>

ህወሓት እና ኢትዮጵያ ከጥቅምት 2013 በኋላ...!!!  (ዶ/ር ታደሰ ብሩ ከርሰሞ)

ህወሓት እና ኢትዮጵያ ከጥቅምት 2013 በኋላ…!!!

 (ዶ/ር ታደሰ ብሩ ከርሰሞ)

_________________________________

ሳምንታት ብቻ የቀሩት የትግራይ ክልል ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ “በከፍተኛ የሕዝብ ድምጽ” ያሸነፈው ህወሓት የሚቀጥለው መስከረም ላይ አዲስ መስተዳደር ያቋቁማል። ከዚያስ? እኔ ህወሓት የትግራይን ነፃ መንግሥትነት የሚያውጅ ወይም አቶ ጌታቸው ረዳ እንደተናገረው de facto state (dfS) ለመሆን የሚመርጥ አይመስለኝም። የህወሓት ምርጫ ከዚህ የከፋ ነው የሚሆነው።
“የቢሆንስ ትንተና” (scenario) ሲዘጋጅ “ተዋንያን” ጥቅሞቻቸውን የሚያውቁና በሥርዓት ማሰብ የሚችሉ ሰዎች እንደሆኑ አድርጎ መገመት ይገባል። እኔም የህወሓት ስትራቴጂስቶች ጥቅሞቻቸውን ያውቃሉ፤ ያሰላስላሉ፤ የሚበጃቸውን መንገድ ይመርጣሉ ብዬ ማሰብ እፈልጋለሁ። በዚህ እሳቤ መነሻነት ነው የሚከተለውን የምጽፈው።
ትግራይን de facto state (dfs) ለማድረግ “ከዛሬ ጀምሮ ትግራይ ራሷን የቻለች ነፃ አገር ናት” ብሎ ማወጅ ይጠይቃል። የአንቀጽ 39 መኖር አለመኖር ይህን ለማድረግ የሚኖረው ፋይዳ እምብዛም ነው። ማወጅ ከፈለጉ አንቀጽ 39 ኖረም አልኖረም ይችላሉ። ቁምነገሩ “በማወጃቸው ምን ያተርፋሉ?” ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነት ሳይኖር መንግስትነታቸውን የሚያውቅላቸው አንድ አገር እንኳን የሚያገኙ አይመስለኝም። ከዚህም በተጨማሪ ነፃነት ባወጁ ማግስት በዙሪያቸው ካሉ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሱዳን) እንዲሁም ክልሎች (አፋርና አማራ) ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ።
ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ወዲህ ተገንጥለው እውቅና ያገኙ አገሮች ሶስት ብቻ ናቸው (1) ኤርትራ፣ (2) ምስራቅ ቲሞር እና (3) ደቡብ ሱዳን፤ ሶስቱም ከህግ አንፃር የተሳካ መገንጠል የፈፀሙት ቀድሞ አካል የነበሩባቸው አገር መንግስታት ድምፀ ውሳኔ አሰጥተው እንዲሄዱ ስለፈቀዱላቸው ነው። ይህንን “ፈቃድ” ለማግኘት ደግሞ እያንዳንዳቸው ለአስርት ዓመታት ተዋግተዋል። በተከፋ ጊዜ ሁሉ “እገነጠላለሁ” የሚለው ልሂቅ ይህን ሳያገናዝብ የሚናገር ነው።
በራሳቸው ፈቃድ ነፃነታቸውን አውጀው ቀድሞ አካል የነበሩነት አገር መንግስት ባለመፍቀድ የሌሎች አገራት አገሮች እውቅና ለማግኘት የተቸገሩ አገሮች ቁጥራቸው ከላይኖቹ ይበልጣል። እነዚህ አገሮች ናቸው de facto state (dfs) የሚባሉት ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ወዲህ የተፈጠሩ 5 dfs አሉ –
1) 5 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ፍልስጤም (The State of Palestine) 138 አገሮች እውቅና ሰጥታል ለተቀሩት dfs ናት፣
2) 3.8 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኮሶቮ (Republic of Kosovo) 97 የ UN አገሮች እውቅና ሰጥተዋታል፣
3) ደቡብ ኦሴቴ (Republic of South Ossetia) 5 አገሮችና ሁለት dfs እውቅና ሰጥተዋታል፣
4) 250 ሺ ሕዝብ ያላት አብሃዚያ (Republic of Abkhazia)6 አገሮችና 3 dfs እውቅና ሰጥተዋታል፣
5) 200 ሺ ሕዝብ ያላት አርሳክ (ናጎርኖ ካራቫኽ) 3 dfs እውቅና ሰጥተዋታል,
6) ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ፕሪድኔስትሮቫ (Pridnestrovian Moldavian Republic) 3 dfs እውቅና ሰጥተዋታል እና
7) 3.6 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሶማሊላንድ (Republic of Somaliland) እስካሁን እውቅና የሰጣት አገር ባይኖርም ከብዙ አገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት አላት።
ትግራይ ነፃነትዋን ብታውጅ ማንን ትመስላለች የሚለውን ለማጥናት ከላይ ከተዘረዘሩት ሁሉ አገሮች ውስጥ (1) እና (2) የተለየ ታሪክ ያላቸው በመሆኑ ማውጣት ይገባል። በዝርዝሩ ከቀሩት ውስጥ የህወሓት ሰዎች በሞዴልነት የሚያይዋት ሶማሊላንድ ብቻ ትሆናለች። ሶማሊላንድ የትግራይን ልሂቃን የሚያማልሉ ነገሮች አሏት፤ ለ 29 ዓመታት እውቅና ባታገኝም እውቅና ካላቸው አገሮች ባላነሰ ሁኔታ ትገኛለች። እኛሽ ከሷ በምን እናንሳለን ለማለት የሚዳዳቸው ይመስለኛል።
