>

ጊዜ ነው ጀግና! (ስለ አምናው ባለቀን) አሳፍ ሀይሉ

ጊዜ ነው ጀግና! (ስለ አምናው ባለቀን)

አሳፍ ሀይሉ



«የአምናን ቀን አማሁት፣ ለአፌ ለከት የለው
የዘንድሮው መጣ፣ እጅ እግር የሌለው»

(የአዝማሪ ግጥም)

ከጥቂት ዓመታት በፊት ባዲሳባ በአንዱ ጥግ ከድሮ ወዳጆቼ ጋር የተነጋገርነው ነገር ሰሞኑን ድንገት ትዝ አለኝና እየደጋገመ ህሊናዬን ጨቀጨቀኝ፡፡ ብዙ ዓመት አብረን በወዳጅነት ከዘለቅን (እና ስማቸውን መጥራት ከማልፈልገው) የወያኔ ጓደኞቼ ጋር ጥጋችንን ይዘን የሆድ የሆዳችንን እየተጫወትን ነበር፡፡

ለብዙ ዓመት የፖለቲካ አቋም ልዩነታችን የጓደኝነት ክራችንን ሳይበጥሰው በክፉ-ደጉ አብረን ኖረናልና፣ ብቻችንን እስከሆን ድረስ የልባችንን ፊትለፊት አውጥተን ለመጨዋወት ችግር አልነበረብንም፡፡ እና በመሐል አንድ የልቤን ጥያቄ ጠየቅኳቸው፡፡ ከክፋት አልነበረም፡፡ ከሀዘኔታም ተነስቼ ነው፡፡ ብዙ የወደፊት አላስፈላጊ ነገሮችን አውጠንጥኜ ነው፡፡ እነሱም መንፈሴን ተረድተውት ነበር፡፡ መሰለኝ፡፡ «ለምን ግን ሥልጣናችሁን አትለቁም?» ነበር ያልኳቸው እንደዘበት፡፡

«ለምን ግን ሥልጣናችሁን አትለቁም? በቃችሁ እንጂ!ልቀቁት ሥልጣኑን፣ እስከመቼ ድረስ ነው እንዲህ ሀገር ምድሩን እያስፈራራችሁ፣ እያባበላችሁ፣ እያበላላችሁየምትኖሩት!? ለሌላም አማራጭ ዕድል ስጡ እንጂ!በቃችሁ! ለናንተም ግልግልኮ ነው! በቃ ሁሉም ነገር
ሲበዛ ይመራልኮ!  ! ለምን በሠላም ሕዝቡ የሚፈልገውንመርጦ ያሻውን እንዲኖር አትተዉትም? የምሬን እኮ ነው! እንደክፋት አትውሰዱብኝ! ይህን ብታደርጉኮ ምን ትሆናላችሁ? ታሪክ ነበር የምትሰሩት! ምን  ይመጣብናል ብላችሁ ነው የምትፈሩት?»

አልኳቸው፡፡ ተያዩ እርስበርሳቸው ያለምንም ቃል፡፡ ብዙ አውርተን ስለነበር ሃሳብ ለሃሳብ በደንብ ተግባብተናል፡፡ እኔም የልቤን ተናግሬ ስጨርስ በዝምታቸው ተቀላቀልኩ፡፡ እና በመጨረሻ አንዱ በዕድሜ ከሶስታችንም የሚተልቀው፣ በረዥሙ እየተነፈሰና በቆዘሙ ዓይኖች በደብዛዛው የክፍላችን ብርሃን ላይ በሃሳብ ርቆ እየሄደ.. ረጋ ባለ የትህትና መንፈስ እንዲህ አለኝ፡-

‹‹አሣፌ፣ እኛኮ ሥልጣን መልቀቅ አልቸገረንም፣ በተለይ አሁን አሁን ሁሉም የራሱን ኑሮ መኖር ነው የሚፈልገው፣ ሁሉም ሰልችቶታል፣ ይክፋም ይልማም ሁሉም የራሱን ቤተሰብ መሥርቶ የራሱን ኑሮ እየኖረ ነው፣ ልክ ነው የምንለውንና ያመንበትን አድርገናል፣ ከዚህ በኋላ ይሄን ሥርዓት አንፈልግምየሚልም ቢመጣ፣ አበጃችሁ የሚለንም ቢመጣ፣ እንደፈለገው ያድርገው ብለን ከወሰንን ቆየንኮ እኛ፣ ችግሩ ግን… ምን መሠለህ..?

