>

አዲስ አበባ የወንጀል መናኸሪያ!!   (የፍትሕ መጽሔት ርእስ አንቀጽ)

አዲስ አበባ የወንጀል መናኸሪያ!!

  (የፍትሕ መጽሔት ርእስ አንቀጽ)

የወንጀል ድርጊቶች በየትኛውም የዓለማችን ከተሞች ትላንትም ሆነ ዛሬ ያለና የተለመደ መሆኑ ይታወቃል። ሌላው ቀርቶ፣ ወንጀልን በረቀቀ ቴክኖሎጂ እየታገዙ ለመከላከል የተደራጁ የጸጥታ ተቋማት በላቡት አገራት ሳይቀር፤ በተለይ ግድያ፣ ስርቆት፣ ሕገ-ወጥ ንግድ፣ የትራፊክ አደጋ እና የመሳሰሉት የወንጀል ዐይነቶች በከፊል እንጂ፤ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አለመቻሉ ይታወቃል። ይህም ነው፣ ችግሩን በሦስተኛው ዓለም አገራት ብቻ ሳይሆን፤ በዘመናዊ መሳሪያዎች እና በፖሊስ ሳይንስ የሰለጠኑ ሙያተኞች በተሰማሩበት አሜሪካም ሆነ አውሮፓ፣ የተባበሩት ኤምሬትስም ሆነ እስራኤል፣ ቻይናም ሆነ ሩሲያ… ክሱት እንዲሆን ያደረገው።
በኢትዮጵያ፣ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ወደፊት ከመጣ በኋላ እየታየ ያለው የወንጀል ድርጊት ብዛት እና ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ ግን፣ ከዚህ ጋር በፍፁም ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም። ይህን እውነታ በቀላሉ ለመረዳት፣ ከ2010ሩ ለውጥ በፊት የነበረውን እና ከዚያ በኋላ እየተከሰተ ያለውን የወንጀል ሪኮርድ በግርድፉም ቢሆን ማየቱ በቂ ነው።
የእዚህ ርዕሰ አንቀጽ ማጠንጠኛም (የኑሮ ውድነቱ እና የሥራ-አጥ ቁጥሩ የትየ-ለሌነት አንድ ገፊ-ምክንያት መሆኑ ሳይዘነጋ፤) በኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል ተከትሎ በመጣ ለውጥ ላይ፣ በተለይ በአዲስ አበባ በዚህ ደረጃ የተጋነነ ክፍተት እንዴት ሊፈጠር ቻለ? በማንስ ድክመት ነው፣ ወንጀለኞች ከፖሊስ ዐቅም በላይ ሊሆኑ የቻሉት? የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው።
ዛሬ በስፋት እየተስተዋለ እንዳለው፣ ችግሩ በመርካቶ እና ፒያሳ ወይም አራት ኪሎ እና ቦሌ የተገደበ አይደለም። በሁሉም ከፍለ ከተማዎች በሚባል መልኩ፣ የወንጀል ድርጊቶች በዐይነትም ሆነ በመጠን ንረዋል። ግድያዎችን ጨምሮ፤ የተለያዩ ወንጀሎች የእለት ተእለት ክስተት መሆናቸው እየተለመደ መጥቷል። ይህም ሆኖ፣ ከብዛቱ አኳያ፣ የፌደራሉም ሆነ የከተማዋ ፖለስ ተከታትለው የሚደርሱባቸው ወንጀሎች፣ እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ሌላው ቀርቶ፣ “በቁጥጥር ስር እንደዋሉ” ከተነገረው ውስጥ ራሱ፣ በምልዓት ሊያሳምኑ ያልቻሉ እንዳሉ ይታወቃል።
የወንጀል መከላከሉን ሥራ እጅግ የወረደና የደከመ መሆኑን የበለጠ የሚያጎላው ደግሞ፣ ከጥቃቅን ንብረቶች በተጨማሪ፤ የትላልቆቹ (የግዙፍ) ንብረቶች ዝርፊያም መድራቱ ነው።
