አ.ሚ.ኮ.
❝ ውጡ አሉን ከቤት ሆነን ዝም አልን። ደጃፉን ከፍተው ገቡ። ላሚቱን መትተው ገደሏት። በሬውንም አረዱ። ዱቄት፣ ቤት ያፈራውን ሁሉ አወጡ። ባለቤቴን እስከነ ልጇ ገደሏት❞
“ጭና የደም ምድር፣ ብዙዎች አልቀውባታል፣ የክፉ ሰይፍ አርፎባታል። ልጆች የእንባ ማዕበል እየፈነቀላቸው አልቅሰውባታል። እናቶች በሐዘን ኩርምት ብለውባታል።
“መቅረታችሁ ነው…መለያየቱ ቁርጥ ሆነ ወይ…ብቻዬን መኖሩን አልቻልኩትም…ምነው ልባችሁ ጨከነ…ምነው በአውደ ዓመቱ ያለ ሰው ተዋችሁኝ…” የሚሉና ሌሎች የሐዘን ድምፆች ይሰማሉ።”
የሆነውን ያየ ሁሉ ፈጣሪን “ምነው አትወርድምን ? የቁጣህንስ በትር በጠላቶችህ ላይ አታሰርፍምን? ይላል።” ግፉ ከባድ ነውና።
❝ከደብረ አሚን ጭና ተክለሃይማኖት አፀድ ሥር❞
ጀንበር ከሰማይ ደመና ጋር እየታገለች በምሥራቅ ንፍቅ መፍገግ ጀምራለች። የደጋውን ቆፈን በቶሎ ማላቀቅ ያቃታት ይምስላል። ረጋፊው ጤዛ እንኳን ረግፎ አልጨረሰም። የሰው ልጅ ጤዛን ይመስላል፣ ጠዋት ታይቶ አመሻሽ ላይ ይታጣል። በጠዋት የሚያወረዛው ጤዛ ከሰዓት እንደሚደርቅ ሁሉ የሰው ልጅም አሁን አለ ሲሉት ይረግፋል፣ ያልፋል፣ ምድራዊ ዓለም አላፊ፣ ጠፊ ናት እንዳለ።
ከንቱ ዓለም ስንቱን አመጣችው፣ ስንቱን ወሰደችው፣ ስንቱን አስለቀሰችው፣ ስንቱንስ አሳቀችው።
በጠዋት ጉዞ ጀምረናል። ከመዳረሻችን ጥሩ ትዝታ የለንም። መዳረሻችን ባሰብኩ ቁጥር አብዝቶ ማልቀስ፣ ደረት መድቃት፣ ፊት መንጨት ትውስ ይለኝና ልቤ ትጨነቃላች። ነብሴ ትታወካለች። የእናቶችን ለቅሶ፣ የልጆችን ዋይ ዋይታ እያሰላሰልኩ ወደ ፊት አቀናን።
የማለዳው ብርድ ከባድ ቢሆንም በሐዘን ውስጣቸው የበረደውን ሰዎች ሳስብ ረሳሁት። ከባዱ ብርድ ሰው ሲበርድ ነው፣ ሰው ሲታጣ በወገን የሞቀው ቤት ባዶ ሲሆን ነው ከብርዶች ሁሉ የሚከብደው ብርድ። የቀዝቃዛ አየር ብርድ በልብስ ይከላከሉታል። ወገን ሲሳሳ፣ ሰው ሲበርድ ግን እንዴት ያደርጉታል? ልብስ አይደረብበት፣ በአንድ ጀንበር ወገን አይተካበት።
ጭና ተክለሃይማኖት ደርሰናል። መኪናችን ከቤተክርስቲያኑ ግርጌ ከሚገኘው መንገድ ዳር አቁመን ወደ ላይ ወጣን። ጭና የደም ምድር፣ ብዙዎች አልቀውባታል፣ የክፉ ሰይፍ አርፎባታል። ልጆች የእንባ ማዕበል እየፈነቀላቸው አልቅሰውባታል። እናቶች በሐዘን ኩርምት ብለውባታል። በየመንደሩ አጠገብ እንቦሶች ሲፈረጥጡ፣ ሕፃናት ሲቦርቁ አይታይም። እረኞች ዋሽንት አይነፉም። ለጨዋታም አይሰለፉም። ሁሉንም ሐዘን ቀምቷቸዋልና።
ደብረ አሚን ጭና ተክለሃይማኖት አፀድ ሥር ደርሰናል።