«ችግሩ በቃን ብለን ሥልጣኑን ብንለቅ… እነሱ አይለቁንም! በሠላም አያስቀምጡንም! ካላጠፉን ሠላም የማያገኙ ብዙ ክፉ ጠላቶች አሉን! ሥልጣኑ ላይሙጭጭ ብለን የቀረነው ያንን እያልን ነው! እውነቱን ልንገርህ? የምናም ነው የለም! ሁሉም ሊያጠፋንና ሊበቀለን አመቺ ጊዜ እስኪመጣለት እየጠበቀ አድፍጦ የተቀመጠ ነው!

«እንጂማ ሰለቸን እኮ እኛ! ስንት ዓመት ይዘለቃል?! ያኔ በበረሃ፣ ደሞ በከተማ፣ ደሞ በዚህ ግባ፣ በዚያ ውጣ እየተባሉ መኖርኮ ይመርራል፣ እኛም ከዚህ
ከፖለቲካ መገላገል ነው የምንፈልገው! ግን… እንዲህ ብለን ወደየቤታችን ብንገባ፣ በህይወት የማያኖሩን አሉ! ለዚህ ነው.. እንጂ ወንበርን ታቅፎ መቅረት
ሳያንገፈግፈን ቀርቶ እንዳይመስልህ! አንድ ቀን ይህን የምልህን ነገር እውነትነት ትረዳዋለህ… ››

ብሎ በምስል ላይ ምስል ሲቀየር ሳታውቀው እንደሚሸጋገር የፊልም ምስል… ቀስ እያለ ደበዘዘ ንግግሩ፡፡ እየተናገረ ዝም አለ፡፡ የዚያን የወዳጄን መልስ ወያኔዎቹም እኔም አብረን በዝምታ ነው የሰማነው፡፡ ብዙ ዓመት አብረን ኖረናል፡፡ በደንብ እናውቀዋለን፡፡ ከልቡ ነበር የሚያወራው፡፡ ማንንም ለመስበክ የተነገሩ ቃላት አልነበሩም እነዚያ ቃላት፡፡

የዚያን ሰው ቃላት ሰምቼ ጥቂት ቆየሁ በፅሞና፡፡ እና ግን በዝምታዬ መቀጠል አልቻልኩም፡፡ አንድ ነገር ማድረግ አለባቸው፡፡ መልሼ እኔ የማስበውን፣ ወያኔዎች ሥርዓቱን አሻሽለው፣ ሁሉን ነገር አመቻችተው በሠላም ህዝብ ለሚመርጣቸው መሪዎች ሥልጣኑን ቢለቁ፣ ምንም የሚመጣባቸው ነገር እንደሌለ፣ የቻልኩትን ሁሉ መልካም ምኞት የተሞላበት ሀሳብና መጪ ዘመን በትህትና ደረደርኩላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ያን ያህል ክፋት ያለው ህዝብ እንዳልሆነም በብዙ የታሪካችን ምሳሌዎች እያስደገፍኩ ለማስረዳት ሞከርኩ፡፡

ሁሉም በተመስጦ ድባብ ላይ ነበር መሰለኝ፡፡ ስናገር ያቋረጠኝ አልነበረም፡፡ በመጨረሻ ያው ሰው፣ አንዲትን ነገር ተናገረኝ፡-

«አሴ፣ ሰዉ ሁሉ እንዳንተ አይደለም!»

የምትል አጭር ሐረግ፡፡ ውዳሴ አይወድም፡፡ ውዳሴ አልወድም፡፡ እነሱም፣ እኔም፣ ማንም አይወድም፡፡ ለዚህ ነው ብቻችንን ስንሆን፣ ከአሽቃባጭና ጮሌ ገለል ስንል ደስ የሚለን፡፡ ስለድሮ የጓደኝነት ጨዋታዎችና፣ ስለተለያዩ የጓዳ ነገሮች እያነሳን የምናወራው፡፡ ስለፖለቲካ ካወራን፣ ሌላ ሰው ከሌለ፣ ማንንም ሳናስቀር የልባችንን እንዳሻን ነበር፡፡ በዚያ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን ለማንም ውዳሴና ሽንገላ ለማዝነብ ዳድቶንም፣ ነካክቶንም አያውቅም፡፡

ግን ያቺ ውዳሴ የመሰለች ቃል ሁሌ በውስጤ እንደተሰነቀረችብኝ ቀረች፡- «አሴ፣ ሰዉ ሁሉ እንዳንተ አይደለም!»፡፡ ወቸ ጉድ! አልተቀበልኩትም፡፡ ውዳሴ አለመሆኑን እያወቅኩትም አልተቀበልኩትም፡፡ ምክንያት ነበረኝ፡፡ በእርግጥ ሰፋ አድርገን ካየነው፣ አዎ! ሰው ሁሉ እንደኔ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰውና ሰው ይለያያል! ማንም ማንንም የሚመስል የለም! ሁሉም የየራሱን ነው! ሁሉም እንደ አሻራው ራሱን ነው፡፡ አዎ ልክ ነው፡፡ ግን ያ ጓደኛዬ ቃሎቹን ያወጣበት መንፈስ ትካዜን ጭምር የተላበሰ ነበርና፣ ከባድ ሸክም ሆነብኝ፡፡

