የኢትኖግራፊ ጉዞ ወደ ጎጃም
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
ያ በእውቀቱ ስዩም የሚሉት ጎጃሜ ብላቴና አምናና ዘንድሮ የኛዋን ኦሮሚያን በብዕር መነካካቱን አብዝቷል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ “ይሄ ልጅ ለምን አያርፍልንም? እኛም እርሱን ስላፈራችው ጎጃም መጻፍ የማንችል መሰለው እንዴ” እያልን ከራሳችን ጋር ስንነጋገር ቆይተናል (“እኛ” ወልደ-ገለምሶ ዘብሔረ ሀረርጌ በመሆናችን ባሰኘኝ ጊዜ እንደ ጃንሆይ “እኛ” የማለት ሊቼንሳ ያለን ባለመብት መሆናችንን እያስታወሳችሁ!)፡፡ በዛሬዋ ሌሊት ግን ነገሩ ይለይለት አልኩኝና ስለጎጃም መጻፍ ጀመርኩ፡፡ “አነ ወጠንኩ እጽሕፈ መጣጥፈ ሕሩይ ለምድረ ጎጃም ዘነገደ ግዮን” እንዲል ግዕዙ!
አንቺዬ ጎጃም ነን ያላችሁ
ውረዱ እንያችሁ!
አዎን!! ዛሬ ወደ ጎጃም ልንጓዝ ነው! ደጀን ላይ ምሳ ልንበላ ነው! ዲማ ጊዮርጊስ ላይ ቅኔ ልንዘርፍ ነው፡፡ ደብረ ወርቅ ላይ “ድጓ” ልንማር ነወ፡፡ ደብረ ኤሊያስ ላይ “ታሪከ አበው” ልናነብ ነው፡፡ ማንኩሳ ላይ “ታሪከ ሀገር” ልንመረምር ነው፡፡ መርጡለ ማሪያም ላይ “ታሪከ ነገሥት” ልንበረብር ነው፡፡ ቢቸና ላይ የበላይ ዘለቀን ጀግንነት ልናደንቅ ነው፡፡ መራዊ ላይ በ“ድርሳነ እጽ” ልንፈወስ ነው፡፡ ባሕር ዳር ላይ ዓሳ ለብለብ ልንበላ ነው፡፡ የዛሬው የኢትኖግራፊ ጉዞአችን ወደ ጎጃም ነው፡፡ ዳይ! ዳይ! ዳይ!
——–
ጎጃምን በቀዳሚው ዕድሜአችን (ከ1983 በፊት) በሚዲያና በትምህርት ቤት ባወቅናቸው የጣና ሐይቅና የጢስ ዐባይ ፏፏቴ ውበት፣ የበላይ ዘለቀ የጀግንነት ገድል፣ የየትኖራ ገበሬዎች ማህበር ብልጽግና እና የግሽ አባይ ኪነት ቡድን ሀገር አቀፍ ዝና አማካኝነት ተዋውቀናት ነበር፡፡ ጉርስምና መጥቶብን ለአቅመ አዳም ካበቃን በኋላ በተጠናወተን የንባብ ባህል ልደታቸው በጎጃም የተበሰረውን እነ አራት ዐይና ጎሹን፣ እነ ተድላ ጓሉን፣ እነ ራስ አዳልን (ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን)፣ እነ ቆምጬ አምባውን፣ እነ ሙሉጌታን ሉሌን፣ እነ ብርሃነ መዋንና ሌሎችንም ሀገር-አቀፍ አድባሮችን ስናውቅና ዝክረ ታሪካቸውን ስንመረምርማ ጎጃምን ስለማየት ማለም ጀመርን፡፡ እያደር የህልማችን ጡዘት እንደ አባይ ወንዝ እየተጥመለመለ ሲያራውጠን ደግሞ እኛም የወንዙ ልማድ ተጋብቶብን ህልማችንን እንደ ግንድ ይዘን ስንዞር ባጀን፡፡ ይኸው እንግዲህ ብሩህ ህልም አልመን፣ ብሩህ ምኞት አርግዘን፣ በአምሮት እየተጠለዝንና በፍላጎት እየተንጠራወዝን ከህልማችን ጋር እዚህ ደርሰናል፡፡
ዋናው ተስፋ አለመቁረጥ ነው ጓዶች!! “ተስፋ…የደሃ ወዚፋ” እንዲሉ የሱፊ ከቢሮቻችን (የ“ደሃ ሀብት” ማለታቸው ነው)፡፡ በርግጥም ጎጃምን ባናየውም “እናየዋለን” ማለታችንን አላቆምንም፡፡ ወደፊትም በዚሁ እንቀጥላለን፡፡ ጀሊሉ አንድ ቀን ህልማችንን ያሳካልናል ብለንም እናምናለን! ያ ቀን መጥቶ ምኞታችን እውን እንዲሆንልን በብርቱ እየተመኘን የህልማችን ማስቀጠያ ትሆን ዘንድ ጎጃምን በዐይነ ህሊናችን ያየንባትን ጽሑፍ ለጀማው እንዲህ እናበረክታለን፡፡
——–
አዎን! ዛሬ ፍኖተ ሰላም ነን! ዛሬ ጎዛምን ነን! ዛሬ ዳንግላ ነን! ዛሬ ሞጣ ነን! ዛሬ ዱርቤቴ ነን! በምናባችን እንደ ኢስከንደር (እስክንድር) ባለ ክንፉን ሐሳብ-ወለድ ፈረሳችንን እየጋለብን ወደ ተናፋቂው የጎጃም ምድር ገባን!
