>

ጠቅላይ ሚኒስትር «ከቁርበትዎ» ይምከሩ (ዓለማየሁ ገላጋይ፤«መለያየት ሞት ነው» )

ጠቅላይ ሚኒስትር «ከቁርበትዎ» ይምከሩ

(ዓለማየሁ ገላጋይ፤ «መለያየት ሞት ነው» ጥር 2010)

ይህንን የደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይን – «ከቁርበትዎ ይምከሩ» የሚል ጽሑፍ ፤ በመጽሐፉ «መለያየት ሞት ነው» ውስጥ እንደወጣ ባበረከተልኝ አንድ የልብ ወዳጄ ሥጦታ አጋጣሚ – ካንጀቴ ስፍስፍ ብዬ ነበር ያነበብኩት፡፡

ግርም ነበር ያለኝ የደራሲው ግልጽ እና አስደማሚ ህሊናዊ መልዕክት፡፡ በጣም ልብ የሚነካ ግልፅ ደብዳቤ ነበር የጻፈላቸው ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡

እና ደግሞ… በጣም ያስገረመኝ ነገር… ደራሲው ይህን መልዕክቱን በመጽሐፍ መልክ ባሳተመ… በጥቂት (በ3) ወራት ውስጥ… ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሣለኝ በገዛ ፈቃዳቸው ከመሪነት ሥልጣናቸው መልቀቃቸውን አሳወቁ፡፡

ምናልባት ይህ የደራሲው «ከቁርበትዎ» ይምከሩ መልዕክት – እርሳቸው ዘንድ ደርሶ ይሆን? አላውቅም፡፡ እስካልነገሩን አናውቅም ማናችንም፡፡ ለማንኛውም ግን የደራሲውን ግልጽ ደብዳቤ አሁን ላይ ሆነን – የያኔውን እያሰብን እናንብበው፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በአንድ ወቅት ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በሀገራችን ዕውቀትን ከታጠቀ ምሁር ይበልጥ ጠብመንጃ የታጠቀ ባለጊዜ እጅግ እንደሚከበር እየተበሳጩ ሲያስረዱ የተናገሯቸው አይረሴ ቃላት ነበሩ፦

“ለምሳሌ ለእኔ ጀግናዬ ዶ/ር ኃይሉአርአያ ነው፤ እርሱ የጠብመንጃን ኃ ይል ንቆ – ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ፊት ለፊት ሥልጣንዎትን ይልቀቁ! ብሎ በቆራጥነት ተናግሯቸዋል፤ ለእኔ ጀግናዬ የመንፈስ ልዕልና ያላቸው እንደ ኃይሉ አርአያ ያሉት መንፈሰ-ጠንካራ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

“ነገር ግን እዚህ ሀገር ለራሳቸው ሳይሆን ለሀገርና ለትውልድ አስበው – እነዚያን አንገታቸውን ለባለጠብመንጃ  አሳልፈው የሰጡትን የብዕር ጀግኖች –
እንደ ብሔራዊ ጀግና የሚያስታውሳቸው፣ ታላላቅ ጀብዱዎቻቸውን የሚዘክርላቸው ትውልድ የለም፤ ያሳዝነኛል፡፡

“ያ፤ እዚህ ሀገር ዕውቀት እስካልተከበረ ድረስ፤ ምሁራን እስካልተከበሩ ድረስ፤ መቼውኑም ከጉልበት እና የጉልበተኝነት አስተሳሰብ ልንላቀቅ አንችልም፤”

ነበረ ያሉት ፕሮፌሰሩ፡፡ ደስ የሚል ትንተና ነው፡፡ መራርም እውነታ ነው፡፡ እኛ ሀገር ባመዛኙ የገደለ ነው ጀግና እየተባለ ታፍሮ ተከብሮ የሚኖረው፡፡ እንጂ በአዕምሮ ኃይል የሚሞግት፣ ለትውልዱ የጭንቅላቱን አንጡረ ሃብት ያንጠፈጠፈ ኢትዮጵያዊ – እስከዛሬ አንድም ኃውልት አልተሠራለትም፡፡

