>

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት ....!!! (ክፍል 3). አንዳርጋቸው ጽጌ

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት ….!!!
(ክፍል 3). አንዳርጋቸው ጽጌ

የ1968ቱና የ2013ቱ የወያኔ ስነዶች ተመጋጋቢነት
ወያኔዎች በ1968 አም የህወሃት የድርጅት ፕሮግራም አዘጋጁ። ይህ ፕሮግራም የ1968ቱ ማኒፌስቶ በመባል የሚታወቀው ሰነድ ነው። የዚህ ሰነድ አዘጋጆች ሶስት ሲሆኑ ሁለቱ በህይወት የሉም። ለገሰ (መለስ) ዜናዊና አምሃ (አባይ) ጸሃዬ። አንዱን በሽታ፣ ሌላውን ጥይት ወስዷቸዋል። ሶስተኛው ሰው ስብሃት ነጋ ከተምቤን ዋሻ ተጎትቶ ወጥቶ በስተርጅና አዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይገኛል።
ከዚህ ሰነድ የምናነሳው ነጥብ ሂሳብ ከማወራረዱ ስራችን ጋር አይን ባወጣ መንገድ የተያያዘውን ብቻ ነው። ሰነዱ “የትግራይ ህዝብ፣ ኢትዮጵያ በሚል ሽፋን የሚያጭበረብር “አማራ” በተባለ ብሄር በቅኝ ግዛትነት የተያዘ” እንደሆነ በግልጽ ያስቀምጣል። ከዚህ ተነስቶ የህወሃት የትግል አላማ “ትግራይን ከአማራ/ኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ አውጥቶ” የትግራይ ሪፐብሊክ መመስረት እንደሆነ ያትታል።
ይህ ሰነድ በዋንኛነት በወጣቶቹ (በወቅቱ 25 አመት ያልሞላቸው ነበሩና) በመለስና በአባይ ጸሃዬ ድንቁር እና ድፍረት ወይንስ በጎልማሳው በስብሃት ነጋ መሰሪነት የተጻፈ ይሁን የማውቀው ነገር የለም። የድንቁርና እና የመሰሪነት ድምር ውጤትም ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ይህ ሰነድ፣ በወቅቱ ሌሎቹን የወያኔ አመራሮች ሳይቀር የሚያሳምን ሰነድ አልሆነም። ይህን ተረት የሰማ የትግራይ ህዝብም በወቅቱ የጠየቀውን ጥያቄ እነ ስብሃት ነጋ ሊመልሱለት ያልቻሉት ነበር። “ይቺ በአማራ/ኢትዮጵያ በቅኝ የተያዘች የምትሏት ጥንታዊት የትግራይ ሃገር ስሟ ማን ነበር?” ስብሃትና ውርንጭላዎቹ መልስ አልነበራቸውም። “እኛ ኢትዮጵያውያን ካልሆንን ማነው ታዲያ ኢትዮጵያዊ?” መልስ አልነበረም። ማኒፌስቶው በሌሎች የወያኔ አመራሮች፣ በሰፊው ታጋይና በትግራይ ህዝብ ፈጽሞ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ።
በዚህ ማኒፌስቶ ምትክ ህወሃት ሌላ ሰነድ ይዞ ብቅ አለ። በዚህ ሰነድ “ወያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ለትግራይ ህዝብ ብሄራዊ እኩልነት የሚታገል ድርጅት እንደሆነ” ተነገረ። ሆኖም ግን  የእኩልነቱ ጥያቄ መልስ የማያገኝ ከሆነ፣ ወያኔ “ትግራይን ገንጥሎ ሃገር የመመስረት መብት” ያለው መሆኑን አዲሱ የድርጅቱ ፕሮግራም በማያሻማ ቋንቋ ግልጽ አድርጓል። የ1968ቱን ማኒፌስቶ የተካው የወያኔ የድርጅት