>

አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ ደርግ እና መስከረም 2/1967....!!! -( ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ)

አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ ደርግ እና መስከረም 2/1967….!!!

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

በፎቶው ላይ የምትመለከቱት እንደ ጎርጎርሳው አቆጣጠር ህዳር 3/ 1930 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥቅምት 24/1923) የታተመውን የታይም መጽሔት የፊት ሽፋን ነው፡፡ “ታይም” በዚህ እትሙ ዓለም አቀፍ አትኩሮት ስቦ የነበረውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዓለ ሲመትን የሽፋን ዘገባ በማድረግ በሰፊው ጽፎ ነበር፡፡ ታዲያ አጼው የታይም አብይ ርዕስ የሆኑት በዚህን ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ በበርካታ እትሞች ላይ ሰፊ የዘገባ ሽፋን አግኝተዋል፡፡ ይሁንና ከአጼው በስተቀር የሌሎች የኢትዮጵያ መሪዎች ህይወትም ሆነ የአስተዳደር ዘይቤ የታይም መጽሔት የሽፋን ዘገባ ሆኖ የቀረበበት ወቅት የለም፡፡ በሌላም በኩል ግን ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ እ.እ.አ. በ1935 የታይም መጽሔት “የዓመቱ ምርጥ ሰው” (Person of the Year) የሚለውን ክብር ተቀዳጅተዋል፡፡ በዚህም ረገድ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ በአፍሪቃ ደረጃም ቢሆን ከግብጹ አንዋር አል-ሳዳት በስተቀር ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር ይህንን ክብር የተጋራ ሰው የለም፡፡
  አጼ ኃይለ ሥላሴ በርግጥም በውጪው በጣም ነበር የሚከበሩት፡፡ የሚናገሩት ቃልም ተሰሚነት ነበረው፡፡ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትንና የገለልተኝነት ንቅናቄ ሀገራት ማህበርን በማቋቋም ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪቃ ሀገራት ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል፡፡ በሀገር ቤቱ ጉዳይ ግን ብዙም አልተሳካላቸውም፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን ህገ መንግሥት ያረቀቁት እኚሁ መሪ እውነተኛው ስልጣን የህዝብ ይሆን ዘንድ አልፈቀዱም፡፡ የባሪያ ንግድን በማጥፋት የዘመናዊነት ተስፋን የፈነጠቁት ንጉሥ በኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎች እንኳ ተወግዶ የነበረውን የገባር ስርዓት እንደገና በህዝብ ላይ ጭነዋል፡፡ ውሳኔዎችን በፓርላማ የማሳለፍ ባህልን ያስተዋወቁት “አጼ” ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ላለማስፈን በብርቱ ታግለዋል፡፡ በአገዛዝ ዘመናቸው የሀገሪቱን “አፈር ገፊ” አርሶ አደር አላንቀሳቅስ ካለው የመደብና የኢኮኖሚ ጭቆና  በተጨማሪ የሀይማኖትና የብሔር ጭቆናዎች የሀገሪቷን ቀፍደደው ይዘዋታል፡፡ ሀገሪቷ ወደፊት መንቀሳቀስ አቅቷት ትዋትት ነበር፡፡