ከሁሉም ከሁሉም ከሁሉም በላይ
የጀግና አገር ጎጃም መጣሁ አንተን ላይ፡፡
የአገሬ የወንዜ ሸበላ
ቡሬ ዳሞት ነው ዳንግላ
ቆየኝ መጣሁልህ አንተን ብዬ
ጎጃሜ ነህ ሲሉኝ ተከትዬህ፡፡
ፍቅረ አዲስ ነቅዐ-ጥበብ የዛሬ 24 ዓመት ገደማ ባወጣችው ካሴት ስለጎጃም ያዜመችውን ነው በራሴ መንገድ እንዲህ የጻፍኩት (ዓመታቱ በጣም ስለሄዱ ከግጥሙ ስንኞች ግማሾቹን ረስቼአቸዋለሁ)፡፡ እርሷ ጎንደሬ ስለሆነች በደጃፏ ላይ ያለውን የጎጃም ምድር መዘየርን የውሃ መንገድ አድርጋው እንደኖረችው አንጠራጠርም፡፡ ከዓመታት በኋላ ደግሞ ነዋይ ደበበ ተነሳና እንዲህ ብሎ አዜመ፡፡
ልቤ ፍቅር ሠራ አባይ ወዲያ ማዶ
የበላይዬን ዘር ጎጃሜዋን ወዶ፡፡
ሁለቱ ከያኒያን ለሸበላውና ለጉብሏ ነበር ያቀነቀኑት፡፡ እኛ የኢትኖግራፊ ወግ መሞካከር እንደ ቁራኛ የተለጠፈብን ለማጅ ጸሐፊ ግን እገሌ እገሌ ሳንል ስለጎጃም ህዝብ በሙሉ ብንዘምር ነው የሚያምርብን! የጎጃምን ምድር በሙሉ ብንዞር ነው የሚብስብን!
ጎጃም የነገረ መለኮት ሀገር! የጾመ-ድጓ ሀገር! የስንክሳር ሀገር! የቅኔ ማህሌት ሀገር! የወረብ ሀገር! የሽብሸባ ሀገር! ቱባ የእምነት ርእዮቶችና አስተምህሮዎች የፈለቁበት የሃይማኖት ምድር!
ጎጃም የቅኔ ሀገር! የግጥም ሀገር! የመዲና ሀገር! የዘለሰኛ ሀገር! የክራር ሀገር! የመሰንቆ ሀገር! እጅግ ውብ የሆነ የኪነት ሀብት የሞላበት የጥበብ መንበር!
ጎጃም የሰዋስው ሀገር! የጽሕፈት ሀገር! የሥርዓት ሀገር! የዘይቤ ሀገር! የፈሊጥ ሀገር! የውረፋ ሀገር! የነቆራ ሀገር! የስላቅ ሀገር! የአሽሙር ሀገር! የአንክሮ ሀገር! የኩሸት ሀገር! የአግቦ ሀገር! አስገራሚ የአነጋገር ብሂሎችና የቋንቋ ዐውዶች የፈለቁበት ደብር!
ጎጃም የድግምት ሀገር! የመስተፋቅር ሀገር! የመስተዋድድ ሀገር! የአሸን ክታብ ሀገር! የጥላ ወጊ ሀገር! አነጋጋሪ የሆኑ የመተትና የአስማት ስነ-ቃሎች የገነኑበት መንደር!
