>

እኔም ስለ ድምጻዊ  አለማየሁ እሸቴ...!!! (በእውቀቱ ስዩም)

እኔም ስለ ድምጻዊ  አለማየሁ እሸቴ…!!!

(በእውቀቱ ስዩም)

አለማየሁ እሸቴ በአጸደ- ስጋ አብሮን በነበረበት ጊዜ በተረብም በቁም ነገርም ሳነሳው ቆይቻለሁ  ፤ እና የሚከተሉትን ቃላት የምጽፈው    “ የሞተ ሰው አንገቱ ረጅም ነው” የሚለውን ልማድ ለመከተል አይደለም :: 
  አለማየሁ እሽቴ, አባቴ ከሚወዳቸው ዘፋኞች እንዱ ነበር::   “ አይዘራፍ እያሉ” “ ከሰው ቤት እንጀራ”  የተባሉትን ፤ የልጅነቴን ትዝታ ቀስቃሽ ዘፈኖች ፥  በቅርቡ  ዩቲዩብ ላይ ፈልጌ አጣሁዋቸው ::
አለማየሁ  የፊልም አፍቃሪ እንደነበር ሰምተናል ፤ የወጣትነት ህይወቱም ሲኒማ- መራሽ ነበር፤
   የሆነ ጊዜ ላይ አሌክስ  ሂልተን ሆቴል ገባ፤ በሚዘናፈለው ጠጉሩ ላይ የቴክሳሰስ ባርኔጣ ገድግዷል ፤ ከወደ ቁርጭምጭሚቴ የሚሰፋ ቦላሌ ለብሷል፤ አግሩን የመመገቢያ ጠረቤዛ ላይ እግሩን አንፈራጦ በመቀመጥ   ሲጃራ ማጤ ስ ጀመረ፤ አስተናጋጁ እግሩን እንዲያወርድ ጠየቀው ፤ እምቢ አለ፤  ዘበኛ ተጠርቶ መጣ፤ አሌክስ  ፊሻሌ  ሽጉጥ አወጣና ተኩሶ የዘበኛውን ኮፍያ  አወለቀው ፤  ብዙ ሳይቆይ ፈጥኖ ደራሽና የክቡር ዘበኛ ሂልተን  ሆቴልን ከበበው፤  አሌክስ   ካዛንቺስ አካባቢ ሲግጥ የቆየውን ፈረሱን  በፉጨት ጠራው:: ከዝያ “ እንዳሞራ “  ኮርቻው ላይ ፊጥ ካለ  በሁዋላ ጋልቦ አመለጠ፤  ፈረስ የጠራበትን  ፉጨቱን ወደ እንጉርጉሮ አሳደገው ፤ በለስ የቀናው ዘፋኝ ሆነ::
አሁን ያወጋሁት እልም ያለ ፈጠራ መሆኑን ተማምነን ወደ ቁምነገሩ እንሂድ::
አሌክስ ከሚጥም ድምጹ ባሻገር  ዘናጭ  ፤ ከፍተኛ በራስ መተማመን ያለው ሰው ነበር ፤  እጣፈንታ   በብዙ ነገር አዳልታለታለች:: ተቸግሮ  አልለመነም::  የሆነ ጊዜ  ባለስልጣን ሆኖ ያቅሙን ያክል ህዝብ ነድቷል ::   አርባ ምናመን  አመት በሞቅ ትዳር ቆይቷል፤ ይህንን ያክል ዘመን  ባንዲት ወይዘሮ እቅፍ  ተወስኖ መቆየት   በዘፋኝ አለም ብርቅ ነው ፤  አሌክስ በትዳር የቆየበትን ጊዜ ያክል ኬኔዲ መንገሻ በሕይወት አልቆየም::
ሙሉቀን መለሰ  የሚያደንቀው ብቸኛ  ዘፋኝ የጋሽ እሸቴን ልጅ ነው::  አለማየሁ በዘመናችን ካሉ ዘፋኞች  የጎሳየ ተስፋየ አድናቂ መሆኑን ነግሮኛል::
