>

መኃልይ መኅይልየ  ዘ ጳጉሜ ....!!! (ከማዕበል ፈጠነ )

መኃልይ መኅይልየ  ዘ ጳጉሜ ….!!!

             ከማዕበል ፈጠነ 

*.…. እድሜ ለኩሰው ላበሩን ይሁንልና የድሮ ሊቃውንት የጸሎት አዋጅ የሚያውጁት በዚህ የሥነ ፍጥረት ቀመር መሠረት ነበር። ያ ብቻ አይደለም። ሊቃውንቱ አብነት ለመከለስ እድሜ ለማደስ ጭምር ይህን ቀመር ይጠቀሙ ነበር።
       ……
የጳጉሜ ወር የጸሎት ወር እንዲሆን በቅዱስ ሲኖዶስ እንደ ተወሰነ ሰማሁ። መልካም ውሳኔ ነው!! በተለይ ጳጉሜ ለኢትዮጵያ ሰዎች የበረከት ወር ናት። (ረጅም ነገሩን በዚህ ገጽ ማስፈር ግን አይቻልሁም። )
 የጳጉሜ  ወር  ከጥንት ጀምሮ የጸሎት ዘመን ቢሆንም ቅሉ ነገር ግን እንዲህ አልነበረም። ትንሽ ነገር ይቀረዋል። የሥነ ፍጥረትን ሕግ  ይጠብቃል። እንዲህ አልነበረም ስል ታዲያ እንዴት ነበር  ከርታታው? የሚል አንባቢ አይጠፋም። በከርታታ ኮከቦች ወግ ሲገለጽ ምሥጢሩ ወዲህ ነው!!
                 ……..
  ዓመተ ምሕረቱ እንደ ዘንድሮው የመከራ ዓመት ሲሆን  ድፍን ዓመቱ (2013)  ዓ. ም በምሉዕ በዐውደ ፀሐይ ይቀመራል። ሲቀመር  የፀሐይ ዓመት ነሐሴ ስድስት (6) ላይ ያበቃል። ይህ ድፍን ዓሥራ ሁለት ወር ይሆናል። ዐሥራ ሁለት ወር ማለት በተለመደው ዘይቤ ድፍን አንድ ዓመት ይባላል።  ከነሐሴ 24 ቀን ይቀራል። ከጳጉሜ ዐራት ቀን ያመጧል። 24+4  =28   ይሆናል። ወሩ ዓሥራ ሦስተኛ ወር ይሆናል። አንባቢ ሆይ ልብ ይበሉ ! “ጳጉሜ ዐሥራ ሦስተኛ ወር ናት” ስንል በፀሐይ ዑደት ቆጥረን ነው። ከዚህ ውስጥ ለጸሎት ከተፈለገ ነሐሴ ሃያ አምስት የጸሎት ቀን ይታወጃል። እስከ ሳምንት አንድ ሱባኤ ይገኛል።   የመጨረሻው ቀን ከርኅወተ ሰማይ ጋር ይገጥማል። በዚህ ቀን ጸሎቱ ወደ ሰማይ ያርጋል። ምሕረት ወደ ምድር ይወርዳል። ለሀገር ይቅርታ ለሕዝብ እፎይታ ይሆናል። የጸሎት ጥቅሙ ይኸው ነው። ሐተታው ብዥታ እንደፈጠረባችሁ ቀድሞ ገብቶኛል። ምንም መጨነቅ አያስፈልግም። የታወቀ ነው።
ሌላ ምን ቀረ?
 እድሜ ለኩሰው ላበሩን ይሁንልና የድሮ ሊቃውንት የጸሎት አዋጅ የሚያውጁት በዚህ የሥነ ፍጥረት ቀመር መሠረት ነበር። ያ ብቻ አይደለም። ሊቃውንቱ አብነት ለመከለስ እድሜ ለማደስ ጭምር ይህን ቀመር ይጠቀሙ ነበር።
       ……
አሁን ባለው በግልቦች  ዘመን ግን ብዙ ይቀራል።
ለምሳሌ- ባለፈው ኮሮና ሀገር ቤት ሲገባ እንዲሁ የጸሎት ቀን ታውጆ ነበር። ዳሩ ምን ይሆናል? ጸሎቱ በቴለቨዥን መስኮት  ስለ ተላለፈ የእገሌ ድምፅ ከእገሌ ያምራል። ከመምህር እገሌ ስብከት የእገሌ ይበልጣል። የዘማሬው ውበት የከንፈሩ ዳርዳርታ አቤት ደስ ሲል የሚሉ ቆነጃጅነትን ማርኮ ነበር።  የሚዲያ ወላፈኑ ተደምሮበት ከጸሎቱ ይልቅ የእውቀት መለኪያ የቁንጅና መወዳደሪያ ወደ መሆን ሂዶ ስገረም ነበር።  ሚዲያዎችን እንደ ቡዳ ዐይን ለሚፈራ የእኔ ቢጤ ሰው ግን ከዚህ ጸሎት ሕብረት አልነበረውም።
የሆነው ሆኖ በወቅቱ ጸሎቱ ቅድመ እግዚአብሔር እንደ ደረሰ  ምንም ጥርጥር የለውም።  ደርሷል። ዓለም በኮሮና አውሎ ነፋስ እንደቦቀሎ ሲለሸለሽ ኢትዮጵያ በጸሎቷ ከመዐቱ በከፊል አምልጣለች።
Filed in: Amharic