አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ብርቱካን ሐረገወይን
ታሪክን ወደኋላ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ፤ ባለፉት ወራት የጥበብ ፤ የመረጃ እና የመዝናኛ ሰዎችን ግለ-ታሪክ እያቀረበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በታች የጋዜጠኛ ብርቱካን ሀረገወይንን ታሪክ ታነባላችሁ፡፡ ብርቱካን በኢትዮጵያ ሬድዮ በዜና ፋይል እውቅና ካተረፉ ጥቂት ጋዜጠኞች አንዱዋ ናት፡፡ ብርቱካን ማናት
➨ የ 5 አመቷ ልጅ ብርቱካን በሱቅ ውስጥ…
የተወለደችው ታኅሣሥ 13 ቀን 1958 ዓ.ም በንግድ ሥራ ከሚተዳደሩት ከአባቷ አቶ ሐረገወይን መንበሩና ከእናቷ ወ/ሮ ብናልፈው ሸጋው በቀድሞው በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ደጀን ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ለወላጆቿ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን ቤተሰቦቿ አጠቃላይ 5 ወንድ እና 5 ሴት ልጆች አሏቸው፡፡እንደ መጀመሪያ ልጅ በቤተሰቧ በልዩ ሁኔታ የምትታየው ብርቱካን በልጅነቷ ብዙ ኃላፊነቶች እየተሰጣት ሱቃቸውን በመጠበቅና ዕቃዎችን በመሸጥ ገና በ4 እና በ5 አመት ዕድሜዋ ድጋፍ ታደርግ ነበር፡፡ የአባቷን የንግድ ሥራ ብትወደውም ከልጅነቷ ጀምሮ ለመሆን የምትፈልገው ጋዜጠኛ ወይም ዲፕሎማት መሆን ነበር፡፡ የልጅነት ሕልሟን ለማሳካትም አባቷ የዕለት ከዕለት ድጋፋቸው አልተለያትም፡፡ በዚህ የተነሳ ከቤተሰቦቿ ጋር ልዩ ቅርበት ያላት ብርቱካን በተለይም አባቷን እንደ ጓደኛ ፣ እንደ ታላቅ ወንድም እንደ መምህር ጭምር ትመለከታቸው እንደነበረ በቅርበትም በርካታ ነገሮችን ከአባቷ ጋር እንደምትወያይ አብዛኛውን ጊዜ ታነሳለች፡፡
➨ በ 7 አመቷ የፍርድ ቤት ማመልከቻ ጸሀፊ ሆነች..
ገና በ 7 ዓመቷ ወላጅ አባቷ በወቅቱ ከሰዎች በገዙት መሬት የፍርድ ቤት እና የማዘጋጃ ቤት ክርክሮች ነበሯቸው፡፡ በዛን ወቅት የ7ዓመት ልጅ የነበረችው ብርቱካን ለአባቷ ለፍርድቤት የሚቀርቡ ደብዳቤዎች እና ማመልከቻዎችን ጽፋ በማዘጋጀት አባቷን ትረዳ ነበር፡፡ ብርቱካን እንደ ሌሎች ታዳጊ ልጆች በጨዋታ የልጅነት ጊዜዋን አላሳለፈችም፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ እሁድ ከሰዓት ከወንድሞቿ ጋር በመሆን እግር ኳስ ትጫወት ነበር፡፡ በአብዛኛው ከልጅነቷ ጀምሮ ትወደው የነበረው ጨዋታ የጠረጴዛ ኳስ (Table Tennis) ነበር።ፊደልና ቁጥሮችን መቁጠር እንዲሁም አቡጊዳና መልዕክተ ዮሐንስን ማንበብ በቤት ውስጥ በአባቷ መምህርነት የተማረችው ብርቱካን የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሕይወቷን የጀመረችው ገና በአራት ዓመቷ ነው፡፡ በደጀን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ከፍል ድረስ ትምህርቷን የተከታተለችው ብርቱካን በትምህርት ቤቱ ከትምህርቷ ባለፈም በንጽህና አጠባበቅ የጠቅላይ ግዛቱ ጤና ጽ/ቤት ለሁለት ጊዜያት ያህል ሽልማት አበርክቶላታል፡፡
➨ የሚድያ ዝንባሌ መጣ