ኃውልቶቻችን ሁሉ በነፍጥ የተጋደሉ ኢትዮጵያውያንን (እና ኩባውያንን ጭምር) ብሔራዊ ጀግናዎቻችን አድርገን የምንዘክርባቸው ናቸው፡፡ ለምን እነርሱ ተዘከሩ? አይደለም፡፡ ይገባቸዋልም፡፡

ነገር ግን ስለምን እንደሌላው የሠለጠነው ዓለም – የብዕር ጀግናዎቻችን፣ የጥበብ ጀግናዎቻችን፣ የሞራል ልዕልና፣ የሕሊና ሰብዕና፣ የመንፈስ ወኔና ኃይል፣ ሀበሻዊ የመንፈስ ልዕልና ኖሯቸው – ያንኑ ለዜጎቻቸውና ለሀገራቸው ሲሉ ያለማወላዳት ሰጥተው ያለፉትን ጀግኖች ኢትዮጵያውያንንስ ስለምን አናስታውሳቸውም? ለማለት ነው፡፡

ሁሉንም ጀግኖቻችንን እናድንቅ፡፡ ከሁሉም ገበታ ላይ ሁሉንም ዓይነት ጀግኖችን እናፈራ ዘንድ – ነው መልዕክቱ፡፡ ለማንኛውም አሁን መፅሐፉን ፎቶ አንስቼ ወደገፄ ወዳመጣሁት ወደ አሁኑ የሞራል ልዕልና ባለቤት ደራሲ እናምራ፡፡

ይህን ደራሲ በግል አላውቀውም፡፡ በዚህ «መለያየት ሞት ነው» በሚል መጽሐፉ ግን – በወቅቱ በሥልጣን ወንበር ላይ ለነበሩት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ – ግልጽ ልብ የሚነካ ደብዳቤውን – አክብሮት በተሞላበት እና እጅግ አስገራሚ በሆነ መልኩ ያቀረበ፣ ደፋር የብዕር ጀግና ነው ለእኔ።

ነገሮች መቀየር ካልቻሉ – ስለምን ሥልጣንዎትን አይለቁም? እያለ – የሕሊና ሙግት ይሞግታል ጠቅላይ ሚኒስትሩን፡፡

ይህ መጽሐፍ በወጣ በጥቂት ወራት ዕድሜ ውስጥ – ደራሲው እንደሞገተው – ወይ እንደተነበየው – ወይም ውስጣዊ እሳቤያቸውን በሀገር መሪ ህሊና ውስጥ ገብቶ ገልጾ እንዳሣየን – ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምም ሥልጣናቸውን ለቀቁ፡፡ ለእኔ አስገራሚ ግጥምጥሞሽ ነበር፡፡ ለብዙዎችም መጽሐፉን ላነበቡ እንደሚሆንባቸው አልጠራጠርም፡፡

ብዙውን ጊዜ የኛ ታሪክ የሚመዘግበው ጠብመንጃ የተኮሱትን ስለሆነ፣ የዚህ ደራሲ ይህ መፅሐፍ ለሕዝብ ታትሞ ከወጣበት ጊዜና ከተከተለው ክስተት ጋር አብሮ በታሪክ ድርሳናት ላይ እንዲሰፍር መመኘት፣ ለኛ በጠብመንጃ ሥር ተደፍተን ለኖርን ሕዝቦች ቅንጦት እንደሚሆንብን አውቃለሁ። ቢሆንም ደጋግሜ እዘክረዋለሁ።

ለማንኛውም ሀተታዬን እዚህ ላይ ልቋጭና በቀጥታ ወደ ደራሲው ታሪካዊ ጽሑፍ ላሻግራችሁ፡፡ ርዕሱ፦ 《«ጠቅላይ ሚኒስትር «ከቁርበትዎ» ይምከሩ》ነው የሚለው። እነሆኝ ወደ ጽሑፉ፡-