“ የወይን አረጊቱ” “፥  አዲሳበባ ቤቴ’  ፥ “ አምባሰል “ እንደ ጥንቱ  መስሎኝ””፥  ልተለየሽኝም “ ታሪክሽ ተጽፏ ል” የሚሉት ዘፈኖቹ ዘመን አልሻራቸውም፤  በጸጋየ ወይን ገብረመድህን( ደብተራው)  የተደረሰው “ ያ ጥቁር ግስላ” የተሰኘው  ዘፈኑ ራሱን የቻለ አቢዮት ነው ማለት ይቻላል ::  “ የአስር ሳንቲም ቆሎ ፤ ቁርጥም አደርግና “ እሚለው ዘፈኑ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከየት ወዴት እንደ ሄደ ያመላክታል  ፤   ለካ አስር ሳንቲም  ሙዝየም ከመግባቱ በፊት  ይሄን ያህል ሙያ ነበረው ::
“ ካጣን ምናባቱ እንብላ ሽንብራ
የሰው እጅን ብቻ እንዳናይ አደራ “ የሚለውን ዘፈንስ  እንዴት ይረሳል? በአሌክስ የጉርምስና ዘመን፥  ያጣ የነጣው ድሃ ሽምብራ ተመጋቢ ነበር፤  አንዳንዴ ዜጎች  የድሮውን ቢናፍቁ ምክንያት አላቸው ::
አሌክስ  የተረፈው ሀብታም ልጅ ነበር ፤ በጉርምስና ዘመኑ አንዴ ለመሰደድ የወሰነው እንጀራ ለማደን ሳይሆን የሆሊውድ አክተር የመሆን ምኞቱን ለማርካት ነበር ::  ቢሆንም ስለ ድህነት አብዝቶ በመዝፈን  ድሀ- አደግ ዘፋኞችን ሳይቀር ይቦንሳል :: በተለይ  ኮለኔል ግርማ  ሐይሌ  ከተባለ ደራሲ የተቀበላቸው እንጉርጉሮዎች ከምሾ በላይ  ሆድ የሚያስብሱ  ናቸው  ::  እዚህ ላይ “ ስቀሽ አታስቂኝ “ የሚለው ፒያኖውን የሚያስለቅስበት ዜማው ትዝ ይለኛል፤ የዘፈኑ ባለታሪክ  የሙት ልጅ የሆነች ድሃ ናት::   ኑሮን ለማሸነፍ “ትፍጨረጨራለች” ፤ በመከራዋ ላይም ትስቃለች ::   ይህ በእንዲህ እያለ  ወንድምየው ጣልቃ ገብቶ  “ ስቀሽ አታስቂኝ “ ይላታል ፤  ““ ትፍጨረጨርያለሽ ወጉ አይቀር ብለሽ “ እያለ ያዳክማታል ::  ጭራሽ “ ውሃ ጉድጉዋድ ግቢ የምየ ልጅ ባክሽ ” እያለ ይጎተጉታታል ፤
 የሰው ልጅ ሁኔታ በጠቅላላው፤  በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሁኔታ ተስፋ አስቆርጦኝ ያውቃል ፤ “ስቀሽ አታስቂኝ”ን ስሰማ ግን እኔን ብሎ ተስፋ ቆራጭ እላለሁ፡:  እንደዚህ ተስፋን ከጎድንና ከዳቢቱ እሚቆርጥ ዘፈን  ገጥሞኝ አያውቅም ::
 ሰው ማለቂያ በሌለው ውድቀት መሀል እንኳን  እየኖረ ተስፋና መጽናኛን የሚያማትር ፍጡር ነው  ፤ ከአለማየሁ እሸቴ “ ስቀሽ አታስቂኝ “ ይልቅ  የ አለማየሁ ሂርጶ” አታቀርቅሪ ቀን ያልፋል “ የሚለውን ዘፈን ይበልጥ የገነነው ለዚህ  ይሆን ?
Filed in: Amharic