>

በአፍሪካው ቀንድ የሽብርተኞች እንቅስቃሴና አለመረጋጋትን ከመግታት አኳያ የተባባረችው አሜሪካ ዲፕሎማቲክ ክሽፈት (ደረጀ መላኩ )

በአፍሪካው ቀንድ የሽብርተኞች እንቅስቃሴና አለመረጋጋትን ከመግታት አኳያ የተባባረችው አሜሪካ ዲፕሎማቲክ ክሽፈት

ክፍል ሁለት

ደረጀ መላኩ (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


መግቢያ

     ለዛሬው ጽሁፌ አላማ ይረዳኝ ዘንድ የአፍሪካው ቀንድ ማለት ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ዲጁቢቲ፣ሶማሊያ/ሶማሌ ላንድን እንደሚያካትት አንባቢውን አስታውሳለሁ፡፡ እነኚህ ሀገራት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ አደገኛ የአለማችን የግጭት ቀጠናዎች እንደሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች ከስመ ጥሩው አሜሪካዊው ዲፕሎማት ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን የጥናት ወረቀት ላይ ፍንትው ብሎ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በሌላው የአለም ክፍል የብዙ ሰው ሰለማዊ ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ለአብነት ያህል በቬትናም፣ላኦስ እና ካምቦዲያ ( እ.ኤ.አ. 1960ዎቹ-1970ዎቹ)፣በበእስራኤል-ፓሊስትን ግጭቶች መሃከል እጃቸውን በዶሉ በርካታ ሀገራት ምክንያት፣ በደቡብ ምስራቅ ኤሽያ እና በመሃከለኛው ምስራቅ ሀገራት ማለትም አፍጋኒስታን፣ኢራቅ፣ሶሪያ፣ፓኪስታን እና ኢራን፣በአሰከፊው የታላቁ ሀይቅ የአፍሪካ ግዛት በተካሄዱ ጦርነቶች longstanding conflicts in the Great Lakes region of Africa የሰው ልጆች እንደ ቅጠል እረግፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ባለፉት ስልሳ አመታት በአፍሪካው ቀንድ የተከሰቱ ግጭቶች ተወዳዳሪ የማይገኝላቸውናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ግጭጦች ውጤት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ንጹሃን ዜጎችን ህይወት መቅጠፍ እና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዝብሮችን ተፈናቃይ ያደረገ፣ዘተጎችን በሀገራቸው ምድር ባይተዋር ያደረገ ነበር፡፡

የግጭቶች ምክንያት

      በዚህ የአፍሪካ ክፍል በእስልምና እና ክርስቲኖች መሃከል ክፍተት እንዳለ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የሄዱበት ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሀገራት በቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ጊዜ የሶሻሊስቱ አለም ካምፕ እና የምእራቡ አለም መራኮቻ የነበሩ ሲሆን፣ዛሬም የዛን ሌጋሲ የሚያስፈጽሙ ናቸው፡፡ አካባቢው በአጠቃላይ በድህነት አረንቋ የተዘፈቀ ሲሆን፣ የኢኮኖሚ እኩልነት ፈጽሞ ያልፈጠረበት፣የፖለቲካ ማግለል የሰፈነበት፣ የሕዝብ ቁጥር በመጨመሩ እና የተፈጥሮ ሀብት እጥረት ምክንያት የተነሳ  በመሬት እና ግጦሽ ይገባኛል በሚል ግጭቶች የተስፋፉበት አካባቢም ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች ደግሞ ውሃ፣ነዳጅ እና የግጦሽ ሳር ፍለጋ ሲሉ ያልተቋረጠ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ የአየር ጸባዩ ደግሞ አስቸጋሪ እና በየግዜው የሚቀያየር ነው፡፡ የአየር ጸባይ ለውጥ ውጤቱ ደግሞ ተደጋጋሚ የምግብ እጥረትና ችጋርን ማስከተሉ እሙን ነው፡፡ በነገራችን ላይ የአየር ጸባይ ለውጥ የምግብ እጥረቱን አባብሶታል፡፡

      እንደማናቸውም ቀሪው የአፍሪካው ክፍል ሁሉ የአካበቢውን ድንበር ያሰመሩት በግዴለሽነት ሲሆን፣ መሰረቱም ጎሳ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በአከባቢው ያሉ ሀገራት በመልካም አስተዳደር አኳያም ቢሆንም ጥሩ ሪኮርድ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ በአምባገነኖች የሚገዛ፣ሙስና የነገሰበት፣ብሔራዊ ድንበሮች ጥብቅ ጥበቃ የሚጎድለው፣ ከመሃከለኛው ምስራቅና ደቡብ ኤሽያ የመነጩ  እንደ አሸባሪነት፣የሃይማኖት ጽንፈኝነት ለም መሬት  ( አካባቢ ) ነው የአፍሪካው ቀንድ፡፡