በተጨማሪም፣ በትምህርቷ በተማሪ ሞዴልነት በምስጉን ባሕሪይ ባለቤትነት ከጠቅላይ ግዛቱ ዋና አስተዳዳሪ ከደጃዝማች ደረጀ መኰንን የሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡ በትምህርቷም እጅግ ጎበዝ የነበረችው ብርቱካን የአንደኝነት ደረጃን እየያዘች ነበር ትምህርቷን የምታጠናቅቀው፡፡ በዚህም ምክንያት በዓመት ሁለት ጊዜ ከክፍል ወደ ክፍል (ደብል ክፍሎችን እየመታች) የማለፍ ዕድል ቢኖራትም ዕድሜዋ ገና ልጅ በመሆኑ ምክንያት ያ ሳይሆን እንደቀረ በትውስታ ታነሳለች፡፡ ብርቱካን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በጎጃም በር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለችው፡፡ ዘወትር እሁድ ይተላለፍ የነበረውን “የነገው ሰው” በመሰኘት በዶ/ር ልዑልሰገድ ዓለማየሁ አማካኝነት የሚዘጋጀው የሬዲዮ ፕሮግራምን እየተከታተለች ጥያቄዎችን በመጻፍ ዜናዎችን በማዘጋጀት በሰንደቅ ዓላማ መስቀያ ሰዓት ላይ ለተማሪዎች ታቀርብ ነበር፡፡ በተጨማሪም ትምህር ቤቱ ዘወትር ዓርብ ያዘጋጅ የነበረው የትምህርት ቤት የክርክር መድረክ ዝግጅት ላይ በልጅነት ዕድሜዋ በሰብሳቢነት ትሳተፍ ነበር፡፡
➨ በ19 አመቷ ጉዞ ወደ ሶቭየት
በ 1977 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ለማግኘትም ብርቱካን በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት በተሰጣት ነጻ የትምህርት ዕድል ለመሳተፍ የዛሬዋ የሩሲያ ፌዴሬሽን ርዕሰ- መዲና ወደሆነችው ሞስኮ እንድታቀና ተደረገ፡፡ በሞስኮ ሶሻል ሳይንስ ኢንስቲቲዩት ውስጥ በመግባትም ከ84 አገራት ከመጡ ተማሪዎች ጋር ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡ በቆይታዋም ማኅበረሰቡን የማጥናት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት፡፡ በትምህርት ክፍሏም ውስጥ ብቸኛ ሴት ተማሪ ነበረች፡፡ በቆይታዋም የፖለቲካ ሳይንስ እስፔሻላይዝድ ያደረገችበት ትምህርትም አጸፋዊ ፕሮፖጋንዳ (Counter Propaganda) ነው፡፡ በተጨማሪም የጋዜጠኝነት ትምህርትን በዛው ለመማር የቻለችው ብርቱካን በሞስኮ በትምህርት ቤት ቆይታዋም የሚኒ ሚዲያ ተሳትፎ ታደርግ ነበር። የሩሲያ ቀዝቃዛውና በረዶማው የአየር ንብረት እጅግ ፈታኝ ቢሆንም አባቷ የሰጡዋትን አደራ ጠብቃ ከ5ዓመት ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታ ከመመለሷ በተጨማሪም አገሯን ለማስተዋወቅ በርካታ ሥራዎችን ሰርታለች፡፡
የመመረቂያ ጽሑፏም በአገራችን ሴቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሆኖ ሴቶችን ለማብቃት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችና ፈተናዎች የሚል ርዕስ ነበር፡፡በ 1981 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላ መጥታለች፡፡
➨ በሠርቶ አደር ጋዜጣ ሪፖርተር
በ1982 ወደ ስራ ሕይወት የገባችው ብርቱካን በወቅቱ የነበረው መንግስታዊ ሥርዓት ውስጥ በነበሩት የስራ መዳቢ ኮሚቴ አማካኝነት በሠርቶ አደር ጋዜጣ ሪፖርተር ሆና እንደተመደበች ሲነገራት ብርቱካን ስራውን አልተቀበለችም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለ8 ወራት ያህል ያለስራ ህይወቷን ለማሳለፍ ተገድዳለች፡፡
➨ በ 1983 -ኢትዮጵያ ሬድዮ
