“ከተማሩ ሰዎች ይልቅ በመከራ ያለፉ ሰዎችን አከብራለሁ…!!!”
የዶክተር ወዳጀነህ
*…. አልማዝ የሚሆነው የድንጋይ ከሰል ነው !
አልማዝ በተፈጥሮ መንገድ እንዴት እንደሚሰራ ልንገራችሁ። አልማዝ የሚሰራው HPHT በሚባል Process ነው። HPHT ማለት High Pressure High Temperature ማለት ነው። አንድ አልማዝ አልማዝ ከመሆኑ በፊት አራት ደራጃዎችን ማለፍ ይኖርበታል። አንደኛ ከምድር በታች ከ300 እስከ 600 ኪሎ ሜትር ዝቅ ብሎ መቀመጥ። ሁለተኛ ከፍተኛ ሙቀት መታደል፣ ከ1200 ዲግሪ ሴንቲ ግሬት ቃጠሎ ውስጥ መቀመጥ። ሶስተኛ ከፍተኛ ጭነት ማግኘት። አራተኛ ለረዥም ጊዜ ውስጥ በነዚህ ሁኔታ ውስጥ መቆየት ! እንግዲህ አንድን የድንጋይ ከሰል ወስዳችሁ ከምድር በታች 600 ኪሎ ሜትር ብታወርዱት፣ 1200 ዲግሬ ስንቲ ግሬት ቃጦሎ ውስጥ ብታኖሩት፣ በከፍተኛ ፕሬዠር ውስጥ ብታስቀምጡት እና ለረዥም ጊዚያት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ብትተዉት። ከሰሉ አልማዝ ይሆናል ! ከሰሉ ወደ ዳይመንድ ይለወጣል።
አንዳንዶቻችሁ በህይወታችሁ ግራ ይገባችኋል፣ በጣም የሚወዳችሁ አምላካችሁ ከጓደኞቻችሁ በታች 600 ኪሎ ሜትር አውርዷችሁ ይሆናል። በማይገባችሁ ፈተና 1200 degree cent great ቃጠሎ ውስጥ አስቀምጧችሁ ፤ በማጣት፣ በመገለል፣ በመገፋት ለረዥም ጊዚያት እየፈተናችሁ “ምንድነው እየተካሄደ ያለው” ብላችሁ እስክትጠይቁ ድረስ ለአምስት አመት፣ ለአስር አመት ከሰው፣ ከወዳጅ፣ ከዘመድ፣ ከጓደኛ ዝቅ አድርጓችሁ ይሆናል። ….
“ምን ማለት ነው የሚወደኝ አምላክ ይሄን የሚፈቅደው” ስትሉ …. አልማዝ አድርጎ ሊሰራችሁ፣ ውብ አድርጎ፣ ሊሰራችሁ፣ የምታበሩ አድርጎ ሊያበጃችሁ፣ እንቁ፣ ዳይመንድ፣ አልማዝ ሊያደርጋችሁ ስላሰበ ነው !
አልማዝ ሰባት ባህሪዎች አሉት። አንደኛ ጠንካራ ነው። ወስዳችሁ በድንጋይ ቀጥቅጡት አይሰበርም። በሰይፍ ምቱት አይሰነጠቅም። በመጋዝ ገዝግዙት አይቆረጥም። በአልመዝ ግን ብረት ይቆረጣል፣ በአልማዝ ግን ሰይፍ ይቆረጣል። በአልማዝ ግን ድንጋይ ይፈርሳል። አልማዝ የሚቆረጠው በሌላ አልማዝ ነው። ሁለተኛ የአልማዝ ባህሪ ልንገራችሁ። ከፍተኛ የማንጸባረቅ ባህሪ አለው። refractive index ይባላል። የተቀበለውን ብርሃን መልሶ የማብራት ባህሪ አለው። ያንጸባርቃል። ሶስተኛው የአልማዝ ባህሪ የተቀበለውን የጸሐይ ብርሃን፣ ነጩን ብርሃን ወደ ተለያዩ በርካታ ቀለማት የመበተን ችሎታ አለው። አራተኛ የአልማዝ ባህሪ ልንገራችሁ። እጅግ በጣም ንጹህ ነው። አልማዝ የሚታወቀው በነጹህነቱ ነው። አምስተኛ የአልማዝ ባህሪ ልንገራችሁ። አልማዝ በእሳት አይቃጠልም። አንድ ቤት ውስጥ አልማዝ አለ እንበል ያ አልማዝ ያለበት ቤት ሙሉ ለሙሉ ቢቃጠል አልማዙ ምንም አይሆንም። ምንም። በነበረው ቅርጹ፣ በነበረው ንጽህናው እናገኘዋለን። የሚያስገርመኝን ስድስተኛውን የአልማዝን ባህሪ ልንገራችሁ። ወርቅ ላይ አሲድ ድፉበት ወርቁ ይበላሻል። አልማዝ ላይ አሲድ አፍስሱበት ምንም አይሆንም። አይበላሽም። የመጨረሻው እና ሰባተኛው የአልማዝ ባህሪ በጣም ውድ ነው። በጣም ውድ ነው። የአውራጣትህን ራስ የምታክል ዳይመንድ አንድ ትልቅ ፎቅ ይገዛል። በጣም ውድ ነው።
ከጓደኞቻችሁ በታች 600 ኪሎ ሜትር ወርዳችሁ ፣ በ1200 ዲግሪ ሴንቲ ግሬት ስቃይ ውስጥ ያለፋችሁ፣ በፕሬዠር ውስጥ ለበርካታ አመታት ያለፋችሁ እናንተ አልማዝ ሁናችሁ የተሰራችሁ ሰዎች ናችሁ። ሰዎች ጠጠር ብትመስሏቸውም አልማዞች ናችሁ። ዋጋችሁ በጣም ውድ ነው። … ከተማሩ ሰዎች ይልቅ፣ ብዙ ድግሪ ከተሳካላቸው ሰዎች ይልቅ፤ በመከራ ያለፉ ሰዎችን አከብራለሁ። ዋጋ የከፈሉ ሰዎችን አከብራለሁ። በስቃይ ውስጥ ያለፉ ሰዎችን አከብራለሁ። ምክንያቱም ዋጋቸው በጣም ውድ ነው።