የአፍሪካው ቀንድ ከመልካም አስተዳደር አኳያ ያለው ሪኮርድ 

     በአለም አቀፍ ደረጃ እና በመላው አፍሪካ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚሳዩት ይህ የአፍሪካ ክፍል ከመልካም አስተዳደር አኳያ ጥሩ ሪኮርድ የለውም፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2015 የሞ ኢብራሂም ድርጅት 54ቱን የአፍሪካ ሀገራት መንግስታት አወዳድሮ ባወጣው ደረጃ መሰረት ሶማሊያን በ53ኛ ደረጃ፣ደቡብ ሱዳንን 53ኛ፣ሱዳን 51ኛ፣ኤርትራ 50ኛ፣ዲጂቡቲ 36 እና ኢትዮጵያን ደግሞ በ31ኛ ደረጃ አስፍሯቸው ነበር፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር በአፍሪካው ቀንድ ከሚገኙት ስድስት ሀገራት መሃከል አራቱ በመጨረሻው ረድፍ የተሰለፉ ናቸው፡፡

       እንድ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር 2014 ደግሞ ትራንሰፓረንሲ ኢንትርናሽናል በ174 ሀገራት ያደረገውን ጥናት ተንተርሶ ሙስና የተስፋፋባቸውንና የቀነሰባቸውን ሀገራት በተመለከተ ሪፖርቱን ለአለም አሳወርቆ ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት ሶማሊያን 174ኛ፣ሱዳን በ173ኛ ደረጃ፣ደቡብ ሱዳን 171፣ኤርትራ 166፣ኢትዮጵያ 171 እና ዲጂቡቲን በ107ኛ ደረጃ ላይ አስፍሯቸው ነበር፡፡ አንድም የአፍሪካው ቀንድ ቢያንስ ቢያንስ ወደ መሃከለኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ አልቻለም ነበር፡፡

      እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2014 ፍሪደም ሀውስ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ነጻ አይደሉም ብሎ ፈርጇቸው ነበር፡፡ ኤርትራ፣ሱዳንና ሶማሊያ በፖለቲካ እና ሲቪል ነጻነት (both political rights and civil liberties.) አኳያ ከአለም አስር ጨቋኝ ሀገራት እንደሚሰለፉ ተጨማሪ ሪፖርትም አውጥቶ ነበር፡፡ በፍሪደም ሀውስ ሪፖርት መሰረት ከፊል ነጻነት አላት ብሎ የገለጻት ሶማሌ ላንድን ነበር፡፡

 

የጨነገፉ ሀገራት እና ሰላም የራቃቸው ሀገራትን ደረጃ የሚያወጣው The Fund for Peace Fragile States Index የተሰኘ አለም አቀፍ ድርጅት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2015 በ178 ሀገራት ጥናቱን አድርጎ በደረሰበት ድምዳሜ መሰረት ደቡብ ሱዳንን በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ የጨነገፈች ሀገር ሲል ሰይሟታል፡፡ ሶማሊያ 2ኛ፣ሱዳን 4ኛ፣ኢትዮጵያን በ20ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጣት፣ኤርትራን በ24ኛ ደረጃ እና ዲጂቡቲን በ40ኛ ደረጃ ላይ አስፍሯቸው ነበር፡፡

የቅርስ ጥበቃ ድርጅት (Heritage Foundation) በበኩሉ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2015 የኢኮኖሚ ነጻነትን በተመለከተ በ178 ጥናት አድርጎ በደረሰበት ድምዳሜ መሰረት ኤርትራ በ174ኛ ደረጃ፣ኢትዮጵያ 149ኛ ደረጃ፣ዲጂቡቲ በ112ኛ ደረጃ ላይ ይገኙ እንደነበር ይፋ አድርጎ ነበር፡፡በግዜው ደቡብ ሱዳን፣ሱዳንና ሶማሊያ ደረጃ ውስጥ አልገቡም ነበር፡፡

      እንደ ጎርጎሮሲያኔ አቆጣጠር 2015 በወጣው የፕሬስ ነጻነት ኢንዴክስ ላይ የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters without Borders ranked 180 countries.) ጥናት መሰረት ኤርትራን ከ180 ሀገራት መሃከል በ180ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጣት፣ሱዳን 174ኛ፣ሶማሊያ 172ኛ፣ዲጂቡቲ 170ኛ፣ኢትዮጵያ 142ኛ፣ደቡብ ሱዳን ደግሞ125ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ለአለም ሕዝብ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

