>

“ፉጉግ” እና የሀረርጌ ኦሮሞ (ጸሐፊ፡- አፈንዲ ሙተቂ)

ፉጉግ” እና የሀረርጌ ኦሮሞ

ጸሐፊ፡- አፈንዲ ሙተቂ

በማለዳ ወይም ቀትር ላይ “የቻልኩትን ያህል ልመልከት” ብላችሁ ዓይናችሁን በነጻነት ብትለቁት ከአንድ የተፈጥሮ ግድግዳ ጥግ ትደርሳላችሁ፡፡ ከዚያ ወዲያ ላማትር ብትሉ በጭራሽ አይሆንላችሁም፡፡ ይህም በአማርኛ “አድማስ” የሚባለው ጠርዝ ነው፡፡ ፈረንጆቹ “horizon” ይሉታል፡፡ በኦሮምኛስ (Afaan Oromoo) ምን እንደሚባል ታውቃላችሁ?  
 
ኦሮምኛ ብዙ ዘዬዎች ያሉት በመሆኑ ስያሜው እንደ የአካባቢው ይለያያል፡፡ እኔ አፍ በፈታሁበት የሀረር ኦሮምኛ አድማስ ማለት ከፈለጋችሁ ግን “ፉጉግ” ትላላችሁ፡፡
በሀረርጌ ገጠሮች ውስጥ ስትዘዋወሩ ከፊት ለፊቱ የተዘረጋውን ሰፊ አድማስ አየት አድርጎ “Ar’a Fugug Rooba Hima” የሚል የሀረርጌ ገበሬ በየአፍታው ያጋጥማችኋል፡፡ የሀረርጌ ገበሬ እንዲህ ሲል “ዛሬ ፉጉግ ስለዝናብ ይናገራል” ማለቱ ነው፡፡ መልእክቱ ግን “ዝናብ እየመጣ ነው” የሚል ይሆናል፡፡ በሀረር ኦሮምኛ “ከአድማስ ባሻገር” ለማለት ካሻችሁ ደግሞ “ፉጉጊን ገመ”(Fugugiin Gama) ነው የምትሉት፡፡
 
በጥንቱ የኦሮሞ ባህላዊ አስተዳደር ዘመናት ከሞት ፍርድ ቀጥሎ በወንጀለኞች ላይ የሚጣለው ትልቁ ቅጣት ከሀገር መባረር ነበር ይላሉ- የሀረርጌ ሽማግሌዎች፡፡ ይህ ቅጣት በበርካታ ማህበረሰቦች ዘንድ የሚታወቅ በመሆኑ አስገራሚ ላይሆን ይችላል፡፡ እኔ ጨዋታውን ያመጣሁት የሀረርጌ ኦሮሞ ለዚህ ቅጣት የሰጠው ስያሜ ስለሚደንቀኝ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ቅጣት የወሰኑ ሽማግሌዎች “ፉጉጊን ገመ ጌሳ ደርባ” በማለት ለፍርድ አስፈጻሚዎች ትእዛዝ ይሰጣሉ፡፡ በአማርኛ “ከፉጉግ ወዲያ ውሰዱትና ጣሉት” ማለት እንደማለት ነው፡፡ 
 
የሀረርጌ ኦሮሞ ከአዋሽ እስከ ጅጅጋ ድረስ በተዘረጋ ሰፊ መሬት ላይ የሚኖር ቢሆንም በአንድ ቀበሌ ለሚኖር ሰው ከ“ፉጉግ ወዲያ” ያለው መሬት በርሱ ሀሳብ ሌላ ክልል ነው፡፡ “ፉጉግ” ለጥቅላላው የሀረርጌ ህዝብ ደግሞ ሌላ ውስጣዊ “ማዕና” (ፍቺ) አለው፡፡ ለመሆኑ “ፉጉግ” የሚለው ቃል ምንጩ ከየት ነው? የፉጉግ ውስጣዊ “ማዕና”ስ ምንድነው? 
—————–
=የፉጉግ ተራሮች= 
 
የጂኦግራፊ ካርታዎችን ከፊታችሁ ዘርግታችሁ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ዓይናችሁን ጣል ካደረጋችሁ “Ahmar Mountains” በሚል ስያሜ የሚጠራ የተራራ ሰንሰለት ትመለከታላችሁ፡፡ ይህም ከአርባ ጉጉ (አርሲ) እስከ ፋፈም ሸለቆ (ጉርሱም) ድረስ ለተዘረጉ ሰንሰለታማ ተራሮች መጠሪያ የሆነ የጋራ ስም ነው፡፡ ስያሜው ለተራሮቹ ለምን እንደተሰጠ በትክክል አላውቅም፡፡ “አሕመር” በዐረብኛ “ቀይ” ማለት በመሆኑ በተራሮቹ ላይ ፈጠው ከሚታዩ ቀያይ ዐለቶች ጋር የተያያዘ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡  ሆኖም የሀረርጌ ኦሮሞ ሰንሰለቱን ሲጠራ “አህመር” አይልም፡፡ ይህንን የተግተለተለ የተፈጥሮ ስሪት “ፉጉግ” ይለዋል፡፡
 