በደብሩ ዙሪያ በረድፍ የቆሙት ረጃጅም ፅዶች ስለሆነው ሁሉ የሚያዝኑ ይመስላሉ። በቅፁሩ አጠገብ፣ በረጃጅም ዛፎች ሥር ለሥር የጸሎት መጻሕፋቸውን ገልጠው ፈጣሪያቸውን የሚማፀኑ ሰዎች ይታያሉ።
ዓይኔ ዙሪያ ገባውን እያመተረ ቅፁርን አልፌ ወደ ውስጥ ዘለኩ። በጠዋት ለጸሎት የሚተጉት ምዕመናን ፈጣሪያቸው መልካሙን ለምድር ይሰጥ ዘንድ መማፀን ላይ ናቸው። ከረጃጅም ፅዶች መካከል ከአንደኛው ግርጌ ቆምኩ።
ከቅፅሩ ውጭ በሚገኙ አዳዲስ መቃብሮች ዙሪያ ልብን የሚሰብር፣ አንጀትን የሚያሳርር ለቅሶ ይሰማል።
❝መቅረታችሁ እነው…መለያየቱ ቁርጥ ሆነ ወይ…ብቻዬን መኖሩን አልቻልኩትም…ምነው ልባችሁ ጨከነ…ምነው በአውደ ዓመቱ ያለ ሰው ተዋችሁኝ…❞ የሚሉና ሌሎች የሐዘን ድምፆች ይሰማሉ።
ድምፆቹ ከአካባቢው ብን ብለህ ጥፋ ያሰኛሉ። ልብን እየሰረሰሩ የሚሆኑትን ያሳጣሉ። ክፉዎች ብዙዎችን ገድለውባቸዋልና ሐዘናቸው አልሽር ብሏቸዋል። በደብሩ ዙሪያ የተሠደሩት ረጃጅም ዛፎች በቀስታ ይወዛወዛሉ። ካለሁበት ሳልንቀሳቀስ ስለሆነውና እየሆነ ስላለው እያሰላሰልኩ ቆምኩ።
በክፉዎች አገልጋዮቹን ተነጥቋል ታላቁ ቤተክርስቲያን ደብረ አሚን ጭና ተክለሃይማኖት። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን የኖረ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ እሴት፣ የነብስ ምግብ ሕይወት ያለበት፣ የመላበት ታላቅ ደብር ነው። በዘመነ ይስሃቅ እንደተመሠረተ ይነገርለታል።
ጊዜው 1400ዓ.ም ነበር ብለውኛል አበው። በዘመነ ሱስንዮስ ደግሞ ታድሷል። ረጅም ዓመትን ባስቆጠረው ዘመኑ ከምሥረታው ጀምሮ በየዘመናቱ የነገሡ ነገሥታት በረከት ያገኙ ዘንድ ውድ ውድ ስጦታዎችን አበርክተውለታል። የብርና መጻሕፍት፣ እንቁ መስቀሎች፣ ፅሕና፣ አልባሳት እና ሌሎች ውድ ስጦታዎች።
ልብ ይበሉ በተከበረው አፀድ ሥር፣ በተቀደሰው ምድር ነው ግፍ የተፈፀመበት። አሸባሪው ትህነግ ደም ያፈሰሰበት፣ ንጹሐንን የጨፈጨፈበት።
ቀኑ ፃዲቁ ተክለሃይማኖት ከፍ ብለው የሚከበሩበት ነበር። በክርስቲያኖች የእርሳቸው ቀን ይባላል። የዓመት በዓላቸው የሚከበርበት፣ ስማቸው የሚመሰገንበት፣ የፃዲቁ ምልጃና በረከት የሚለመንበት ነሐሴ 24 ነበር።
ድግስ ተደግሷል፣ ጠላው ተሹሟል፣ እንጀራው ተጋግሯል፣ ሁሉም ሙሉ ሆኗል። የጭና ነዋሪዎች ከአፀዱ ሥር በደስታ ውለዋል። ተመራርቀው በአዲሱ ዓመት ያገናኛቸው፣ ከርሞም ያደርሳቸው፣ ዓመትም ይደግማቸው ዘንድ ተመኝተው ተለያዩ። ያቺ ሌሊትም በሰላም አለፈች። በማግሥቱ ግን ያልጠበቁት መጣባቸው። የትህነግ አሸባሪ፣ ወራሪና ሰው በላ ቡድን ወረራቸው። ብዙዎችን ነጠቃቸው። ሀብትና ንብረታቸው ዘረፋቸው።
