“መዝመት ያለበት ጎንደርና ወሎ? ወይስ ዐቢይ ወደሚገኝበት አራት ኪሎ???”
አቻምየለህ ታምሩ
*….. በልደቱ “የመፍትሔ ሀሳብ” የሚስማማ መዝመት ያለበት ወዴት ነው? ፋሽስት ወያኔ በግፍ ወደወረራቸው ጎንደርና ወሎ? ወይስ ዐቢይ ወደሚገኝበት አራት ኪሎ?
ልደቱ አያሌው “የመፍትሔ ሀሳብ” ብሎ ስለ ዋናው የኢትዮጵያ ችግርና የኅልውና አደጋ አንድ መስመር እንኳን ሳይተነፍስ በደረተው ቅራቅንቦ ዙሪያ በሰነዘርሁት ትችት የተበሳጩና የሰደቡኝን በተለይም ራሳቸውን እንደ አማራ የሚቆጥሩ ሰዎችን ለመታዘብ ወደ ፌስቡካቸው ጎራ ብዬ ነበር።
ልደቱ እንካችሁ ያለው ሀሳብ የሌለው “የመፍትሔ ሀሳብ” ለምን ተተቸ ብለው በውስጥ መስመርም በውጭም ሲሳደቡ የተመለከትኋቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ፤
1ኛ. ፋሽስት ወያኔ በግፍ የወረራቸውን የወሎና የጎንደር አካባቢዎች ነጻ ለማውጣት መሰማራታቸውን የሚያሳይ ፎቶ የለጠፉ ወይም የዘመቱ ወዳጆቻቸውን ባድናቆች በመመልከት በፌስቡካቸው ያጋሩ ናቸው፣
2ኛ. ፋሽስት ወያኔን እየተፋለመ ከሚገኘው ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ኢትዮጵያውያን እንዲቆሙ ሲቀሰቅሱና ግጥም ሳይቀር እያቀረቡ ሠራዊቱን ሲያጀግኑ የነበሩ ናቸው፤
3ኛ. ፋሽስት ወያኔ በወረራቸው ወሎና በጎንደር አካባቢዎች የፈጸመውን የዘር ማጥፋትና ያደረሰውን ሁለንተናዊ ውድመት የሚያሳዩ የፎቶና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በፌስቡካቸው ያጋሩ ናቸው፤
4ኛ. በተለይም የሰሜኑ አማራ ወጣት ቀፎው እንደተነካበት ንብ በነቂስ ተነስቶ በመዝመት ፋሽስት ወያኔ በጎንደርና ወሎ እየፈጸው የሚገኘውን ዘግናኝ የዘር ማጥፋትና ውድመት እንዲያስቆም ሲወተውቱ የሚውሉ ናቸው።
እነዚህ ሰዎች አንድም ልደቱ የጻፈውን አላነበቡትም፤ ቢያነቡትም አልገባቸው። ልደቱ ያወናከረውን ካነበቡትና ከገባቸው ፋሽሽት ወያኔን እንደ ኢትዮጵያ ዋና ችግርና የኅልውና አደጋ ከማይቆጥረው ልደቱ “ሀሳብ” ጋር ተስማምተው ሲያበቁ 180 ዲግሪ በመገልበጥ ፋሽስት ወያኔን እንደ የኢትዮጵያ ዋነኛ ችግርና የኅልውና አደጋ ቆጥረው ለመፋለም እንዴት ብለው ወደ ወሎና ጎንደር ሊዘምቱ ቻሉ?
እንዴትስ ብለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፋሽስት ወያኔ ጋር እየተፋለመ ከሚገኘው ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንዲቆም ይቀሰቅሳሉ? የአማራ ወጣትስ ፋሽስት ወያኔ በጎንደርና ወሎ እየፈጸመ የሚገኘውን የዘር ማጥፋት ለማስቆም እንዲዘምት ለምን ተነስ፣ ዝመት እያሉ ይቀሰቅሱታል?
በልደቱ ሀሳብ የሚስማማ ሰው መዝመት ያለበት ወዴት ነው? ፋሽስት ወያኔን ለመፋለውም ወደ ወሎና ጎንደር? ወይንስ ዐቢይ አሕመድን ከሥልጣን አውርዶ የልደቱን ሀሳብ እውን ለማድረግ ወደ አራት ኪሎ? ፋሽስት ወያኔን ለመፋለም ጎንደርና ወሎ ዘመትን ያላችሁ የልደቱ ሀሳብ ደጋፊዎች እስቲ መልሱልን? የምትደግፉትንና የምትስማሙበትን የልደቱ ሀሳብ እውን ለማድረግ ወዴት ነው መዝመት የነበረባችሁ? ፋሽስት ወያኔ በግፍ ወደወረራቸው ወደ ጎንደርና ወሎ? ወይስ ዐቢይ ወደሚገኝበት ወደ አራት ኪሎ?