ያ የወያኔው ወዳጄ ያወራበት መንፈስ፣ ከከባድ ሸክም የተነሳ ከዛለ ሰው በወጣ አነጋገር ዓይነት ነበር፡፡ በታከተው አነጋገር፡፡ ከባድ ሸክም ተሸክሞ እየተጓዘ፣ ገና ብዙ መንገድ እንደቀረው እያወቀ፣ ድንገት መሐል ላይ አረፍ ልበል ብሎ ከጫንቃው ላይ ጭነቱን ወደመሬት ያወረደ፣ የሩቅ ለፊ፣ የሩቅ መከራው የሚታየው የሩቅ ተጓዥ ዓይነት የድካም ንግግር ነበር፡፡ ምን ነካው? ለምንድነው እንዲህ የታከተው? ለምንድነው በሰዉ እንዲህ ተስፋ የቆረጠው? ገርሞኝ ነበር፡፡ በዚያው ዝምታ ቆይተን ወደሌላ የሚያስረሳ ነገር ገብተን ታለፈ ምሽቱ፡፡

ሰሞኑን በምን እንደሆነ ባላውቅም ያ ቀን ትዝ እያለ አስቸገረኝ፡፡ የተናጋገርናቸው ነገሮች ደግመው ደጋግመው ትዝ አሉኝ፡፡ ሥልጣን ልቀቁ፡፡ ደክሞናል፡፡ ሁሉም ሰው እንዳንተ አይደለም፡፡ ወዘተ፡፡ ወዘተ፡፡ ወዘተ፡፡ የሚሉት ቃሎቻችን፡፡ እነዚህ ሁሉ ሳቅ ያልጎበኛቸው የውስጥ ጨዋታዎቻችን፡፡ ድንገት በሰው ሀገር ብቻዬን እየተጓዝኩ ትዝ አሉኝ፡፡ ተኝቼም አልፋታ አሉኝ፡፡ እና ራሴን ደጋግሜ ከለስኩ፡፡

በትዝታ ቀስቃሽነት አቋሜን ደጋግሜ ፈተሽኩ፡፡ ምናልባት እነዚያ ወዳጆቼ እውነታቸውን ይሆን? ከዚያ ወዲህ በሀገራችን በተግባር የታየው ነገር፣ በተግባር የሆነው ታሪክ የሚያረጋግጠው የእኔን የዋህነት፣ እና የእነሱን ትክክለኝነት ይሆን? ራሴን ታዘብኩት፡፡

ከኢትዮጵያ ከወጣሁ እነዚያ ሰዎች ምን ላይ አንደሆኑ፣ የት እንደደረሱ አላውቅም፡፡ ከመውጣቴ በፊትም ለብዙ ጊዜያት ሳንገናኝ ቆይተን ነበር፡፡ ሀገሬን ተሰናብቼ ስወጣም አልነገርኳቸውም፡፡ የረሳሃቸውንና የረሱህን ወዳጆች ሁሉ እየጠራህ በል ደህና ሰንብት አይባልም፡፡ ዓለም ጠባብ ነች፡፡ በአንድ ጀንበር ካለም ጥግ እስከ ጥግ ትንቀሳቀሳለህ፡፡ ምን ዜና ሆኖ ነው ካገር ወጣሁ ብዬ ለማውራት የምደውለው የሰው ሰው ጋር? አላደረግኩትም፡፡ አሁን እነዚያን ወዳጆቼን አሰብኳቸው፡፡ እነሱም ያስቡኝ ይሆን? የነገርነው እውነት መሆኑን አሁን አይቶ፣ የሞገተው ሀሳባችን በትክክል ይገባዋል – ብለው ይሳለቁ ይሆን?

ማነው ነገሮችን እንዲህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው? በወያኔዎች ላይ የተረገዘ፣ በምንም ይቅር የማይባል፣ ለዓመታት የተከመረ ጥላቻና ቂም ይሆን ለዚህ ለደረስንበት መጠፋፋት ያበቃን? ወይስ እውነት ሚዲያውን መንግሥቱን በያዙት እንደሚነገረው በወያኔዎቹ የመጠፋፋት ሱስ የተፈጠረ ነው ይህ ሁሉ?