በ 1983 ዓ.ም ማስታወቂያ ሚኒስቴር በመሄድ ለጋዜጠኝነት ስራ አመለከተች፤ ማመልከቻዋም ተቀባይነት አግኝቶ የተለያዩ ፈተናዎችን ካለፈች በኋላ በሬዲዮ ስራ መመደብ ቻለች፡፡ በዚህ ያላበቃው የብርቱካን ፍላጎት፣ ወደ ቴሌቪዥን በመሄድ የስክሪን እና የንባብ ችሎታን ፈተናን መውሰድ ቻለች፡፡ ፈተናውን አልፋም በፍሪላንሰርነት ሥራዋን መሥራት እንደምትችል በዜና ክፍል ኃላፊው ተገለጸላት ፡፡ ይሁንና በሬዲዮ በፍሪላንሰርነት የሙሉ ጊዜ ሰራተኛ በመሆን የዜና ክፍልን ተቀላቀለች፡፡ ምክንያቱም የቴሌቪዥን ዜና ክፍልን ፈተና በብቃት መወጣት ብትችልም በቋሚነት ሳይሆን በዜና አንባቢነት ብቻ ልትሰራ እንደምትችል ሲነገራት በዚህ ያልተስማማችው ብርቱካን የቀረበላትን የቴሌቪዥን የሥራ ዕድል በመተው ሙሉ በሙሉ የሬዲዮ የዜና ክፍል ሥራዋን ለመስራት ወሰነች፡፡
በወቅቱም ከነበሩት የብሔራዊ ሬዲዮ ጋዜጠኞች ገነት አስማረ፣ አለምነህ ዋሴ፣ ተፈሪ አንለይ፣ ንግስት ሰልፉ፣ ፣ ዋጋዬ በቀለ ፣ ነጋሽ መሐመድ፣ ጌታቸው አላምረው ፣ ዳሪዮስ ሞዲ ፣ ብርሐነመስቀል ታፈሰ ፣ አማረ መላኩ ጋር በመሆን የዜና ክፍል ስራዋን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 1983ዓ.ም. ጀመረች፡፡
ዜና ፋይልን ከተቀላቀለች በኋላም የሥራ ላይ ስልጠና በአቶ ጌታቸው ኃይለማርያም አማካኝነት ከእነተፈሪ አንለይ ጋር እየተሰጣት የመጀመሪያ የድምጽ ዜናዋን አየር ላይ ያዋለችው የውጪ ዜና ትርጉም በማንበብ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት አስመልክቶ በየአካባቢው ለዘመቻው ድጋፍ ተብሎ ይደረግ የነበረውን ስንቅ የማዘጋጀት ስራ ለገሃር ጀርባ ባለ አንድ ቀበሌ በመሄድ ቦታው ላይ ያለውን ሁነት በመዳሰስ የመጀመሪያ የሬዲዮ ዜና ሪፖርት መስራቷን ታስታውሳለች፡፡ የዜና ዕውቀቷን ለማሳደግም በርካታ መጻህፍትን ታነብ ነበር፡፡ በተጨማሪም ለሪፖርት ሥራ ስትመደብና ስትላክ ስለምትሄድበት ስፍራ ቀድማ ለማወቅና መረጃ ለማግኘት ጥረት ማድረግ የሥራዋ የሁልጊዜ ቀዳሚ ተግባሯ ነበር።
➨ ደሞዝ 500
በሥራዋ ሳትሰለች በብርታት ትሰራ ነበር፡፡ በቀን ሁለት ጊዜ ጠዋትና ማታ ዘገባዎችን ለመስራት መሄድ የማለዳ ተረኛ በማይኖርበት ወቅትም በርካታ ጊዜያትን ሽፋን ሰጥታ ለመስራት የማትሰለች እና ድካም የማታውቅ ሰራተኛ ነበረች፡፡ ስራዋን ስትጀምር በወቅቱ ይከፈላት የነበረው ደሞዝ 500 ብር ነበር፡፡ የደረጃ ዕድገት ባይኖራትም የፈረቃ ኃላፊ ሆና አገልግላለች፡፡ ከሥራና ኃላፊነት መጨመር በስተቀር ለ7 ዓመታት ያህል ያለምንም ደመወዝ ጭማሪ አገልግሎት ሰጥታለች፡፡ ለ 7 ዓመታት ያህል በፍሪላንሰርነት ካገለገለች በኋላም በ1990 ዓ.ም የሬዲዮ ጣቢያው የመዋቅር ማሻሻያ ሲያደርግ ብርቱካንም ቋሚ ሠራተኛ ለመሆን በቃች፡፡ ቋሚ ሠራተኛ ሆና ስትመደብ ትልቅ የሚባል ዕድገትን አገኘች፡፡ በዚህም ምክንያት ምክትል ዋና አዘጋጅ በመሆን ተመደበች፡፡
በሥራዋ አርአያ መሆን ዋና ዓላማዋ የነበራት ብርቱካን ሐረገወይን ሠርቶ ማሰራትን ፣ ሥራን መውደድ ፣ ሥራን በአግባቡ፣በጥራት እና በጊዜ መጨረስ ፣ ሥራን ወድዶ መስራት ፣ ለሙያው ፍቅርም ለአድማጭም አክብሮት እንዲኖር ማድረግ እርሷ በኃላፊነት ባገለገለችበት ወቅት ብዙዎች ዘንድ እንዲኖር የምትፈልጋቸው፣ መፈለግ ብቻ ሳይሆን በተግባር ሰርታ ያሳየችባቸው ጥንካሬዎቿ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1988 ዓ.