ስድስቱም የአፍሪካው ቀንድ ሀገራት በተለያዩ መስፈርቶች በአፍሪካም ሆነ በአለም ደረጃ የመጨረሻውን ደረጃ የያዙ ናቸው፡፡

በአፍሪካው ቀንድ የተከሰቱ ግጭቶች በወፍ በረር ሲቃኙ

ሱዳን

የካርቱምን መንግስት በመቃወም በደቡብ ሱዳን የአኛኛ 1 እና አኛኛ 2 የደፈጣ ውጊያ ወይም አመጽ The Anyanya I and II insurgency against Khartoum እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ እንደተጀመረ ከቀንዱ የፖለቲካ ታሪክ እንማራለን፡፡ ከዚህ ባሻግር እንደ አውሮፓውኑ አቆጣጠር የተኩስ አቁም ስምምነት እስከተደረሰበት 2003 ድረስ በሰሜን ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የርስበርስ ጦርነት ተካሂዷል፡፡ ሱዳን አሁን ድረስ የቀጠለ በሶስት ማእዘኑ የሃሊያብ ድንበር (the Halaib Triangle) አኳያ ከግብጽ ጋር እስጥ አግባ ውስጥ ትገኛለች፡፡ በምስራቅ ሱዳን ደግሞ ግዜውን እየጠበቀ የሚፈነዳ ጠጎሳ ግጭት አለ፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አወቆጣጠር 2003 ላይ የተቀሰቀሰው የዳርፉር ግጭት አሁን ድረስ መፍትሔ አልተበጀለትም፡፡ ከቻድ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አኳያ ድንገት የሚነሳ ግጭት በየግዜው ታስተናግዳለች፡፡ ኡጋንዳን በአስርቱ ትእዛዘት አስተዳድራለሁ በማለት ጦር መዞ የነበረው አማጺ ቡድን The Lord’s Resistance Army (LRA)  መነሻውን ደቡብ ሱዳን በማድረግ ኡጋንዳን ይበጠብጥ ነበር( ሱዳን አንድ ሀገር በነበረችበት ግዜ ማለቴ ነው) ፡፤ ከዚህ ባሻግር ሱዳን በርካታ አሸባሪ ቡድኖችን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1970ዎቹ ጀምሮ እስከ 1990ዎቹ ድረስ ትረዳ እንደ ነበር የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ የተባበረችው አሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን በአንድ ጥናታቸው ላይ እንደጠቀሱት ኦሳማ ቢንላደን (እ.ኤ.አ. 1991-1996 ) በአሉት አመታት በሱዳን ምድር የጥገኝነት ከለላ አግኝቶ ነበር፡፡

በደቡብ ሱዳን ድንበር በተለይም በኑባ ተራራ the Nuba Mountains ፣አቢዬ ግዛት Abyei እና ደቡብ ኮርዶፋን ግዛት Southern Kordofan ከባድ ጦርነት ተካሂዷል፡፡ የዚህ ጦርነት ውጤት ደግሞ አዲስ አፍሪካዊት ሀገር ደቡብ ሱዳንን አዋልዷል፡፡ ( ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ያወጀችው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 9 2011 ነበር፡፡)

ለ. ደቡብ ሱዳን

የደቡብ ሱዳን ነጻነቷን አወጀች ከተባለ ወዲህ በጎሳ ሚሊሻ ታጣቂዎች መሃከል በየግዜው ግጭቶችን አስተናግዳለች፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2013 የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከትሎ የሀገሪቱን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዜዴንት ሬይክ ማሻርን(1st vice president Riek Machar )ከስልጣናቸው ገሽሽ እንዲሉ ከማድረጉ በሻግር በዲንካ Dinka እና ኑዌር Nuer ጎሳዎች መሃከል የርሰበርስ ጦርነት እንዲቀጣጠል አድርጎ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሁለቱም ጎሳዎች በደቡብ ሱዳን በርካታ የህዝብ ቁጥር ያሏቸው ናቸው፡፡

ሐ. ኢትዮጵያ

የግራ ክንፍ የወታደሮች ቡድን (ደርግ) እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1974 የአጼ ሀይለስላሴን መንግስት ገርስሶ ስልጣን መጨበጡ በታሪክ ማህደር ውስጥ ፍንትው ብሎ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡ ( የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲ እና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና አስተማሪዎችን ከባድ መስእዋትነት፣የታክሲ ሹፌሮች፣ የሰራተኛው ማህበር መሪዎች እና ሰራተኞች ( የእነ አበራ ገሙ ወዘተ ወዘተ ትግልና መሰእዋትነት የሚዘነጋ አይደለም፡፡) ይህን ተከትሎ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትና ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ባደረጉት ትግል. እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ ታክሎበት የኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም መንግስት በ1991 ( እ.ኤ.አ.) ተንኮታኩቶ ወድቋል፡፡

     እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በበኩሉ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል ተንቀሳቅሶ ነበር፡፡ በ1980ዎቹ(እ.ኤ.አ.) አጋማሽ ላይ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅት የራስ ገዝ ጥያቄ ከማቅረቡ ባሻግር ፣ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል ትግል አድርጎ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መሰረታቸውን ጎሳ ላይ ያደረጉ የነጻ አውጪ ድርጅቶች በጋምቤላ፣አፋር፣ቤኒሻንጉል እና ሲዳማ ክልሎች ይንቀሳቀሱ እንደነበር ይታወቃል፡፡

         ፕሮፌስር ዴቪድ ሺን በአንድ ጥናታቸው ላይ እንዳስቀመጡት፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ከገልፍ ሀገሮች መነሻውን ያደረገው የውሃቢ ፍልስፍና ተጽእኖ ያደርግባቸዋል፡፡ ( ይህ ሲባል ግን በኢትዮጵያ የሚገኙ አጠቃላይ የእስልምና እምነት ተከታዮች ሁሉ በውሃቢ ፍልስፍና ተጽእኖ ስር ናቸው ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡) ኢትዮጵያ ትኩረት ባልተሰጣቸው አንዳንድ የአሸባሪዎች ጥቃት አልፎ አልፎም ቢሆን ተጎድታለች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2006 በሶማሊያ የሽግግር መንግስት ጥያቄ መሰረት የእስላሚክ ፍርድ ቤት ታጣቂ ቡድንን ለማጥፋት ወደ ሶማሊያ ግዛት በመግባቷ ምክንያት በቀጥታ ለጥቃት የተጋለጠች ሀገር ሆናለች፡፡