ለመሆኑ ይህን አሁን እየሆነ ያለውን አሳዛኝ ክስተት፣ ወያኔዎች አውቀውት፣ ተዘጋጅተውበት፣ አቅደውት የቆዩበት የታሪክ ምዕራፍ ነበር? ከሆነ… መሪዎቻቸው ለምን እንደዚያ በጠራራ ፀሐይ እየታደኑ የውሻ ሞት ሞቱ? ያ ሁሉ መደናበር፣ ያ ሁሉ እልቂትና ውርደት፣ ያ ሁሉ ዋይታ፣ ያ ሁሉ መርዶ፣ ያ ሁሉ ጥፋትና ውድመት፣ ያ ሁሉ ቂምና በቀል እንዴት ተከተላቸው? እውነት ወያኔዎቹ ይሄ ይመጣብናል ብለው ጠብቀውት ነበር? ወይስ የኢትዮጵያ ህዝብ ሥልጣኑን ከለቀቅን ይቅር ይለናል ብለው – ያኔ በየዋህነት እንደሞገትኳቸው በመሰለ የዋህ ጎናቸው – ገምተው ነበር?

በበኩሌ የሆነው እንደዚያ ይመስለኛል፡፡ እንደዚያ የገመቱ ይመስለኛል፡፡ እንደዚያ እንደገመቱ ያስታውቃል፡፡ ብዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ፡፡ ለዓለም ሀገራት፡፡ ለወዳጅም ለጠላትም፡፡ ብዙ ወትውተዋል፡፡ ብዙ አስተዛዝነዋል፡፡ ብናጠፋም ወገን ነን ብለዋል፡፡ እውነት የሆነው ሁሉ፣ ያን ልመናቸውን ጆሮ ዳባ ያላቸው ህዝብ ያሳረፈባቸው የቅጣት መቅሰፍት ነው? ጥፋታችንን ሁሉ የወለደው ያልሻረ ቂም ነው? ከውስጣችን ሊሽር ያልቻለ የዘመን ቁርሾ ነው? ወይስ እውነት የወያኔዎች የአጥፍቶ መጥፋት ዕቅድ ነው?

እንደኔ እንደኔ፣ ወያኔዎቹ ይህ ይመጣብናል ብለው ያሰቡ አይመስለኝም፡፡ የአብይ አህመድ ከማር የጣፈጠ ምላስ አማልሏቸው ነበር መሰለኝ፡፡ ከገዱ አንዳርጋቸው ጋር ጳጳሳትን ይዘው ላንወጋህ-ላትወጋን የሚል የሽማግሌ እግዚኦታ ሲያወርዱ – ምንም ክፋት አይመጣብንም ብለው ያሰቡ ይመስለኛል፡፡ በብዙው መልክ ብቻችንን ያደረግነው፣ እና ብቻችንን የምንጠየቀው ነገር አይኖርም ብለው ያሰቡ ይመስለኛል፡፡

ወያኔዎቹ ገና በጊዜ፣ ኢትዮጵያን አብረው በመውጋት ከሚታሙባት የበረሃ ወዳጃቸው ከሻዕቢያ ጋር ሲቆራረጡና አፈሙዝ ሲማዘዙ፣ ወያኔዎቹ ወገንተኝነታቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ከኤርትራ ጋር አለመሆኑን በተግባር ደማቸውን ምሥክር አድርገው እያረጋገጡ መሰለኝ፡፡ ይሆን? ወያኔዎቹ በሀገሪቱ ሁሉ መንገድ ሲሰሩ፣ ከየብሔሩና ጎሳው ጋር ሲወዳጁ፣ ያንንም ይሄንንም ለመጥቀምና የሥርዓታቸው ተሠላፊ ለማድረግ ሲጥሩ አንድ ቀን የከፋብን ዕለት ለምህረት ይሆነናል ብለው አስበው መሰለኝ፡፡ ይሆን?

ወያኔዎቹ የአባይ ግድብን እንገነባለን ብለው የኢትዮጵያ ነገሥታት ሁሉ ሲያልሙትና ሲመኙት የነበረውን ነገር መጀመራቸው፣ ሀገሪቱን ግድብ በግድብ ለማድረግ የሮጡት ሩጫ፣ ከቻይናና ከአሜሪካ፣ ከአይ ኤም ኤፍና ከዎርልድ ባንክ እየተበደሩ የገነቧቸው መዓት ነገሮች ኋላ ኃጢያታችንን ያካክሱልናል ብለው አስበው መሰለኝ፡፡ ይሆን?

