አቻምየለህ ታምሩ
የአገራችንን ታሪክ ያላነበቡ አንዳንድ ግልቦች ባንዳንነትና አርበኛነትን በነገድ፣ በአካባቢና በሃይማኖት ሲወስኑት ማየት የተለመደ ሆኗል። በመሰረቱ አርበኛነት የግለሰብ ውሳኔ፣ ብርታትና ጥንካሬ ውጤት እንጂ አንድ ሰው የአንድ ነገድ አባል ስለሆነ፤ ከአንድ አካባቢ ስለተወለደና የሆነ ሃይማኖት ተከታይ ስለሆነ የሚሰፍርበት ዛር አይደለም። ባንዳነትም እንዲሁ ነው። አንድ ሰው የአንድ ነገድ አባል፣ የአንድ አካባቢ ተወላጅ ወይም የአንድ ሃይማኖት ተከታይ መሆኑ ባንዳ አያደርገውም ወይም ባንዳ እንዳይሆን አያግደውም።
የአገራችን ባንዶች ከሁሉም የአገራችን ነገዶች፣ አካባቢዎችና ሃይማኖቶች ይመዘዛሉ። ጸረ ፋሽስቶቹን አርበኛ አባቶቻችንን በዱር በገደሉ እያሳደዱ የወጓቸው ከሮም የመጡ ነጭ የጣሊያን ወታደሮች አይደሉም። ጀግኖች አባቶቻችን በብዛት የወጓቸው ባንዶች አጎቶቻችን ናቸው።
የአገራችን ባንዶች በነገድ፣ በአካባቢና በሃይማኖት ሳይወሰኑ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ያገለግሎ እንደነበር ለግንዛቤ ያህል ለማሳየት በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት ፋሽስት ጣሊያንን እስኪያልባቸው ድረስ ያገለገሉና ጀግኖች አርበኞቻችንን እያሳሰዱ የፈጁ የአማራ፣ የትግሬና የኦሮሞ ዋናዋና ባንዶችን ስም ዝርዝር እንደሚከተለው አቀርባለሁ፤
የአማራ ባንዶች
1ኛ. ልዑል ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት [ጎጃም]
2ኛ ራስ ሥዩም መንገሻ አቲከም [ጎጃም]
3ኛ. ራስ ገብረ ሕይዎት ሚካኤል [ወሎ] (የልጅ ኢያሱ ወንድም)
4ኛ. ደጃዝማች አመዴ አሊ [ወሎ]
5ኛ. ደጃዝማች አያሌው ብሩ [ጎንደር]
6ኛ. ደጃዝማች አርአያ ገብረ መድኅን [ጎንደር]
7ኛ. ራስ ጌታቸው አባተ [ሸዋ]
8ኛ. ደጃዝማች አባውቃው ብሩ [ሸዋ]
የትግሬ ባንዶች
1ኛ. ልዑል ራስ ኃይለ ሥላሴ ጉግሣ [እንደርታ]
2ኛ. ልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ [አድዋ]
3ኛ. ደጃዝማች ተክሉ መሸሻ [አድዋ] ( የስብሀት ነጋ አጎት]
4ኛ. ደጃዝማች ተስፉ ትኩእ [ሽረ]
5ኛ. ደጃዝማች አርአያ ገብረ እግዚያብሔር [ሽሬ] (የኃየሎም አርአያ አባት]
6ኛ. ደጃዝማች አስረስ ተሰማ [አድዋ] (የመለስ ዜናዊ አያት)
7ኛ. ደጃዝማች አርኣያ መሸሻ [ተምቤን]
8ኛ. ደጃዝማች ገብረ እግዚያብሔር አብርሃ [አድዋ] (የሞንጆሪኖ [ፈትለ ወርቅ] አባት)
የኦሮሞ ባንዶች
1ኛ. ሱልጣን አባ ጆቢር አባ ጅፋር [ጅማ]
2ኛ. ደጃዝማች ሐብተ ማርያም ቁምሳ [ወለጋ]
3ኛ. ደጃዝማች ሆናዕና ጆቴ [ወለጋ]