«ጠቅላይ ሚኒስትር «ከቁርበትዎ» ይምከሩ

«ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፡-

«ይሄ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አመት ተመንፈቅ ሞላውም አይደል? «አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር» ማለታችንም እየተዘነጋ ሄደኮ፡፡ አመት ተመንፈቅ የሞላው ስልጣንዎ ልጅ ቢሆን ኖሮ ያለድጋፍ፣ በሁለት እግሩ የሚቆምበትና ያለመውተርተር የሚጓዝበት ዕድሜው ላይ ነበር፡፡

«ስልጣንስ በእድሜ መጨመር በሁለት እግር መቆምና ያለመውተርተር መጓዝ ግዴታው ሳይሆን ይቀራል? ከሰው ራዕይ በተስፋ አንቀልባ መታዘሉም ሳያበቃ ይቀራል?… ዛሬ ይሄን የአመት ተመንፈቅ የስልጣን እድሜ ታሳቢ በማድረግ «ከቁርበትዎ ይማከሩ» ለማለት ወደድኩ፡፡ «ከቁርበትዎ ይማከሩ» ስል…

«… የሰሜን አርሶ አደር ከበድ ያለ የሕሊና ጥያቄ ሲቀርብለት ለመልስ አይቸኩልም፡፡ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ጊዜ የሚወስደው ነፍስ-አባቱን ወይም ሚስቱን አለበለዚያም አምቻ ጋብቻውን ለማማከር አይደለም፡፡ ከበድ ያለ ጥያቄ ይዞ የመጣን ሰው ጊዜ የሚጠይቀው «ከቁርበቴ ልማከር» በሚል ነው፡፡

«እውነትም ደግሞ ከቁርበቱ ይማከራል፡፡ ከቁርበቱ የሚማከር ዕለት በጊዜ ራቱን ይበላል፡፡ መጠጥ በአፉ አይዞርም፡፡ የሚያደክም ቦታ አይውልም፤ ከወትሮው ሰዓት ቀድሞ ይተኛል፡፡ ከቤተሰቡ ሁሉ ማልዶ ወፍ ሳይንጫጫ ይነቃል፡፡

«እንደምንጭ ውኃ ኩልል፣ ጥርት ባለው የማለዳ መንፈሱ የተኛበትን ቁርበት በጣቱ እያንቋቋ ከቁርበቷ ቅኝት ጋር ነገሩን ያወጣል፣ ያወርዳል፡፡ ያለማንም ተፅዕኖና ያለማንም ጣልቃ-ገብነት ውሳኔ ላይ ይደርሳል፡፡ ለአርሶ አደሩ፣ የቁርበቱ ቅኝት የሕሊናው ማደላደያ ናት፡፡ ቁርበቱን ሳያማክር ሐሳቡን አደባባይ ይዞ አይወጣም፡፡

«ጠቅላይ ሚኒስትር፤ «ከቁርበትዎ» የሚማከሩበት ወሳኝ ወቅት ደርሷል፡፡ የሌላ ሰው አምሳያ ስልጣንዎን በእጓለ-ምውታን ልጅነት ተቀብሎ፣ በጉዲፈቻ አባትነት ማሳደግ ሊበቃ የሚገባው ቀን አሁን ነው፡፡ ስልጣንዎ የራስዎ አምሳያ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

««መልኩ» ብቻ ሳይሆን ማጋጊያጫውም ምርጫዎን እንዲከተል ግድ ይልዎታል፡፡ በሰው «ማተብ» በሰው «አልቦ» እና በሰው «ቃጭል» የተብጠለጠለ ሥልጣን ለአሻንጉሊት መንግስትነት መዳረጉን አሌ ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ በሰሜን አርሶ-አደር ስልት በነገሩ ላይ ከቁርበትዎ ይማከሩ፡-