ም የምሽት ሁለት ሰዓት የዜና ፋይል ዝግጅትን በቀጥታ ስርጭት ካነበቡ ግንባር ቀደም ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ብርቱካን ሐረገወይን ነች፡፡ በዚህ ምክንያት ተቀርፆ ለአድማጭ ይቀርብ የነበረው የምሽት ሁለት ሰዓት ዜና በቀጥታ ለአድማጭ ይደርስ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሳምንቱ ታላቅ ዜና የተሰኘው ፕሮግራም ሲጀምር የቀድሞዋ ዛየር(የዛሬዋ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) መሪ ስለነበሩት ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ የመጀመሪያውን ፕሮግራም በመስራትና በማቅረብ ግንባር ቀደም ነች።
➨ በ 1991 ሲስተም ዘረጋች
በ 1991 ዓ.ም የዜና እና ወቅታዊ ጉዳዮች ክፍልን እንድትመራ ኃላፊነት ተሰጣት፡፡ በኃላፊነቷ ወቅትም አተኩራ ስትሰራ የነበረው በምትመራው ክፍል ውስጥ ሲስተም የመዘርጋት ስራን ነበር ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በእርሷ ቦታ ቀድመው በኃላፊነት ይሰሩ የነበሩት አቶ ጥላሁን በላይ በጡረታ ምክንያት ከመሥሪያ ቤቱ ቢገለሉም በብርቱካን ጠያቂነት ካላቸው የ36 ዓመታት የጋዜጠኝነትና የኃላፊነት ልምድ አንፃር አቶ ጥላሁን ወደ ስራቸው ቢመለሱ ጥቅማቸው ከፍ እንደሚልና ለዜና ክፍልም የእርሳቸው መኖር በርካታ ትርፎች እንደሚኖሩት በማሳመን ወደ ስራቸው በፍሪላንሰርነት እንዲመለሱ አድርጋለች፡፡ ለዜና ክፍሉ ጥንካሬና ለዜና ፋይል በተደማጭነት መቀጠል ትልቅ ሚናና ድርሻ እንዲጫወቱ ሆኗል፡፡ የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎችን የሚያቅፈው የዜና ማዕከል ከዜናና ወቅታዊ ክፍል ጋር የተነጠለ ነበር፡፡ ብርቱካን ወደ ኃላፊነት ከመጣች በኋላ ግን የዜናና ወቅታዊ ክፍሉን ከዜና ማዕከሉ ጋር እንዲዋሃድ እና አንድ እንዲሆን ለተቋሙ ኃላፊዎች በማቅረብ ሃሳቧ ተቀባይነት አግኝቶ ሁለቱን ተለያይተው የነበሩ ክፍሎች በአንድነት እንዲሰሩ አስችላለች፡፡
➨ ዜና ክፍሉን ኮምፒዩተራይዝድ ማድረግ
በዚህም የዜና ክፍሉ እንዲያድግ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክታለች፡፡ በተጨማሪነትም የብርቱካን ቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫዋ የነበረው የዜና ክፍሉን ኮምፒዩተራይዝድ የማድረግ ሃሳብ ነበር፡፡ በ 1993 ዓ.ም ብርቱካን የነበራትን የተወሰነ የኮምፒዩተር ዕውቀት በመጠቀም በሬዲዮ ኢንጅነሪንግ ክፍል ከነበረው ከሥራ ባልደረባዋ ሌዊ ጋር በመሆን በውስጥ የተቋሙ አቅም በሲስተም በማስተሳሰር ዜናዎችን የትኛው ዜና መጣ፣ የትኛው ዜና ተሰራ፣ አልተሰራም፣ የትኛው ዜና ተላለፈ አልተላለፈም የሚለውን ሁሉ የሚያስችል ሲስተም መዘርጋት ችላ የተሰራውን ስራ ለተቋሙ ኃላፊዎችና ለቦርድ አመራሮች አስጎበኘች፡፡ በጉብኝቱ ወቅትም ከዛሬ ጀምሮ በታይፕ ራይተር መጻፍም ሆነ ጋዜጠኞች የዜና ፀሐፊዎችን መጠቀም አቁመው ሁሉም ጋዜጠኛ የራሱን ዜና እንዲጽፍ የሚል መመሪያ ተሰጠ፡፡ ይህ ወቅት የሬዲዮ ዜና ክፍል ሥራዎቹን በታይፕ ራይተር ከማከናወን ተላቅቆ ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ወደሚያስችለው የኮምፒዩተር አጠቃቀም የተሸጋገረበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