—-
ስለጎጃም ልጽፍ ስነሳ “እኔም ትረካዬን እንደ በእውቀቱ ስዩም፣ እንደ ደመቀ ከበደ እና እንደ ኑረዲን ዒሳ በግጥም ላስኪደው እንዴ?” አሰኝቶኝ ነበር፡፡ ምክንያቱ ምን መሰላችሁ?… በጎጃሜዎች ዘንድ እንደ ልዕላይ ንግግር (elite speech) የሚወሰደው የመግባቢያ እና የመናበቢያ መንገድ ቅኔ መዝረፍና የግጥም ስንኞችን መቋጠር ስለሆነ ነው፡፡ በርግጥም የጎጃምን ሰው ረብጣ ብር አስታቅፈኸው ስድ-ንባብ ከምታነበንብለት ይልቅ የሀረሩን “ሁልበት ብላሽ” በልተህ፣ የብላሽ ብዕርእን ጨብጠህ፣ ሁለት ስንኞችን ብቻ በመወርወር ጆሮውን ብትኮረኩረው ይመርጣል ነው የሚባለው፡፡ ጎጃሜው ስለራሱ እንዲናገርና ስለሀገሩ እንዲገልጽ በተፈቀደለት ጊዜም ግጥምና ቅኔውን ቢያስቀድም ነው የሚሻለው፡፡ ሌላው ነገር ይቅርና በርካታ የጎጃም ተወላጅ ስሙ ከአባቱ ስም ጋር ተቀናጅቶ ሲጻፍ አንድ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ትገነዘባላችሁ፡፡
እያደር አዲስ
ፍቅር ይልቃል
አዱኛው ሲፈራው
እስከ-አድማስ ማን-በግሮት
ስንሻው ተገኘ
ወዘተ….ወዘተ….
በእርግጥም የጎጃም ምድር ከቅኔና ከግጥም ጋር መርፌና ክር መሆኑ ዘወትር የሚያስገርመኝ ጉዳይ ነው፡፡ እስቲ እንደ ዋዛ ተቋጥረው የሁላችንም ሀብት ለመሆን የበቁ ህዝባዊ ግጥሞቻችንን ተመልከቷቸው፡፡ በጣም ልብ ከሚሰረስሩት መካከል ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ከጎጃም የፈለቁ፣ አሊያም በጎጃሜዎች የተገጠሙ፣ ወይ ደግሞ ስለጎጃም ስም የሚያወሱ ሆነው ነው የምታገኟቸው፡፡ ለአብነቱም ይህንን ግጥም ውሰዱ!!
ሞጣ ቀራንዮ ምነው አይታረስ
በሬ ሳላይ መጣሁ ከዚያ እዚህ ድረስ፡፡
“ክፉ ቀን” እየተባለ በሚጠራው የረሀብና የጠኔ ዘመን ህዝብ እንደ ቅጠል መርገፉን ያየ ተመልካች ነው ይህንን የተቀኘው፡፡ በዘመኑ የረሀቡን ጽልመታዊ ገጽታና የጠኔውን አሰቃቂ ድባብ የሚያሳዩ ብዙ ግጥሞችና ቅኔዎች ከየአቅጣጫው የተወረወሩ ቢሆንም ከሁሉም በላይ ገንኖ የወጣው ይህ ጎጃም-በቀል ግጥም ነው፡፡ ገጣሚው “ቀራንዮ” እና ሞጣ በሚባሉት አካባቢዎች ያየው የሬሳ መአት ናላውን ቢያዞረው ነው አሉ እንዲህ ብሎ የተቀኘው፡፡
ጀግናው በላይ ዘለቀ “ስዩመ እግዚአብሄር የሆኑትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከስልጣን ለመገልበጥ አሲረሃል” በሚል ያለ ጥፋቱ ተወንጅሎ በስሙኒ ገመድ በተሰቀለበትና ጣሊያንን በባንዳነት ያለገለገሉ ሰላቶዎች በየአጥቢያው በተሾሙበት ወቅት ደግሞ እንዲህ ተብሎ ተገጥሞአል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡፡
ጎጃም በአንድ ክፍለ ሀገር ብቻ በተማከለበት ዘመን ዋና ከተማው ደብረ ማርቆስ ነበረች፡፡ ለዚህች ከተማ መቆርቆር ምክንያት የሆነው ሰው ሳሊሕ ጠይብ የተባለ ነጋዴ ነው አሉ፡፡ ይህ ነጋዴ ለአካባቢው የመጀመሪያ የሆነውን ቆርቆሮ ቤት በአሁኗ የደብረ ማርቆስ ከተማ የሠራው 20ኛው ክፍለ ዘመን እንደባተ ነው፡፡ ታዲያ የጎጃም ሕዝብ የርሱን ቤት በጥንቱ ዘመን ተወዳጅ ከነበረው “ደንገላሳ” የተባለ የፈረስ ግልቢያ ስልት ጋር በማቆራኘት እንዲህ የሚል ግጥም ቋጥሯል ይባላል፡፡