4ኛ. ደጃዝማች ዮሐንስ ጆቴ [ወለጋ]
5ኛ. ሱልጣን አብዱላህ አባ ጅፋር [ጅማ]
6ኛ. ደጃዝማች ግዛው ጂማ [ሸዋ]
7ኛ. ደጃዝማች ቡሰሪ በያን [ሸዋ]
8ኛ. ደጃዝማች የማነ ቁምሳ [ወለጋ]
ልብ በሉ! እነዚህ ባንዶች ዋና ዋናዎቹና ከዋናዋናዎቹም በጣት የሚቆጠሩት ናቸው እንጂ በየነገዱ፣ በየአካባቢውና በየሃይማኖቱ የፈላው የባንዳ ቁጥር እልቆ ቢስ ነው። የሆነው ሆኖ ይህ የአገራችን ዋና ዋና ባንዶች ማንነትና ስብጥር የሚያሳየን ነገር ቢኖር ጀግኖች አባቶቻችንን ሲያሳድዱ የነበሩት ባንዶችአጎቶቻችን በነገድ፣ በአካባቢና በሃይማኖት ያልተወሰኑ በሁሉም ነገዶች፣ አካባቢዎችና ሃይማኖቶች ውስጥ የፈሉ ጉዶች መሆናቸውን ብቻ ነው።
ባጭሩ ባንዳ የሌለበት ነገድ፣ አካባቢና ሃይማኖት እንደሌለ ሁሉ አርበኞም የሌለበት የኢትዮጵያ ነገድ፣ አካባቢና ሃይማኖት የለም። ስለዚህ እያንዳንዱ ያገራችን ነገድ፣ አካባቢና ሃይማኖት አርበኛ እንዳለው ሁሉ እልቆ መሳፍርስት ባንዳም አፍልቷልና ባንዳነትን በነገድ፣ በአካባቢና በሃይማኖት በመወሰን የሚደረገው የአላማቂዎች መመጻደቅ የእውቀት ጾመኛነታቸውን ከማስመስከር ባለፈ ቁምነገር የለውም።
የኢትዮጵያ ባንዶች በነገድ፣ ባካባቢና በሃይማኖት ያልተወሰኑ፤ ብሔር፣ ብሔረሰብ ከሚባሉት በሚሉ የተውጣጡና በየአካባቢው የነበሩ ባንዶች ቁጥራቸው ከአርበኞቻችን እጅጉን ይልቅ እንደነበር ከነማንነታቸው ማወቅ የሚሻ ቢኖር፤
1ኛ. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” [ቅፅ ፩]፣
2ኛ. የደጃዝማች ከበደ ተሰማን “የታሪክ ማስታወሻ”፣
3ኛ. የቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይዎትን “የሕይወት ውጣ ውረድ”፣
4ኛ. የአቶ ገብረ ሕይዎት ኅዳሩን “ያቺም ቀን ተረሳች”፣
5ኛ. የቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴን “ቀሪን ገረመው”፣
6ኛ. የአቶ ሐዲስ አለማየሁን “ትዝታ”፣
7ኛ. የመቶ አለቃ ገሪማ ታፈረን “ጎንደሬ በጋሻው”፣
8ኛ. የአቶ ተስፋ ሚካዔል ትኩእን “የሀገሬ የሕይወቴ ጥሪ”፣
9ኛ. የአቶ ታደሰ ሜጫን “ጥቁር አንበሳ፣ በምዕራብ፣ኢትዮጵያ”፣
10ኛ. የአቶ ግብረ ወልድ እንግዳ ወርቅን “ማይጨው፤ የማይጨው ዘመቻና የጉዞ ታሪክ”፣
11ኛ. የአቶ ብርሀኑ ድንቄን “ከወልወል እስከ ማይጨው”፣
12ኛ. የአቶ ሰይፈ ሥላሴ አባ ወሎን “የታሪክ ቅርስ”፣
13ኛ. የአምባሳደር አለማየሁ አበበ ሸንቁጥን “የሸንቁጥ ልጆች”፣
14ኛ. የአቶ መኮነን ዘውዴን “የማይጨው ቁስለኛ” እና
15ኛ. የኮሎኔል ዳዊት ገብሩን “ከንቲባ ገብሩ ደስታ የኢትዮጵያ ቅርስ” መጽሐፍ ያንብብ!