>

‹ዋጋዬማ አትታረድም!›› - ሀገሬስ ለእኛ ለዜጎቿ እንዲህ አይነት እረኛ የምታቆመው መቼ ነው??? (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

‹ዋጋዬማ አትታረድም!›› – ሀገሬስ ለእኛ ለዜጎቿ እንዲህ አይነት እረኛ የምታቆመው መቼ ነው???
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

‹‹ዋጋዬማ አትታረድም!››.. ‹የስነጥበብ ግብ ከማህበረሰብ ፊት ቀድሞ ለነገው ማዋጣት እንጂ፣ ከኋላው እየተከተሉ በጣለው ቆሻሻ መጫወት አይደለም› የምለው ለዚህ ነው፡
ስነጥበብ በምጡቅ ምናብ (elivated imagintion) እና በውበት ስሱነት (sensitivity to beauty) ዳግም የሚፈጠር እውነት ነው፡፡ እቅጬ እውነት (fact) አይደለም፣ እውነት (truth) ነው፡፡ እውነት ከእቅጬ እውነት የሰፋ፣ የፋፋ፣ የተንሰራፋ ነው፡፡ ይህ መስፋት – መፋፋቱ ነው የምንኖርበትን ሁለንተናዊ መስተጋብር ውጤት (እቅጬ እውነታችንን) እንድናጠይቅ የሚጎነትለን፡፡ ስነጥበብ እቅጬ እውነታችንን እንድንቀበል ሳይሆን እንድንጠይቅ፣ እንድንመረምር ሲያደርግ ለግቡ በቅቷል፡፡
.
የስነጥበብ ጉንተላ የማህበረሰብን ህሊናዊ ልእልና ይሞርዳል፤ የተሞረደ ህሊና ሳይቆርጥ – ሳያደማ በተወረወረለት ሀሳብ ላይ አይደላደልም፡፡
.
‹‹ዋጋዬማ አትታረድም!›› (እረኛዬ ተከታታይ ድራማ፣ ክፍል 4) ትላለች እናና፤ ከከብቶቿ ጋር ገደል የምትገባዋ እረኛ፡፡ ‹‹ሀገሬስ ለእኛ ለዜጎቿ እንዲህ አይነት እረኛ የምታቆመው መቼ ነው? በከተማ በገጠሩ፣ በየወንበሩ እንደ እናና ያሉ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያንስ አይሞቱም!›› የሚሉ፣ ከሚያስተዳድሯቸው ዜጎች ቀድመው ገደል የሚገቡ፣ በተተኮሰበት ጥይት ፊት የሚቆሙ እረኞች የምናገኘው መቼ ነው? . . . ይጎነትላል፡፡
የራሔል ጌቱ ‹‹ኢትዮጵያዬ›› የሚለው ዘፈን በዘነጋነው እቅጬ እውነት የገነነ ውበት ነው፡፡ ውበቱ ይቆጠቁጣል፤ እውነቱ ይሸነቁጣል፤ አይደለድልም፤ ይፈረፍራል፡፡ . . . .
እንደነዚህ ያሉ ስራዎች ዛሬያችንን አስጠይቀው ለነገ መልስ ያንደረድራሉ፣ የዛዬያችንን ጥቀርሻ ባንጠርገው መኖሩን አውቀን እንድንጸየፈው ያደርጋሉ፡፡  . . ‹የስነጥበብ ግብ ከማህበረሰብ ፊት ቀድሞ ለነገው ማዋጣት እንጂ፣ ከኋላው እየተከተሉ በጣለው ቆሻሻ መጫወት አይደለም› የምለው ለዚህ ነው፡፡

 

Filed in: Amharic