>

ከሊቢያ ውደቀት የምናገኘው ትምህርት መማር ከቻልን?... ( ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ከሊቢያ ውደቀት የምናገኘው ትምህርት መማር ከቻልን

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


ከአስር አመት በፊት ማለትም የአረቡ የጸደይ አብዮት በተጋጋመበት ጊዜ ይህቺ በሰሜናዊው የአፍሪካ ክፍል ጫፍ የምትገኘው ሊቢያ በሰሜኑ የጦር ቃለኪዳን ሀገሮች ጥምረት የጦር አይሮፕላኖች በሚያዘንቡት ቦምብ ክፉኛ መደብደቧ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ለሲቪሉ ማህበረሰብ ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ እንዲያስችል በሚል ሰበብ የአለሙ ጸጥታው ምክር ቤት በሊቢያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እውን እንዲሆን መፍቀዱን የታወቁ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ይህ ውሳኔ ለማማን የሚያዳግት፣ገና ያልተነገሩ የህይወት መቀጠፍና የንብረት ውድመትን አስከትሎ አልፏል፡፡ የብይነ መንግስታቱ የጸጥታ ምክር ቤት ወደ ሊቢያ ምድር ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊነት የሰጠው ውሳኔ፣ የሰብዓዊ እርዳታ በቅጡ ለማቅረብ እንዲያስችል ነው የሚል ምክንያት በግዜው ቢያቀርብም እውነታው ለየቅል እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የሚደስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡እውነትን ለመደበቅ ካልፈለግን በቀር፣ እውነታው ጠንካራውን ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ(Muammar Gaddafi) ለመግደል ያለመና ሊቢያን የተዳከመች ሀገር ለማድረግ ነበር አላማው፡፡ ከሰሜኑ የጦር ቃልኪዳን አባል ሀገራት (NATO nations) መሃከል ፈረንሳይ እና የተባበረችው አሜሪካ ሊቢያን ከማዳከም አኳያ ዋነኛ ተዋናዮች ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ በሊቢያ ምድር ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እውን የሆነው የቆየውን የምእራቡን አለም ፣ በተለይም የተባበረችውን አሜሪካ ፕሮጄክት ማለትም የአገዛዞችን ለውጥ ገቢራዊ ለማድረግ የታለመ ነበር፡፡ ይህ በአንድ ሀገር ላይ ጣልቃ በመግባት የአገዛዝ ለውጥ ማድረግ ዛሬም ምእራባውያን የሚጫወጡበት ካርድ ነው፡፡