ከብዙ ዝምታ በኋላ ከቆምኩበት ዛፍ ሥር ለቅቄ ለረጅም ሰዓት ጸሎት ሲያደርሱ ቆይተው ወደ ጨረሱት አባት ተጠጋሁ። ቄስ ጥፍጡ እጅጉ ይባላሉ። የደብረ አሚን ጭና ተክለሃይማኖት አስተዳዳሪ ናቸው። አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ብዙ ነገር ቀምቷቸዋል።
ስለነበረው ነገሩን ❝ሳናስበው መጥተው ወረሩን። ባለቤቴ የሦስት ዓመት ሕጻን ይዛ ነበር። ውጡ አሉን ከቤት ሆነን ዝም አልን። ደጃፉን ከፍተው ገቡ። ላሚቱን መትተው ገደሏት። በሬውንም አረዱ። ዱቄት፣ ቤት ያፈራውን ሁሉ አወጡ። ባለቤቴን እስከነ ልጇ ገደሏት❞
አትሙች ያላት ነብስ እርሳቸው ተረፉ። የመከራውን ጊዜ አልፈው ያወጉት ዘንድ ሰነበቱ። እሳቸው የልጃቸውንና የክሕነት ባለቤታቸውን ሕይወታቸው፣ ማዕረጋቸውን አስከሬን በቤት ዘግተው ወደ ዘመድ ሄዱ። ለመቅበር እንኳን አልቻሉም ነበርና። በማግስቱ በምሽት መጥተው የሚወዷቸውን በሚወዱት ደብር አፀድ ቀበሩ። ❝አመሻሽ ላይ ስንቀብር ሊመቱን ሆነ፣ መብራት አጥፍተን ቀበርን፣ አብረው ያቃበሩንን ሁለት ሰዎች በግንባር በግንባር ደፏቸው። ባለቤቴ በሥላሴ፣ በማርያም እያለቻቸው ነው የመቷት❞ ነው ያሉን።
የደብሩን ቄሰ ገበዝ ቁልፍ ይዘው ሊሸሹ ሲሉ ያሳልሙን ብለው ሊያሳልሟቸው ሲሉ መቷቸውም ብለውናል።
ሌላኛው የደብሩ አገልጋይ ቄስ እባቡ መንገሻ ሰውን ብቻ ሳይሆን ሃይማኖትን ለማጥፋት ነው የመጡት ነው ያሉን። ታላቁን ደብር የቆሻሻ መጣያ አድርገውት ሰንብተዋል፣ ገበዙን ገድለዋል፣ የደብሩን የዓመት ገቢ እንደያዙ ነው የገደሏቸው፣ የአስተዳሪውን ቄስ ሚስትና ልጅ፣ የሰበካ ጉባኤ አባል የሆኑ ቄስ ሚስትም ገድለዋል ብለውናል። ሌላኛውን የሰባካ ጉባዔ አባልና አገልጋይ ቄስም ከቤታቸው ሲበሉ ሰንብተው ገድለዋቸዋል ነው ያሉን።
ወራሪው ቡድን ሁለት አገልጋዮቹን፣ የሁለት የአገልጋዮችን ባለቤቶች ሲገድል፣ ሁለት መካሪ፣ ዘካሪ፣ ታሪክ ነጋሪ የሆኑ ታላላቅ ቀሳውስት የት እንደ ገቡ አልታወቀም። የመጣው አረመኔ ቡድንም በሠራው ክፋት ከጥቂቱ በስተቀር ጭና ላይ ቀርቷል ብለውናል።
የታሪካዊ ደብር ሀብት የነበሩ እንቁ ንዋየ ቅድሳትንም መዝብረዋል። በሰርክ ምስጋና የሚቀርብበት፣ ኪዳን የሚደረስበት፣ ታላቁን ደብር ነው አገልጋይ አልባ ለማስቀረት ነበር ካሕናቱን የመቷቸው። ዳሩ ጌታ ብዙ አገልጋዮችን አዘጋጅቷል።