Ethiopia has been subject to growing Wahhabi influence from the Gulf States among its 36 percent Muslim population.  Ethiopia has experienced periodic low level terrorist attacks by undetermined groups in urban areas.  At the request of the Somali Transitional Federal Government, Ethiopia invaded Somalia late in 2006 to eliminate the administration operated by the Islamic Courts, which Ethiopia concluded was a direct 

 Threat.

(David shin Adjunct Professor, Elliott School of International Affairs)

George Washington University )

መ.ኤርትራ

መሳሪያ ያነገቱ የተገንጣይ ሀይሎች ከኢትዮጵያ ለመለየትና የራሳቸውን ነጻ ሀገር ለመመስረት ወደ በረሃ የወረዱት፣ኤርትራውያን ወንድሞቻችንን እናታቸውን ኢትዮጵያ ክደው ነጻ ሀገር መሆን እንዳለባቸው መስበክ የጀመሩት(የክህደት ቁልቁለት ይሉታል ታላቁ የኢትዮጵያ ልጅ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም(ነብስ ይማር)፣ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1960ዎች ላይ እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡

   ኤርትራ እውቅና ያልተሰጣት ሀገር በመሆን ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ በሸፍጥ የተለየችው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1991 ( de facto independence in 1991)  ፣ ሲሆን ፣ ምስጋና ለሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለሰ ዜናዊ ይሁንና አለም አቀፍ እውቅና የተሰጣት ህጋዊ ሀገር (de jure independence in 1993 )ለመሆን ወጉ የደረሳት ደግሞ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1993 ነበር፡፡ እንደ ሌሎቹ የአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ሁሉ ኤርትራ በየግዜው በድንበር ይገባኛል ምክንያት ከሱዳን ጋር ግጭት ውስጥ ተዱላለች፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1995 በሀኒሽ ደሴት ይገባኛል ምክንያት ከየመን ጋር ጦርነት ገጥማ ነበር፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1998 የኤርትራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ በመግባቱ እስከ 2000 ( እ.ኤ.አ.) የቆየ ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከስቷል፡፡ በአንድ ወቅት ኤርትራ የሶማሊያ የሽግግር መንግስትና የኢትዮጵያ መንግስት ጠላት ለነበረው ጽንፈኛ የሶማሊያ ቡድን ይረዳ ነበር፡፡

ሠ. ዲጂቡቲ

በዚች ሀገር ላይ ዴሞክራሲና አንድነትን መልሶ ለማንበር ሲባል በአፋር እና ሶማሌ ህዝብ መሃከል ለረጅም ዘመን የቆየ የግጭት ታሪክ እንዳለ የአካባቢው የፖለቲካ ተንታኞች የሄዱበት ጉዳይ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን አልፎ አልፎ ግጭቶች መከሰታቸው አልቀረም፡፡

ረ.ሶማሊያ

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ1960 ጀምሮ እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ ድረስ ሶማሊያ በኢትዮጵያና ኬኒያ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ተወላጆችን በአንድ ሀገር ላይ ለማስተዳደር ባላት ምኞት ምክንያት ወይም የቅኝ ገዢዎች እንግሊዞች ተንኮል የሆነውን የታላቋን እንግሊዝ ህልም እውን ለማድረግ ስትል ከኬንያና ኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ጦርነት ገጥማ እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡ የዕብሪተኛው የመሃመድ ሲያድባሬ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር እስከ 600 ኪሎሜትር ዘልቆ በመግባት ወረራ በፈጸመበት ግዜ ማለትም እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ1977-1978 ድረስ ባሉት ግዚያት ሶማሊያ  ከኢትዮጵያ ጋር የለየለት ጦርነት ውስጥ ተዱላ እንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡  There was a major conventional war with Ethiopia in 1977-78 when Somalia briefly captured most of southeast Ethiopia.

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚች ሀገር ላይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1980ዎቹ ላይ በሶማሊያ እና ሶማሌ ላንድ መሃከል የርስበርስ ጦርነት ተከስቶ ነበር፡፡ ከሶማሊያው ፕሬዜዴንት መሀመድ ዚያድባሬ ውድቀት ወዲህ ደግሞ ( እ.ኤ.አ. 1991) የሶማሌ ላንድ የራሷን ነጻ መንግስት ስትመሰረት ሶማሊያ የከሸፈች ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡

     ይህን ተከትሎ  ማለትም በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ አልኢቲሃድ-አል-ኢስላሚ (al-Ittihad al-Islami ) የተሰኘ አክራሪ ድርጅት ተመስርቷል፡፡ የጦር አበጋዞች ዘመን ከመሆኑ ባሻግር፣ በተባበረችው አሜሪካ የሚመራ አለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ሀይል የወታደራዊ ጣልቃ ገብነትም ነበር፡፡ ( ይህ አለምአቀፍ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የነበረው እ.ኤ.አ. 1992 እስከ 1995 ነበር፡፡)

