ ቁሶች የመጠቀሚያ ዘመናቸው ያለፈባቸው፣ አሁን በቀላሉ የማይገኙ፣ ጥንታዊ ቅርሶች ብቻ የሚመስሉኝ እኔን ብቻ ነው ግን? ለምሳሌ ቪትዝ እና ያሪስን ሙዝየም አታስገባቸውም። የምኒልክን ባቡር ግን በአዋሳ ኃይሌ ሪዞርት ውስጥ ለጎብኚ ተወዝታ ታገኛታለህ። ጥንታዊ ስለሆነች። አሁን ስለማትነዳ። አንድ ለእናቷ ስለሆነች።

ከስክሱ ግን አልጠፋም። አሁንም አለ። አሁንም እንጠቀምበታለን። ያውም በብዛት። ሙዝየም መግባት ምን አስፈለገው? ያሁኑስ ሥርዓት ጠባቂዎች ይሄንኑ ከስክስ አይደል የሚጫሙት?

እየቀፈፈኝ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ፡፡ በቀያይ ማህተሞች የተዥጎረጎረ፡፡ በጓድ መንግስቱ የተፈረመ ትዕዛዝ ያረፈበት ኦሪጂናል ወረቀት.. ከከስክሱ ቀጥሎ በመስታወት ውስጥ ተቀምጧል – ለጉድ፡፡ ወታደራዊው ደርግ የንጉሡን ባለሥልጣናት በሞት እንዲቀጡ ያሳለፈው ውሳኔ ነው። የአገዳደላቸውን ሁኔታ፣ ሰዓትና ቦታ የሚገልፅ ትዕዛዝ።

ከዚህ በሰነድ እየተመዘገበ ከሚፈፀም ርሸና ታሪክ፣ ትውልድ ብዙ ትምህርት ያገኛል ብዬ አሰብኩ። ትውልዱ የሰው ልጅ ያለፍርድ መገደል እንደሌለበት ትምህርት ባይወስድ እንኳ፣ ቢያንስ እንዲህ ዓይነቱ የርሸና እርምጃ በወረቀት ተተይቦ መቀመጥ እንደሌለበት ግን ትምህርት የወሰደ መሠለኝ።

የወደፊት የታሪክ ተመራማሪዎች አሳዘኑኝ። እንዲህ ዓይነት የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለታሪክ ፍርድ የሚያጋልጥ ኦፊሴላዊ ሰነድ፣ ዳግመኛ ከዚህች የኢትዮጵያ ምድር የሚያገኙ አይመስለኝም። ሁሉንም በቆዘመ መንፈስ እየገረመምኩ (“መገርመም” ከመጎብኘት ይለያል) ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡

ውስጥ ደግሞ የሬሳ ሳጥኖች ተደርድረዋል፡፡ የብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጉርድ ፎቶዎች በግድግዳዎቹ ላይ ከነሥሞቻቸው ተገጥግጠዋል፡፡ በወታደራዊው መንግስት ጠመንጃዎች በተተኮሱ ጥይቶች እንደ ዶሮ የተረፈረፉ፤ እንደ ከብት የታረዱ፤ ለዚህች ሃገር ‹‹ነፃነት! ነፃነት! ነጻነት!!›› እያሉ እየጮኹ በግፍ የተገደሉ ውድ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ናቸው፡፡

ስንቱን ቤት አጉድለዋል? ብዙ አካለ ጎዶሎ ቤቶች በሀሳቤ ታዩኝ። የሁሉም ቤት ጎዶሎ ነው። ጎዶሎ ዘመን። ጎዶሎ ትውልድ። ጎዶሎ መሶብ። ጎዶሎ ህሊና። በስንቱ ነገር ጎደልን። እነዚህ ሁሉ አሳዛኝ ወጣቶችስ ግን፣ ከመጉደላቸው በፊት ሌላ ያጎደሉት ቤት፣ ያጎደሉት ወገን ይኖር ይሆን? የኛ ነገር ሙላታችንን ማጉደል ነው። ጎዶሏችን የሚሞላው ግን መች ይሆን? ከልቤ አዘንኩ፡፡

ያኔ፡፡ በባምቢስ። ጥይት እንደርችት እየተንጣጣ..። ከሙዝየሙ ፊት ለፊት የረገፉትን እኒያን የዚህች ሃገር ምፃተኛ ወጣቶች… ቅዱስ እስጢፋኖስ ያኔ በህይወት ሳሉ ተመልክቶአቸዋል፡፡ አሁን ደግሞ ሞተውም መታሰቢያቸውን.. እየተመለከታቸው ነው። ስማቸውን፣ ፎቶአቸውን..፣ የማይሰማ የታፈነ የዝምታ ድምጻቸውን… ፈንጠር ብሎ ቆሞ ይመለከታል – ቅዱስ እስጢፋኖስ፡፡

