>
5:21 pm - Sunday July 20, 7823

ስለ ወረርሽኙ ጥቂት ትዝብት  (ከይኄይስ እውነቱ)

ስለ ወረርሽኙ ጥቂት ትዝብት 

ከይኄይስ እውነቱ


አሁን ባለው ትውልድ የተለመደ ሰላምታ ‹ሰላም ነው?› የሚል ነው፡፡ በቀን ውስጥ ይህንን ሰላምታ እስኪሰለቸን እንሰማለን፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን የማይባልበት መንቻካ ሰላምታ፡፡ ለዚህ ሰላምታ መልሱ ያለጥርጥር ሰላም አይደለም ነው፡፡ አገራችንና ሕዝቧ ሰላም ከራቃቸው ግማሽ ምእት ዓመት አለፈ እኮ፡፡ አንዳንድ ሰው እኔ የግልህን ሰላም ነው የጠየቅኹ ይለኛል፡፡ ጎበዝ! አገር ታውኮ÷ ወገኔ በአገዛዝ ሠራሽ ቀጠና እያለቀ እኔ በግሌ እንዴት ሰላም ይኖረኛል? ልዑል አምላክ ለልማትም ሆነ ለጥፋት (ምርጫውና ነፃነቱ የግላችን ነውና) በሕይወት ስላቈየን እንዴት አደርሽ/አደርህ፤ እንዴት ዋልሽ/ዋልሀ፤ እንዴት አመሸሽ/አመሸህ፤ እንዴት ሰነበትሽ/ሰነበትህ፤ እንዴት ከረምሽ/ከረምህ ወዘተ. መባባሉ በስንት ጣዕሙ፡፡ ለማንኛውም ወገኖቼ እንደምን ሰነበታችሁ ለማለት ፈልጌ ነው የሰላምታን ነገር ያነሳሁት፡፡ 

ርእሰ ጉዳዬ ኮቪድ-19 ስለሚባለውና በዓለም ናኝቶ የሚሊዮኖችን ሕይወት እየቀጠፈ ስላለው ወረርሽኝ ነው፡፡ በርግጥ ከዚህ ወረርሽኝ የከፋ መአት በአገራችን መኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አምላክም ይህንን ችግርግር ያለ ችግራችንን (መንግሥት አልባ መሆናችንን) ተመልክቶ ይመስለኛል (የአገዛዙን እና የጀማውን ግዴለሽነት ሳይመለከት) በአንፃራዊነት ኮቪድ-19 የታሰበውን ያህል/ዐውቃለሁ ባዮች ያሟረቱብንን ያህል ጉዳት ያላደረሰብን፡፡ ያም ሆኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ የወረርሽኙ ሥርጭት እየጨመረ በመሆኑ ጥንቃቄው የወገኖቻችን ሞት ሲያስደነግጠን ብቻ ሳይሆን በመደበኛነት ሊቀጥል ይገባዋል፡፡

ሕዝባችንና አገራችን በሁለት የከፉ አፅራረ-ኢትዮጵያ ‹አጋንንት› (ሽብርተኛው ወያኔ እና ኦነጋዊው ብልግና) የስንግ ተይዘው ግቢ ነፍስ ውጪ ነፍስ ላይ እንደሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ የግፍ ጽዋው /ቁናው ሞልቶ እየፈሰሰ በመሆኑ ማንም ሐሳዊ ስለሚናገረው ትንቢት ሳይሆን ከፈጣሪ ባሕርይ በመነሣት ኰናኔ በጽድቅ ፈታሔ በርትዕ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ ፍርዱን የሚሰጥበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ታዲያ በጎውን ጊዜ ለማየት የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እላይ ከጠቀስኋቸው አፅራረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ባለመተባበር ብቻ ሳይሆን በሚችለውም መንገድ በመፋለም እና ከወረርሽኙም በመጠበቅ ረሱን ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡ 

ብዙ ወገኖች ከወረርሽኙ ራሳቸውን ጠብቀው ወገናቸውንም እንዲታደጉ  ሲነገራቸው የእምነትን ነገር ያነሣሉ፡፡ እምነት ጥሩ ነው፤ ያድናል፡፡ በተለይም የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል (ጥርጥር የሌለቤት ሙሉ እምነት) እምነት ካለ፡፡ ግን በእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ/ትድግና ውስጥ የሰው ልጆች ድርሻ እንዳላቸው አለመዘንጋት ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፡፡ 

ኃላፊነት የጎደለውና ለሕዝብ ግድየለሽ አገዛዝ መኖር ከዐቅም ውሱንነት ጋር ተደምሮ ከፈጣሪ በታች ይህንን ያደርግልኛል የምንለው ተቋም ባለመኖሩ እያንዳንዱ ዜጋ ከአምላክ ቸርነት ጋር ራሱንና ወገኑን ከወረርሽኙ የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነትና ግዴታ ለመወጣት ከእኛ ከዜጎች የሚጠበቀው ብዙ አይደለም፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚነግሩን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ/ማስክ ማድረግ፣ እጃችንን ደጋግመን በሳሙና መታጠብና በተቻለ መጠን ርቀታችንን መጠበቅ ነው፡፡ የእምነት አንዱ መገለጫው አብዛኛውን ለሚጠቅም በጎ ሥነ-ሥርዓት ተገዢ መሆን ነው፡፡ ቢያንስ በመጠኑ በማውቀው በክርስትና ሃይማኖት የምናመልከው አምላክ የሥርዓት አምላክ ነው፡፡ ክርስቲያን ደግሞ የወገኑ ደኅንነት ያሳስበዋል ያስጨንቀዋል፡፡ እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይበቅል አይልም፡፡ 