«ከቁርበት በጣት እንደ ክራር መማከር ሕሊናን ማንቃት ነው፡፡ ጥርት፣ ኩልል ባለው የማለዳ መንፈስ ቁርበትን እየቃኙ አደላድሎ በነገሮች ላይ ማሰብን ከእርስዎ የምንጠብቀው ለደንታችንም ጭምር ነው፡፡

«በዚህ ሃያ ሦስት አመት ብዙ የተወላከፈና የጎለደፈ አገራዊ ጉዳይ አለ፡፡ ያፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ባሻቸውና በታያቸው መንገድ ቅርፅና ይዘት ሰጥተው፤ «እፍ» በማለት ነፍስ የዘሩበት አስፈሪ ሁነት ውስጥ እንገኛለን፡፡ በዚህ አስፈሪ ሁነት ላይ ከቁርበትዎ ጋር እንዲመክሩ ግድ ይልዎታል፡፡

«ከኤርትራ ጋር በግፍ ተቆራርጠናል፤ መቆራረጣችን ሳያንስ ሥር የሰደደ ጠላትነት አበጅተና፤ ድንበራችንን በደም አስምረናል፤ ስጋነታችንን ቆራርጠናል፤ እነሱ ያለ እናት እኛ ያለልጅ ቀርተናል፡፡ እነሱ ጉሮሮአችን ላይ፤ እኛ ልባቸው ላይ ቆመናል… ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄን እውነት ከቁርበትዎ ጋር ይምከሩት፡፡

«በሀገር ውስጥም አልደላን፡፡ እኛ ብዙሃን የነፃነት ሽርፍራፊ፣ የመብት እንጥፍጣፊ፣ የሀብት ትርፍራፊ እንኳ አጥተናል፡፡ ተስፋችን ከድንበር ወዲ፣ በስደት ስብዕና ላይ ታንጿል፡፡ ነፃነት፣ መብትና ሀብት ቀድመው ተሰደው ያማልሉናል፡፡

«እነሱን ለማግኘት ሞት የማንፈራ፣ ውርደት የማንጠላ ሆነናል፡፡ ሞትና ውርደታችን የዓለም ማጣፈጫ ጨው ሆኗል፡፡ መታደናችንንና መጨፍጨፋችንን የተቀበልን እንስሳ ሆነናል… ይህ ሁሉ የፖለቲካ ስልጣን ማደላደያ ዋጋ መሆኑ ይቆጫል፡፡

«ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄንን እውነታ ከቁርበትዎ እንጂ ከአማካሪዎችዎ ጋር አይምከሩ፡፡ አሁን አሁን አማካሪነት ረክሶ ቦታው የማይፈለጉ ፖለቲከኞችና የተጠረጠሩ አባሎች መወርወሪያ ወና ክፍል ሆኗል፡፡ ያም ባይሆን ለአንጡራው ሀበሻ ከቁርበት የተሻለ አማካሪ ከየት ሊመጣ? አንዳንዴ ስለቁርበት መማክርትነት እንዲህ አስባለሁ…

«አፄ ዳዊት የመነኑት ከቁርበታቸው የተማከሩ ዕለት ይመስለኛል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ አልማረክም ብለው ራሳቸውን ያጠፉት ከቁርበታቸው የተማከሩ ዕለት መሆን አለበት፤ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ የጀመሩት ቁርበታቸውን ያማከሩ ዕለት…፤

«አፄ ኃይለሥላሴ መአት የወረደባቸው ከቁርበታቸው ባለመምከራቸው፤ መንግሥቱ ኃይለማርያም የሸሹት የሚያማክሩት ቁርበት በማጣት፤ መለስ ዜናዊ አገር የጎነዳደሹት ለቁርበታቸው ጊዜ በማጣት መሆን አለበት፡፡

