>

ይድረስ ለባልደራስ አባላት በሙሉ ከምርጫ 2013 ባሻገር (እስክንድር ነጋ፣ በቂሊንጦ እስር ቤት)

ይድረስ ለባልደራስ አባላት በሙሉ

ከምርጫ 2013 ባሻገር

እስክንድር ነጋ፣ በቂሊንጦ እስር ቤት

ማሳሰቢያ፡- ይህ ፅሁፍ፣ የሰሜኑ ጦርነት በፌደራል መንግሥቱ የበላይነት ይጠናቀቃል የሚለው ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
 
1.1. ታሪክ መሥራት አለብን! 
የ2013 ምርጫ ውጤት ተረት ተረት ነው፡፡ መሬት ላይ ካለችው ኢትዮጵያ ጋር በፊት ለፊትም በጓሮ በርም ፈፅሞ አይገናኝም፡፡ ብንታደል ኖሮ፣ የምርጫው ውጤት ለሀገራችን መስታወት በመሆን፣ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የዘመናችን ትልቅ የሆኑና ሚሊዮኖችን ያሰለፉ ልዩነቶቻችን የተወከሉባቸው መድረኮች ይሆኑ ነበር፡፡ መጥፎ ዕድላችን ሆኖ ግን፣ ከህዝብ ይልቅ የገዥው ፓርቲ መስታወት ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በስግብግብ ባህሪው እንጂ፣ ይህ መሆኑ ገዥውን ፓርቲ አሸናፊ አላደረገውም፡፡ እንደ ሀገር ሁላችንም የተሸነፍንበት ምርጫ ነበር፡፡
ሕወሓት በአካል ይክሰም እንጂ፣ በአስተሳሰብና በአሰራር ግን በብልፅግና ውስጥ እንደቀጠለ የምርጫው ውጤት ጥሩ ማሳያ ሆኗል፡፡ ከአስተሳሰብ መካከል፣ በሥልጣ ላይ መኖሩን ለኢትዮጵያዊነቱ እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ እጅግ አደገኛውና አሳሳቢው ነው፡፡ ይህ አባዜ የብልፅግና የስበት ማዕከል በሆነው የኦሮሞ ብልፅግና ውስጥ በሰፊው ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ በዚህ ሁኔታ፣ ሥልጣን ልቀቅ የተባለው ሕወሓት እንደ ሆነው፣ ሥልጣን ልቀቅ የሚባለው የኦሮሞ ብልፅግና ይሆናል፡፡ በዚህ የማይቀር ፈተና እንደ ሀገር መዘጋጀት አለብን፡፡ በዚህ አውድ ውስጥ ነው የባልደራስ ተልዕኮ የሚገኘው፡፡ ከዚህ በኋላ፣ ስኬታችን ምርጫ በማሸነፍ ብቻ የሚለካ አይደለም፡፡
በድህረ – ምርጫ  2013 ህጋዊ ቁመናችንና ድርጅታዊ እንቅስቃሴያችንን ከአዲስ አበባ ወደ ሀገር አቀፍ ደረጃ ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡ ከውጭም ከውስጥም ተወጥረን ካሳለፍነው የአንድ ዓመት ተኩል ጉዞ ብዙ የተማርን እንደመሆናችን መጠን፣ ይህን ሂደት በከፍተኛ ጥያቄ የምናደርገው ይሆናል፡፡
ለሀገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች – ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ- በውጪ ካለው ጠላት ይልቅ፣ ተመሳስሎ ከውስጣቸው የሚገባው ሰርጎ ገብ የበለጠ አደጋ ነው፡፡ የትኛውም ድርጅት ቢሆን፣ ራሱን ሙሉ በሙሉ ከሠርጎ ገቦች – የደህንነት አባላት፣ ሌቦች፣ አፍራሾች፣ ሥርዓተ አልበኞች፣ ከፋፋዮች፣ ውሸታሞች፣ ሱሰኞች፣ አድመኞች፣ ሐሜተኞች፣ቀናተኞች፣ ሰነፎች፣ አስመሳዮች፣ ዝና ፈላጊዎች፣ ጠባቦች – ሊያፀዳ አይችልም፡፡ ለድርጅቱ ዓላማ መሳካት በተልዕኮ፣ በአመለካከት፣ በባህሪ ችግር እንቅፋት የሆኑ ሁሉ ሠርጎ ገቦች መሆናቸው ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ ከደህንነት አባላት ባሻገር ለሆኑ ሰርጎ ገቦችን ዘብ መሆን እንዳለብን የትግል ተሞክሯችን ያስተምረናል፡፡ ያው እንደሚባለው – ከታሪካችን ካልተማርን፣ ስህተታችንን እየደጋገምን እንኖራለን፡፡
ሠርጎ ጎቦችን በምኞት፣ በመፈክር፣ በውግዘት፣ ወይም ትልቁንም ትንሹንም እየተጠራጠሩ ልንዋጋቸው አንችልም፡፡ ፍቱን መድኃኒቱ ግምገማ ነው፡፡ ግምገማ ማለት ደካማ አባላትና አመራሮች የሚራገፉበት፣ ጠንካራ ድርጅታዊ ዲስፕሊን እንዲኖር የሚደረግበት አሠራር ነው፡፡ “ደካማ” ማለት፣ የተሰጠውን ተልዕኮ ማስፈፀም የማይችል አባል ወይም አመራር ነው፡፡ እውቀት ለአመራርነት አስፈላጊ ቢሆንም፣ ተልዕኮ ማስፈፀም ላልቻለ በድን ነው፡፡ ታላቁ መፅሃፍ እንደሚለው፣ እምነት ያለ ሥራ ሙት ነው፡፡ አውቀትም ያለ ተግባር እንደዚያው፡፡
የግምገማ ሚና፣ ተልዕኮ ማስፈፀም የሚችለውንና የማይችለውን አመራር መለየት ነው፡፡ የዲስፕሊን ሚና፣ ተልዕኮ ማስፈፀም እንደማይችል በግምገማ የተለየው አመራር ላይ የሚወስደው ርህራሄ የሌለው እርምጃ ጋር ይመጣል፡፡ “ርህራሄ የሌለው” ሊባል፣ “ፍትህ ጭፍን ናት” እንደሚባለው፣ ግምገማ በሁሉም ደረጃ ባሉ አባላትና አመራሮች ላይ እኩል ተፈፃሚ የሚደረግ ዲስፕሊን ማለት ነው፡፡ይህን ዲስፕሊን ነው መለስ ዜናዊ፣ “የኢህአዴግ ሹመት የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው” ያሉት፡፡ ኢህአዴግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላትን በዋዛ አላሰባሰበም፡፡ ማስፈራሪያው፣ ጥቅማ ጥቅሙ፣ ከአባላት ዲሲፕሊን ጋር ተደማምሮ ያመጣው ውጤት ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ማሳያ ግምገማ ነው፡፡  በእያንዳንዱ እርምጃችን እየተገማገምን፣ በመጀመሪያ በመቶዎች ከዚያም በሺህዎች፣ ከዚያም በአሥር ሺህዎች፣ ብሎም በመቶ ሺህዎችና ሚሊዮኖች አባላት ያሉት ድርጅት መገንባት እንችላን፡፡ ታሪክ መሥራት አለብን!
 