    ለበርካታ ዘመናት ህዝቡ ጭቆናውንና መከራውን በግላጭ መቃወም ያልቻለው ህዝብ በውስጡ እየነፈረ ኖረ፡፡ ብሶቱ በቁጭት ሲያንተከትከው ከቆየ በኋላ የመጨረሻው ጥግ ደረሰ፡፡ ከ1965 መጨረሻ እስከ 1966 አጋማሽ ድረስ ሲታዩ የነበሩት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጦች ህዝቡን በስርዓቱ ላይ አነሳሱት፡፡ በየካቲት 1966 አብዮት ፈነዳ፡፡ ስልጣን ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ አመለጠች፡፡ ለብዙ ክፍለ ዘመናት ሲወራረስ የቆየው የሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ግብአተ መሬትም ሊፈጸም ተቃረበ፡፡
*****  *****  *****
ከየካቲት 12 እስከ ሰኔ 20/1966 የነበረው ጊዜ ድንግዝግዝ ያለ ነበር፡፡ በህዝብ አመጽ ስልጣን በለቀቀው የጸሓፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ካቢኔ ምትክ የተሾመው የልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ ሀገሪቱን እየመራ ነው ቢባልም እንደ ድሮው ተዋረድን በጠበቀ መልኩ አመራር መስጠትም ሆነ ውሳኔዎችን ማስፈጸም አልቻለም፡፡ ይህንን የተረዱ አንዳንድ የጦር ክፍሎችና የሲቪክ ቡድኖች አመራሩ ላይ ጉብ ለማለት ቢያሰፈስፉም በድፍረት ሊቀጥሉበት አልቻሉም፡፡ ሁሉም “ቀጣዩ ምን ይሆን” እያለ ሲቆዝም ከረመ፡፡
በዚያን ጊዜ ከሁሉም በላይ ነገሮችን የወጣጠረው የጦር ሀይሉ ለበላይ አመራር አልገዛም ብሎ ማፈንገጥ ነው፡፡ በተለይም ጦሩ “የጄኔራል ማዕረግ ያለው ማንኛውም ሰው አጠገቤ እንዳይደርስ” የሚል አቋም መያዙ በህዝብ ዘንድ የወደፊቱ ሁኔታ አስፈሪ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡
    ልጅ እንዳልካቸው ጦር ሀይሉን በዘዴ ሊያቀርቡት ሞከሩ፡፡ በአየር ወለዱ አዛዥ ኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ የሚመራ ቡድን በመመስረት ተቃውሞዎችን ሊያፍኑ ሞከሩ፡፡ ነገር ግን ጥረታቸው ፍሬ አልባ ሆኖ ቀረ፡፡ በሰኔ ወር አጋማሽ ገደማ ሁሉም የጦር ክፍል የየራሱን ኮሚቴዎች እያዋቀረ በነርሱ መመራት ጀመረ፡፡ በየኮሚቴዎቹ መካከል በተደረገ የመረጃ ልውውጥም ሀገሪቱን የሚመራ አንድ ቡድን ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ በዚህም መሰረት እያንዳንዱ የጦር ክፍል ማእረጋቸው ከሻለቃ በታች የሆኑ ተወካዮቹን በመምረጥ አዲስ አበባ ወደሚገኘው አራተኛ ክፍለ ጦር እንዲልክ ተነገረው፡፡ የጦር ክፍሎቹም እንደተባለው አደረጉ፡፡
   ከየጦር ክፍሎቹ የተላኩት ተወካዮች በአራተኛ ክፍለ ጦር ተሰባሰቡ፡፡ በሰኔ 21/1966 “የጦር ሀይሎች፣ የፖሊስ ሰራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ” የሚባል 120 አባላት ያሉት ወታደራዊ ሸንጎ መሰረቱ፡፡ ከሶስተኛ ክፍለ ጦር የመጡት ሻለቃ መንግሥቱ ሀይለማሪያም የኮሚቴው ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ የአራተኛ ክፍለ ጦሩ ሻለቃ አጥናፉ አባተ ምክትል ሊቀመንበር ተብለው ተሰየሙ፡፡ በሊቀመንበር መንግሥቱ ጠያቂነትም የሶስተኛ ክፍለ ጦሩ ሻለቃ ገብረየስ ወልደሃና የኮሚቴው ዋና ጸሓፊ ጠያቂነት ሆኑ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ኮሚቴው “ለምን በፈረንጅ ስም እንጠራለን” በሚል ምክንያት “አስተባባሪ ኮሚቴ” የተሰኘውን መጠሪያውን “ደርግ” በማለት ቀየረው (“ደርግ” የሚለውን ስም ያመነጨው የደርጉ የባህል ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበረው ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ ነው፤ በደርግ ወገን ሆነው ታሪኩን የጻፉ ወገኖች እንደገለጹት “ደርግ” የግዕዝ ቃል ሲሆን እኛ “ኮሚቴ” ከምንለው ጋር ተቀራራቢ ፍቺ አለው)፡፡