በዚህን ወቅት 10 የሚደርሱ ታይፒስት ወይንም ዜና ፀሐፊዎች በዜና ክፍሉ ውስጥ ነበሩ፡፡ እነርሱ በዚህ ሲስተም መምጣት ምክንያት ስራቸውን የማጣት አደጋ ተጋረጠባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ብርቱካንን አኮረፏት፡፡ በዚህ ያልተረታችው ብርቱካን ፀሀፊዎቹም ሆኑ ጋዜጠኞች የኮምፒዩተር ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የተወሰኑ ፀሃፊዎች ወደ ፕሮግራም ክፍል እንዲሄዱ ተደርጎ እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ሲስተም እንዲሰራ ማድረግ አስችላለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሲስተሙ ዕለታዊ ዜናን ከማግኘት ባለፈም ዜናዎች ለሁለት ዓመት ያህል እንዲሰነዱ (አርካይቭ) በማድረግ ዘመናዊ ሥርዓቱን መጠቀም ችላለች፡፡
በዚህም ጥናት ለሚያጠኑ ባለሙያዎች፣ ለተመራማሪዎች መረጃዎችን በቀላሉ ለመስጠትና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ፤ እንዲሁም ተቋሙ ላይ ዜናን በሚመለከት የሚመጡ ክሶችን ለመከላከል ከማስቻሉም በላይ ዜና ክፍሉ ተገቢ ያልሆነ ዜና አስተላልፎብናል በሚል የደርግ ባለስልጣናት በሬዲዮ ጣቢያው ላይ አቅርበውት የነበረውን ክስ ጭምር በዚህ በተዘረጋው ሲስተም አማካኝነት በቀላሉ መረጃ ማቅረብ በመቻሉ በክሱ ምንም ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ችላለች፡፡ በተጨማሪም የሞኒተሪንግ ክፍሉ የዜና ሞኒተሪንግን በአደገኛና በተቀናጀ መልኩ እንዲሠራ የሚያስችል አሰራርንም መዘርጋት ችላለች፡፡ ዜናን አቅዶ መስራት ፣የፕሮጀክት ዜናዎችን በተከታታይነት እንዲሰሩ በማድረግ፣ ጋዜጠኛው አቅዶ መጥቶ በመረጃ የዳበሩ በይዘት ከፍ ያሉ ዜናዎችን እንዲሰሩና እንዲቀርቡም ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከት ችላለች፡፡
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሲቀላቀልም፣ በዜና ክፍል ውስጥ ስታገለግልም ፕሮጀክት በመቅረፅ ያልተዳሰሱ አካባቢዎችና ያልተዳሰሱ ጉዳዮች እንዲዳሰሱ ትኩረት አንዲያገኙ ከፈታኝ ሁኔታዎች ጋር በትጋት ትሰራ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ተቋሙ በዜና እራሱን የቻለ ተቋም አንዲሆን ለማስቻል የግሏን ጥረትና አስተዋፅኦ አበርክታለች፡፡
➨ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም አከባበር እና ብርቱካን
ከዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ክፍል ኃላፊነት በኋላም የኢትዮጵያ ሚሌኒየም አከባበር ብሔራዊ ጽ/ቤት ሲቋቋም የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ በመሆን ለሁለት ዓመት በውሰት መስራት ችላለች፡፡ በሚሌኒየም አከባበር ብሔራዊ
ጽ/ቤት በ 1999ዓ.ም በታህሳስ ወር ላይ ስራዋን ከጀመረች በኋላ ሁለት ዛፍ በሁለት ሺህና ሶስት ዛፍ በሁለት ሺህ የሚሉ ፕሮጀክቶችን በማስፈጸም የሚሌኒየም አከባባር ደማቅ እንዲሆን፣ ሕዝቡ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ እንዲያከብረው ከሚዲያዎቻ ጋር በመተባበር ሕዝቡን የሚያሳትፉ ስራዎችን እንዲሁም ትላልቅ ብሔራዊ ሁነቶችን በማደራጀትና በማዘጋጀት የመምራት እና የማስፈፀም ስራዎችን በኃላፊነት በመውሰድ ስኬታማ ስራን መስራት ችላለች፡፡