1.2. የመጀመሪያው ተግባራችን
ፊት ለፊታችን ያለው የመጀመሪያ ተግባር፣ የድርጅታችንን መዋቅር ከማዕከል እስከ ሰፈር መዘርጋት ነው፡፡ ይህን ተግባር፣ በአጭር ጊዜ፣ በአነስተኛ ገንዘብ፣ በአነስተኛ ጉልበት ከላይ ወደ ታች (top to bottom) መተግበር የሚያስችል አሠራር በእጃችን ላይ አለ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ባለፉት 30ዓመታት ከኢህአዴግ ውጭ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሰራ አደረጃጀት  (an organization that is functional) መገንባት አልቻሉም፡፡ የኖሩትም የሞቱትም ወረቀት ላይ ነበር፡፡ “የሚሰራ አደረጃጀት” ሲባል፤ ቢያንስ በሺህዎች የሚቆጠሩ አባላት ያሉት፣ የአስተዳደር ወጪዎችን በአባላት ወጪ የሚሸፍን፣ የተዋረድ (vertical) እና የጎንዮሽ (horizontal) የሥራ ክፍፍል ያለው፣. በውስጥ ዲሞክራሲና በአባላት ዲስፕሊን መካከል ሚዛን የጠበቀ አሰራርና መዋቅር ያለው ድርጅት ማለት ነው፡፡
 