ብዙ ጊዜ ነው። ይህ እግዜሩ በደም መፋሰሶች ውስጥ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ፣ እንደ ባዳ ከሩቅ ቆሞ የሚመለከተው ነገር አልዋጥልህ የሚለኝ። ሳስበው እግዜሩ ብቅ የሚለው ለጭቦ መሰለኝ። የእኛ እግዜር ከአዳኝነቱ ይበልጥ፣ የጭቦ አምላክነቱ ያመዝናል። መሠለኝ። የሙታኑ ምስኪን መንፈስ ውስጤ ገብቶ ይሆን ከእግዜሩ ጋር የሚያዋቅሰኝ?

ክፍሉ ጭልም ያለ ነው፡፡ ደሞ የኢህአፓ ወጣቶች በድብቅ ዲሞክራሲያን እያተሙ የሚያሰራጩበት፣ ጭለማን ተገን አድርገው አብዮታዊ መልዕክቶችን በየከተማው የሚበትኑበትን በራሪ ወረቀት፣ በእጅ የሚያትም መሣሪያ – “ዳምጠው” – እንደ እሣት የሚንበለበሉ ቃሎቹን ሁሉ ውጦ በረዥም ዝምታ እንደተዋጠ ከጎኔ አርፏል፡፡

እነዚያ ወጣቶች ለዚህች ሃገር። ለህዝባቸው..። ለመጪዎቹ ታናናሽ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው…። ያላቸውን ተስፋ..። ያላቸውን የእድገትና እኩልነት ቨፈብስራት…። የዲሞክራሲና ሰላም ራዕይ..። ሌሊቱን ቁጭ ብለው… ሲጽፉ፤ ሲያትሙ እና ሲያሰራጩ .. ያድረሉ። ያለጊዜያቸው የተሰዉ የአብዮት አክፋዮች። ለውጣቸውን የተቀሙ የለውጥ ቀዳሾች።

መንገድ ለመንገድ ሲሳደዱ። መንገድ ለመንገድ ሲረሸኑ። መንገድ ለመንገድ ሲታሰሩ። ሲገረፉ። ሲተለተሉ። የነበሩት እነዚያ የዚህች ሃገር የቁርጥ ቀን ወጣቶች…። ከአጥንቶቻቸው መሐል። ሥጋ ለብሰው። ከነትኩስ ትንፋሻቸው። ከነማይሞት ልባቸው። ፊቴ ላይ ግጥም፣ ድቅን አሉብኝ፡፡ ታሪክ ምንኛ ፍርደገምድል ነው?

ከጎን በኩል የማዕከላዊ የወፌ ላላ ታሣሪዎችን ማሰቃያ እንጨት አለ፡፡ ፈራሁት። የሙታኑን መንፈስ። ጨለማውን ክፍል። የተስፋና የተጋድሎ፣ የሞትና የስቃይ ትውስታቸውን ሁሉ።

እነዚያን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወጣቶች…። በተሰበረ መንፈስ…። እግሩ እምቢ ብሎት በደረቱ እየዳኸ እንደሚሳብ ቁስለኛ..። በቆሰለ ልቤ..። እየዳኽኩ..። እየተሳብኩ…። ወደ ግድግዳው ተጠጋሁ።

በሐዘንና በሰቀቀን በቦዙ አይኖቼ…። በግድግዳው ላይ የተገጠገጠ ፎቶና ስማቸውን። ከመሐል ጀምሬ። በተሰበረ ልብና መንፈስ አይኔን በግድግዳዎች ላይ አንከራተትኩ፡፡ ስማቸው በጭለማው ከሞታቸው በላይ እንደሰማይ ከዋክብት እያበራ በአይኖቼ ላይ ያንፀባርቃል፡፡

መኮንን ተፈራ። ጌታቸው ገቢሣ። ደጉ ደበሌ። ወ/ት ትብለጥ ምህረትአብ፡፡ ተዘራ ተክለሚካኤል፡፡ ኃይሉ ተክለፃድቅ፡፡ አድነው ከየሮ፡፡ ሽጉጤ አለሙ፡፡ ኦሪኦን አያልነህ፡፡ አሮን ተኬ፡፡ ፉአድ ኢብራሂም፡፡ ካሣይ ወልደማርያም፡፡ መሃመድ ከማል የኑስ፡፡ እንድሪስ ሁሴን፡፡ ኡመር አብደላ እንድሪስ፡፡ ንጉሴ አሥገዶም፡፡

