>

*ጦርነት ይብቃን! ውይይት እንጀምር...!!! (ጎዳና ያእቆብ)

ጦርነት ይብቃን! ውይይት እንጀምር…!!!* 

ጎዳና ያእቆብ
ድርድር እና ውይይት  ሲባል ወንጀለኛው ከአንገት በላይ የሆነ ይቅርታ ጠይቆና የሰረቀውን ይዞ ካለምንም ቅጣት የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ ታዝቢያለሁ::
ይህ የሰላም መሰረቱ ፍትህ እንዳልሆነ ካለመረዳት እናም በሀገራችን የለመድነው የቅልድ ይቅርታ ባህል ከመሆኑ አንፃር ነው ብዬ አስባለሁ:: ሌባ የሰረቀውን ይዞ ይቅርታ ብሎ ወይም እስሩን ጨርሶ የሚከብርበት ሀገር ስለሆነ ነው:: አሁን የደረስንበት ቀውስም ከዚህ የሚመነጭ ነው::
ፍትህ በሌለበት ሰላም የለም:: የሰረቀውም ሳይመልስ እና ሳይክስ ይቅርታ የለም::
ወንጀለኛው በወንጀሉ ሳይቀጣ ይቅርታ የለም::
ስለዚህ ውይይት/ድርድር ሲባል የሆነን አካል ከተጠያቂነት ነፃ ለማውጣት የሚመስለንና በዚህ ስሁት አመለካከት ምክንያት ውይይት/ድርድር ሲባል የሚሰማው ተቃውሞና ቁጣ በልክ እናም በእውቀት ቢሆን ጥሩ ነው::
 ግን ድርድር መቼ? እንዴት? የሚሉት መልስ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ናቸው:: መቼም ሰው አፈ ሙዝ ተደቅኖበትም ይሁን ተከቦ ወይም ደግሞ ከባድ መሳሪያ እየዘነበበት ተወያይ ማለት ቀልድ ነው::
ውይይት/ድርድር እና ሰጥቶ መቀበል ፓለቲካዊ እና ማህበራዊ ሲሆን እራስን ከግልፅና ተጨባጭ አደጋ መከላከል ተፈጥሮአዊ ነው:: ስለዚህም የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው:: እራስን ከጥቃት መከላከል የተፈጥሮ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ስለሆነ ማለት ነው::
ትላንት በትግራይ ማኅበረሰብ (ሕዝብ የሚለው ሕዝቦች የሚለውን ስለሚወልድና አንድ ሰው አንድ አካል እንጂ አካላት ሊኖሩት እንደማይችል ሁሉ አንድ ሐገር አንድ ማኅበረሰብ ብዙ ሕዝቦች ኖሮት አንድ ሐገር አንድ አካል ሆኖ መኖር መቀጠል ስለማይችል ነው:: በአንድ አካል ላይ የተለያየ ባህሪ ያላቸው የአካል ክፍሎች እንዳሉት ሁሉ አንድ ሕዝብም ብዙ ባህል ቋንቋ ውግ ልማድ ቢኖረውም አንድ ሕዝብ ከሚለው ጋር ስምም እንጂ ግጭት አይኖረውም:: መጨፍለቅም አህዳዊነት አይደለም) በኃይል ተይዞና ህልውና አደጋ ውስጥ ሆኖ ውይይት ድርድር ሰላም የሚታሰብ አይደልምና በመጀመሪያ ተፈጥሮአዊ የሆነው የህልውና ጥያቄ በሀይልም ይሁን በፀባይ ይከበር ከዛ ባኃላ ስለ ፓለቲካዊ ሀገራዊና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች መነጋገር ይቻላል እንዳልኩ ሁሉ ዛሬም የአማራ እና የአፋር ክልል የጦርነት አውድማ መሆኑ ይቁምና በሞት ሸለቆ ውስጥ ያሉ ሰዎች ህልውና ይረጋገጥና ከዛ በኃላ ስለ ድርድር ውይይት ይታሰብ የሚለው ገዢ ሀሳብ ነው::