ፕሮግራም አቀራረቡ እንጂ ይዘቱ የእነመለስና የስብሃት ነጋን የነጻ ሃገርና ሪፐብሊክ ምስረታ ህልም እንደያዘ ነበር። ወያኔ በትግል በቆየባቸው 17 እና ቀጥሎም ስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 አመታት ሲመራ የነበረው አማራን በቅኝ ገዥነት በፈረጀበትና ትግራይን ነጻ ማውጣት የሚለው ህልሙን ባሰፈረበት የ1968ቱ ማኒፌስቶ አማካኝነት እንደነበር የሚያሳዩ በቂ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል።
በቦታው የምንመለስበት ቢሆንም፣ የትግራይን ግዛት በአማራና በአፋር ህዝብ የግዛት ኪሳራ ማስፋት፣ ልዩነትን መሰረት ያደረገና የመገንጠልን መብት የሚፈቅድ ህገ መንግስት መደንገግ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር ከፋፍሎና በጥላቻ እርስ በርሱ እንዲጠራጠርና እንዲናቆር የሚያደርግ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ስርአት መዘርጋት፣ በተለይ ለነስብሃት ነጋ ኢትዮጵያን የማፈራረስና ትግራይ የምትባል ነጻ ሃገር ምስረታ ህልም እንቅፋት ይሆናል ያሉትንና “ቅኝ ገዥ” በማለት የፈረጁትን አማራ ነጥሎ የሚያዳክም ስነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ጥቃቶችን መፈጸም፣ ቁልፍ የሆኑ የወታደራዊ፣ የደህንነትና ሌሎችን መንግስታዊ ተቋማት በወያኔዎች ቁጥጥር ስር ማዋል፣ በመንግስት እና በግል የተያዘውን የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በጥቂት የወያኔ አባላትና ከወያኔ ጋር ቅርበት ባላቸው ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ማስያዝ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ አጥንቱ እስከሚቀር በመጋጥ፣ ሃብቱን መዝረፈና ከሃገር ማሸሽ፤ ወያኔ ለ27 አመታት ያለ እረፍት ያከናወናቸው ድርጊቶች ናቸው። ርእዮተአለማዊ  መሰረታቸው የ1968ቱ ማኒፌስቶ ነው።
እነዚህን ድርጊቶች በደንብ ላጤናቸው አንድ የውጭ ወራሪ አንድን ሃገር በቅኝ ሲይዝ በተግባር የሚያውላቸው እንጂ በእኩልነት  በአንድ ሃገር ውስጥ ለመኖር የወሰነ የአንድ ድርጅት ተግባራት እንዳልሆኑ ግልጽ ነው።
ይህ ማኒፌስቶ 1968 አም ላይ ተቀብሮ እንዳልቀረ፣ መስከረም 30 2013 አም  ወያኔ ያወጣውን የ86 ገጽ፣ ኢትዮጵያን የማፈራረስና የትግራይን ሃገር የመመስረት የስትራተጂ ሰነድ ማየት ብቻ በቂ ነው። ልዩነቱ በ1968 አም ወያኔ፣ “ትግራይ የኢትዮጵያ/አማራ ቅኝ ነበረች” ባለበት ወቅት በትግራይ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው የህዝብና የትግራይ ልሂቃን ሰፊ ተቃውሞ ዛሬ አለመኖሩ ብቻ ነው።
“ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እንወርዳለን” የሚል ንግግር የሚናገሩና “ኢትዮጵያ ስትፈርስ ለማየት የሚያስችል ዘመን ውስጥ በመፈጠራቸው እድለኛ እንደሆኑ በአደባባይ የሚናገሩ የእነመለስና የስብሃት ጸረ ኢትዮጵያ ቫይረስ ተሸካሚዎች  በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት የተበራከቱበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ይህ ሃቅ የትግራይን ህዝብ ከገዛ ታሪኩና ማንነቱ ጋር የተጣላ ለማድረግ በ1968 የተጀመረው ስራና ሴራ ምን ያህል እንደተሳካ የሚያሳይ ነው። ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ይህን ሃቅ አሳንሶ ማየት ማንንም አይጠቅምም።
ከላይ የጠቀስኩት 86 ገጽ ሰነድ ወያኔ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ ከአንድ ወር በፊት የተዘጋጀ ስለሆነ ከዛ በኋላ የተገደሉትና ዛሬ በእስር ቤት የሚገኙት እነስብሃት ነጋ፣ እንዲሁም ከእስራትና ከሞት ያመለጡት እነደብረጽዮን እና ጻድቃን በጋራ የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት እንደሆነ ይታወቃል። በፕሮፓጋንዳ ደረጃ ከአማራ ህዝብ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን ከሚለው የወያኔዎች ድንፋታ አንስቶ በተግባር በአማራ ህዝብ ላይ ወያኔዎች እያካሄዱት ያለው ወረራ፣ ጭፍጨፋ፣ ዘረፋና ውድመት ወያኔዎች “ቅኝ ገዥ” ያሉትን አማራ ለመበቀል ከ40 አመታት በላይ የተዘጋጁበት መርሃ ግብር አካል እንደሆነ ይህ ሰነድ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ወደ ተነሳንበት ቁም ነገር ስንመለስ፣ የ1968ቱን ማኒፌስቶ የተካው የህወሃት ፕሮግራም፣ የትግራይ ህዝብ ለዘመናት “በአማራ ገዥዎች/  አስከፊ ብሄራዊ ጭቆና እና መደባዊ ብዝበዛ ሲደርስበት እንደነበር በማብራራት ትግሉ በቅድሚያ ከአማራ ብሄራዊ ጭቆና ነጻ መውጣት መሆኑን ይገለጻል። በሂደት እንደታየው ወያኔ ብሄራዊ ጭቆና ወይም ቀደም ብሎ በማኒፌስቶው ቅኝ መገዛት የሚለው ነገር በመሰረቱ ልዩነት የሌላቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ነው።
ቀጥሎ የምንመለከተው የቅኝ ተገዥነት ሆነ የብሄራዊ ጭቆና የወያኔ ትርክት ከአማራ ጋር ሂሳብ ማወራረጃ መነሻ ሆኖ ስለሚቀርብ የሂሳብ ማወራረዱ ስራ ማንን ባለእዳ አድርጎ እንደሚያርፈው ወደማሳየት ነው። ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ የተከተለውን ከቅኝ ገዥዎች ያልተለየ ጸረ አማራና ጸረ ኢትዮጵያ ድርጊቶቹን እያስታወሰን ወደዛው እንሻገር።