ፉጉግን በየትኛውም የሀረርጌ ክፍል ሆናችሁ ለማየት ትችላላችሁ፡፡ የ“ፉጉግ” መነሻ ግን በምስራቃዊ የአርሲ ክፍለ ሀገር ያለው የአርባ ጉጉ ተራራ (በኦሮሞ ህዝብ አጠራር “ጋረ ጉጉ”) ነው፡፡ 
 
“ፉጉግ” ከመነሻው ላይ ቀለል ያለ ነው፡፡ ወደ ገለምሶ፣ ዋጩ እና በዴሳ አካባቢ ሲደርስ መወሳሰብ ይጀምራል፡፡ ወደ ቁኒ፣ አርበ ረከቴ፣ ደበሶ እና ሂርና ሲደርስ ግን መላ ቅጡ የጠፋ ትብታብ ጠፍር ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ የሚያካልለው መሬት ስፋትም በጣም ይጨምራል፡፡ እንዲህ ውስብስብ እንደሆነ ወደ በሮዳ፣ ቆቦ፣ ጨለንቆና ቀርሳ አካባቢዎች ይደርሳል፡፡ ወደ ሀረማያ እና ሀረር ሲመጣ መቃለል ይጀምራል፡፡ ጅጅጋ ከመድረሱ በፊት ግን ይጠፋል፡፡ 
 
ከላይ እንደጠቀስኩት በየትኛውም የሀረርጌ ክፍል የሚኖር ሰው “ፉጉግ”ን ለማየት ይቻለዋል፡፡ ስለዚህ ሩቅ የሆነ ነገር ሁሉ ለርሱ “ከፉጉግ” ወዲያ ያለ ነው፡፡ የፉጉግ ተራሮች አግራሞትን የሚያጭሩት ግን ውስብስብ ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ አይደለም፡፡ የተራሮቹ አስደማሚ ምእራፍ በቋንቋ፣ በስነልቦና እና በእምነት አንድ የሆነውን የሀረርጌ ኦሮሞ በባህላዊ አወቃቀር፣ በአሰፋፈር እና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ረገድ በሶስት ቦታ ስለሚከፍሉት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ሊገነዘብ የሚችለውም ሁኔታዎችን በአንክሮ የተመለከተ ወይንም ጠለቅ ያሉ የምርምር ጽሁፎችን ያነበበ ሰው ብቻ ነው፡፡ የፉጉግ አስፈላጊነትና ትንግርተኛነት ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ 
 
አዎን! ፉጉግ በግላጩ (reality) አንድ የሆነውን የሀረርጌ ኦሮሞ በሶስት ትላልቅ ማህበረሰቦች ይከፍለዋል፡፡ እነርሱ እነማን ናቸው?
******
ፉጉግ እጅግ በጣም በተወሳሰበት ምእራባዊ ክፍሉ “ቡርቃ” የሚባል ትልቅ ጅረት ይፈሳል፡፡ “ቡርቃ” ከበሮዳ ከተማ አቅራቢያ ተነስቶ የደቡብ አቅጣጫን ይዞ ይፈስና የዋቤ ወንዝ (ዋቤ ሸበሌ) ዋነኛ ገባር ከሆነው “ራሚስ” ጋር ይቀላቀላል፡፡ ከ“ቡርቃ” በስተምእራብ በኩል የሰፈረው የሀረርጌ ኦሮሞ “ኢቱ” ተብሎ ይጠራል፡፡ 
ቡርቃ በፉጉግ ተራሮች ላይ በተሸነቆረ ሸለቆ ውስጥ ሌት ተቀን ይፈሳል፡፡ እርሱን ተሻግራችሁ እስከ ፋፈም (ጅጅጋ) ድረስ በተዘረጋው መሬት ውስጥ መጓዝ ካሰኛችሁ በሌላኛው የሀረርጌ ኦሮሞ ቅርንጫፍ ውስጥ መግባታችሁ ነው፡፡ በዚህኛው ክፍል የሰፈረው የሀረርጌ ኦሮሞ “አፍረን ቀሎ” ይሰኛል፡፡
 
ፉጉግ ወደ ቀድሞው የጋረ ሙለታ አውራጃ ሲደርስ የሰማይ ጣራ ይነካል፡፡ የፉጉግ ከፍተኛ ቦታ የሚገኘውም እዚህ አካባቢ ነው፡፡ እንዲያውም የትክክለኛው ፉጉግ መገኛ እዚህ ሳይሆን አይቀርም! በርካታ የተራራ ጫፎች አንደኛ ለመሆን የሚፎካከሩት በዚህኛው የተራራው ሰንሰለታማ ክፍል ነውና፡፡ ሆኖም ከነዚህ ተራሮች መካከልም በቁመቱ አንደኛ የሆነው “ጋረ ሙለታ” እንደሆነ ማንም ይነግራችኋል፡፡ “ጋረ ሙለታ” የሚለው ስያሜ ራሱ ተራራው ከሁሉም ቦታ ተሁኖ የሚታይ መሆኑን ያመለክታል፡፡
 