ማንም አካል እኔ ህልው ሆኜ እንድኖር ሌላውን አካል ልውረር ላስጨንቅ ልግደል ላስገብር ማለት ቅለል ባለ ቋንቋ ከባልሽ ባሌ ይበልጣል የሚሉት አይነት ነው:: ስለዚህ የተኩስ አቁም ይደረግ:: የተወረሩት ቦታዎች ይለቀቁ:: ከዛም በስምምነት ላይ እንጂ በማንም ግለሰብ ይሁን ቡድን መልካም ፍቃድ (will) ወይም ጊዜአዎ ስሜት (whim) ላይ ያልተመረኮዘ ተኩስ አቁም ስምምነት ያስፈልጋል::
 ተኩስ ከቆመና የዜጎች ሰቆቃ ካበቃ በኃላ ለዘለቂ ሰላም ውይይት/ድርድር ያስፈልጋል:: ውይይት ሲባል ዜጎች በከባድ መሳሪያ እየተጨፈጨፉ ማለት ሳይሆን ጭፍጨፋው ቆሞ: በወረራ የተያዘ ይዞታ ተለቆና ተመልሶ የዜጎች ህይወት ከነክብራቸው እና የደህንነት ስሜታቸው መሆኑን ፓለቲካን በንቃት ለሚከታተሉ ጭምር ማስረዳት አስፈላጊ መሆኑና ይህ ነው የማይባል ቁጥር ያለው አክቲቪስቶች  ጭምር መኖሩ እንኳን በተፋላሚ ሀይሎች መካከል ይቅርና በሀገር ወዳድ ዜጎች መካከልም እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል::
ፓለቲካ ህግ መርህ እና ግልፅ የሆነ አካሄድ አለው:: ለዚህም ነው በትምህርት ደረጃ የሚሰጠውና ሳይንስ ነው የሚባለው:: በስሜት በመነሳሳት ዝም ብሎና ካለምንም ንባብ የሚሆን አይደለም:: አንድ ሺ አንድ ትንተናዎችን በመስማትም የመጫወቻ ህግጋቶቹን ማወቅ አይቻልም::
ውይይት ማለት ምን ማለት ነው? ቅድመ ሁኔታዎቹ ምንድናቸው? የሚሄድበት ሂደትስ ምንድነው? የሚሉ ግልፅ የሆኑ ህጎች ስላሉት ነው  ሀገራት ባይስማሙ እንኳን ተግባብተው የሚሰሩ:: ችግሮቻቸውን የሚፈቱት እናም ወደ ችግሮች የሚገቡት::
 ጦርነትም ህግጋት አሉት በጦነት ጊዜ ያጋጥማል የሚሉ እውቀት አልባ ንግግሮች መጨረሻቸው በጦር ወንጀለኝነት መከሰስ ነው ስንል የነበረው:: ፍትሀዊ ጦርነት እንዴት ነው በአለም አቀፍ ህግ መርህ መሰረት የሚታየው? እራስን የመከላከል ጦርነትስ እንዴት ነው የሚዳኘው?  አፀፋዊ ጦርነትስ በምን መልኩ ነው የሚበየነው? ሲባል መፅሀፉ ምን ይላል ከሚለው ይልቅ እንደየስሜቱ እንደየፍቅርና ጥላቻው ወይም ፍራቻው ፍርድ የሚሰጠው በዝቷል:: ይህ አካሄድ ጤነኛ አይደልም:: መጨረሻውም ጥፋት ነው::
ሰው የሰላም ውል  እንዴት ከጠላቱ ጋር ያደርጋል የሚሉ አሳዛኝ አስተያየቶችን መስማትም የተለመደ መሆኑ ሀገራችን ምን ያህል መከራ ውስጥ እንዳለች ያሳያል:: ወይ ዘመናዊ እውቀቱን አልያዙ ወይ ባህላዊ የእርቅ ስርአትን አላስተዋሉምና በምን ቋንቋ መግባባት ይቻላል የሚል ግርታ ይፈጥራል:: ይህን የምለው ለወቀሳ አይደለም:: ለማሳነስም አይደለም:: ፓለቲካ በእውቀት እንጂ በስሜት አይመራምና ንቁ ተሳታፊ መሆን የሚሻ አጨዋወቱንም የጫወታ ህጉንም መማር አለበት:: በንባብ መታነፅ አለበት:: መዳበር አለበት እንጂ ማሊያ ስላገኙ ብቻ ትጥቅ አሟልቶ ሜዳ ውስጥ መግባት ተጫዋች አያደርግም ለማለት ነው:: ዝግጅት ያልታከለበት ፍላጎት ምን ያህል አጥፊ እንደሆን እያየኝና ውድ ዋጋ እየከፈልንበት ስለሆነ ዘመዴ እንደሚለው በግልፅ ነጭ ነጯን መነጋገር ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነንና ነው::