ወያዎቹ አዲሳባ ላይ ያካሄዱት መጠነ ሰፊ ግንባታና ከተማዋን ለመቀየር፣ ትላልቅ በጎ አሻራቸውን ትተው ለማለፍ የተሟሟቱት ሁሉ፣ ምናልባት ከሥልጣናችን ስንለቅ፣ ቢያንስ ሰው በዓይኑ የሚያየውን በጎ ነገር ለማስተዛዘኛ ትተን እንለፍ ብለው ተመኝተው መሰለኝ፡፡ ግን እንዲያ አስበው ይሆን?

ብዙ ነገሮችን አሰብኩ! ብዙ እነርሱ ሠርተናቸዋል የሚሏቸውን በጎ ነገሮች አወጣሁ አወረድኩ! እና ሳስበው… ወያኔዎቹ… በይፋ ባይናገሩትም፣ እልህ ቢተናነቃቸውም፣ ጥፋትም ቢኖርብን፣ ይኸው ሥልጣኑን ለቅቀናል፣ ይክፋም ይልማም ሀገርን አስተዳድረናል፣ ብንከፋም ብንለማም ለሀገር ስንል የቻልነውን አድርገናል፣ የበደልነውን ህዝብ ለመካስ የቻልነውን ጥረናል፣ ጥረታችንን አይታችሁ ይቅርታ አድርጉልን… ለማለት ፈልገው መሰለኝ አሁን፡፡ ይሆን? እንደዚያ እያሉን ይሆን ግን?

ብዙ ጊዜ አስበዋለሁ ወያኔዎቹ የደረሰባቸውን ነገር! የገቡበትን አስከፊ አጣብቂኝና አሰቃቂ እጣፈንታ፡፡ አሳቃቂ መነጠል፡፡ ከኢትዮጵያ መሪነት፣ ወደ ኢትዮጵያ ጠላትነት የመሸጋገር (ቢያንስ የመፈረጅ) አስከፊ ጉዟቸው፡፡ ብዙ ጊዜ አስበዋለሁ፡፡

ከወያኔዎቹ ጋር ተሻርከው የኢትዮጵያን ህዝብ ሲግጡም ሆነ ሲያንቆራጥጡ የነበሩት ሁሉ እንዴት፣ እና በምን ተዓምር ሁሉን ነገር በወያኔዎቹ ላይ አላክከው፣ እነሱ ከደሙ ሁሉ ንጹህ፣ ወያኔዎቹ ደግሞ የሁሉም በደልና ሀጢያት ተሸካሚዎች ሆነው ሊቀርቡ እንደቻሉ? ብዙ ጊዜ አስበዋለሁ..! ብዙ ጊዜ ተደንቄ አላባራም፡፡ የዚህ ሁሉ አሳዛኝ ትያትር ዳይሬክተር ማን ይሆን?

የእነዚያን ወያኔ ጓደኞቼን ከልብ የተነገረ ሥጋት አሁን ላይ አስበዋለሁ..! እኛ ከሥልጣን ብንለቅ… አይለቁንም! የማይለቁን፣ የሚያጠፉን፣ ቂማቸውን ሊወጡ ጊዜ የሚጠብቁት ናቸው በእግራችን የሚተኩት…! ከሥልጣን ብንለቅ ያሳድዱናል! የሚል ሰቀቀናቸው ሁሉ ይመጣብኛል አሁን፡፡ የተለሳለሰ ተተኪ ሲጠባበቁ… ሁለት ልብ ሆነው.. ‹‹የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል›› የሆነባቸው ይመስለኛል አንዳንዴ ዝም ብዬ ሳስበው፡፡

‹‹ሁሉም ሰው እንዳንተ አይደለም!›› ይቺ አባባልም ደጋግማ ትመጣብኛለች፡፡ አዎ ሁሉም ሰው እንደኔ አይደለም፡፡ መሰለኝ፡፡ ያለምንም ማጋነን እንደማስበው፣ የወያኔዎቹን ታሪክ በሚገባ አውቃለሁ፡፡ የወያኔዎቹን የተሳሳተም፣ ክፋትም ሆነ አለማወቅ የሞላበት ብዙ ነገራቸውን አውቃለሁ፡፡ ብዬ አስባለሁ፡፡ እነሱን በምክንያት አብጠልጥዬ ስተች፣ ራሳቸውም ምላሽ እስካይኖራቸው ድረስ ነበር፡፡