ፈረሴን ኮርኩሬ ብለው ደንገላሳ
የሳሊሕ ጠይብ ቤት ቆርቆሮው ተነሳ፡፡
እንደዚህ ግጥም አዋቂ የሆነውን ጎጃሜ በአክብሮት ከቀረባችሁት በእጥፍ ያከብራችኋል፡፡ በነገር ወጋ ካደረጋችሁት ግን አለቀላችሁ!! ለትንኮሳችሁ ምላሹን ሲሰጥ ለጊዜው እንጀራ ፍርፍር የመሰለ ቅኔ ቋጥሮ በሳቅ ያንፈራፍራችኋል፡፡ ምሳ ሰዓት ላይ “ወስዋስ” ቢጤ ይጀማምራችሁና “ይህ ጎጃሜ የወረወረብኝ ቅኔ የመስተፋቅር ፍላጻ ይሆን እንዴ?” በማለት ህብሩን ለመመርመር ትነሳሳላችሁ፡፡ በምሽት ሰዓት የቅኔው ሚስጢር ሲገባችሁ ደግሞ ቀን ከሳቃችሁት በላይ ንዴቱ አንጀታችሁን ንፍር ያደርጋችኋል፡፡
በቃ እመኑኝ ነው የምላችሁ!! ጎጃሜውን በፍቅር ብትቀርቡት ነው የሚያዋጣችሁ!! በመውደድና በመደድ ከቀረባችሁት በሐሴት ፌሽታ ያንበሸብሻችኋል፡፡ በሙሐባ ድር ተብትቦአችሁ ወደ ፍስሐ አፀድ ያስገባችኋል፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም አርቲስቱ እንዲህ በማለት የዘፈነው፡፡
የበላይን ጸባይ ይዘዋል ሰዎቹም
ለፍቅር ነው እንጂ ለጸብ አይመቹም፡፡
——-
ታዲያ ጎጃሜ ገጣሚ ብቻ አለመሆኑን እያስታወሳችሁ ጓዶች!! በዝርው ጽሑፍም ቢሆን አደገኛ የሆነ ህዝብ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የአማርኛ የልበ ወለድ ድርሰት የጻፈው አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ እና “አልወለድም” በተሰኘው አነጋጋሪ መጽሐፍ የሚታወቀው አመጸኛና ልበ ደንዳና ደራሲ አቤ ጉበኛ የተወለዱት በጎጃም ምድር ነው፡፡ ከሁሉም ጸሐፊዎቻችን ብዙ የተነገረለትና ልደቱ በጎጃም የተበሰረው የልብ ወለድ ደራሲ ግን ሌላ ነው፡፡
“ፍቅር እስከ መቃብር”ን የማያውቅ አለን?…የአማርኛ ልብ-ወለድ ድርሰቶች ጉልላት ተደርጎ የሚታየው እርሱ ነው፡፡ በመጽሐፉ የተወሱት እነ በዛብህ፣ እነ ሰብለ ወንጌል፣ እነ ጉዱ ካሳ፣ እነ ፊታውራሪ መሸሻ ከቤተሰቦቻችን አባላት አንዱ እስኪመስሉን ድረስ በብዙዎቻችን ልብ ኖረዋል፡፡ የወጣት አንባቢዎችን ልብ ሰቅሎ የሚወዘውዘው የመጽሐፉ አጸቅ በበዛብህና በሰብለ-ወንጌል መካከል የነበረው ጥልቅ ፍቅር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቴዲ አፍሮ በለቀቀው አዲስ አልበምም በጥንዶቹ መካከል የነበረውን ፍቅር እጅግ ልብ በሚነካ ግጥምና በተዋበ ዜማ ዘክሮታል፡፡ የመጽሐፉን ይዘት በዘመኑ ከነበረው የተዘበራረቀ የማኅበረሰብ አወቃቀር እና የደራሲው ተራማጅ አስተሳሰብ ጋር በማነጻጸር የገመገሙ ምሁራን ግን “መጽሐፉ የተጻፈበት ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተጭኖ የነበረውን የፊውዳል ስልተ-ምርት አስከፊነት በተዋዛ ቋንቋ ማስተማርና የስርዓት ለውጥ እንዲደረግ በስልታዊ ዘዴ መጎትጎት ነው” ይላሉ፡፡