   በርግጠኝነት ለመናገር ጋዳፊ መልአክ አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ጋዳፊ የአፍሪካ ጠላት አልነበረም፡፡ የቀድሞው አምባገነን ፕሬዜዴንት ጋዳፊ ለአፍሪካ አንድነት የቆመ ነበር፡፡ ፕሬዜዴንቱ በምእራባውያን ጥርስ ውስጥ ገብቶ የነበረው የአፍሪካን አንድነትና ህብረት የበለጠ ለማጠናከር በመነሳቱ እንደሆነ የሚከራከሩ አፍሪካዊ የፖለቲካ ጸሃፊዎች ይከራከራሉ፡፡ ለሊቢያ ዴሞክራሲ ያስፈልጋታል፤ሊቢያ የሰብዓዊና የህግ የበላይነት የተከበረባት ሀገር መሆን አለባት የሚሉ ሀይሎች ወይም ሀገራት በሊቢያ ምድር አልታዩም፡፡ ምናልባት እነኚህ የውጭ ሀይሎች የታዩት የነዳጅ ጉድጓድ በሚገኙበት የሊቢያ ክፍሎች ታይተው ይሆናል፡፡ በዛች ሀገር ላይ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ በቃል በብዙ የሚደሰኩሩት ምእራባውያን ከጀርባ በብዙ ተሸክመው የመጡት ድብቅ አጀንዳ ነበራቸው፡፡ ለሊቢያ ህዝብ ነጻነትን ሊያጎናጽፉት አልተቻላቸውም ነበር፡፡ ለአብነት ያህል ፈረንሳይ በሳህል የአፍሪካ ክፍል የራሷ የቆየ ድብቅ አጀንዳ ያላት ሀገር ናት፡፡ የፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት የምእራብ አፍሪካ ሀገራት የሚጠቀሙበት የጋራ ገንዘብ የፈረንሳይ ፍራንክ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ገንዘባቸው የሚታተመው በፈረንሳይ ሲሆን የብድር ገንዘብ የሚመቻችላቸው በዋነኝነት በፈረንሳይ በኩል ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የፈረንሳይ የኑክሌር ማብላያዎች የኤሌክትሪክ ፍጆታን ለሟሟላት የሚረዳውን የዩራኒየም ንጥረ ነገር የምትገዛው ከሚጀር ሲሆን፣ በወርቅ አምራችነታቸው ከሚታወቁት ቡርኪናፋሶ፣ማሊ፣ኮትዲቯር እና ጊኒ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላት፡፡ እንደ የምእራቡ የአፍሪካ ክፍል ሁሉ በሊቢያ ያለውን ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ለመቀራመት ካላት ፍላጎት ይልቅ የምእራብ አፍሪካ ሀገራት ወደ የበለጠ አንድነት እንዲመጡ ስለማትፈልግ ነበር ሊቢያን ለማዳከም ቆርጣ የተነሳቸው፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ያላችው የተባበረችው አሜሪካ በአሜሪካ የአፍሪካ ወታደራዊ ጥምረት ስም(under the aegis US Africa Command)) በአፍሪካ ምድር ያልተቋረጠ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ማድረግ የዘመናት ፍላጎቷና ስትራቴጂክ አቅዷ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ለመቆጣጠር ሁነኛ መንገድ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን የደረሱበት ሀቅ ነው፡፡ ከምእራባውያን የፕሮፓጋንዳ ማሺነሪዎቻቸው ባሻግር የምእራባውያን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በአፍሪካ ምድር ያሉና የነበሩ ግጭቶችን ነዳጅ አርከፈከፉባቸው እንጂ አላበረዱትም፡፡ በአፍሪካ ምድር የምእራባውያን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሰላምን ማምጣት አልተቻለውም፡፡ ለአብነት ያህል የምእራብ አውሮፓን ያህል የቆዳ ስፋት ባላት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ምድር ላይ ሰላም ማምጣት አልቻሉም፡፡ በማሊ ለብዙ ግዜ ወታሮቿን አዝምታ የነበረችው ፈረንሳይ ሰላም ማምጣት ተስኗት ወታደሮቿን ይዛ ጥርግ ብላለች፡፡

    ያቺ በነዳጅ ዘይት የበለጸገችውና ሀብታም ነበረችው ሊቢያ ዛሬ  ወደ ሁለት ክፍልፋዮች ተከፍላ ምእራብ እና ምስራቅ ሊቢያ ተብላ ሁለት የወቀዱ ሀገሮች( ወይም አለም አቀፍ ህጋዊ እውቅና የሌላቸው) ለመሆን በቅታለች ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ነገዶችና የጦር አበጋዞች የነዳጅ ጉድጓዶችን ለመቆጣጠር ሲሉ የርስበርስ ጦርነት ከገጠሙ አመታቶች ነጎዱ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እውነተኛ አሸናፊው ማን እንደሆነ  አልታወቀም፡፡ የርስበርስ ጦርነት መጨረሻው እልቂት እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ የለውም፡፡ ዛሬ በሊቢያ ምድር ፍንትው ብሎ የሚታየው እውነት አለመረጋጋት፣የሰላም እጦት፣ችግርና የህይወት ዋስትና ማጣት ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በሊቢያ ምድር ያለው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ዳፋው ለሳህል ሀገራትም ጭምር እየተረፈ ይገኛል፡፡ የሊቢያ ህዝብ ወደ ሰላም፣አንድነትና ህብረት የሚመጣበትን መንገድ ለማግኘት ሁነኛ እቅድ ማውጣት ካልተቻለ የዚች ሀገር እጣ ፈንታ ከድጡ ወደ ማጡ የማይሄድበት ምንም ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አብዛኛው የአፍሪካ ሀገሮች በተለይም ኢትዮጵያ ሀገራችን ሊቢያ ከደረሰባት መከራ ፣ችግር፣የርስበርስ ጦርነት እና ውደቀት መማር ይገባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ከሊቢያ የሚከተለውን መገንዘብ፣መረዳት እንችላለን፡፡