ኢትዮጵያ የአማኞች ሃገር ናት። ሁለቱም የሃገሪቱ ጥንታዊና ግዙፍ እምነቶች መነሻቸው ወያኔዎች “የኛ” ከሚሉት መሬትና “የኛ” ከሚሉት ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው። ክርስትናም ሆነ እስልምና በመላው ኢትዮጵያ ለመስፋፋት መነሻው አክሱም ነው። ይህን አይነት የእምነት ሃገራዊ የበላይነት በየትኛውም አለም በቅኝ የተገዙ ወይም በብሄራዊ ጭቆና ስር የወደቁ ህዝቦች ሲያከናውኑት ታይቶ አይታወቅም።
በትግራይ ምድር ወደምትገኘው አክሱም ጺዮን ሄዶ፣ ዘውድ ያልደፋ ንጉስ ወይም ንጉሰ ነገስት ሆኖ የማይታይበትን ለሺ አመታት የዘለቀ መንግስታዊ ስርአት የተከለ አካል ቅኝ ተገዢ ወይም ብሄራዊ ተጨቋኝ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ወያኔዎች ሊያስረዱን አይችሉም። ቀደም ብዬ በክፍል ሁለት የጠቀስኩትን ለሽህ አመታት የዘለቀውን በይኩኖ አምላክ የተጀመረው ሰሎሞናዊ ስርወ መንግስት የአክሱም ታሪክና ስልጣኔ ወራሽ ተደርጎ እንዲታይና ርእየተአለማዊ ቅቡልነት እንዲያገኝ የትግራይ ቀሳውስት የተጫወቱትን ወሳኝ ሚና እዚህ ላይ ጨምረን ስንመለከተው እኛ እንደ ወያኔዎች እንጥመም ብንል “መንፈሳዊ ቅኝ ገዥዎቹ ብሄራዊ ጭቆና ፈጻሚዎቹ” አማሮች ሳይሆኑ የወያኔ ቀደምቶች ነበሩ ማለት እንችላለን። ታሪክ ውስብስብ ነውና እኛ እንደዛ አንልም። ከወያኔ ትርክት ይልቅ ለእውነታው የሚቀርበው የኛ ሃቅ መሆኑ ግን ሊሰመርበት ይገባል። ይህን ጉዳይ አሳንሰን ማየት የለብንም። ለሽህ አመታት የዘለቀ የአንድን ሃገር መንፈሳዊና ርእዮተአለማዊ ህይወት የተቆጣጠሩ እሴቶችና እይታዎች ዋና ባለቤት ተሁኖ “ቅኝ ተገዛሁ፣ በብሄራዊ ጭቆና ስር ወደቅሁ” የሚል ይሉኝታ ቢስ ክርክር ቦታ የሌለው መሆኑ የሚያሳይ ነውና።
ወያኔዎች ይህን ስንላቸው ክርክራቸውን ቁሳዊ ወደ ሆነው አለም መመለሳቸው አይቀርም። ቀጥሎ አጠር ባለ መልኩ የምንፈትሸው ይህንን ነው። ወያኔዎች “እራሳችንን በራሳችን እንዳናስተዳድር ተደርገናል። ቋንቋችን ባህላችን እንዳያድግ ተደርጓል። በኢኮኖሚ ተበዝብዘናል ብሄራዊ ጭቆና የምንለው ይህን ነው” ይሉናል። ይህ የጭቆና ታሪክ በ2013ቱ የመስከረም ወር ሰነድ ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን።
በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን፣ የመጀመሪያው የወያኔ አመጽ በከሸፈበት ማግስት ራስ አበበ አረጋይ ለአጭር ጊዜ የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው ነበር። ራስ አበበ አረጋይ በወያኔዎች የዘር መነጽር ሲታዩ የተዋቂው ኦሮሞ የምኒሊክ የጦር መሪ የነበሩት የእውቁ የራስ ጎበና ዳጬ የልጅ ልጅ መሆናቸውን ማስታወሱ ተገቢ ነው።  ከዚህ ወቅት በስተቀር ትግራይ ከራሷ መኳንንቶች፣ መሳፍንቶች ወይም ንጉሶች ውጭ ከሌላ አካባቢ በመጡ የመንግስት ባለስልጣናት ተገዝታ ወይም ተዳድራ አታውቅም። በደርግ ጊዜ ሳይቀር የትግራይ አስተዳዳሪዎች የትግራይ ተወላጆች ወታደራዊ መኮንኖች ነበሩ። ከደርግ ውድቀት የመጨረሻዎቹ ጥቂት ወራት በስተቀር።