ኢትዮጵያን ማስተዋወቁ እንዲሁም ያላትን ከመላው ዓለም የተለየ የዘመን አቆጣጠር ጭምር እንዲተዋወቅ በማድረጉ ረገድ በዚሁ አርዕስት ጉዳይ ትልቅ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት አገሯን የማስተዋወቅ ስራዎችን በፊታውራሪነት መምራት እና ማስፈፀም ችላለች፡፡
➨ ፈተና እና ብርቱካን
ለሁለት ዓመት በሚሌኒየም አከባበር ብሔራዊ ጽ/ቤት የነበራትን የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊነት አጠናቅቃ ከምስጋና ደብዳቤ ጋር ዕድገቷና ጥቅሟ ተጠብቆ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተመልሳ እንድትሰራ ቢባልም በወቅት የነበሩት አመራሮች ግን ወደ ስራዋ መመለስ እንደማትችል ገልጸውላት ከስራዋ ያለምንም ምክንያት እንድትሰናበት አደረጓት፡፡
ከስራዋ ብትሰናበትም ከጥቅምት እስከ መጋቢት ወር ድረስ ያለስራ በቤቷ እንድትቀመጥ ቢደረግም ደመወዟ ግን በክፍያ መልክ ይደርሳት ነበር፡፡
መጋቢት 2001ዓ.ም በአገሪቱ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የሁለት ወር ስልጠና በደብረዘይት ሲዘጋጅ ጥሪ ቀርቦላት ስልጠናውን መካፈል ቻለች፡፡ ከዚህ ስልጠና በኋላ በደረሳት ደብዳቤ መሰረትም ከነበራት የስራ ደረጃ ዝቅ ብላ እንድትሰራ ተደረገ፡፡ የስራ መዘርዝርእንዲሰጣት ጥያቄ ብታቀርብም የስራ ደረጃንና ደመወዝን የሚገልጽ ደብዳቤ እንጂ የስራ መዘርዝር ጥያቄዋ “የፊውዳል አስተሳሰብ ” በሚል ፍረጃ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡
ወደ ስራዋ ስትመለስ በቢሮዋ ውስጥ የነበራት ወንበር እና ጠረጴዛ ብቻ እንጂ ለአንድ ጋዜጠኛ ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል ኮምዩውተር እንኳን እንዳይሰጣት ተብሎ በወቅቱ የበላይ ኃላፊዎች ያልተጻፈ ውሳኔ ተወሰነባት፡፡
በወቅቱም አዲስ ተቀጣሪ ጋዜጠኞችን በማሰልጠንና የፕሮጀክት ዜናዎችን በመቅረፅ እንዲሰሩ በማድረግ ብዙ እገዛዎችን አድርጋለች፡፡ ብርቱካን ሰውን ማገዝ መደገፍ ከተቻለ ብዙዎች ያላቸውን ተሰጥኦ በቀላሉ አውጥተው በመጠቀም በሚዲያ ስራው ላይ በርካቶችን ማፍራት ለሚዲያው ዕድገትም ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚቻል በደንቡ ታምናለች፡፡ በዚህም ብዙዎችን ለውጣለች፡፡
ወደ ስራዋ ከተመለሰችና ለ 8 ዓመታት በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ ስትሠራ ከቆየች በኋላ በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ሙያዊ አገልግሎት ስትሰጥ ከነበረችበት ከምትወደው መሥሪያ ቤቷ ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለቅቃለች፡፡
➨ በውጣውረድ ውስጥ ትጋትን ማሳየት