*****  *****  *****
ወታደሮቹ ያቋቋሙት “ደርግ” እንቅስቃሴውን ጀመረ፡፡ ከሁሉም በፊት ህጋዊነትን ማግኘት አስፈላጊው ስለነበረ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ቀርቦ ታማኝነቱን ገለጸላቸው፡፡ አጼውም ደርጉን በይሁንታ ተቀበሉት፡፡ በዚህ መሰረት ወታደራዊው ደርግ ከሲቪሉ የልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ ጎን ለጎን ሆኖ አመራር መስጠት ጀመረ፡፡ በስልጣናቸው ባልገዋል የተባሉ ባለስልጣናትንም አሰረ፡፡ ይሁንና ሁለቱ የአመራር አካላት በሚወስዷቸው የተቃረኑ እርምጃዎች ሊጣጣሙ ባለመቻላቸው አብረው መቀጠል ተሳናቸው፡፡ ይባስ ብሎም በሐምሌ  መገባደጃ ላይ ወታደራዊው ደርግ የልጅ እንዳልካቸውን ካቢኔ አፈረሰው፡፡ ከሚኒስትሮቹም መካከል በርካቶቹ ታሰሩ፡፡
     የወታደሮቹ ደርግ የንጉሠ ነገሥቱን ስልጣን ቀስ በቀስ መገዝገዝ ጀመረ፡፡ እንደ ዘውድ ምክር ቤት፣ የዙፋን ችሎትና የጸጥታ ካቢኔ (ልዩ ካቢኔ) የመሳሰሉ ተቋማትን አፈረሰ፡፡ በጥናት ላይ የነበረው አዲሱ ህገ መንግስትም እንዲታገድ ወሰነ፡፡ ፓርላሜንቱም ዳግመኛ ላይሰበሰብ ተበተነ፡፡
    ከዚህ ጎን ለጎን ደርግ የህዝቡን ስነ-ልቦና ለራሱ አመራር ዘመን የማዘጋጀቱን ተግባር ተያያዘው፡፡ የንጉሡንና የዘውዳዊውን ስርዓት ገመና ማጋለጥ ጀመረ፡፡ ንጉሡ ከጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካና ከከተማ አውቶቡስ አገልገሎት ከፍተኛ ገቢ እንደሚዝቁ የሚገልጹ ፕሮግራሞችን በመገናኛ ብዙሀን አስተላለፈ፡፡ በመጨረሻው ላይ ግን መላውን ህዝብ ያስለቀሰውንና የ1965ቱን የወሎ ረሐብ የሚዘግበውን ዶክመንተሪ ፊልም አሳየ፡፡ በዚህም ህዝቡ ለስርዓቱ ያለውን ገደብ የለሽ ጥላቻ አሳየ፡፡
*****  *****  *****
መስከረም ሁለት/1967….. ከጧቱ 3፡00 ሰዓት… በብሔራዊ ቤተ መንግሥት…..
በደርጉ ውስጥ የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆነው የተሰየሙት ሻለቃ ደበላ ዲንሳ ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን መውረዳቸውን እንዲያረዳቸው የተመረጠውን አስራ ሶስት አባላት ያሉትን ቡድን እየመሩ ከቤተ መንግሥት ደርሰዋል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ንጉሡ ፊት ቀርቦ መልዕክቱን የሚነግርበትን ድፍረት አጣ፡፡ ጥቂት ካሰቡ በኋላ ግን ሻለቃ ደበላ አንድ ዘዴ ብልጭ አለችባቸው፡፡ የንጉሡ የቅርብ የስጋ ዘመድ የሆኑት ልዑል ራስ እምሩ ሀይሥ ስላሴ “ለደሃው ገበሬ የሚቆረቆሩ ተራማጅ መስፍን ናቸው” ማለትን ስለሰሙ እርሳቸው ባሉበት ንጉሡ መልዕክቱን እንዲሰሙት ቢደረግ ግዳጃቸውን ያለ አንዳች ችግር መፈጸም የሚችሉ ሆኖ ታያቸው፡፡ በዚህም መሰረት ጉዳዩን ለራስ እምሩ አስረዱ፡፡ ራስ እምሩም ይሁንታቸውን ገለጹላቸው፡፡ በቀጣይ የሆነውን ሻለቃ ደበላ ዲንሳ እንደሚከተለው ተናግረውታል፡፡