1.2.2. በርካታ አባላት ማለት?
በርካታ አባላት ያሉት ድርጅት ሲባል ምንድን ነው? አንፃራዊ ነው፡፡ የተቆረጠ ቁጥር የለም፡፡ እንደ አውዱ ይለያያል፡፡ በሀገራችን አውድ፣ ከ100 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላትን ኢትዮጵያ እወክላለሁ የሚል ድርጅት፣ 2 ሚሊዮን ህዝብ የማይሞላን ብሄር እወክላለሁ ከሚል ድርጅት፣ አንድ ዓይነት በርካታ አባላት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ እወክለዋለሁ ከሚሉት ህዝብ አንፃር መመዘን አለበት፡፡
ከዚህ አኳያ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለመመዝገብ ያወጣው መሥፈርት ጥሩ ነው፡፡ ሁለት መሥፈርቶች አሉት፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ (በመላ ኢትዮጵያ) ለመንቀሳቀስ የሚመዘገቡት በአራት ክልሎች የሚኖሩ 10,000 ሰዎችን መልምለው ማስፈረም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአንድ ክልል ተገድበው የብሄር ድርጅት ለመሆን የፈለጉት ደግሞ፣ የ4000 አባሎቻቸውን ፊርማ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አንድ ድርጅት የሚሠራ አደረጃጀት አለው እንዲባል፣ ከመዘገባቸው አባላቱ መካከል ቢያንስ ከ65 በመቶው ወርሃዊ መዋጮን የሚሰበሰብ መሆን አለበት፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ድርጅት፣ አረንጓዴ ዞን ውስጥ ያለ ነው፡፡ አረንጓዴው፣ መደላደልን እና ጤናማነትን ያመላክታል፡፡ ከ50 እስከ 65 በመቶ አባላቱ ወርሃዊ መዋጮን የሚሰበስበው ደግሞ በመካከለኛ ቁመና ላይ ያለ ሊሆን፣ ወይም ባለበት የቆመ፣ ወይም በቁልቁለት ጉዞ ላይ ያለ ነው፡፡ በዚህ ቁመና ያለ ድርጅት ቢጫ ዞን ውስጥ ይገኛል፡፡ ቢጫ የማስጠንቀቂያ ደውልን ያመላክታል፡፡ ከ50 ከመቶ በታች የሆነው ጤናማ ያልሆነ ነው፡፡ ቀይ ዞን ውስጥ ይገኛል፡፡ ቀዩ በጠና መታመሙን ያመለክታል፡፡ አረንጓዴው ሩቅ ግብ መሆኑን ተቀብለን ወደ ጎን እናስቀምጠውና፣ ከቢጫ ወደ አረንጓዴ ያለው ጉዞ እንኳን ረዥም ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ በአጭር ጊዜ ሊሸፈን ይችላል፡፡ ማናቸውም ድርጅት በጥቂት ሰዎች ነው የሚጀመረው፡፡ እነዚያ ጥቂቶች ከተናበቡ፣ ከተጉ፣ ከሁሉም በላይ ግን፣ ከብረት በጠነከረ ዲስፕሊን ከተሳሰሩ ተዓምር መሥራት ይችላሉ፡፡
1.2.2. የተዋረድና የጎንዮሽ የሥራ ክፍፍል
በተጨባጭ ከሚታየው እንነሳ፡፡ በተቃዋሚዎች በኩል ያው የተዋረድ የጎንዮሽ የሥራ ክፍፍልም ጥሩ ቁመና የለውም፡፡ በድርጅቶቹ እንቅስቃሴ ውስጥ በተግባር የሚሳተፍ አባላት ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑ አኳያ፣ በወረቀት ላይ ያለውን የተዋረድም ሆነ የጎንዮሽ የሥራ ክፍፍል መተግበር አልተቻለም፡፡ ከዚህ ሳቢያ፣ ድርጅቶቹ በራሳቸው አባላት የምር ሊወሰዱ (Seriously ሊወሰዱ) ባለመቻላቸው፣ የቅቡልነት ችግራቸው ከራሳቸው ውስጥ መነሻ ያገኛል፡፡