     የእስልምና ፍርድ ቤቶች ሀይል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 ላይ ስልጣን ቢይዝም፣እ.ኤ.አ. በ2007 ወደ ሶማሊያ ድንበር ዘልቀው የገቡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከስልጣኑ አሽቀንጥረው ጥለውታል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ውጤቱ አላማረም ነበር፡፡ ሌላ የበለጠ አክራሪ የሆነ እና 

ከአል-ቃኢዳ ጋር የግንኙነት መረብ የፈጠረ አል-ሸባብ (al-Shabaab )የተሰኘ ጽንፈኛ ድርጅት ሊፈጠር ችሏል፡፡

     አንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2008 ላይ በሶማሊያ የሽግግር መንግስት ጋባዥነት ከሶማሊያና ኢትዮጵያ የተወጣጡ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ምድር ከገቡ በኋላ አልሻባብ ከያዛቸው በርካታ ድንበሮች ለመልቀቅ ቢገደድም ለተደጋጋሚ ግዚ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ እና ኬኒያ ግዛት መፈጸሙ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

   የውክልና ጦርነቶች (Proxy Wars)

    አብዛኞቹ የቀንዱ ሀገራት በጎረቤቶቻቸው ላይ የውከልና ጦርነቶችን  ከመደገፍ አኳያ ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ታሪክ አላቸው፡፡ በሌላ አነጋገር በአንዱ ሀገር መንግስት ላይ ጦር ያነሳን አማጺ ሀይል የሌላው ሀገር መንግስት ሲደግፍ ይታያል፡፡ ለብዙ አመታት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የካርቱምን መንግስት ለመጣል ይንቀሳቀሱ ለነበሩት ለሱዳን ህዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ እና ለብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ሀይል የፖለቲካ ድርጅቶች ይረዱ እንደነበር ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን ባቀረቡት የጥናት ወረቀት ላይ አስፍረውታል፡፡ ከብዙ አመታት በፊት ኢትዮጵያ በርካታ የሶማሊያን መንግስት የሚቃወሙ የፖለቲካ ድርጅቶችን ትረዳ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

    በአንድ ወቅት ኤርትራ የሱዳን ተቃዋሚ የነበረውን የምስራቅ ሱዳን ቤጃ ብሔራዊ ኮንግረስ ስትረዳ የቆየች ሲሆን፣ ካርቱም ከብዙ አመታት በፊት የኢትዮጵያን መንግስት ይታገሉ ለነበሩ የፖለቲካ ሀይሎች ማለትም የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን፣ የኤርትራ ነጻነት ግንባር፣የቤንሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ግንባርን ትረዳ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር የኤርትራ ኢስላሚክ ጂሃድ የተሰኘ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ፣ የጌታ ተዋጊዎችና የምእራብ ናይል ግንባር የተሰኙ የኡጋንዳን መንግስት ተቃዋሚዎችን በተለያዩ መንገዶች ትደግፋለች፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሱዳንና ደቡብ ሱዳን  አንዱ የሌላውን የተቃዋሚ  ፖለቲካ ፓርቲ ይረዳሉ፡፡

     ከብዙ አመታት በፊት ሶማሊያ በበኩሏ የኢትዮጵያን መንግስት ይቃወሙ ለነበሩ እና በምስራቅ ኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ የነጻ አውጪ ግንባሮች ትረዳ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በአፍሪካው ቀንድ የሚገኙ ሀገራት ከሀገራቸው ውጭ ለሚንቀሳቀሱ ብረት አንጋቾች በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ስለሚያደርጉ አካባቢው ከግጭት አዙሪት መውጣት ተስኖታል፡፡ ወይም በዋነኝነት የአፍሪካው ቀንድ ከግጭት አዙሪት መውጣት የተሳነው አንደኛው ሀገር የሌላውን ሀገር ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት በመደገፍና በመርዳታቸው ነው፡፡

የወታደራዊ ድርጅቶች ባህሪ

እንደ ወታደራዊ ሳይንስ አዋቂዎች ጥናት ከሆነ ኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ኤርትራ በወታደራዊ ሳይንስ ሙያ የተካኑ ወታደራዊ ሀይል ለመገንባት ችለዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን በአቀረቡት ጥናት እንደገለጹት ከሆነ በአጽ ሀይለስላሴ ዘመን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ ሳይንስ እውቀት ያለቸውን የጦር መኮንኖችን ማፍራት የቻለች ሀገር እንደነበረች፣ እ.ኤ.አ. በ1950ቹ በሰሜን ኮሪያ፣ ለሁለተኛ ግዜ ደግሞ  በኮንጎ ካታንጋ ግዛት ሰላም ለማስከበር ዘመናዊና ብረት ለበስ የጦር ሀይል  መላክ የቻለች ሀገር ነበረች፡፡

      ሱዳን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ካለቸው ሶስት ግንባር ቀደም ሀገራት አንዷ እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ዴቪድ የጥናት ወረቀት ከሆነ ሱዳንን የሚቀድሟት የደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክና ግብጽ ናቸው፡፡