የዳባት ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካሕናት መላከ አሚን ሳሙኤል ገበየሁ እና የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን እስጢፋኖስ ጥፍጤ በሀገረ ስብከቱ አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ኀይል በገባባቸው አድባራትን መዝረፉን ነግረውናል። አብያተ ክርስቲያናትንም በከባድ መሣሪያ መትተዋል። ምዕመናንን ገድሏል፣ ሀብታቸውም ዘርፏል ነው ያሉት። አድባራቱ እና ምእመናኑ ድጋፍ እንደሚሹም ነግረውናል።
በደብረ አሚን ጭና ተክለሃይማኖት የተገኘሁት ለ13 ቀን የተዘጋው ቤተ መቅደስ በበዓል ማግሥት በዕለተ ሰንበት ተክፍቶ ዳግሞ ልጆችን በሰበሰበት ቀን ነበር። ብዙ በደሎችን ተመለከትኩ። ዓይኔ ግፍ የተፈፀመባቸውን ዓየች፣ በግፍ የተገደሉ የንጹሐን መቃብሮችን ተመለከተች። ጀሮዬ ስለ መከራዎቹ ቀን ሰማች፣ እግሬ ታላቁን ቦታ ረገጠች፣
❝ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ! እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፣ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፣ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ፣ አሕዛብም በፊትህ ይንቀጠቀጡ ዘንድ። ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ፣ ወረድህ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም❞ እንዳለ መጽሐፍ በዚያ ቤተክርስቲያን የሆነውን ያየ ሁሉ ፈጣሪን ምነው አትወርድምን ? የቁጣህንስ በትር በጠላቶችህ ላይ አታሰርፍምን? ይላል። ግፉ ከባድ ነውና።
❝አባቶቻችን አንተን ያመሰገኑበት የተቀደሰና የተዋበ ቤታችን በእሳት ተቃጥሎአል፣ ያማረውም ስፍራችን ሁሉ ፈርሶአል። አቤቱ በውኑ በዚህ ነገር ትታገሣለህን? ዝምስ ትላለህን? አጥብቀህስ ታስጨንቀናለህን?❞ እንዳለ የተቀደሰውን ቤት መትተዋል። የቤቱን አገልጋዮች ገደለዋልና። የተቀደሰውን ቤት ምሽግ አድርገው። ወደ ቤተመቅደሱ ተኩሰዋል።
ከሞት የተረፉት ቀሳውስት ቤቱን ከፈቱት፣ ምሕላውን አደረሱት፣ ዙሪ ገባውን ባረኩት። ፅሕናው ተንሿሿ፣ ቀሳውስቱ ዘመሩ፣ ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ። በዙሪያ ገባው የቆሙት ምእመናንም ተመስገን ሲሉ ይሰሙ ነበር። የቀሳውስቱ ለስላሳ ዜማ፣ በመቃብር አቅራቢያ የሚያለቀሱ ሰዎች ድምፅ በአንድነት እየተከተሉኝ ከአፀዱ ወጥቼ ወደታች አዘገምኩ። እግሬ አፀዱን ለቃለች፣ ልቦናዬ ግን በአፀዱ ዙሪያ ስላለው ነገር ታምሰለስላለች።