ቤቴልሔም-ወልደየስ
የቀድሞው የ ኢትዮጵያ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ-ወልድ ለደርግ የምርመራ ኮሚሽን ‘ዓለም በቃኝ’ እስር ቤት ሆነው ያዘጋጁትን “የታሪክ ማስተወሻ” ላኩ። በመስከረም ወር 1986 ዓ/ም በጦብያ መጽሔት ላይ የወጣው ይኼው የታሪክ ማስታወሻ ለሕይወት ታሪካቸው ዋቢ ምንጭ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሀብተወልድን በአጭሩ :- የአፍሪካ ህብረት ባለውለታ
“የደረሰው ይድረስ ደካማ ሆኜ መታየት አልፈልግም የሀገሬን ጥቅምና መብት የሚነካ መስሎ ከታየኝ መናገሬን አልተውም” የአፍሪካ ህብረት ባለውለታ ጸሃፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፡፡ አክሊሉ ሀብተወልድ ገና በ 19 ዓመቱ ጀምሮ በተማሪነቱ ለሀገሩ ይሟገት ነበር፡፡
መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ/ም ሸዋ ቡልጋ የተወለደው አክሊሉ የአብነት ትምህርት እና አማርኛ ቋንቋን በቤተክርስቲያን አጥንቷል፡፡ ከግብፅ እስክንድሪያ እስከ ፓሪስ ህግ ና ፓለቲካን በጥሩ ሁኔታ ተምሮ አጠናቋል፡፡
በ 1920 ዎቹ ጀምራ ጣሊያን ኢትዮጲያን ለመውረር የምታደርገውን ጥድፍያ ለመመከት ከተማሪነቱ ጀምሮ ለሀገሩ ነፃነት ገና በወጣትነቱ ብዙ ደክሟል፡፡
በ 1928 ዓ/ም ጣሊያን የአድዋን ውርደቷን ለመመለስ ዓይኗን በጨው ታጥባ ለቅኝ ግዛት ከሰሜን ወደ መሃል ኢትዮጲያ ዘለቀች፡፡
ያኔ አክሊሉ ሀብተወልድ በወቅቱ የዓለም ልዕለ ሀያል የነበረችው ፈረንሳይ እንድታሸማግል ብዙ ጥረዋል፡፡ በጀኔባም የኢትዮጵያ ድምፅ ሆነው የጣሊያንን ሴራ አጋልጠዋል፡፡
ጽሃፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ፣ የፈረንሳይን ወዳጆች እንግሊዝን እና አሜሪካን ከጣሊያን በተቃራኒ እንዲቆሙ የዲፕሎማሲ ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡
በ1933 የነ ፅሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ድምፅ ተሰምቶ እንግሊዝ ጦሯን በጣሊያን ላይ ሰበቀች፡፡ አርበኞች ከእንግሊዞች ጋር ሆነውም ጣሊያን በመጣችበት መንገድ አንገቷን ደፍታ እንድትመለስ አደረጉ፡፡፡
ከነፃነት በኋላም ኤርትራን ለማዋሃድ ፅሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ብዙ ወጥተዋል፡፡ በመጨረሻም ተሳክቶላቸው፣በ 1942 ዓ/ም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ለመዋሃድ ይሁንታዋን ቸረች፡፡ ጉዳዮ ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነትም አገኘ፡፡
በ 1953 ዓ/ም በነ ጀኔራል መንግስቱ ንዋይ በተመራው መፈንቀለ መንግሥት ራስ አበበ አረጋይን ጨምሮ ሌሎች ሹማምንቶች ተረሸኑ፡፡ ጸሀፌ ትዕዛዝ አክሊሉ በተረሸኑ ሚኒስትሮች የሚሾም ሲፈለግ ለአክሊሉ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት በጃንሆይ ተቸራቸው፡፡
አክሊሉ ሀብተወልድ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እንዲመሰረት ትልቁን ሀላፊነት ከኢትዮጵያ ተቀብለው የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡
በተለይ የህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን የህብረቱን ህንጻ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስገንብተው ለአገልግሎት እንዲውል ያደረጉ ባለውለታ ናቸው፡፡
ትልቁን የማማከር ስራም በመስራት ህብረቱ እንዲጠነክር የማይዘነጋ ስራ ሰርተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ እስከ አብዮቱ አጋማሽ 1966 ዓ/ም ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
መስከረም 2 ቀን 1967 ጃንሆይን ጨምሮ ፣ ሌሎች ሹማምንቶችም ወደ ወህኒ ሲወርዱ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉም አብረው ወደ እስር ተወረወሩ፡፡
እራሳቸው ፅፈውት የአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ ያሳተመላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ማስታወሻ እንደሚያትተው ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ የኤርትራ ጉዳይ መስመር እንዲይዝ እና በሌሎች የሀገር ጉዳዮች ላይ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ታይቶ ይቅርታ እንዲደረግላቸው እና ለሀገራቸው ተጨማሪ ነገር እንዲሰሩ ጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ደርግ አልራራም፡፡
ይቅርታውን አልተቀበለም፡፡ የኋላ ኋላ እንደሚገደሉ ሲያውቁ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ለደርግ ሹመኞች ይሄን ተናገሩ
“እኛን በመግደል ኢትዮጵያን ከድህነቷ የምታወጧት ከሆነ ድርጊታችሁን እንደ ታላቅ በረከት በፀጋ እንቀበላለን።”
ህዳር 14 ቀን1967 ዓ/ም አክሊሉ ሀብተወልድን ጨምሮ ደርግ ብሎ እራሱን ያደራጀው ቡድን 60ዎቹ እየተባሉ በታሪክ ከሚታወቁት “የጃንሆይ” ሹማምንቶች ጋር ያለምንም ፍርድ በግፍ ተረሸኑ፡፡
አክሊሉ ሀብተወልድ በተማሪነታቸው ጀምሮ ለሀገራቸው እንደኖሩ፣ በ 63 ዓመታቸው በጥይት እስከ ዓላማቸው ተገደሉ፡፡