የሚሠራ አደረጃጀት ባለው ድርጅት ውስጥ፣ የተዋረድና የጎንዮሽ የሥራ ክፍፍልም መልክ ይኖረዋል? የሚለውን ደግሞ እንየው፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት የመንግሥት ጥላ ነው፡፡ በመንግሥት ውስጥ ያለው የህግ አውጪ፣ የህግ ተርጓሚ እና ሥራ አስፈፃሚ ክፍፍል በድርጅቱ ውስጥም ይኖራል፡፡ ሶስቱም የህዝቡ ጥላ በሆነው የድርጅቱ ጉባዔ የሚመረጡ ናቸው፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን የተዋረድ መዋቅሮችን ያደራጃሉ፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ይህ የሥራና የኃላፊነት ክፍፍል በአንድ ድርጅት ውስጥ ያሉ በመሆኑ፣ በአተገባበሩ በመንግሥት ደረጃ ካለው ይለያል፡፡ ለምሳሌ፣ የህግ አውጪ የሆነው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች አይንፀባረቁም፡፡ የማዕከላዊ ኮሚቴው ተልዕኮ በድርጅቱ ጉባዔ ለፀደቀው ፕሮግራም ዝርዝር ፖሊሲዎችን ማውጣት ነው፡፡ እነዚያን ፖሊሲዎች ማስፈፀም የሥራ አስፈፃሚው ኃላፊነት ነው፡፡ በመንግሥት ደረጃ፣ የሥራ አስፈፃሚውና ህግ አውጪው የተለያዩ ፓርቲዎች እጅ ሲወድቁ ተገዳዳሪዎች ይሆናሉ፡፡ በድርጅት ደረጃ ግን፣ ሥራ አስፈፃሚውና ማዕከላዊ ኮሚቴው ለአንድ ዓላማ ስለሚንቀሳቀሱ ሁሉም ተደጋጋፊ ናቸው፡፡
1.2.3. ፕሬዝዳንታዊና ፓርልመንተራዊአ ደረጃጀት
አንድ ድርጅት መሪውን በጉባዔ ካስመረጠ ፕሬዝዳንታዊ አሠራር ይከተላል ማለት ነው፡፡ መሪውን በማዕከላዊ ኮሚቴው ካስመረጠ ደግሞ፣ ፓርላማዊ አሠራር አለው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ መሪያቸውን በጉባዔ የሚያስመርጡ ድርጅቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
ለዚህ ተጨባጭ ምክንያት አለ፡፡ በአንድ በኩል፣ በ1966ቱ “ፀረ – ፊውዳል” አብዮት “ እኩልነት” የተተረጎመበት መንገድ፣ “ሁሉም እኩል መብት አለው” ከሚለው ይልቅ፣ “ሁሉም እኩል ችሎታ አለው” ወደሚለው በማጋደሉ፣ በፖለቲካ አውዱ በየደረጃው ያሉ መሪዎች በቀላሉ ቅቡልነት እንዳያገኙ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል፣ ለኢትዮጵያን ባህልና ሥነ ልቦና ጠንካራ መሪ ይፈልጋል፡፡
በእነዚህ የተለያዩ ሁኔታዎች ሳቢያ፣ የእንግሊዙ ፓርልመንተሪ አሠራር ደካማ መሪዎችን፣ የአሜሪካዊያኑ ፕሬዝዳንታዊ አሠራር ጠንካራ መሪዎችን እንደሚያፈሩ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ተሞክሮ በተጨባጭ ተረጋግጧል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ባልደራስ ፕሬዝዳንታዊን አደረጃጀት መርጧል፡፡ በዚህ  ሁኔታ ጠንካራ መሪ ማውጣት ካልቻለ፣ ሁሉ ነገር ገና ከመነሻው ይከሽፋል፡፡ ዘመናችን ጠንካራ መሪ ይፈልጋል፡፡ ያለነው በተለየ ዘመን ውስጥ ነው፡፡ ጠንካራ መሪ ማውጣት ያልቻለ ድርጅት፣ በፖለቲካ ሜዳው ትርጉም ያለው ተጨዋች መሆን አይችልም፡፡
 
