>

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገዥ የነበሩት አቶ ተፈራ ደግፌ ስለሚወዷት ኢትዮጵያ ምኞታቸው ምን ነበር...?! (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገዥ የነበሩት አቶ ተፈራ ደግፌ ስለሚወዷት ኢትዮጵያ ምኞታቸው ምን ነበር…?!

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


ክቡር አቶ ተፈራ ደግፌ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ (ጥቁር/አፍሪቃዊ) የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በኋላም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገዥ የነበሩ ትልቅ ሰው፣ ሐቀኛ ምሁር ነበሩ፡፡ ክቡርነታቸው ሀገራቸውን አብዝተው የሚወዱ፣ ለወገናቸው የሚቆረቆሩ፣ ኢትዮጵያ በዕድገትና በልማት ጎዳና ላይ እንድትራመድ በማድረግ ረገድ ደግሞ ትልቅ የታሪክ አሻራን የተዉ ኩሩ ኢትዮጵያዊ፣ ፓን-አፍሪካኒስት ነበሩ፡፡

ክቡርነታቸውን፤ ነፍሰ ኄር፣ አቶ ተፈራ ደግፌን ለዛሬ ላስታውሳቸው የወደድኩት ከ20 ዓመታት ገደማ በፊት በ1991 ዓ.ም. አቢሲኒያ ባንክ ሲከፍት፣ በምርቃቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ያደረጉት ንግግራቸው – በአሁን ወቅት ሀገራችን፣ ኢትዮጵያ ካለችበት ፈታኝ ጊዜ አንጻር መልካም ምክር/ምኞት መስሎ ስለታየኝ ነው፡፡ ደግሞስ አዲስ ዓመትን ልንቀበልም አይደል፣ እናም እንሆ አቶ ተፈራ ደግፌ ለሚወዷት ሀገራቸው፣ ኢትዮጵያ መልካም ምኞታቸውን በጥቂቱ እናስታውስ ዘንድ ወደድኹ፤

‘‘… እኔ ለሀገሬ ኢትዮጵያ የምመኘው ከጦርነት ውጥረትና ከሚያስከትለው ጥፋት አምልጠን በመልማት ላይ እንዳሉት ሌሎች ሀገሮች ወደ ልማቱና ማኅበራዊ ዕድገት እንድትደርስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ራእይ ያለው አመራር፣ ተግባብቶ የሚኖር ሕዝብ፣ በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ የሚኮራና አገሩን የሚያስከብር ዜጋ መኖር ወሳኝ ነው…፤’’

እግረ መንገድም፤ ነፍሰ ኄር፣ አቶ ተፈራ ደግፌ ለሀገራቸው ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ትልቅ ክብር የነበራቸው ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ ከዚህም የተነሳ አቶ ተፈራ በሀገር በውስጥ እና በውጭ ሀገር በትምህርትና በሥራ በቆዩባቸው ጊዜያት ያሰባሰቧቸውን፤ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታሪክ፣ ቅርስና ባህል የተመለከቱ በርካታ መጻሕፍትን (በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛና በኢጣሊያንኛ ቋንቋዎች የተጻፉ መሆናቸውን ልብ ይሏል) ለአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ቤተ-መጻሕፍት በስጦታ ማበርከታቸውን አስታውሳለኹ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገዢ ስለነበሩት፣ ስለአቶ ተፈራ ደግፌ ፈገግ የሚያሰኝ አንድ ገጠመኛቸውን ልጨምርና ልሰናበት፡፡ በነገራችን ላይ ይህን የክቡርነታቸውን ፈገግታ የሚያጭር ታሪክ/ገጠመኛቸውን ያጫወቱኝ- የአቶ ተፈራ ደግፌ የቀድሞ ወዳጅ፣ ከነበሩት የቀድሞ ፕሬዚደንት፣ ነፍሰ ኄር፣ መ/አ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጋር – በሰላምና በአረንጓዴ ልማት ረገድ ያደረጉትን አስተዋጽኦ በተመለከተ ለአንድ የፕሮጀክት ሥራ ባደርግነው የቃለ-መጠይቅ ቆይታ ወቅት ነበር፡፡ እነሆ የአቶ ተፈራ ገጠመኝ፤