«እርስዎ ግን ቁርበትዎን ያማክሩ፤ አዋጆችንና ህጎችን ይመርምሩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከሀገር ስጋት ሳይሆን ከግለሰብ ፍርሃት የሚመነጩ ህጎች እንዳሉ ልብ ይሉ፡፡ «የፈሪ ጦሩ፣ እቅፍ ሙሉ» ተብሎ እንደተተረተው ያለ ማለት ነው፡፡

«እቅፍ ሙሉ ጦር ለአንድ ጦረኛ የነጠላ ጦርን ያህል ሙያ እንደማይሰራ ይታወቃል፡፡ እንደውም አንዱን ጦር ሳይቃጠሉ ከእነ እቅፍ ሙሉ ጦር ጠላት እጅ ላይ መውደቅ ይከተላል፡፡

«የዚህ ዘመን ህጎችና አዋጆች መብዛታቸው ለአይን እየከበዱ ኑሮን ለስጋት ዳርገውታል፡፡ ሙያ ሲሰሩ ግን አይታይም፡፡ ከውጭ ጥቃት መከላከያነት ይልቅ የአገር ውስጥ መብት ላይ መፏለያ እቅፍ ሙሉ ጦር ሆነዋል፡፡

«ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ይሄን ይመርምሩ፤ ቁርበትዎን ያማክሩ፡፡ «በሽብርተኛ ህግ ስም ስንት ግፍ ተሰራ? መከራከሪያቸው ሳይሆን ፍርዳቸው ጆሮ እየሳበ፤ በይቅርታ በሉኝ ኩፈሳ ከመንጎማለሉ ምን ተተረፈ? አንሶ ከማሳነስ ውጭ ምን ጠብ አለ?

«ካፈጠጠ ጋር ሁሉ ማፍጠጥ ከመንግስትነት አውርዶ የተራ-አስከባሪ ባህርይ አያላብስምን? በውረድ እንውረድ የጎረምሳ ጠባይ መፍትሄ የሚፈለግለት ነገር አልበዛም?…

«ጠቅላይ ሚኒስትር፤ እንዳላሰለችዎ ፈራሁ እንጂ ጣጣችን ብዙ ነው፡፡ «ለውጭ አልጋ፣ ለውስጥ ቀጋ» የሆነ መንግስትዎ የተራ አስከባሪ ባህሪውን ደማችንን ደመ-ከልብ የሚያደርጉ መንግስታት ላይ ቢተገብር እንዴት በኮራን ነበር፡፡

«ነገር ግን «የምታሸንፈውን ምታ» እንደተባለው ፈሪ ባል «ሽመሉን» ተግባር ላይ የሚያውለው «እቤት» ገብቶ እኛ ላይ ብቻ ነው፡፡ እሱ ያላከበረን አሞሌ ነንና ባለዕዳ ባይቀበለን አይገርመንም፡፡ ይሄ ሁሉ ሰሞኑን የሚመረምሩት፣ ቁርበትዎን የሚያማክሩት ነው፡፡

«ክቡር ሆይ! አንዳንድ ጊዜ መንግስትዎ ፍቺ የሌለው የጅል ስራ ሲሰራ ይታያል፡፡ ለምሳሌ መሬት ወይንጠጅ ይመስል አክርሞ ለማብሰል መሞከሩን እንዴት ያዩታል? አፈናቅሎ፣ አፍርሶ፣ አጥሮ ሳይጠቀምበት ደግሞ ሌላ ማፈናቀልና ማፍረስ ይጀምራል፡፡ እንደወራሪ ጦር ስራው ማፍረስ ብቻ ይሆን እንዴ? ያሰኛል…

«ደግሞስ በዓለም ምግብ እጥረት የተባባሰው የኑሮ ውድነታችን አለም ሁሉ ወደነበረበት ሲመለስ ምነው እኛ ብቻ እዛው ቀረንሳ? ይሄም ከቁርበትዎ ጋር የሚመክሩበት አብይ ጉዳይ ነው፡፡ ሆድን አሸንፎ ማደር የዕለት ተዕለት ጀብዱ ሆኖ ከተሞቻችን «በጀብደኞች» ተጥለቀለቁ’ኮ ጃል!!