ሞገስ ተረፈ፡፡ ሞገስ ደሣለኝ፡፡ ሞሃመድ ሰይድ፡፡ ሙሉእመቤት ወልዴ፡፡ ሙሉጌታ ገብረማርያም፡፡ ሙሉጌታ ዱባለ፡፡ ሞላ ጌጤ፡፡ ሙጂብ ሱሩር፡፡ ሙላቱ ብርሃኔ፡፡ ሙህዲን ኡመር፡፡ ሙላቱ ምትኩ፡፡ ሙለታ ፈይሣ፡፡ ሙሉ አየለ፡፡ ሙሉ ተካ፡፡ ትዕግስቱ ወልየ እየሱስ፡፡ በመጨረሻ እጄን ሰጠሁ።………. አልቻልኩም፡፡

ከደብዛዛው ክፍል የእውር ድንብሬን ልወጣ ስውዘመዘም.. በመውጫዬ በግራ በኩል.. መዓት የሙታን ራስቅሎች.. የሙታን አጥንቶች ተከምረዋል…፡፡ በመስታወት ውስጥ ለትውልድ ዕይታ የቀረቡ፣ የትኩስ ወጣቶች ያላረፉ ነፍሶች፡፡

ሞት አይቀርም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው። ከበድን አጥንታቸው የሚተንን የሆነ የቀዘቀዘ የሞት መንፈስ በሰራ አከላቴ ላይ እንደ ጉም ሆኖ የተነዛብኝ መሰለኝ፡፡ እና .. መላ አካሌን… ፍራት ፍራት አለኝ።

ሃዘን አንሰፈሰፈኝ፡፡ ቁጭት… እና.. ሳግ እየተናነቀ አላላውስ አለኝ። ሳላስበው ትኩስ የእንባ ዘለላዎች ከዓይኖቼ መቀነት አምልጠው የረገጥኩትን ምድር እያራሱት ነበር። አኬልዳማ። የእንባ ምድር ላይ የቆምኩ መሠለኝ።

አጎንብሼ ከጨለማው ክፍል እየወጣሁ… ድንገት ከፊት ለፊት በመውጫዬ አቅጣጫ የገባውን የብርሃን ድንግዝግዝ ለማየት ቀና አልኩ፡፡ እና አንድ በጭለማው መሐል እንደ መብረቅ የሚያስገመግም ቃል አየሁ። ይህ ቃል በቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም ያየሁት የመጨረሻ ቃል ነው፡፡ ደግሜ እንደማላየውም ይታወቀኛል፡፡

በመውጫው በር ላይ በትልልቁ የተጻፈው ቃል እንዲህ ይላል፡-

‹‹እ ን ዳ ይ ደ ገ ም !››

አይኖቼን እያሻሸሁ አሁንም ደግሜ ጽሑፉን ተመለከትኩት፡፡ ለስንብት፡፡ ያው ነው፡፡

‹‹እ ን ዳ ይ ደ ገ ም !››
‹‹እ ን ዳ ይ ደ ገ ም !››
‹‹እ ን ዳ ይ ደ ገ ም !››
‹‹እ ን ዳ ይ ደ ገ ም !››

“እ ን ዳ . . .” የሚሉት ቃላት በጆሮዬ ላይ እያቃጨሉ ለሰማዕታቱ ጀርባዬን ሰጥቼ ከጨለማው ክፍል ወደ ደጁ ብርሃን ወጣሁ፡፡ ወደ ደጅ ስወጣ ፊት ለፊቴ የታየኝ ብቸኛ ነገር ቢኖር..፣ ወደ ሰማይ ከፍ ብሎ የተሰቀለው…፣ በፀሐዩ የሚያብረቀርቅ፣ የምስኪኑ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ብርማ ቀለም የተላበሰ ጉልላት ነው፡፡ ስብሃት ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ.. ብዬ ካለሁበት አጎንብሼ አማተብኩ፡፡

ህይወት ብዙ ቦታዎች ወስዳኛለች። ብዙ ትውስታዎችን አዝዬአለሁ። አሁንም የወታደሮቹ ከስክስ ይመጣብኛል፡፡ የእነዚያ ወጣቶች ከሳሽ ምስል ብቅ ይልብኛል፡፡ እነዚያ የህትመትና የማሰቃያ መሳሪያዎች በፊቴ ይመላለሳሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ደግሞ ደጋግሞ በሃሳቤ ሰተት.. መሰስ.. እያለ የሚመጣብኝ ያ የመጨረሻው ቃል ነው፡፡ ‹‹እ ን ዳ ይ ደ ገ ም !›› የሚለው፡፡ ‹‹ይ ደ ገ ም !›› የሚል ትውልድ እንደማይመጣ ተስፋ አለኝ። አዎ። ‹‹እ ን ዳ ይ ደ ገ ም !››፡፡

‹‹እ ን ዳ ይ ደ ገ ም !››፡፡ ‹‹እ ን ዳ ይ ደ ገ ም !››፡፡

Filed in: Amharic