በጣም የጥንቱን ትተን፣  ከዘመነ መሳፍንት መግቢያ ጀምሮ ያለውን ዘመን ስንመለከት እንደ ራስ ሚካኤል ስሁል አይነቶች የትግራይ መሳፍንት እንዳሻቸው ጎንደር ላይ ማን እንደሚነግስና እንደማይነግስ ይወሰኑ እንደነበር ይታወቃል። ወያኔዎች ኢትዮጵያ የሚባል “ኢምፓየር አጼ ምኒሊክ በጉልበት ፈጠሩት” ከሚሉበትና ወሳኝ ከሆነው የታሪክ ወቅት ስንነሳ የምናገኘው ስእል ወያኔዎች ሊያሳምኑን ከሚሞክሩት በጣም የተለየ ነው።
አጼ ምኒሊክ ሆኑ አጼ  ሃይለስላሴ ልጆቻቸውን ለትግራይ መሳፍንትና መኳንንት እየዳሩ የትግራይን ሃገረ ገዥነት ከትግራይ ተወላጆች ውጭ እንዳይወጣ አድርገው በከፍተኛ ክብርና እንክብካቤ የያዙበት ሁኔታ እንጂ ትግራይን የሚያሳንስ ወይም የሚበድል ስራ ሲሰሩ ታይቶ አይታወቅም። ምኒሊክ ልጃቸውን ሸዋረጋን ለአጼ ዮሃንስ ልጅ፣ አጼ ሃይለስላሴም ልጃቸውን ልእልት ዘነበወርቅን  ለደጃዝማች ሃይለስላሴ ጉግሳ አርአያ ድረው እንደነበር ይታወቃል። የመጨረሻው የትግራይ ልኡል የራስ መንገሻ ስዩም ባለቤት የአጼ ሃይለስላሴ የልጅ ልጅ ልእልት አይዳ ደስታ እንደነበሩ ማስታወስ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ነገስታት የትግራይ መሳፍንት ግንኙነት በእኩዮችና በአቻዎች አመለካከት እንጂ በቅኝ ገዥና ተገዥ፣ በብሄራዊ ናቂና ተናቂ ዙሪያ የተገነባ እንዳልነበር ከዚህ በላይ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም። የነበረውን እውነታ በጥቅሉ ስናየው፣ በአስተዳደራዊ ተጽእኖ ፈጣሪነት፣ ትግራይ በህዝብ ብዛትም ይሁን በኢኮኖሚ ለሃገሪቱ ከምታዋጣው በላይ የፖለቲካ ተጽእኖ ፈጣሪ የነበረች መሆኗን ነው።
ይህን የሚያነቡ ወያኔዎች፣ “እኛ የምናወራው ስለመሳፍንቱና መኳንንቱ ግንኙነት አይደለም” እንደሚሉ እናውቃለን። ከነገስታቱ፣ ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ በታች ወዳለው የህብረተሰብ ክፍል ስንወርድም የምናገኘው ሃቅ የወያኔ  የጭቆና ትርክት ሃሰት መሆኑን ነው። የትግራይ ገበሬ በሌሎች የሃገሪቱ ግዛቶች እንደነበሩ ገበሬዎች ለማእከላዊ መንግስት እንዲገብር ወይም በጭሰኝነት እንዲወድቅ አልተደረገም። ገዥዎቹ በሙሉ የራሱ የትግራይ መሳፍንቶችና መኳንንቶች ነበሩ። የሚገብረውም ለነሱ ብቻ ነበር።  ለመሳፍንት የመገበር ስርአት ከሆነ ወያኔዎች የሚጠሉት  “ቅኝ ገዥ” የሚሉት የአማራ ህዝብ የቀረለት ጉዳይ አልነበረም። ድህነት፣ የአስተዳደር በደል፣ የፍትህ እጦት የትግራይ ህዝብ እንደ አማራ ህዝብ የዘመናት እጣው ነበር። ይህ የሰቆቃ ህይወት የሁለቱም ህዝቦች የጋራ እጣቸው እንጂ ወያኔዎች እንደሚሉት የተለየ የትግራይ ህዝብ እጣ ብቻ አልነበረም።