    ሶማሊያ በአብዛኛው ወታደራዊ ሳይንስ የታጠቀ ጦር ለመገንባት ገና ብዙ ርቀት መጓዝ እንዳለባት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ያለመታደል ሆኖ በዚች ሀገር ላይ መሳሪያ የታጠቀው ሀይል ታማኝነቱ ለነገድ፣ጎሳና ለአካባቢያዊ ስሜት ላይ ነው፡፡

   ከአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያ ለብይነ መንግስታቱ የሰላም አስከባሪ ሀይል በርካታ ወታደሮችን በማዋጣት፣ በብዙ ሀገራት የአለምን ሰላም ከማስከበር አኳያ ጥሩ ስም እና ወርቃማ ታሪክን ለማስመዝገብ የቻለች ናት፡፡

  አሸባሪነት በወፍ በረር ሲቃኝ

በርካታ የአካባቢው የፖለቲካ ተንታኞች እንደሄሱት ከሆነ ሱዳን ለአሸባሪዎች መጠለያ ወይም ከላለ የምትሰጥ ሀገር ነበረች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኬኒያ ናይሮቢና፣ በታንዛኒያ ዳሬሰላም የሚገኙት የተባበረችው አሜሪካ ኤምባሲዎች የአሸባሪዎች ጥቃት ሰለባ በሆነበት ግዜ አሜሪካ ጥቃቱን የሰነዘረው በኦሰማ ቢንላደን የሚመራው አሸባሪ ቡድን ነበር በማለት ስሌት በስህተት የሱዳንን የመድሃኒት ፋብሪካ በክሩዝ ሚስኤል ጥቃት እንዳልነበረ ማድረጓን በግዜው በዜና አውታሮች በሰፊው የተናኘ ዜና ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሱዳን ያንዬ ለኦሳማ ቢንላደን ጥገኝነት የሰጠች ሀገር ነበረች፡፡

       እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1992 ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው የውጭ ሀገር ተዋጊዎች፣አልሻባብ የተሰኘ ጽንፈኛ ቡድን በሶማሊያ ምድር የበቀሉ አሸባሪዎች ናቸው፡፡ አልሻባብ አደገኛና አካባቢውን ለስጋት ያጋላጠ ቡድን ነው፡፡

      በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ የተባበረችው አሜሪካ የጸረ አሸባሪነት ትግል አጋር በመሆን አሸባሪነትን የተዋጋች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በምድሯ ላይ እንደ ሌሎች ሀገራት በእስ በአሸባሪዎች ሰፋ ያለ ጥቃት እንዳይደርስባት መከላከልም የቻለች ሀገር ናት፡፡

     ኤርትራ ለአሸባሪዎች ጥቃት ያልተጋለጠች እና የማትበገር  ሀገር መሆኗን ለአለም አሳይታለች፡፡ ዲጂቡቲ የአለም አቀፉ የጸረ ሽብር ትግል ተባባሪ የሆነች፣የጃፓን፣የተባበረችው አሜሪካ፣ፈረንሳይ ጦር ሀይሎች ወዘተ መጠለያ ወይም ወታደራዊ ቢዝ እንዲመሰረተ ብትፈቅድም  ከአለም አሸባሪዎች የደረሰባት ጥቃት አልነበረም፡፡ 

ሶማሊያና የባህር ላይ ውንብድና

እንደ አካባቢው የፖለቲካ ተጠባቢዎች ጥናት ውጤት ከሆነ በሶማሊያ የባህር በሮች ላይ ፣የባህር ውንብድና ተስፋፍቶ የነበረው እንደ ጎርጎሮሲያ አቆጣጠር ከ2004- 2005 አመታት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሶማሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ የባህር ላይ ጸጥታ ካርታ ውስጥ እንድትገባ ሆኗል፡፡ ይህም ማለት ይህ የውሃ አካል የጸጥታ ስጋት አንዳለበት በአለም አቀፍ የባህር ጸጥታ ካርታ ውስጥ ወድቃለች፡፡

      በ2008 (እ.ኤ.አ.) የሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች አንድ መርከብ አግተው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በ2008 (እ.ኤ.አ.) በአለም ላይ ከተፈጸሙት የባህር ላይ ውንብድና መሃከል 86 ፐርሰንቱ የባህር ላይ ውንብድና የተፈጸሙት በሶማሊያ የውሃ አካል ላይ ነበር፡፡በ2009 (እ.ኤ.አ.) የበለጠ የጨመረ ሲሆን፣ ለ445 ያህል ግዜያት በባህር ላይ ወንበዴዎች በመርከቦች ላይ ጥቃት ተከፍቷል፡፡ 49 መርከቦች ወይም ጀልባዎች ታግተው ነበር፡፡ ይህም ብቻ አይደለም እ.ኤ.አ. በ2010 በአለም ላይ ከተፈጸሙት የባህር ላይ ውንብድናዎች መሃከል 92 ፐርሰንቱ የተፈጸመው በሶማሊያ የውሃ አካል ላይ( ሶማሊያን በሚያዋስናት የህንድ ውቅያኖስ አኳያ ማለቴ ነው) በሚንቀሳቀሱ መርከቦች እና ጀልባዎች ላይ ነበር፡፡  ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሮፌሰር በአንድ የትናት ወረቀታቸው ላይ እንደጠቀሱት እ.ኤ.አ. በ2010 መጨረሻ ላይ የሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች 28 መርከቦችን ይዘዋል፣638 የመርከብ ሰራተኞችን ደግሞ አግተው ነበር፡፡