በነዚህ ዓመታት ውስጥም ከ1993-1995 ዓ.ም ለሁለት ዓመታት ያህል በዋልታ ኢንፎሜሽን ማዕከልና በትምህርት ሚኒስቴር ይዘጋጅ የነበረውን ብሔራዊ የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ዝግጅት የሚመለከተው አገራዊ ኮሚቴ ውስጥ ተቋሟን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በመወከል ከመሳተፍ በተጨማሪ ፕሮግራሙን ትመራ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ሬዲዮን ዜናና ወቅታዊ ፕሮግራም ክፍልን ከመምራት ባሻገር ልጆቿን ከማሳደግ ጎን ለጎን ወደ የክልሎች በመጓዝ የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ዝግጅት ፕሮግራም በመምራት የተሳካ ሥራ ሰርታለች፡፡ በብሄራዊ ኮሚቴዎች ጭምር ጣቢያዋን በመወከል በስፖርት ጉዳዮች የሴካፋ ውድድር በሀገራችን ሲዘጋጅ የኮሚቴ አባል በመሆን የሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን ሀላፊ በመሆን አርቲክሎችን በመፃፍም ጭምር ተሳታፊ መሆን ችላለች፡፡
በተጨማሪነትም የአፍሪካ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ፣ የአፍሪካ ካሪቢያን አውሮፓ ህብረት ፓርላማ ጉባኤ ፣ የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ቀንና በመሳሰሉት አገራዊ መድረኮች የኮሚቴ አባል እና የሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን አስተባባሪ በመሆን አገልግላለች፡፡ በ 2007 – 2008 ዓ.ም የሥራ ዘመኖቿ ወቅት ብርቱካን የምትመራው የባለሙያዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የዜና አሰራር ማኑዋል ፣ ስታይል ቡክ ፣ የግራፊክስ ማኑዋል ከባልደረቦቿ ጋር በመሆን አዘጋጅታ ለጣቢያው አቅርባለች፡፡ የማኑዋሎች ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላም ተገቢው ዕውቅና እንዲሰጥ እና በጥቅሉ 500 የሚደርስ ገፅ ያሉት ማኑዋል እንዲታተም ጥያቄ አቅርባ ተቀባይነት ቢያገኝም ማኑዋሉ ሊታተም ሲቃረብ በወቅቱ የነበሩት አመራሮች ማኑዋሉን ያዘጋጁት ባለሙያዎች ዕውቅና ማግኘት የለባቸውም፣ ስማቸውም በህትመቱ ውስጥ ሊካተት አይገባም በሚል ህትመቱ እንዲቆም አደረጉ፡፡
በመጨረሻም ማኑዋሎቹን ያዘጋጁት ባለሙያዎች ብርቱካንን ጨምሮ ስማቸው ሳይገባ እንዲታተም ተደረገ፡፡ ይህን በማዘጋጀት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተችው ብርቱካን የማኑዋሎቹ ረቂቅና የመጨረሻ የህትመት ዝግጅት ሶፍት ኮፒ በእጆቿ ቢኖሩም የታተሙት ማኑዋሎች እንዳይሰጧት ሆነ፡፡
ማኑዋሎቹን እያዘጋጀችና ዝግጅቱን እየመራች በነበረችበት ወቅት በተጓዳኝ ሁለት ጥያቄዎችን የያዘ ምክረ ሃሳብ ለተቋሙ ኃላፊዎች አቀረበች፡፡ አንደኛው የዜና ክፍሉ ጋዜጠኞች ለሥራቸው ምቹና ተመጣጣኝ የሆነ የአልባሳት አቅርቦት እንዲኖራቸውና ሁለተኛው ደግሞ መስክ የሚወጡ ጋዜጠኞችና የካሜራ ባለሙያዎች ከሚይዟቸው መሣሪያዎች የዋጋ ውድነት አንጻር ለደህንነታቸው የሚመጥኑ ሆቴሎች እንዲያርፉ የሚረዳ የአበል አከፋፈል እንዲፈቀድ የሚጠይቅ ነበር፡፡ ሁለቱም ጥያቄዎች ተቀባይነት አግኝተው ተፈጻሚ መሆን እንዲችሉ አድርጋለች፡፡
ከዚህም ሌላ ተቋሙ የሚጠቀምበት ህንጻ ለሚዲያ ሥራ ተብሎ የተገነባና ለአሠራር ምቹ ባለመሆኑ ባለበት ሁኔታ ለአሠራር ምቹ እንዲሆን የሚያስችል ሌይ አውትና የቢሮ አደረጃጀት እንዲኖርና ደረጃውን የጠበቀ የውስጥ ማሻሻያ እንዲደረግ በተቋሙ አመራሮች ኃላፊነት ተሰጥቶአት የተቋሙን የሥራ ባህሪይ ባማከለ ሁኔታ የውስጥ አደረጃጀቱን የሚመጥን ሰነድ አዘጋጅታ አቅርባለች፡፡