በ1981አም ወያኔ ከትግራይ ወጥቶ በአማራ ግዛት በስፋት መንቀሳቀስ ሲጀምር ታጋዮችን ያስገረማቸው ነገር የአማራ ህዝብ እንደ ትግራይ ህዝብ በድህነት የተቆራመተ፣ ከቋንቋ ልዩነት በስተቀር፣ በእምነቱ፣ በባህሉ፣ በአኗኗሩ፣ በአስተራረሱ በሁለመናው ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ እንደሆነ በመገረም ተናግረዋል። እንዳውም በጆሮዬ የሰማሁት የዛን ዘመን የወያኔ ታጋዮች ትዝብት የአማራ ህዝብ ከትግራይ በከፋ ሁኔታ የሚኖር ሆኖ እንዳገኙት ነበር። ለዚህ የሰጡት ምሳሌ የትግራይ ገበሬ በድህነት የተቆራመተ ቢሆንም ለእግሩ መጫሚያ የነበረው ሲሆን የአማራ ገበሬ ግን በባዶ እግሩ የሚሄድ እንደሆነ ነበር። (የጫማ ጉዳይ ጣሊያኖች በኤርትራ ካስፋፉት ባህል ወደ ትግራይ የዘለቀ መሆኑ ይታወቃል።) እነዚህ የወያኔ ታጋዮች በወያኔ ፕሮፓጋንዳ የተነገራቸው ጠላታቸው አማራና በመሬት ላይ ያገኙት አማራ አንድ እንዳልሆነ በወቅቱ  በአደባባይ ሲናገሩ ስምተናቸዋል።
እንግዲህ አንድ በወያኔዎች እጅ የቀረ ጉዳይ የቋንቋ ጉዳይ ነው። በቋንቋ ቢሆንም አማርኛና ትግርኛ አንድ አይነት ፊደል የሚጠቀሙ፣ ከአንድ ግንድ የተመዘዙ ናቸው። የአማርኛ ቋንቋ ሃገራዊ ቋንቋ በመሆን የበላይነት ማግኘት የጀመረበት ዘመን ሩቅ ሲሆን ሂደቱም ከሴራ ጋር የተያያዘ አልነበረም። እንኳን ከሰማኒያ በላይ ቋንቋዎች በሚነገሩባት የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ቀርቶ፤ ኢትዮጵያ ቁጥራቸው አናሳ የነበሩ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በነበሩበት ወቅት ሳይቀር ሃገራዊ የስራ ቋንቋ ሳይኖር እንደ ሃገር መቆም አትችልም ነበር። ስልጣን ለመያዝ እድል ያገኙ እንደነ አጼ ዮሃንስ አይነቶቹ ሳይቀሩ ይህን ሃቅ በመረዳታቸው ነው፣ አማርኛን የስራ ቋንቋቸው አድረገው የቀጠሉት።
አማርኛ ኦፊሴሊያዊ ሃገራዊ ቋንቋ በመሆን ተጽእኖ ካደረገባቸው ሌሎች የሃገራችን ቋንቋዎች ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ተጽእኖ ያረፈበት ቋንቋ ትግርኛ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህም ወያኔዎች የፈጠሩት የሃሰት ትርክት ሲከሽፍባቸው የመጨረሻ መንጠልጠያ ሊያደርጉት የሚሞክሩት የቋንቋ ጉዳይም የትም አያደርሳቸውም። ወያኔዎች “ቅኝ ገዥ፣ ደመኛ የትግራይ ጠላት” እያሉ ሂሳብ በማወራረድ ስሌት ዘር ማንዘሩ እንዲጠፋ እኩይ ድግስ የሚደግሱለት፣ በዘሩ ተለይቶ በየቦታው እንዲታረድ ጠላት የሚያደራጁለት፣ የሚያስታጥቁለት፣ መልካም ስብእናውን ስሙን የሚያራክሱት አማራ የሚባል ህዝብ እውን ወያኔዎች እንደሚስሉት የትግራይ ህዝብ ስትራተጂያዊ ጠላት ነውን?
በሚቀጥለው ክፍል ከሁሉ አስከፊ ወደሆነው የወያኔ ዘመን ጠጋ ብለን የሂሳብ ማወራረዱን ስራ እንቀጥላለን። ይህ ዘመን ከሌሎቹ ሁሉ የከፋ፣ ብዙዎቻችን በወሬ ወይም በታሪክ የምናውቀው ብቻ ሳይሆን የኖርንበት ዘመን ነው። በቸር እንገናኝ።
Filed in: Amharic