       በነገራችን ላይ የሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች የጥቃት ሰበዛቸውን እስከ የአረብ ባህረ ሰላጤና ሲሼልስ የባህር ግዛት፣ሰሜን ማደጋስካር እና ኦማን የባህር በር ድረስ አስረዝመውት እንደነበር የሚያሳዩ ጽሁፎች እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡

    የባህር ላይ ወንበዴዎች ጥያቄያቸው ገንዘብ ነው፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ደግሞ አርፒጂ የመሰሉ ከባድ መሳሪያዎችን በመርከብ ላይ በመተኮስ ካስቆሙ በኋላ ገንዘብ ይዘርፋሉ፡፡ አንድ መርከብ ካስቆሙ በኋላ የ3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ክፍያ ይጠይቁ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡

 አብዛኞቹ የፖለቲካ ኤክስፐርቶች በጥናታቸው እንደደረሱበት ከሆነ የባህር ላይ ወንብድና ከአልሻባብ ፍልስፍና ጋር የሚገናኝ አልነበረም፡፡ የርዮትአለምም ተልእኮ አልነበረውም፡፡ የባህር ላይ ወንበዴዎች አንድና አንድ ጥያቄያቸው ገንዘብ ነበር፡፡

      በአፍሪካው ቀንድ የተባበረችው አሜሪካ የዲፕሎማሲ ተግዳሮቶች

     የተባበረችው አሜሪካ በአፍሪካው ቀንድ አካባቢ የዲፕሎማሲ ተግዳሮት የሚታይ.የሚጨበጥ ነው፡፡ አፍሪካ ከዲፕሎማሲ አኳያ በተባበረችው አሜሪካ ትኩረት የተሰጣት አትመስልም፡፡ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን በአንድ የጥናት መድብላቸው ላይ እንዳስቀመጡት የተባበረችው አሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣኖች በብዙ የአለም ክፍልና በቀሪው የአፍሪካ ክፍል የሚሰጡት ትኩረት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የሚመድቡት ባጀትም እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በአፍሪካው ቀንድ የአፍሪካው ክፍል የሚሰጡት ትኩረት ከፍተኛ ሲሆን፣ጠቀም ያለ ባጀት ይመድባሉ፡፡

      የተባበረችው አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት መልካምና ሞቅ ያለ የነበረ ሲሆን፣ዛሬ ደግሞ የተቀዛቀዘ እንደሆነ ከፖለቲካ ተንታኞች ጥናት መረዳት ይቻላል፡፡ ይህቺ ሃያል ሀገር ከሚጢጢዋ ዲጂቡቲ እና ሶማሊያ ጋር ያላት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጥሩ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር አይንሽ ላፈር ስትላት የነበረውን ሱዳን ዛሬ ደግሞ መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እየሞከረች ትገኛለች፡፡ ከኤርትራ ጋር ግን መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት የላትም፡፡ ከደቡብ ሱዳን ጋር ደግሞ ያላት የዲፕሎማሲ ግንኙነት እጅጉን የተወሳሰበ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሳ በአፍሪካው ቀንድ የአሜሪካ ተጽእኖ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የተባበረችው አሜሪካ አንዱን ሀገር ፊት በመንሳት፣ሌላውን በማባበል፣ በየሀገሩ ግፍ የሚፈጽሙትን እንደ ወያኔ የመሰሉ ዘረኛና የጦር ወንጀለኛ፣የሀገርን ሀብት በጠራራ የዘረፈ ማፊያ ቡድን በአንቀልባ ለማዘል መሞከሯ ወዘተ ወዘተ በአፍሪካው ቀንድ የዲፕሎማሲ ክሽፈት እያጋጠማት ይገኛል፡፡

     የተባበረችው አሜሪካ በአፍሪካው ቀንድ ሰላም በማስከበር የሚታወቀውን ዋነኛውን ክፍለ አህጉራዊ ድርጅት ኢጋድን በከፍተኛ ደረጃ በገንዘብም ሆነ ቴክኒካል እርዳታ እንደምታቀርብ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ይህ ክፍለ አህጉራዊ ድርጅት በአፍሪካው ቀንድ ሰላም ለማስፈን አልሆነለትም፡፡ ወይም በሌላ አነጋገር በሀገራት መሃከል ወይም በአንድ የአፍሪካው ቀንድ ሀገር ውስጥ የሚከሰቱ የርስበርስ ጦርነቶችን ማስቆም አላስቻለውም፡፡