ብዙ ነገር በቅንነትም፣ በብስጭትም ከእነርሱ ያየሁት ህጸጽ አለ፡፡ ብዙ፡፡ ሆኖም አንድ የማምንበትና ሁልጊዜም የማልረሳው አንድ ነገርም ግን አለ፡፡ የሰው ልጅ አንድን ነገር ብቻ ሆኖ እንዳልተፈጠረ፡፡ የሰው ልጅ በፍጹም አንድን ነገር ብቻ ሆኖ አልተፈጠረም፡፡ ወደፊትም አይፈጠርም፡፡

ወያኔዎቹ የፈለጉትን ያህል ክፉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በቻሏት አቅም ጥሩ ነገር ሠርተው ለማለፍ፣ ስማቸውን አስጠርተው፣ ሥርዓታቸውን ተክለው፣ የአፍሪካ የዓለም ሞዴል አድርገው ለማለፍ የተፍጨረጨሩትም ደግሞ ብዙ ነገር አለ፡፡ ስኬታማ የሀገር አስተዳዳሪ ለመሆንም፣ ለመባልም፣ ብዙ ጥረዋል፡፡

የሚወደሱበት፣ በሥልጣንም የሚሰነብቱበት፣ ስኬታማ ኢኮኖሚ ለመፍጠር! ብዙ ጥረዋል፡፡ ሀብታሞችን ለማብዛት! ብዙ ጥረዋል፡፡ ሀገሪቱን በመሰላቸው መንገድ ለመቀየር! ብዙ ጥረዋል፡፡ ህዝቡን በመሠላቸው መንገድ ለመያዝ! ብዙ ጥረዋል፡፡ የግድ የእኔን ዓይነት ሀሳብ ይከተሉ አልልም፡፡ በራሳቸው መንገድ ግን ለአንዲትም ቀን ብትሆን – ከነክፋታቸው – ሐገርን ተረክበው አስተዳድረዋል፡፡

ይህን የሰውን ልጅ የክፉነትና የበጎነት ተቃራኒ ገጽታ መርሳት የሰውን ልጅ ተፈጥሮ መካድ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የሣንቲሟን ተቃራኒ ገፅ ከስሌቶቼ ላወጣ የምችል ፍጥረት አይደለሁም፡፡ ራሴን ተቃራኒ ገጽ አለብኝ፡፡ ሁሉም አለበት፡፡ ሁሉም ይገኝበታል፡፡ ወይም ይገኝለታል፡፡

ለጎፈሩ ተስተካከይ የሆነ፣ የላሟን ተቃራኒ መንታ ገጽ መስጠት የማይገባ ከመሰለኝ፣ ቢያንስ የሳንቲሟን ክርክር የምታህል የጎማ ጠርዝ ጥሩ ነገር ትወጣቸዋለች ብዬ እንደ ፍርድ ማቅለያ ለክፉዎች እይዝላቸዋለሁ፡፡ የማርያም መንገድ የማይገባው ፍጡር የለም ብዬ አምናለሁ፡፡

የወያኔዎቹን ህጸጽ ሳሰላም፣ ይሄን ነገራቸውን እቆጥረዋለሁ፡፡ ወያኔዎቹን ብቻ ሳይሆን፣ ህጻናት ልጆቻቸውን፣ አቅመደካማ እናት አባቶቻቸውን አስባቸዋለሁ፡፡ ምንም የማያውቁ ዘመዶቻቸውን አስባቸዋለሁ፡፡ ከማንኛውም የኢትዮጵያ ምስኪን ደሃ የማይለይ ምስኪን ዘራቸውን አስበዋለሁ፡፡ እና አጥብቄ የምተቻቸውን ያህል፣ ሆዴ ይራራል፡፡

ስለ እነርሱ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ስለ ሁሉም፡፡ ስለማንም ነው፡፡ ስለ መንግሥቱ ኃይለማርያምም፣ ስለ አጼ ኃይለሥላሴም፣ ስለ ጄኔራል አማን አንዶምም፣ ስለ ጄ/ል ተፈሪ በንቲም፣ ስለ ልጅ እያሱም፣ ስለ ንግሥት ዘውዲቱም፣ ስለ አፄ ምኒልክም፣ ስለ አፄ ዮሀንስም፣ ስለ አፄ ቴዎድሮስም፣ ስለ ንጉሥ ተክለሀይማኖትም፣ ሌላ ቀርቶ ስለ ግራኝ መሀመድም እንኳ ሳይቀር.. ስለሁሉም አነሳስና አወዳደቅ ሳስብ፣ የአወዳደቃቸው መቅሰፍት መክፋት… ይሄንኑ አሁን የሚሰማኝን የመሰለ የርህራሄ መንፈስ ያመጣብኛል፡፡ አዘኔታ ይጸናወተኛል፡፡