ለዚህ ቀላሉ ማሳያ፣ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች የመኪና ስርቆት ባልተለመደ ሁኔታ የተጋነነ ደረጃ መድረሱ ነው። መቼም እንዲህ ዐይነት ንብረቶችን በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ እንደማይቻልም ሆነ የውስጥ አካላቸውን በታትኖ፤ ወይም በዘራፊዎቹ ቋንቋ “አርዶ” ለገበያ ማቅረቡ፣ ሞባይል ነጥቆ እንደ መሮጥ የቀለለ አይደለም። ድርጊቱ የቡድን ተሳትፎን ይጠይቃልና። ይህ ደግሞ፣ ለምርመራው ክትትል የሚገኘውን ፍንጭ ከፍ እንደሚያደርገው ለፖሊስ ‘ይጠፋዋል’ ብሎ ማሰብ፣ ለቀባሪው ማርዳት ነው። ምንም እንኳ ገሃድ የወጣው እውነታ የሚነግረን ተቃራኒውን ቢሆንም።
በዚህ ላይ፣ የታጠቁና የተደራጁ ወንጀለኞች እንደ አሸን እየፈሉ ነው። እነዚህን ቡድኖች የፖለቲካ ዓላማ መስፈጸሚያ ለማድረግ የሚሽቀዳደሙ ኃይሎች ደግሞ በብዛት መኖራቸው ተገማች ነው። እንዲሁም ይህንን መሰለ የወንጀል ቡድን እያደራጀ ‹የገቢ ምንጩን ሊያጠናክር የሚፈልግ ብረት-ነካሽ የፖለቲካ ድርጅት የለም› ብሎ መደምደም አይቻልም።
ይህ ሁኔታም ‘እውነት አዲስ አበባ የፖሊስ ኃይል አላት ወይ?’ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድዳል።
የሆነው ሆኖ፣ መንግሥት በፖሊስ ተቋማት ላይ መሠረታዊ ለወጥ እንዲመጣ የማድረግ ሥራ በፍጥነት መሥራት ይኖረበታል። በተጨማሪ፣ በየሰፈሩ የተቋቋሙትን የ“ማኀበረሰብ ዐቀፍ ፖሊስ” በደንብ በማጠናከር፣ የመረጃ ፍሰቱ ወንጀልን ለመከላከልም ሆነ የወንጀል ድርጊቶች ከተፈጸሙ በኋላ አጥፊዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚያስችል ደረጃ እንዲሆን አድርጎ መግራቱ ጠቀሜታው የበዛ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው፣ የፖሊስ ወንጀልን የመከላከል ዐቅም በአስደንጋጭ ደረጃ ማሽቆልቆልም ሆነ የወንጀለኞቹ እንደ ችግኝ መፍላት፣ በሂደት ሥርዐት አልበኝት የሚያነብር እና አገሪቱንም ወደማትወጣው አዘቅት የሚገፋ መሆኑ አይቀሬ ነው።
ሌላው እዚህ ጋ ሳይጠቀስ የማይታለፈው፣ በቢሮክራሲውም ሆነ በፖሊስ ተቋማት ውስጥ ካሉ ኃላፊዎች ጋር የጥቅም ሽርክና የፈጠሩ አደገኛ ወንጀለኞች የመኖራቸው እውነታ ነው። ይህም፣ ችግሩን የበለጠ ሊያወሳስበው እንደሚችል ከግምት ከትቶ መሥራት ያስፈልጋል።
በመጨረሻም፣ ደግመን ደጋግመን ለማሳሰብ የምንወደው፣ አዲስ አበባ የተደራጁ ወንጀለኞች መናኸሪያ እየሆነች ነው። ይህንን ሁኔታ በቶሎ መቆጣጠር ካልተቻለ፣ በአምስት እና ዐሥር ዐመት ውስጥ እንደ ጣሊያን ወይም ኮሎምቢያ ማፊያዎች አይነኬ ወደሚሆኑበት ደረጃ መድረሳቸው ተፈጥሯዊ ነው። አገሪቱ ከተሸከመቻቸው አያሌ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥያቄዎች ላይ፣ የተደራጀ ወንጀለኝነት ሲደመርበት በቸልታ መመልከቱ ደግሞ፤ በፍቃደኝነት የመታነቂያ ገመድን እንደማቀበል ያለ የማይታረም ስህተት መሆኑን ልብ ማለቱ ይመከራል።
Filed in: Amharic