1.2.4. ዲሞክራሲና ዲስፕሊን
በውስጥ ዲሞክራሲና በአባላት ዲስፕሊን መካከል ያለውን ሚዛን የሚጠብቀው የድርጅት ዘርፍ፣ በብዙዎቹ ዘንድ “ ኦዲትና ቁጥጥር” ተብሉ የሚታወቀው ክፍል ነው፡፡
በዚህ ዘርፍ አንዱ ተግባር የድርጅቱ ገቢና ወጪ በሥርዓት መከናወኑን መከታተል ነው፡፡ ይህ ተግባር በውስጥም በውጭም ባለሙያዎች መመራት አለበት፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት፣ ተቃዋሚዎች ገንዘብ እንደሚያባክኑ ተደርጎ ሰፊ ፕሮፖጋንዳ መሠራቱ፣ህዝባዊ ተቀባይነታቸው ላይ አፍራሽ እንድምታ አሳድሯል፡፡ የሚሠራ አደረጃጀት ያለው ድርጅት በቀዳሚነት ከሚፈፅማቸው ተግባራት መካከል ለፋይናንስ ሥርዓቱ ግልፅ የሆነ አሠራር መዘርጋት መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ፣ ወርሃዊ መዋጮን መሰብሰብም ሆነ በሌሎች መንገዶች ገቢ ማሰባሰብ አዳጋች ይሆናል፡፡
በዚሁ ዘርፍ የሚከናወነው የአባላት ዲስፕሊን ቁጥጥርም፣ በተቃዋሚዎች ዘንድ በአግባቡ ሊተገበር አልቻለም፡፡ ይህ ሁኔታ ድርጅቶቹ በርካታ አባላት ማፍራት ካለመቻላቸውና ብቃት ያለው አመራር የሌላቸው ከመሆኑ ጋር የተሳሰረ ድክመት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ችግሮች አስቀድመው ከተፈቱ በኋላ፣ የውስጥ ህገ-ደንቦች በአግባቡ መተግበር አለባቸው፡፡ ህገ-ደንቦቹን ማስከበር ያልቻለ ድርጅት፣ ወይ አምባገነንነት ወይ ሥርዓት አልበኝነት ይሰፍንበታል፡፡ ሁለቱም ውለው አድረው ድርጅት ያጠፋሉ፡፡
ሆኖም፣ ከሥርዓተ አልበኝነት ይልቅ አምባገነንነት እንደሚሻል ብዥታ መኖር የለበትም፡፡ በሥርዓት አልበኝነት ውስጥ የወደመ ወይም በመውደም ላይ የሚገኝ አውድ ነው ያለው፡፡ ከአዙሪቱ ለመውጣት፣ ሀገር ከሆነ መንግሥትን፣ ድርጅት ከሆነ ተቋምን ከሥረ-መሠረቱ እንደ አዲስ መገንባት ይጠይቃል፡፡ የአምባገነንነት መገለጫ ግን፣ አፈና እንጂ ሙሉ ለሙሉ የሆነ መዋቅር ውድመት አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ዲስፕሊን በሌለበት ሁኔታ ድርጅት ሊኖር አይችልም፣ አፋኝ ዲስፕሊን ባለበት ሁኔታ ግን በትግል ዲሞክራሲያዊ ሊሆን የሚችል ድርጅት ይኖራል፡፡
1.3. ማጠቃለያ
ትግሉ ጠንካራ ድርጅት ይፈልጋል፡፡ ያለ ጠንካራ አባላት ጠንካራ ድርጅት ሊኖር አይችልም፡፡ ያለጠንካራ ዲስፕሊን ጠንካራ አባላት ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ያለ ጠንካራ ህገ – ደንብ ጠንካራ ዲስፕሊን ሊኖር አይችልም፡፡ እንዲሁም፣ ያለ ጠንካራ መሪ (በዋናነት አናቱ ላይ፣ ከዚያም በየደረጃው) ጠንካራ ዲስፕሊን ሊኖር አይችልም፡፡ ሁሉ ነገር የተያያዘ ነው፡፡ አንድ ነገር ልጨምር፡፡ በፖለቲካው ዓለም የታዘብኩት ነው፡፡ በሕወሓቶች ዘንድ፣ ከግለሰብ ይልቅ የድርጅትን ስኬት እንደሚያስቀድሙ ታዝቤያለሁ፣ በሌሎቻችን በኩል ግን፣ “ከእኛነት” ይልቅ“ እኔነት” እንዳለ ነው የሚታየኝ፡፡ በብዙዎች አንደበት የምሰማውም ይህንኑ ነው፡፡ “እኔን”  “በእኛ” ሳንተካ ግባችንን አንመታም፡፡
Filed in: Amharic