በርግጥም ደራሲው ለህዝብ የነበረውን ተቆርቋሪነት ያስተዋለ ሰው ከምሁራኑ አባባል ጋር ይስማማል፡፡ ለምሳሌ በደራሲው ብዕር የተቀረጸው ካሳ ዳምጤ (ጉዱ ካሳ) የተሰኘ ገጸ-ባሕሪ የፊውዳሉን ሥርዓት በመረሩ ቃላት ሲሸረድደው ከመጽሐፉ እናነባለን፡፡ ይህ ገጸ-ባሕሪ “በአጥር ካብ ከስር ሆኖ ከላዩ ሌላ ግዑዝ የተጫነው ድንጋይ ለዘልዓለም እንዲሁ አይኖርም፣ ካቡ ሲያረጅ ከላይ ያለው ድንጋይ ተንዶ መንከባለሉ የማይቀር ነው” እያለም የሥርዓቱን መውደቅ ሲተነብይ እናያለን (ዐረፍተ-ነገሩ ቃል በቃል አልተጻፈም)፡፡ በሌላ በኩል በዘመኑ ቱባ የመንግሥት ባለስልጣን የነበሩት የመጽሐፉ ደራሲና እንደርሳቸው ተራማጅ የነበሩት አስር የዐፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት በቢሾፍቱ ሐይቅ ዳር ተሰባስበው ከተነጋገሩ በኋላ በቃለ-ጉባኤ መልክ የጻፉት ደብዳቤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ታትሞ አንብበነው ነበር፡፡ ያ ደብዳቤ ንጉሠ ነገሥቱ በሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን በማካሄድ ለኢትዮጵያ ህዝብ የተሻለ ነፃነት እንዲሰጡ ይጠይቃል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ግን ጥያቄአቸውን በጄ አላሉትም፡፡ ሁሉንም ሹማምንት ጥርግርግ አድርገው ከስልጣን አባረዋቸዋል፡፡
እንግዲህ በዚያ ታላቅና ዘመን ተሻጋሪ (classic) ድርሰት የተነገረው ታሪክ በአብዛኛው የተፈጸመው በጎጃም ነው፡፡ ከዘመኑ ቀድሞ ማየት የቻለውን ያንን አስተዋይ ደራሲ ያፈራውም የጎጃም ምድር ነው፡፡ ሐዲስ ዓለማየሁ ይባላል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአማርኛ ስነ-ጽሑፍ እድገት ላበረከተው አስተዋጽኦ በ1991 የክብር የዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቶታል (አንቱታውን የተውኩት ወደዚህ ላቀርበው ብዬ ነው)፡፡
——-
ስለጎጃም ሳስብ ዘወትር የሚደንቀኝ ሌላኛው ነገር ስሙ በታሪክ ድርሳናት የተጻፈበት አኳኋን ነው፡፡ ያ ምድር በጽሑፍ ምንጮች “ጎጃም”፣ “ጎዣም”፣ “ጐጃም” እና “ጐዣም” እየተባለ ተወስቷል፡፡ ከዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመን ጀምሮ በተጻፉ ድርሳናት ውስጥ አራቱንም ስሞች ለማየት ይቻላል፡፡ ስሞቹ የተለያዩ ፍቺዎች እንዳሏቸው ሰምቼ አላውቅም፡፡ በስሞቹ መጀመሪያ ላይ የሚጻፉት “ጎ” እና “ጐ” ተመሳሳይ ድምጽን እንደሚወክሉ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ይሁንና በስሞቹ መሀል ያሉት “ጃ” እና “ዣ” የተለያዩ ድምጾችን እንደሚወክሉ እየታወቀ ክፍለ ሀገሩ “ጎጃም” እና “ጎዣም” ተብሎ መጠራቱ ሁል ጊዜም ሲገርመኝ ኖሯል፡፡ ለዚህ ማብራሪያ የሚሰጠን አካል ይኖር ይሆን? በከፍተኛ በጉጉት እንጠብቃለን፡፡
—-
(በብዙዎች ጥያቄ የተደገመ)