  “የደርጉ መልዕክተኞች ሆነን የመጣነው አስራ ሶስታችንም ስድስት በአንድ በኩል፣ ስድስት በሌላ በኩል ተሰልፈው፣ እኔ መሀከላቸው ሆኜ ነበር የቆምኩት፡፡ ትንሽ ከጠበቅን ኋላ ጃንሆይ ከፎቅ እየወረዱ መሆናቸው ተነገረንና በተጠንቀቅ ቆምን፡፡ ትልቁ የዙፋን አዳራሽ ውስጥ ነበርን፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ገብተው ወንበራቸው ላይ እንደተቀመጡ አንድ እርምጃ ወደፊት ሄጄ በመቅረብ ወታደራዊ ሰላምታ ግጥም ካደረግኩ በኋላ በደርጉ ተዘጋጅቶ የተሰጠኝን ጽሑፍ አነበብኩና እንደገና ወታደራዊ ሰላምታ ሰጥቼ አንድ እርምጃ ወደኋላ በመራመድ ከጓደኞቼ ጋር ተቀላቅዬ ቆምኩ፡፡ ከስልጣን መውረዳቸውን የሚገለጽ ከሁለት፣ ሶስት መስመር ያልበለጠ አጭር ጽሑፍ ነበር፡፡”
(ገነት አየለ አንበሴ፣ የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ትዝታዎች፣ 1994፣ ገጽ 22-23)
ሻለቃ ደበላ መልዕክቱን ከተናገሩ በኋላ እንዲህ አሉ፡፡
  “ግርማዊ ሆይ! የጦር ሀይሎች፣ የፖሊስ ሰራዊትና የብሔራዊ ጦር ደርግ ለግርማዊነትዎ ጤንነትና ደህንነት በሰፊው የሚያስብ እንደመሆኑ መጠን ለርስዎ ደህንነት የተዘጋጀ ስፍራ ስላለ ወደዚያ እንዲሄዱልን በትህትና እንለምናለን”
   አጼ ኃይለ ሥላሴ በሻለቃ ደበላ የተነበበውን ጽሑፍ ካዳመጡ በኋላ ጥቂት ደቂቃዎችን በዝምታ ቆዩ፡፡ ከዚያም በአጭሩ
   “ያነበባችሁትን ሰምተናል! አሁን እናንተ በተራችሁ ሀገራችሁን ትመሯት ዘንድ ፈቅደናል፣ ሁሉንም ተቀብለናል” የሚል ቃል አሰሙ፡፡
  (የሻለቃ ደበላንና የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን የመጨረሻ ንግግር ለማዳመጥ የሚከተለውን ሊንክ ይንኩ፡፡ http://www.youtube.com/watch?v=aL8dh8jcqzQ )
 *****  *****  *****
ከጠዋቱ 4:00… ከቤተ መንግሥት ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር….. 
ደርጎች ለሁለት ወራት ያህል ሲያካሄዱት የነበረው “ረጅም መፈንቅለ መንግሥት” በዚህ ሁኔታ ተገባደደ፡፡ ለአርባ ሶስት ዓመታት ሀገሪቱን በፍጹም ዘውዳዊ ስርዓት የገዙት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ በዚህ መንገድ ከዙፋናቸው ወረዱ፡፡ ቢሆንም ግን ንጉሥ ነበሩና ተቃዋሚ ሀይል እንዳያንቀሳቅሱባቸው የሚፈሩት ደርጎች ከቁጥጥራቸው ነጻ እንዲሆኑ አልፈቀዱላቸውም፡፡ ስለዚህ በአራተኛው ክፍለ ጦር በተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንዲቆዩ ተወሰነ፡፡ በዚህም መሰረት ወደ ክፍለ ጦሩ ግቢ ሊወሰዱ ሆነ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ደርጎች ወደሚፈልጉት ቦታ ለመሄድ ተነሱ፡፡ ከቤተ መንግሥቱ ወጥተውም መኪናቸውን በዓይናቸው ፈለጓት፡፡ ነገር ግን እርሳቸው ፍጹም አይተዋት በማያውቋት “ቮልስዋገን ቢትልስ” እንዲሄዱ መወሰኑ ተነገራቸው፡፡ “ምነው?” ቢለው ቢጠይቁ “ለደህንነትዎ ሲባል ነው” የሚል መልስ ተሰጣቸው፡፡
   አጼ ሀይለ ስላሴ ወደ መኪናዋ ገቡ፡፡ በሾፌርነት የተመደበው የደርጉ ዘመቻና ጥበቃ ሃላፊ ኮ/ል ዳንኤል አስፋው መኪናዋን ማንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ሆኖም መኪናዋ ገና የቤተ መንግሥቱን ግቢ ከመልቀቋ “ሌባ..ሌባ..ሌባ…ሌባ…” በሚሉ ጯሂ ሰልፈኞች ተዋከበች፡፡ ኮ/ል ዳንኤል ግን በጩኸቱ ሳይረበሽ ትርምሱን ሰንጥቆ አለፈ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም አራተኛ ክፍለ ጦር ከደረሱ በኋላ ለአስራ አንድ ወራት የሚቆየውን የግዞት ህይወታቸውን ጀመሩ፡፡
*****  *****  *****
መስከረም 2/2006
—–
Filed in: Amharic