ረጋ ብለው ሲያስቡት ግን ትግራይና ሶማሊላንድ ለየቅል መሆናቸውን ለመረዳት አይቸግራቸውም ብዬ እገምታለሁ። ሶማሊላንድ በነፃነት ለመቆየት የረዷት ሁኔታዎች ትግራይ እንደሌላት ለመረዳት እጅግም አይቸገሩም። እነዚህም
(1) የሶማሊያ መንግስት መዳከም፣
(2) የጎረቤት ባላንጣ የሌላት መሆኑ፣
(3) ውስጣዊ አንድነቷ ከሶማሊያ በጣም የተሻለ መሆኑ፣
(4) ብዙ ወዳጆች ያሏት መሆኑ – እንግሊዝ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ኬንያ (እውቅና ለመስጠት እየዳዳት ነው)፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ወዘተ፣
(5) ስትራቴጂያዊ አቀማመጧ፣ እና
(6) ዲያስፒራዋን በሚገባ መጠቀሟ።
በአሁኑ ሰዓት ትግራይ ከእነዚህ ውስጥ አንዱም የላትም። ጥቂቶቹን ግን አቅደው ቢሠሩ የሚያመጧቸው አድርገው እንደሚወስዱ እገምታለሁ – በተለይም የመጀመሪያውን።
የፌደራል መንግስት ከተዳከመ የህወሓት ስትራቴጂያዊ አማራጮች ይሰፋሉ። ከፈለጉ ከሌሎች አጋሮች ጋር የፌደራል መንግስትን ጥሎ የፌደራልን ስልጣን መጋራት ይችላሉ፤ አሊያም ያኔ de facto state ማወጅ ይችላሉ። የፌደራል መንግስትን ማዳከም ለህወሓት ቁልፍ የአጭር ጊዜ – አጣዳፊ – ግብ ነው። ህወሓት ይህንን ለማሳካት የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም።
የፌደራል መንግስትን ለማዳከም ህወሓት ከማናቸውም ኃይል (ከአልሸባብ እና ISIS ጭምር) ከመተባበር ወደኋላ የሚል አይመስለኝም። ባጭሩ ከመስከረም 2013 በኋላ በህወሓት አመራር ስር የምትገኘው የትግራይ ክልል የአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነት ማዕከል ትሆናለች። የጠ/ሚ አቢይ አሕመድ መንግስት ይህን ሁኔታ በዚህ መንገድ ስለመረዳቱ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለኝ።
በለውጥ ቲዎሪ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የኃይል ሚዛን ጥናት ነው። የለውጥ ደጋፊዎችና የለውጥ ተቃዋሚዎችን ኃይል በየጊዜው መመዘን ይገባል። የለውጥ መሪ ሁለት ዓይነት ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተግባራዊ እንዲያደርግ ይመከራል።
1) የለውጡን ደጋፊዎች ኃይል የሚያጎለብቱ ስትራቴጂዎች፣ እና
2) የለውጡን ተቃዋሚዎች ኃይል የሚያዳክሙ ስትራቴጂዎች
ከሁለቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሁለተኛው ነው – የለውጡን ተቃዋሚዎች ኃይል ማዳከም።
የለውጥ ደጋፊዎች ኃይል ማጠናከር የአዳዲስ ተቋማት ግንባታ የሚጠይቅ በመሆኑ አድካሚና ጊዜ የሚወስድ ነው። ስለሆነም የለውጥ መሪ ቀዳሚ ትኩረት መሆን ያለበት የለውጥ ተቃሚዎችን ኃይል ማዳከም ነው። ይህ ለማንኛውም ዓይነት ለውጥ የሚሠራ ንድፈሀሳብ ነው።
የጠ/ሚ አቢይ መንግስት ድክመት እዚህ ላይ ይመስለኛል፤ የለውጡ ተቃዋሚዎች ኃይላቸውን እንዲያሰባስቡ ዕድል ሰጥቶዓቸዋል። ከመስከረም 30 2013 ጀምሮ በልበሙሉነት “ተመርጠንበታል” የሚሉት ክልል እንዲኖራቸው ፈቅዷል። የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መንግስት ህወሓት በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ፣ በደቡብና በአዲስ አበባ የተደራጁ ተከታዮች እንዲኖሩት ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በቅርቡ የተጀመረው ህግ የማስከበር ሥራ መወሰድ የነበረበት ከመጀመሪያው ቢሆንም ዘይግይቶም መደረጉም መልካም ነገር ነው። አሁንም ግን ለህወሓት አጋር የሚፈጥሩ ተግባራት በደቡብም በአዲስ አበባም እየተፈፀሙ ነው።
ህወሓት ትግራይ ውስጥ Terrorist Semi State (TSS) በመሆን በቀጠናው ያሉ እኩይ ኃይሎች ሁሉ በማስተባበር ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ኤርትራንም ሱዳንንም ችግር ውስጥ መክተቱ የማይቀር ነው። ጠ/ሚኒስትሩና አማካሪዎቻቸው የህወሓትን ጉዳይ በቸልታና በንቀት መመልከታቸው ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ቡድናቸው ስህተቶቻቸውን ለማረም ያላቸውን ጊዜ አጭር ነው፤ ይጠቀሙበት። ያ ካልሆነ የራሳቸውን ስልጣን ብቻ ሳይሆን የሚወዷትንና የምንወዳትን ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል
Filed in: Amharic