የዜና አዘገጃጀት ስልጠናዎች ለብዙ ጋዜጠኞች በአሰልጣኝነት ከመስጠት ባለፈም ከመሪዎች ጋር በመሆን ብዙ ሀገራት ላይ ተንቀሳቅሶ በመስራት ብዙ ልምዶችን አካብታለች፡፡በኒዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤዎችን፣ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኋላም የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤዎችን፣ የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ድርድርና ስምምነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም የመሪዎች ጉባኤ፣ የቡድን ስምንት አባል አገራት መሪዎች ስብሰባዎች፣ የቡድን ሃያ አባል አገራት የመሪዎች ጉባኤዎች፣ በደቡብ አፍሪካ መሪ በኔልሰን ማንዴላና በታንዛኒያው መሪ ጁሊየስ ኔሬሬ ይመራ የነበረው የቡሩንዲ ተፈላሚ ወገኖች የሰላም ድርድር፣ የዓለም የሥነ ሕዝብ ጉባኤ፣ የሰነዓ ፎረም የመሪዎች ጉባኤዎች፣ የሶማሊያ ተፈላሚ ወገኖች ድርድሮች፣ በሩዋንዳ የሰላም ማስከበር ሥራዎችና የሩዋንዳ ዕልቂት 10ኛ ዓመት መታሰቢያ፣ የአገራችን መሪዎች ከአሜሪካ መሪዎች ከፕሬዚዳንት ክሊንተን፣ ከፕሬዚዳንት ቡሽና ከፕሬዚዳንት ኦባማ፣ ከሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን፣ ከጣሊያኑ ቤሮሎስኮኒ፣ ከብሪታኒያው ቶኒ ብሌርና ጎርደን ብራውንና ከሌሎችም ጋር ያካሄዷቸውን የሁለትዮሽ ውይይቶች ጨምሮ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ዐበይት ሁነቶችን ዜና ዘግባለች፡፡
የሚዲያ ሥራ አመራርን (ማኔጅመንት) ጨምሮ ስለ ምርመራ ጋዜጠኝነት፣ ስለ ፍርድ ሂደቶች አዘጋገብ፣ ስለ አየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ጥበቃ አዘጋገብ፣ በርካታ ዓለምአቀፍ ስልጠናዎችን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማግኘት የቻለች ድንቅ ሴት ጋዜጠኛ ነች ብርቱካን ሐረገወይን። በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈችው ብርቱካን ለ26 ዓመታት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ብታገለግልም ምንም አይነት ዕውቅና ሳይቸራት የምትወደውን ሙያ በመተው ቤቴ የምትለውን ተቋሟን ለቅቃለች። ከጋዜጠኝነት ሙያዋ በተጨማሪ የሚሰጧትን ኃላፊነቶች በዕውቀት ታግዛ ለመወጣት ቢዝነስ ማኔጅመንት አጥንታለች፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት የሆነችው ብርቱካን ከ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ አሁን ያለችበትንና በሎጅስቲክስ ዘርፍ ላይ ያተኮረውን የኢትዮጵያ ፍሬት ፎርዋርደርስና ሺፒንግ ኤጀንትስ አሶሴሽንን በሥራ አስኪያጅነት እየመራች ነው፡፡
የዚህ ጽሁፍ የቃለ-መጠይቅና የጽሁፍ ስራ በአቤል እንዳቅሙና በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ሲሆን ብርቱካን ሀረገወይን ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ የሰጠችውን ቃለ-ምልልስ መሰረት አድርጎም የተጻፈ ነው፡፡