>

ጳውሎስ ኞኞ―የማያልቀው የጋዜጠኝነት፣ የድርሰት፣ የሰውነት ሃብታችን!!! (ጥላሁን ማሞ)

ጳውሎስ ኞኞ―የማያልቀው የጋዜጠኝነት፣ የድርሰት፣ የሰውነት ሃብታችን!!!

ጥላሁን ማሞ

ጳውሎስ ኞኞ ልክ እንደ አብርሃም ሊንከን  የተማረው እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ ነበር። የዚህ ምክንያት ድህነት ነበር። አብርሃም ሊንከን አንድ አባባል ነበረው―”እግዚአብሔር ድሆችን በጣም ይወዳቸዋል ለዚህ ነው አብዝቶ የፈጠራቸው”። ጳውሎስ የተማረው መደበኛ ትምህርት ጥቂት ቢሆንም እራሱን በራሱ በንባብ አስተምሮ የበቃ ጋዜጠኛ ሆኗል።
§§§
ጳውሎስ በልጅነቱ በድህነት ምክንያት ትምህርቱን አለመከታተል ብቻ ሳይሆን ገንዘብ ለማግኘት ስራ መስራት ነበረበት። ታዲያ ጳውሎስ እንቁላል ለስላሳ የመሳሰሉትን ይሸጥ ነበር። በገበያው ለመላቅ የሚሸጣቸውን እንቁላሎች በህብረቀለም እያስዋበ ይቸበችብ ነበር። የራሱን የሆነ የለስላሳ መጠጥ ቀምሞ ይሸጥ ነበር። አእምሮው ውስጥ የነበረው የፈጠራ እርሾ በሁሉም መስኩ ራሱን ይገልጥ ነበር። ኋላ ጳውሎስ ጋዜጠኛ ሲሆን የፈጠራ ችሎታው ትልቁን ቦታ አገኘና ግሩም ፀሐፊ ሆነ።
§§§
ጳውሎስ ከአብራኩ ለወጣው ልጁ ሃዋርያው ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህፃናት አባት ነበር። ሁለተኛው አባባ ተስፋዬአችን ነበር። ባለ ስድስት ቅፁ “አስደናቂ የአለም ታሪኮች” ለሁላችንም የተበረከተ ስጦታ ነበር። እነዚህ መፅሀፍት ውስጥ የተካተቱት እልፍ ጣፋጭ ታሪኮች ልጅነታችንን አጣፍጠውልናል።
§§§
 ጳውሎስ ሁሌም “የማያልቀው ሀብቴ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው” ይል ነበር። ይሄም አባባል ለማሳመር ሳይሆን ጳውሎስ ቤቱን በሁላችንም ልብ ውስጥ ለመስራቱ መግለጫ ነው።
§§§
ከደርግ መውደቅ በኋላ የፕሬስ ነፃነትን ተከትሎ ብዙ መጽሔቶች እንደ አሸን ፈልተው ነበር። ከሁሉም በላይ ግን ሩሕን አስታውሳለሁ። ምክንያቱም ሩሕ እንደ ሌሎቹ ደረቅ አሰልቺ ፖለቲካ ሳይሆን ሰው ሰው የሚሸት ነበር። የዚህ ምክንያት ደግሞ ዋና አዘጋጁ ጳውሎስ ኞኞ ነው። ሩሕ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የጳውሎስ ኞኞ ፅሁፎች ውስጥ ሃሳቡን ብቻ ሳይሆን ልቡን ማየትም ይቻላል። ጳውሎስ ትልቅ ልብ ያለው ጋዜጠኛ ነበር። ታድያ ጳውሎስ ብዙም ሳይቆይ በህመም በማረፉ መጽሔቱ በድሮው ተወዳጅነቱ መቀጠል ስላልቻለ ቀስ በቀስ ከሰመ።
§§§
 ጳውሎስ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ “አንድ ጥያቄ አለኝ” የሚል አምድ ነበረው። አዝናኝነቱ አሁን ድረስ ይታወሰኛል። ልቆንጥርላችሁ፦
፩) ጥያቄ፦ ጳውሎስ አዲሳባ ውስጥ ዱርዬ ሰፈር የቱ ነው?
  ጳውሎስ፦ አልናገርም! ከጨርቆስ ልጆች ጋር ልታጣሉኝ ነው!
፪) ጥያቄ፦ ጳውሎስ …የኢሰፓን ልሳን የሆነውን ‘ሰርቶ አደር’ ጋዜጣን ትወደዋለህ?
ጳውሎስ፦ ሰውየው “ማርያምን ትወዳታለህ ወይ?” ተብሎ ሲጠየቅ፡ “ከግንድ የሚያላትም/የሚያላጋ/ልጅ እያላት እንዴት አልወዳት?” ብሏል አሉ…
ጳውሎስ በዚሁ ጋዜጣ “ለእግዚአብሔር የተፃፈ ደብዳቤ” ብሎ ያስነበበውም የማይረሳ ነው። ደብዳቤው ሲጀምር እንዲህ ይላል(ቃል በቃል አይደለም)
“እግዜር ለመሆኑ እንዴት ነህ? በእርግጥ ጤንነት አንተ የምትሰጠውና የምትነሳው ጉዳይ ስለሆነ አንተን መጠየቁ ተገቢ አይደለም  . . . ” እያለ ይቀጥላል። ብቻ ጳውሎስ ደፋር ነበር።
§§§
 የጳውሎስን ሰውነት እና ድፍረት የሚያሳይ አንድ ታሪክ ልጨምር። በ66ቱ ረሃብ ወቅት የንጉሡ መንግሥት ረሃብተኞቹን ትኩረት ነፈገ። ሰውዬው ጳውሎስ ግን ገንዘብ አሰባስቦ ከብት አርዶ ረሃብተኞቹን መገበ። ለስሙ ሳይሆን ሰብአዊነቱ ነበር። ንጉሱ የዘውድ በአላቸውን እያከበሩ የረሃቡን መኖር ክደው ነበር። ይህ የጳውሎስ ድፍረት ሊያሳስረው ቢችልም ጉዳዩ አልነበረም። ጉዳዩ ረሃብተኞቹን መመገቡ ነበር። ጳውሎስ ሰው በጠፋበት ሰው የሆነ ሰው ነበር።
§§§
በኢትዮጵያ ታሪክ ፅሁፍ ውስጥ ተክለፃድቅ መኩሪያን የሚያክል የለም። የኢትዮጵያን ታሪክ በስፋትና በጥልቀት በ13 ቅጾች አቀብለውናል። መፅሀፎቻቸው በመረጃ የደለቡ ናቸው። በአፃፃፍ ለዛ ግን የጳውሎስ አራት የታሪክ ስራዎች ይረቁብኛል።
Filed in: Amharic