“ጋረ ሙለታ” በሚገኝበት አካባቢ ምእራባዊ ክፍል ደግሞ “ደባል” የሚባል የተራራ ጫፍ አለ፡፡ “ደባል” በሳንሳዊ ልኬት የፉጉግ አንደኛ ተራራ አለመሆኑ ቢረጋገጥም በትውፊት “ጋረ ሞቲ” (የተራራ ንጉስ) የሚባለው እርሱ ነው፡፡ “ጋረ ሙለታ” እና “ደባል” ባሉበት ስፍራ የሚኖረው ከላይ የጠቀስኩት “አፍረን ቀሎ” ነው፡፡ እነዚህን ተራሮች ተሻግራችሁ በስተደቡብ አቅጣጫ ቁልቁል ስትወርዱ ደግሞ የሀረርጌ ኦሮሞ ሶስተኛ ቅርንጫፍ ከሆነው የ“አኒያ” አሮሞ መሬት ትገባላችሁ፡፡ 
 
ፉጉግ የሀረርጌን ኦሮሞ እንዲህ ይከፋፍለዋል፡፡ ከሶስቱ ማህበረሰቦች መካከል በፉጉግ ላይ የማይኖረው አርብቶ አደሩ “አኒያ” ነው፡፡ ሆኖም እርሱም ራቅ ብሎ ስለ ፉጉግ ይጠበባል፡፡ ስለፉጉግ ብትጠይቁት እስኪበቃችሁ ድረስ ይነግራችኋል፡፡ 
 
ከ“አኒያ” ቀጥሎ ሰፊ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ የምታገኙት በኢቱ ኦሮሞ ዘንድ ነው፡፡ ከአዋሽ ፈንታሌ እስከ ሚኤሶና አፍደም ድረስ የሰፈረው የኢቱ ኦሮሞ ሙሉ በሙሉ አርብቶ አደር ነው፡፡ በዚህ አካባቢ አራሽ ገበሬ የምታገኙት የአሰቦት ከተማን በሚያካልለው ሜዳማ ስፍራ ላይ ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከዋቤ ሸበሌ ወንዝ ጋር በሚዋሰኑት የዳሮለቡና ቦኬ ወረዳዎች ከሚኖረው ህዝብ ግማሹ አርብቶ አደር ነው፡፡ 
 
የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ ግን በአብዛኛው አራሽ ነው-ከያዘው ስፍራ አንጻር ሲታይ፡፡ ሆኖም በዚህም ክፍል ያለው አርብቶ አደር በቁጥር ሲቀመጥ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ በጃርሶና ጭናክሰን ወረዳዎች የሰፈረው የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ በአብዛኛው አርብቶ አደር ነው፡፡ 
 
ሶስቱ የኦሮሞ ማህበረሰቦች የሚኖሩበትን ስፍራዎች አብዛኛው ህዝብ በሚያውቃቸው ስያሜዎች መጥራት ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ኢቱ የሚኖርበት ክልል በጥንቱ አጠራር “ጨርጨር” ይባል እንደነበር ሽማግሌዎች ያወጋሉ፡፡ የአኒያ ኦሮሞ መኖሪያ ክልል ደግሞ “ቡርቃ ቲርቲራ” ይባላል፡፡ የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ በበኩሉ መኖሪያ ክልሉን “ጎሮ ፉጉግ” (የፉጉግ ጉብታ) በማለት ይጠራዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ስያሜ ሶስቱም የኦሮሞ ማህበረሰቦች የሚኖሩበት ክልል የወል መጠሪያ በመሆንም ያገለግላል፡፡
 
ከፉጉግ ተራሮች መካከል ለኔ አሰልቺ የሚሆንብኝ ክፍል ከጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ተነስቼ ወደ ገለምሶ ስጓዝ የግዴታ ማቋረጥ ስላለብኝ ብቻ የምተላለፍበት ክፍል ነው፡፡ ከጭሮ ተነስታችሁ ቁኒ እስክትደርሱ አሰልቺ ዳገት! ከቁኒ እስከ በዴሳ አስጨናቂ ቁልቁለት!
 
እጅግ በጣም የተዋበው የፉጉግ ክፍል ደግሞ ቁንድዶ ነው፡፡  ሁኔታው በሙሉ በሰማይ ጠቀስ ህንጻ ላይ የተዘረጋ ሰፊ ሰገነት ይመስላችኋል፡፡ አየሩ፣ አራዊቱ፤ ጫካው፤ አዕዋፉ፣ ምንጩ ወዘተ ሁሉም ማራኪ ነው፡፡ ብቻ ምን ልበላችሁ! ተራራውን መውጣት ከቻላችሁ ወደ ምድራዊ ገነት ደረሳችሁ ማለት ነው፡፡
——
አፈንዲ ሙተቂ
 
(“ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ድሬ ዳዋ” ከተሰኘው መጽሐፌ የተቀነጨበ)።
Filed in: Amharic