«የቋንቋው፣ የብሔሩ፣ የባንዲራው፣ የሕገ-መንግስቱ፣ የፕሬሱ፣ የአንድ ለአምስቱ፣ የሊዙ፣ የሙስናው፣ የቫቱ… ጉዳይ ሁሉ ቁርበትዎን ጠባቂ ነው፡፡ የእነዚህ ነገሮች ሁሉ ባሉበት መቀጠል ስልጣንዎን «የዛር ፈረስ» ጠባይ ይሰጥብዎታልና ከቁርበትዎ ጋር ይምከሩ፡፡

«ይሄን የምልዎ አዳጋችነቱ ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ «የሰይጣንን አመጣጥ የማያውቅ አይመነኩስም» እንደሚሉት ያለ ነው፡፡ የፖለቲካ ምንኩስናዎ የአካባቢ ሰይጣንዎን አመጣጥ ሳይረዳ አልተከናወነም የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ለማንኛውም በዚህም ጉዳይ ላይ ከቁርበትዎ ይምከሩ፡፡»

አበቃ

†የተጠቀሰው ጽሑፍ ምንጭ (ለደራሲው ከልብ ከመነጨ ምስጋና ጋር)፡-

ዓለማየሁ ገላጋይ፤ «መለያየት ሞት ነው» መጽሐፍ፤ «ጠቅላይ ሚኒስትር ‘ከቁርበትዎ’ ይምከሩ»፣ ገጽ 37-40፣ አንደኛ እትም፤ ጥር 2010 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፡፡

የትንቢተኛውን (እና የደፋሩን) ፈላስፋና ደራሲ የዓለማየሁ ገላጋይን ጽሑፍ እዚህ ላይ አመስግኜ አሣረግኹ፡፡ ጽሑፉን እስከ መጨረሻዋ መስመር ያነበበ – ይህ ደራሲ በትክክል የታዩት፣ የሆኑት እና ሊሆኑ ያሉት ክስተቶች ሁሉ – በእርግጥም በእውን እንደሆኑ ማስተዋል አይሳነውም፡፡

ግን ግን… የቀድሞው ጠቅላይ ይህን ጽሑፍ አንብበው ይሆን ወይ? – መልሱን አላውቀውም፡፡ ግን ከቁርበታቸውስ ተማክረው ይሆን ወይ? – በእርግጠኝነት አዎ፣ በደንብ!!!

ለማንኛውም ለዚሁ – በአካል ባላውቀውም በሥራዎቹ ለማውቀው ሣተና ብዕረኛ – ለዓለማየሁ ገላጋይ – አንድዬ የኢትዮጵያ አምላክ – ዕድሜውን፣ ሠላሙን፣ ጤናውን፣ ምክሩን፣ ዕውቀቱን፣ ትዝብቱን፣ ትንቢቱን ሁሉ – እርሱ ለወገኑ፣ ለአንባቢው፣ ለመሪው፣ ለተመሪው ከሰጠው ሁሉ – እጥፍ እጥፉን አባዝቶ አብዝቶ – መርቆ እንዲሰጠው – ከልብ ከልብ ተመኘሁ፡፡

አምላክ – ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ – በያሉበት ሥፍራ – በጸጋው፣ በቸርነቱ፣ በበረከቱ፣ በምህረቱ ይጎብኝልን፡፡ አንድዬ አምላክ ጥበቡን በህሊናችን በልባችን በሁለመናችን አብዝቶ ይግለጥ፡፡ ለሁላችን ከቁርበታችን የምንማከርበት ጊዜና ብልሃቱን አይንሣን፡፡

የብዙሃን እናት – እምዬ ኢትዮጵያ – በፍቅር ሀያል ኃይል ተደምራ – በልጆቿ ጥበብ ተሰማምራ – ለዘለዓለም ፀንታ ትኑር፡፡

Filed in: Amharic