አቶ ተፈራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገዥ በነበሩበት ወቅት፣ አንድ ማለዳ ብሔራዊ ቴያትር አካባቢ ወደሚገኘው በተለምዶ ወርቃማው ባንክ ቢሮአቸው ለመግባት ደረጃውን ፈጠን፣ ፈጠን እያሉ ሲወጡ ሁለት ከገጠር የመጡ በላገሮችን ያያሉ፡፡ እነዚህ ለከተማው እንግዳ የኾኑ ባላገሮች ኩታቸውን መስቀለኛ አጣፍተው፣ ወርቃማውን ባንክ አሻቅበው በአግራሞት፣ በአድናቆት እያዩ፤

‘‘እግዚኦ! እግዚኦ! የአንተ ያለህ… አቤት ጃንሆይ፣ ሺሕ ዓመት ይንገሡ፣ እንዲህ በወርቅ ያሸበረቀ፣ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ቤተስክያን… ይህ ታምር እንጂ ሌላ ምን ይባላል…’’ እያሉ በአድናቆት ደረጃው ላይ ኾነው ወርቃማውን ባንክ ሲሳለሙ ሳለ፣ የባላገሮቹን እንግዶች ሁኔታቸውን ሲከታተሉ የነበሩት የባንኩ ገዥ አቶ ተፈራ ደግፌ ወደ ባላገሮቹ ጠጋ ብለው ሰላምታ ያቀርቡላቸዋል፡፡ እንግዶቹም ልባቸው በአድናቆትና በመገረም እንደተሞላ፤

‘‘ጌታው እንደምን አደሩ፤ እንደው ምን ታምር ነው ዓይናችን ያየው! በወርቅ የተንቆጠቆጠ ቤተስክያን… እንደው ጃንሆይ ምን ፍራንካ በቃቸው ይህን ቤተስክያን ለማሳነጽ… ዕፁብ ድንቅ ነው፤ እንደው ጌታው የሆነስ ሆነና ይህ ቤተስክያን ማን ደብር ነው የሚባለው?’’ በማለት አቶ ተፈራን ይጠይቃሉ፡፡

አቶ ተፈራ ሳቃቸውን እንደምንም እየገቱ፤ ‘‘ወገኖቼ ይህማ ‘ብር አምባው ጊዮርጊስ’ ነው የሚባለው፤’’ በማለት ለባላገሮቹ ምላሽ ከሰጧቸው በኋላ- ኑ እኔም ወደውስጥ ስለሆንክ ይዤያችሁ ልግባ በማለት፤ ‘‘ብር አምባው ጊዮርጊስ’’ ወዳሉት ወደ ወርቃማው ባንክ እየተጨዋወቱ ይዘዋቸው ይገባሉ፡፡ አቶ ተፈራ ለባላገሮቹ እንግዶች ይህ ትልቅ ሕንጻ ቤተስክያን ሳይሆን የገንዘብ ማስቀመጫ እንዲሆን ጃንሆይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያሠሩት ተቋም መሆኑን አስረዷቸው፡፡

አቶ ተፈራ እግረ መንገዳቸውንም ስለባንክ ሥራና ገንዘባቸውን በባንክ ቢያስቀምጡ የሚያገኙትን ጥቅም ሊያስረዷቸው ሞከሩ፡፡ በወቅቱ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ የገጠሩ ሕዝብ ገንዘቡን ባንክ የማስቀመጥ ልምድ አልነበረውም፡፡ እናም ክቡርነታቸው ይህን አጋጣሚ ተጠቀመው ባላገሮቹን ገንዘባቸውን በባንክ በአደራ ቢያስቀምጡ ስለሚያገኙት ጥቅም አስረድተው ባላገሮቹን እንግዶች በቢሮአቸው ውስጥ ቡና ጋብዘውና ጥቂት ገንዘብ ሰጥተዋቸው ተመራርቀው ተለያዩ፡፡

‘‘… እኔ ለሀገሬ ኢትዮጵያ የምመኘው ከጦርነት ውጥረትና ከሚያስከትለው ጥፋት አምልጠን በመልማት ላይ እንዳሉት ሌሎች ሀገሮች ወደ ልማቱና ማኅበራዊ ዕድገት እንድትደርስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ራእይ ያለው አመራር፣ ተግባብቶ የሚኖር ሕዝብ፣ በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ የሚኮራና አገሩን የሚያስከብር ዜጋ መኖር ወሳኝ ነው…፤’’

ክብር ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን በጽኑ፣ የዐለት መሠረት ላይ ላቆዩን ጀግኖቻችን፣ ባለውለታዎቻችን ሁሉ!!

ሰላም ለኢትዮጵያ!! ሰላም ለምድራችን!!

Filed in: Amharic