ህገ መንግስቱን ሳያነቡ የሚያፈቅሩትና በስሙ የሚምሉበት እንዳሉ ሁሉ ሳያነቡት የሚጠሉትና ቀደው ሊጥሉት ቆርጠው የተነሱ ይህ  ነው የማይባል ቁጥር ያላቸው ዜጎች ያሉባት ሀገር ነችና ነው:: ሕዝቤ እውቀት በማጣት ምክንያት ጠፍቷል የሚሉት ሆኖብናልና ነው:: እውቀት ማጣትን ጭንቅላትን እውቀት በመመገብ እንጂ እንዴት እንደዚህ ተባል ብሎ በመቆጣት አይመጣም:: የስድብ ክምርም አንድ እፍኝ እውቀት አይወጣውም:: ወይ ግንበኛነት መማር ነው:: ካልሆነም ግንበኛነትን ለግንበኛው መተው ነው:: ሶስተኛ መንገድ የለውም::
ውይይት ድርድር ሲባል ይሄ እና ያ ተወሮ እንዴት ውይይት ይባላል ብለው የሚቆጡም ውይይት ወረራን መግቻ አንዱ መንገድ እንደሆነና የመወያያ ነጥቦችን የፓለቲካ መፍትሄዎችን አንድ ሁለት ብሎ ቆጥሮ በመወያየት ወራሪውም ከወረረበት ሊወጣ ጦርነትም ሊቆም ዘላቂ ሰላም ሊመጣ እንደሚችል ታሪክም ተሞክሮም ህግም ምስክር ሆነው መቅረብ ይችላሉ:: ትንሽ ጊዜ ሰጥቶና ከስሜቱ ወጥቶ ጥያቄ ለሚጠይቅና ለሚያነብ ሰው::
ኢትዮጵያ በጦርነት አሸንፋ ሳለ የይገባኛል ውዝግ የንበረበቸው ቦታዎች በአልጀርሱ ስምምነት በጦርነት ለተሸነፈው አካል መወሰኑም የቅርብ ጊዜ ትዝታች ነው:: ትላንት በጠላትነት የተያየናቸው መሪዎችም ከዛ ሁሉ እልቂትና ሀገራዊ ክስረት በኃላ እንደወዳጅም እንደ አዳኝ ሲታዩም ታዝበናልና ቢያንስ ስሜት ተለዋዋጭ መሆኑ ተረድተን አቅም በፈቀደ መጠን ለሰላም ለውይይት ለድርድር እድል እንስጥ::
እንዲቆም የምንፈልገውን ወረራን ስለሚገታ: እልቂት ስለሚቀንስ: ፍትህ (ቅጣት:ካሳ) ስለሚጠየቅና ስለሚገኝበት: ነገአችንን ተስፋ ያለው ስለሚያደርግና ኢኮኖሚይችንን የዜጎችን ህይወት በማሻሻል ላይ ማዋል ስለምንችል እናም ጦርነት ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄ ነው ብለን ከተነሳን ከ10 ወራትበኃላ ችግሮቻችን እንኳን ሊፈቱ ይቅርና እየተባባሱ ስለመጡ ለበሽታችን መድኃኒት ብለው የወሰድነው ጦርነት ከበሽታው በላይ ገዳይ እና አውዳሚ ሆኖ ስላገኘነው ነው::
በ10 ወራት ውስጥ ማንም አሸናፊ ሆኖ መውጣት ስላልቻለ ነው:: በሌለን ዶላር እየተገዛ የሚተኮሰው እያንዳንዱ ቀለሀ ዛሬአችንን ስላላሳመረውና ነገአችንን እያጨለመው ስለሆነ ነው:: መፍትሄ ያልነው ችግራችንን ሲያባብሰው እንጂ መፍትሄ ስላልሆነልን ነው:: እቺን ታላቅ ሀገር የአለም የደህንነት ስጋት ተደርጋ እንድትታይ ስላደረጋት ነው::
ስለዚህ  ምን ይሁን?
እንደ እብድ ጦርነትን ደጋግመን እያወጅን በነበርንበት አዙሪት ውስጥ እንኑር ወይስ ሞክረን የማናውቀውን ውይይት በጠረጵዛ ዙሪያ እንሞክረው:: እስቲ አስቡት የተማሪዎቹ ንቅናቄ ከጠየቋቸው የዲሞክራሲ መብቶች የትኛው ቀርቶናል?