የሆነ ያልተሳካለት፣ የከሰረ፣ የወደቀን የቀድሞ ባላንጣህን አይተህ፣ የወደቀን መልሰህ እንደማትረግጠው፣ የተሸነፈን፣ እጅ የሰጠን እንደማትገድለው፣ ጊዜ የጣለውን እንደማትዘባበትበት ዓይነት የአዘኔታ ስሜት ይሰማኛል፡፡ በተወሰነ መልኩ ሊታዘንላቸው፣ በተወሰነ መልኩ ጥሩ ነገር ሊሰሩ የጣሩት ሁሉ ግምት ውስጥ ሊገባላቸው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ የሆነ ርትዕ እንደሚያስፈልጋቸው አምናለሁ፡፡

ይህ ሁሌም የማምንበት መርሄ ነው፡፡ ቅድም ብዬዋለሁ፡፡ ማንም እና ምንም ነገር አንድን ነገር ብቻ ሆኖ የተፈጠረ የለም፡፡ ወደፊትም የሚፈጠር የለም፡፡ ክፉ ብቻ የሆነ ፍጡር፣ ጥሩ ብቻ የሆነ የሰው ልጅ የለም፡፡ ወያኔዎቹ ክፉዎች ናቸው፡፡ ሁሉም ወያኔዎ ግን ክፉዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሌላ ቀርቶ ክፉዎቹም ወያኔዎች፣ ሁልጊዜ ክፉዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የመጨረሻዎቹ ክፉ ሰዎች በምንላቸው ላይ እንኳ፣ አስተውለን ካየንላቸው፣ አንዲት ጥሩ የምንላት ነገር አትታጣባቸውም፡፡ ይሄንን ነው የማስበው፡፡ ሚዛን ማለት ይሄ ነው፡፡

ሚዛን ማለት አንዱን ነገር ብቻ ያለመቆለል ርትዕ ማለት ነው፡፡ አንዱን ስንሞላ ሌላውን ላለማጉደል ማሰብ ማለት ነው፡፡ ለወደድነው ፅድቁን ብቻ እየመረጥን መቆለል፣ ለጠላነው ክፉውን ብቻ እየመረጥን መቆለል – ይሄ ሚዛን የማጣታችን ነገር ይሆን – ለዚህ ሁሉ ሀገራዊ ምስቅልቅልና ጥፋት የዳረገን? እላለሁ አንዳንዴ፡፡ ‹‹አሴ፣ ሰው ሁሉ እንዳንተ አይደለም››፡፡ ወቸጉድ! ሰሞኑን ብዙ ጨቀጨቀኝና ነው ይህን ሀሳብ ያወጣሁት፡፡ አንድ ከብዙ ካቻምናዎች መሐል የማልረሳውን ትዝታዬን አንስቼ ልሰናበት፡፡

አንድ ቀን ነው፡፡ ሜክሲኮ አካባቢ፡፡ ቡናና ሻይ ፊት ለፊት፣ ከጉምሩክ ተጎራብታ በነበረችው ‹‹እናት ጓዳ›› ምሳ በልተን ስንወጣ፣ የቤቱ ባለቤት የበላተኛውን ሂሳብ በልቶ ወደውጭ ወጥቶ እጁን ከታጠበ በኋላ፣ አስፋልት ዳር በዚያ ሁሉ ግርግር መሐል ቆማ ትቀበላለች፡፡ የሰጣት ይሰጣታል፡፡ ያልሰጣትን ቀና ብላ አታይም፡፡ ገረመኝ፡፡

እምነቷ፡፡ የዋህነቷ፡፡ አለመስገብገቧ፡፡ የከፈለው ብቻ ከከፈለኝ ይበቃኛል፣ በዚያም አትራፊ ነኝ – ብላ ማሰቧ ገረመኝ፡፡ የቸገረው ካልሆነ ሳይከፍል አይሄድም፣ ከቸገረው ደሞ በልቶ ይሂድ፣ ይቅር አይክፈለኝ – የሚል አቋሟ ልቤን ነካው፡፡ ሩህሩህ ሴት እወዳለሁ፡፡ እና ወደድኳት፡፡

አንድ ቀን ቀረብ ብላ ስታዋራን፣ እስቲ ከራሷ አፍ ልስማው ብዬ ያልቸገረኝን ነገር ጠየቅኳት፡-

«በመጣሁ ቁጥር አይሻለሁ፣ ግን የገረምሽኝ ነገር፣
ሰዉ ሁሉ ጨርሶ ወዳንቺ እየመጣ ነው ሂሳብ የሚ
ሰጥሽ፣ ይዞብሽ የሚሄድ ቢኖርስ?»