በመሆኑም በሕዝብ ግብር የሚተዳደሩ የሚመለከታቸው ተቋማት በዚህ ረገድ ያለባቸውን ኃላፊነትና ግዴታ (ሕግ ከማውጣት ባለፈ) የሚወጡ ከሆነ እግረ መንገዳችንን እያሳሰብን፣ ወገን ለወገን ቢተሳሰብ ግን መልካም ይመስለኛል፡፡ በተለይም በሕዝብ ማጓጓዣዎች (ታክሲ፣ አውቶቡስ፣ ሎንቺና፣ ባቡር) አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ማንኛውም ተጓዥ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ/ማስክ ሳያደርግ አገልግሎት እንዳያገኝ በማድረግ ረገድ በትጋት ሊሠሩ ይገባል፡፡ በነዚህ መጓጓዣዎች ስንጠቀም የታዘብኹት ጉዳይ በእጅጉ የሚያስደነግጥና የሚያሳስብ ነው፡፡ ያዝ ለቀቁ በሕይወት እንደሚያስከፍል መዘንጋት የለበትም፡፡ ባንፃሩም ወረርሽኙ የለም የሚለው የአንዳንድ ገልቱዎች ንግግር ድንቁርና ከሚባል በቀር ሌላ መገለጫ አላገኘሁለትም፡፡ 

ሌላው ከፍተኛ የሆነ ንዝህላልነት የሚታይባቸው ባህላዊ የገበያ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ሥፍራዎች ቅርርቡ የሚያስከትለው አደጋ እንደተጠበቀ ሆነ በአብዛኛው አገልጋዩም ሆነ ተገልጋዩ ማስክ አያደርጉም፡፡ መልእክቱ ሲነገራቸው በሁለቱም ወገኖች ለስድብና ዝልፊያ የሚጋበዙት ቊጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ በተለይም ወጣቶች፡፡ ወረርሽኙ አይደርስብንም የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ፡፡ እናስተውል በስድብና በዘለፋ ‹ሰው› መሆን አይቻልም፡፡ 

በመናገሻ ከተማችን ሌላ ያየሁት የሚያስገርምና ፈገግ የሚያሰኝ ትዝብት ደግሞ አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ወገኖች ሰላምታ ሲያቀርቡላቸው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛቸውን እንደ ባርኔጣ ማውለቃቸው ነው፡፡ እንደታዘብኹት ብዙዎቹ አዛውንት እና አንዳንድ ጎልማሶች ማስኩን የሚጠቀሙበት ለአፋቸው መሸፈኛ ብቻ ነው፡፡ ይህም ማስክ ያደረጉበትን ዓላማ ከንቱ ያደርገዋል፡፡ የማስኩ ጥቅም ከሌሎች ሰዎች (ማስክ ካደረጉም ሆነ ካላደረጉ) የሚወጣውን ትንፋሽ እና ምራቅ በተወሰነ ደረጃ በመከላከል ከቫይረሱ ለመጠበቅ እንደሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ያስተምራሉ፤ እነዚህ ወገኖች ግን በአፍንጫቸው እየተቀበሉ መሆኑን ያስተዋሉት አይመስልም፡፡ በርግጥ ማስኩ ምቾት የሚነሳ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ንጽጽሩ ደግሞ ሕይወትን ከማትረፍ ጋር በመሆኑ ለዛ የሚከፈል ‹መሥዋዕትነት› አድርጎ መውሰድ ተገቢ ይሆናል፡፡ በአንዳንድ መ/ቤቶችና የግል ድርጅቶች (አገልግሎት የሚሰጡ ጭምር) የታዘብኹት ደግሞ ቢሮአቸውን እንደ ቤታቸው በመቊጠር ማስካቸውን አውልቀው ሲንቀሳቀሱ መመልከቱ ምን ያህል ግዴለሽነት የነገሠበትና ለዲስፕሊን ተገዢ ያልሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ እንዳለን ለመረዳት አይከብድም፡፡ የሚገርማችሁ በአንዳንዱ መ/ቤት የኮቪድ-19 መከላከል ኮሚቴ የሚባል ወይም ተመሳሳይ ስም ያለው አካል እንዳለ ይነገራል፡፡ ከ70ዎቹ ጀምሮ የያዘን ውጤት አልባ የኮሚቴ አባዜ አሁንም አልለቀቀንም፡፡

በአጠቃላይ አብዛኛው የኅብረተሰባችን ክፍል ስለ ወረርሽኙ ያለው የተዛባ አስተሳሰብ ክፉውን ዘመን ተሻግሮ ለበጎው መብቃት የሚያስችል አይመስልም፡፡ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የእምነት እና ባህላዊ እሤቶቻችን በከፍተኛ ሁናቴ በመሸርሸራቸው አማኝ ነኝ የሚለውም ሆነ እምነት የሌለው ወገን ከፍተኛ የግብረገብነት ውድቀት እና የሥነምግባር ብልሹነት ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም የበጎነት እርሾው ጨርሶ አልጠፋምና ለራስ፣ ለቤተሰብና በአጠቃላይ ለወገናችን ስንል የሚገባንን ጥንቃቄ እናድርግ የሚል ወንድማዊ ምክሬን እለግሳለሁ፡፡

አምላከ ኢትዮጵያ ከአፅራረ-ኢትዮጵያም ሆነ ከወረርሽኙ ሕዝባችንን በምሕረቱ ይታደግልን፡፡

Filed in: Amharic