 • አንደኛውና ዋነኛው የይስሞላ ዴሞክራሲ አንድን ሀገር ሊያፈራርስ፣ሰላሟን ሊያሳጣት ይችላል የሚለው ነው፡፡
 • ዴሞክራሲ ወደ የምንፈልገው ግብ ወይም አላማ የሚወስደን እንጂ ፣ ዴሞክራሲ ራሱ የመጨረሻ ግባችን አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ( መንግስታትም ሆኑ) ተራው እንደ እኔ ያለው ዜጋ ዴሞክራሲ የመጨረሻው ግብ እንዳልሆነ መረዳት ይገባዋል፡፡ ሊቢያ በዲሞክራሲ ስም እንዳልነበረች ሆናለች፡፡
 • የዲሞክራሲ ውጤት ሁልግዜ ለዘለአለም ይሰራል ብሎ መገመት ወይም ትክክል ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ አያድርገውና ለአብነት ያህል አብዛኛው ዜጋ ሰው መግደል ወይም የግድያ ወንጀል መፈጸም ትክክል ነው የሚል ድምጽ ሰጠ ቢባል፡፡ ይህ ሁል ግዜ ትክክል ላይሆን የሚችል ነው፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲን ገቢራዊ ከማድረጋችን በፊት አላማውን በግልጽ ማስቀመጥ ይገባናል፡፡ ይህ በሰለጠነው አለም የሚታይ ቁም ነገር ነው፡፡ ግልጽ አላማ ሳይኖረን ዴሞክራሲን ገቢራዊ ለማድረግ መሞከር መጨረሻው በግጭት ላይ ነዳጅ እንደማርከፍከፍ ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲን በእውር ድንብር፣በጭፍን የችግሮቻችን ሁሉ መድሃት አድርጎ መቀበል ( ማለትም ዴሞክራሲ የብዙሃን አሸናፊነት ፣ የጥቂቶች መብት የተጠበቀበት የሚለውን ትተን ዴሞክራሲን እንደ መመሪያ ብቻ መቀበል ) አፍሪካን ለውድቀት ይዳርጋታል፡፡ ይህ አሁን ሊቢያ ካለችበት ውድቀት የምንማረው ቁምነገር ነው፡፡

ሌላው የዴሞክራሲ ሂደት በአንዲት ሀገር ከወደቀ እና ሀገርን ለማዳን ከተፈለገ በዲሞክራሲ ስም የሚነግዱ አምባገነን መሪዎችን በሌሎች ተራማጅ መሪዎች በሰለጠነ መንገድ መቀየር ይሆናል፡፡ ፊታቸውን ዲሞክራት አስመስለው ዋነኛ ባህሪያቸው አምበገነን የሆኑ መሪዎች ለሀገር ህልውና አይበጁም፡፡ በዚህ አግባብ ዴሞክራሲ ማለት የአብዝሃው ህዝብ ድምጽ ያገኘ መሪ ማለት ይሆናል፡፡ የውሸት ዴሞክራሲ፣የውሸት የምርጫ ውድድርን፣የውሸት ተሳትፎን፣የውሸት ፍትህን ወዘተ ወዘተ  ይፈጥራል፡፡ ስለሆነም የሐገር ክሽፈት ይቃረባል፡፡ ህይወትም አጭር ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ውድቀት መማር፣ማጥናት አለባት፡፡ በተለይም ከሊቢያ ውድቀት በፍጥነት መማር አለባት፡፡ ኢትዮጵያ እውነተኛ የዲሞክራሲ መንገድን አጥብቃ መያዝ ይገባታል፡፡ ወደ ፍትህ፣እኩልነት እና ነጻነት የሚወስደንን ዴሞክራሲ ገቢራዊ ማድረግ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ከቅርብ ግዜው የአለም ታሪክ ውስጥ አንድ ጥሩ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ይሄውም የሚከተለው ነው፡፡

የናዚ ጀርመንና ሂትለር የተመረጡት በዲሞክራቲክ አግባብ ነበር፡፡ እውን ናዚ ጀርመኖችና ሂተለር የሰሩት ሁሉ ፍታሃዊ ነበር ማለት እንችል ይሆን ? አይመስለኝም፡፡

የዲሞክራቲክ መርህን በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን ህይወታችን አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡

የሞአመር ጋዳፊ ሞት እና በሊቢያ ምድር ያለው የዛሬው እውነት በወፍ በረር ሲቃኝ

ባሳለፍነው ክረምት ነሀሴ ወር 2013 ዓ.ም. የሊቢያ ማእከላዊ ባክ ገዢ የሆኑት ሚስተር ሳዲቅ አል-ካቢር ለዜና ምንጮች በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ከሆነ በሊቢያ ምድር ያለው እውነት የሚከተለውን ይመስላል

-የጸጥታ ችግሮች ስር ሰደዋል

– የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም የፖለቲካ ቀውስ እውን መሆን

– ሊቢያ በውጭ ሀገር ብድር መዘፈቋ(  የሊቢያ ብድር ከአጠቃላይ የምርጥ መጠኗ 270 ፐርሰንት ይሆናል)