መሬት ላራሹ እንዳልተባለ ዛሬ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግስት ጭሰኛ ነው:: እኩልነት በተለዋዋጭ ተረኞች ታፍና ከሞትች ቆይታለች::
ፍትህ ንፁኃንን አስሮ የሚያሰቃዩ መንግስታት እስራኛ ሆናለች:: ሰላም የለም:: እንኳን የዲሞክራሲና ማህበራዊ (Civic Rights) መብቶች ይቅርና በተፈጥሮ የሚገኘው ከሰብአዊ መብቶች አምድ የሚሆነው በህይወት የመኖር መብት እራሱን እንዲህና እንዲያ ብሎ በሚጠራ ታጣቂ ሀይላት በራቸውን ዘግተው በቤታቸው የተቀመጡ ህፃናት አረጋዊያን ነብሰ ጡሮችን ጨምሮ ስም ዝርዝር ተይዞ በብሄርና በሀይማኖት ማንነታቸው ብቻ   በቤታቸው ውስጥ በግፍ የሚታረዱበት ዘመን ላይ ደርሰናል:: የመኖር ነፃነት ትልቅ አደጋ ውስጥ ገብቷል::
አሁን እኛ ካለንበት ሁኔታ የአንበሳ መንጋ አቅራቢያ የሚኖሩ ዋልያዎች የተሻል የህይወት ዋስትና አላቸው:: አናብስቱ ሲርባቸው ለእለት እንጀራቸው እንጂ በቅናት በጥላቻ በኩራት እና በማንነታቸው ምክንያት አይገድሏቸውምና! ከሰው ተራ ከወጣን ብንቆይም ከእንስሳ ተራ ለመውጣት ሩጫችንን ቢያንስ ገታ አድርገን ችግራችንን ጥልቀት ለመረዳት እንሞክር:: ችግርን ማወቅ የመፍትሄው ግማሽ አካል ነውና:: ከዛም ችግራችንን በውይይት ለመፍታት እንሞክር::
ለምን ውይይት?  ካልን አይቀሬ ስለሆነ:: ውጤታማ ስለሆነ:: ዘላቂ ሰልሆነ:: ውጤት ተገማች ስለሆነ:: አቅማችን የሚፈቅደው ያንን ስለሆነ:: ከዘመናት ሰቆቃ በኃላ እፎይ ማለት እንደህዝብ ስለሚገባን:: ስለሚያስፈልገን:: ሰላሳ አመት ተስማምተው የጋጡን ያሰቃዩን የገደሉት ንሰሀ ይሁናቸውና እብሪታቸውን ቀነስ ጥቅማቸውን በልኩ ያርጉትና የሽግግር ጊዜ ፍትህ ያምጡ:: በሰላም ወጥተን እንድንገባ እፎይታ ይስጡን:: የወለድናቸው ልጆች የጦርነት ሰለባ ሳይሆኑ ይደጉልና ለወግ ለማእረግ ይብቁልን:: ወልጆቻቸውን የሚያከብሩ እነሱም የከበሩ ይሁኑልን::
ለልጆቻችን ወዳጅ ያብዙላቸው እንጂ ጠላት አይፍጠሩላቸው:: ማልቀስ ይብቃን! ሀዘን ይብቃን!! ሰላም በሀገራችን በምድራችን ይሁንልን!!! ከምንም በላይ ደግሞ ልጆቻችንን ሀገር አልባ አያድርጉብን!!! ሀገር ፈረሰች እያልና እያሉ እስከመቼ በፍርሀትና በድንጋጤ እንኖራለን?! ይብቃን!!!
አዎን ይብቃን!!! 
በጦርነት ችግሮቻችን የሚቀረፉ ቢሆን ኖሮ እንደኛ በአጭር ጊዜአት ብዙ ጦርነቶችን ያስተናገደች ሀገር ሰላሟ ከኛ አልፎ ለአለም ይተርፍ ነበር!!! ስለዚህም የአካሄድ ለውጥ አድርገን የሰላምን አማራጭ የውይይትን አማራጭ የድርድርን አማራጭ እንሞክር እያልኩ እንደቁራ መጮሁን ተያይዤዋለሁ! ወደፊትም መጮሁን እቀጥልበታለሁ!!!
Filed in: Amharic