      ምንም እንኳን የተባበረችው አሜሪካ በአፍሪካው ቀንድ ሁነኛ አለም አቀፍ ተዋናይ ብትሆንም፣ የተባበረችው አሜሪካ ብቻ አይደለችም በዚህ አካባቢ ፈላጭ ቆራጭ የሆነችው፡፡ ሌሎች አክተሮች አሉ፡፡ እነርሱም የአውሮፓው ህብረት፣ የብይነ መንግስታቱ ወኪል ድርጅቶች እና የአለም ባንክ ለአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ዋነኛ የልማት አጋሮች ናቸው፡፡ለአብነት ያህል የብይነ መንግስታቱ ድርጅት ‹ የአፍሪካው ህብረት በሱዳን ዳርፉር  እና ሶማሊያ  ሰላም ለማስከበር ላሰማራቸው አፍሪካዊ ወታደሮች ስንቅና ትጥቅ፣ እንዲሁም ሎጂስቲክ  እግዛው ከፍተኛ ነው፡፡ ወይም መተኪያ የለውም፡፡ ምክንያቱም አፍሪካ በኢኮኖሚ የደቀቀች ስለሆነች ለእንዲህ አይነት አለም አቀፍ ስምሪት የሚሆን ወረት ገና ማፍራት ስላልቻለች ነው፡፡ይህም ብቻ አይደለም በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስከበር የብይነ መንግስታቱ የሰላም አስከባሪ ሀይል ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

      በርካታ ቁጥር ያላቸው የአውሮፓና የባህረ ሰላጤው ሀገራት፣ቻይና ጨምሮ ከተባበረችው አሜሪካ በበለጠ ከአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ጋር የምጣኔ ሀብት ግንኙነት እንዳላቸው እንደ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን የመሰሉ ስመጥር አሜሪካዊ የዲፕሎማሲ ሰዎች ሳይቀሩ በጥናታቸው ላይ ያሰፈሩት ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በርካታ የአውሮፓ ሀገራት፣ቻይና፣ ህንድ ጥቂቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነ ሳኡዲ አረቢያና ቱርክ ሳይቀሩ ከአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ጋር ጠንካራ የምጣኔ ሀብት ግንኙነት ፈጥረዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ ፌዴሬሽንና ህዝባዊት ቻይና ለአካባቢው ዋነኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢዎች ናቸው፡፡ እንደ ኪንያ፣ ኡጋዳ፣ ግብጽ እና ቻድ የመሳሰሉት ሀገራት ጠቃሚ የሆነ የፖለቲካ ፍላጎት በአንዱ ወይም ከዛ በላይ በሆኑ የአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ላይ አላቸው፡፡

    ምንም አንኳን አሜሪካ በዲጂቡቲ የመሰረተችው የአፍሪካው ቀንድ ያጋራ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ትልቁ ቢሆንም ፈረንሳይ፣ ጃፓን እና ቻይና በዲጂቡቲ የጦር ሰፈር ገንብተዋል፡፡ በሌላ አነጋገር የተባበረችው አሜሪካ ብቸኛዋ ሃያል ሀገር አይደለችም ማለት ነው፡፡ ዛሬ መረጃው ባይኖረኝም በወያኔ-ኢህአዲግ የአገዛዝ ዘመን  በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ የድሮን እንቅስቃሴ ታደርግ እንደነበር ከተለያዩ ምንጮች ለመረዳት ይቻላል፡፡ The United States also has a drone operation in southwestern Ethiopia.

እነኚህ የተጠቀሱት አለም አቀፍ ተዋናዮች ሁሉ ተደምረው በአፍሪካው ቀንድ ያለውን የተባበረችው አሜሪካን የዲፕሎማሲ ፖሊሲ  ውስብስብ እንዲሆን ተጽእኖ ፈጥሮበት ይገኛል፡፡ ሁላችንም በተባበረችው አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ሶማሊያውያን እና የኤርትራ ተወላጆች ቁጥር እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ የሶስቱም ሀገራት ተወላጅ የሆኑ የተማሩ ሰዎችም እንዲሁ ከፍተኛ ነው፡፡ አንዳንዶች ጎበዞች ደግሞ በተባበረችው አሜሪካ የፖለቲካ ስልጣን ለመቀዳጀት የበቁም አሉ፡፡ ስለሆነም በተባበረችው አሜሪካ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ ተጽእኖ ከማሳደር አኳያ ሚናቸው ቀላል አይደለም፡፡

  በመጨረሻም አንዳንድ ግዜ የተባበረችው አሜሪካ በአልተረጋገጠ (ትክከለኛ ባልሆነ ) መረጃ ወይም በቂ ባልሆነ መረጃ የአፍሪካውን ቀንድ በተመለከተ የምትወስደው መረጃ ውጤትን እንዳላመጣላት ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ የተባበረችው አሜሪካ የተሳሳተ የዲፕሎማሲ ፖሊሲ የአፍሪካውን ቀንድ ብቻ አይደለም ወደ ግጭት ውስጥ የሚዶለው ፣ የተባበረችው አሜሪካን ዲፕሎማሲ ሳይቀር ነው ውስብስብ ችግር ውስጥ  የሚከተው፡፡ ሰላም:-ነሐሴ 30 ቀን 2012

Filed in: Amharic