አልኳት፡፡ የሰጠችኝን ምላሽ እስከዛሬም አልረሳሁትም፡፡ አሁን ልናገረው የፈለግኩትም እሷ ያለችኝን ነው፡፡ ኩም ብዬ ቀረሁ፡፡ ወይም አስቀረችኝ፡፡ እንዲህ ነበር ያለችኝ፡-

«አንተ በልተህ ሳትከፍል ሄደህ ታውቃለህ?»

የምለው ጠፋኝ፡፡

«እኔ…? እኔማ ሳልከፍል ሄጄ አላውቅም!»

አጅሬ ልታቆም ነው? አፋጠጠችኝ፡-

«ታዲያ አንተ የማታደርገውን ነገር፣ ለምን ሌላው
ሰው ያደርጋል ብለህ ገመትክ?»

ተሸማቅቄ ቀረሁ፡፡ «ሰዉ ሁሉ እንደኔ አይደለም!» ልበላት? – በፍፁም!! ልላት አልችልም፡፡ ከሰው የተለየሁ ንፁህ አይደለሁም፡፡ ማነው ጻድቅ ሰው? ማን ነው ከማን የበለጥኩ ጻድቅ ነኝ ለማለት የሚበቃ? የዚያች ልጅ አንገት-አስደፊ ቃል እስካሁን በብዙ የህይወቴ እርምጃዎች ሁሉ የሚታወሱኝ ቃላት ሆነው ቀሩ፡፡ እና ያች የምግብ ቤት ልጅ፣ ለእኔ የህይወት ዘመን ትምህርቴ ሆና ቀረች፡፡

ከዚያች ትምህርት ብዙ ዓመታት በኋላ ነበር፣ ያ የዕድሜ የበለጸገ ወያኔ ወዳጄ፣ በዚያች የሆድ የሆዳችንን እያወራን አረፍ ባልንባት አንዲት የምሽት ጥግ፣ በታከተ ድምጽ፡- «አሴ፣ ሁሉም ሰው እንዳንተ አይደለም!» ያለኝ፡፡ እና አልቀበልህም ብዬ የሞገትኩት፡፡ ምን አሟገተኝ? እኔ ከሰው የተለየሁ አይደለሁማ፡፡ ድርቅ አልኩበት፡፡ አሁንስ? አሁንስ ትክክሉ ማነው?

እውነት ሰዉ የምህረትና የይቅርባይነት፣ የእርቅና የመርሳት፣ የሚዛንና የማስተዛዘን ዕዝነ ልቦና ሳይኖረው ቀርቶ ነው? እውነት ሕዝባችን ርትዕ የለውም? አላውቅም! ብዙ ነገሮችን አላውቅም! እያወቅከው በመጣህ ቁጥር እያላወቅከው የምትመጣው ህዝብ ሁሉ ይመስለኛል ሕዝባችን! ህዝብ አይሳሳትም – በሚለው መርህ አምናለሁ፡፡

ምክንያቴ ደግሞ ህዝብ ለዋዋቴ አለመፍጠኑ ነው፡፡ ሕዝብ እንደ ግለሰብ እፍፍ ብሎ አለመክነፉ ነው፡፡ በዘመናት በተግባር የተፈተሹ እውነቶችን የሙጥኝ ማለት ስለሚመርጥ ነው ሕዝብ፡፡ ሕዝብ አይሳሳትም በሚለው የማምነው፡፡ ነገር ግን ይህን ሳምን፣ አንዲት ማሻሻያም ጨምሬበት ነው፡፡ «ሰው እስካላሳሳተው ድረስ!» የምትል፡፡

ከአሳሳቾች ይሰውረን፡፡ እዝነታችንን ይመልስልን፡፡ ‹‹«ዓይን ያወጣ፣ ዓይኑ ይውጣ!» በሚለው የሙሴ ህግ ከሄድን፣ በመጨረሻ ሁላችንም ዓይነሥውራን ሆነን መቅረታችን ነው›› በማለት በጋንዲ አንደበት የተነገረው የሠላም ቃል በህሊናችን ያቃጭል፡፡ የአባቶቻችን እርቅ ይታወሰን፡፡ የተሸነፈን ንጉሥ ቁስል ያበሰችው፣ የእምዬ የእምባቦ ላባ ትዝ ትበለን፡፡ እንማማር፡፡ ይቅር ለእግዜር ለማለት ልባችንን እናዘጋጅ፡፡ ጥላቻ ይብቃን፡፡ መጠፋፋት ይብቃን፡፡ እንኑር በፍቅር፡፡ እንኑር፡፡

Live and let live!

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡

Filed in: Amharic