– የነዳጅ ዘይት ሽያጭ እንዳይኖር መሰናክሉ ብዙ ነው

– በሊቢያ ምድር ሙስና ቤቱን ሰርቷል

– ከነዳጅ ዘይት ሀብቷ ታገኝ የነበረው ግብር አፈር ድሜ በልቷል፡፡ ለአብነት ያህል  እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 ከነዳጅ ዘይት ሀብቷ ሽያጭ አግኝታ የነበረው የግብር ገቢ 53 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የነበረው ዘንድሮ ( እ.ኤ.አ. 2021 ላይ ማለታቸው ነው) ምንም ከሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል

– በአጠቃላይ የከፋ የኢኮኖሚክ ድቀት በሊቢያ ምድር በገቢርም በነቢብም የሚታይ መራር እውነት ነው፡፡

እውን ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ ከተገደሉ በኋላ ሊቢያ ወደ ታለመላት ዲሞክራቲክ ሂደት ገብታ ይሆን ? አይመስለኝም፡፡ ፕሬዜዴንት ሙአመር የተገደሉት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 18 2011 ሲሆን ፣ ሚስተር ጋዳፊ በሞት ከስልጣናቸው ከወደቁ ካለፉት 10 አመታት ወዲህ ሀገሪቱ ወደ ለየለት መስቅልቅል ገባች እንጂ እንደታሰበው በእድገት ጎዳና መራመድ አልቻለችም፡፡ ምንአልባት የጋዳፊ አገዛዝ ተገርስሶ መውደቅ የሚከተሉት ሁነቶች እውን እንዲሆኑ አድርጎ ሊሆን ይቻለዋል፡፡ እነርሱም፡-

 1. በውጪ ሀገራት በተለይም በምእራቡ አለም የሚረዱት አዳዲሶቹ የሀይል ቡድኖች መጠነ ሰፊ ገንዘብ አከማችተዋል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም የወደቀው የቀድሞው የሊቢያ አገዛዝ የሄደበትን መንገድ ለመድገም እየተንቀሳቀሱ የሚገኙበት መራር ሀቅ እየታየ፣እየተዳሰሰ ይገኛል፡፡
 2. የተለያዩ ነጻና በራሳቸው የሚሊሻ ሀይሎች የሚተማመኑ የጦር አበጋዞች እንደ አሽን መፈልፈል ዛሬዬቱ ሊቢያ አሳዛኝ ገጽታ ሆኖ ይሰተዋላል፡፡
 3. ከዚህ ባሻግር ወንድማማች የነበሩት ሊቢያውያን ጎራ ለይተው ርስበርሳቸው ማለቂያው መቼ እንደሆነ በማይታወቅ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀው ሀገሪቱን የደም አባላ አልበሰዋታል፡፡
 4. የሀገሪቱ ወንድማማቾች ርስበርስ በጠላትነት ተፈራርጀዋል፡፡
 5. ካለፈው በጋ 2014 ( እ.ኤ.አ ) ወዲህ ደግሞ ሀገሪቱ በሁለት ወታደራዊና በሁለት ፖለቲካዊ ክፍሎች ተከፍላ ትገኛለች፡፡ የአንደኛው ጉልበተኛ ካምፕ መቀመጫ የቀድሞዋ ሊቢያ ርእሰ መዲና የነበረችው ትሪፖሊ ስትሆን፣ የሌላኛው ጉልበተኛ ቡድን መቀመጫ ደግሞ ቱብሩክ (Tobruk) በምትባል ከተማ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ግርግር እና ግጭት ምክንያት፣ በአንድነት መላላት ምክንያት የሊቢያ እድገት ተገቷል ወይም ድሮ ከነበረው የእድገት በአፍጢሙ ተደፍቷል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ያቺ በተፈጥሮ ዘይት የበለጸገችው ሀገር፣ያቺ የብዙ አፍሪካውያን የስራ መዳረሻ እና ወደ አውሮፓ ምድር መተላለፊያ የነበረችው ሊቢያ ዛሬ የአፍሪካውያን የዒትዮጵያዊ ዜጎችንም ይጨምራል ምድርአዊ ሲኦል ሆናለች፡፡ በሰለጠነው በዚህ ዘመን በሊቢያ ምድር የሰው ልጅ ሽያጭ በገሃድ፣ በአደባባይ  ይከወናል ተብሎ ቢጻፍ ማን ያምናል? ግን ሆነ፡፡ ያሳዝናል፡፡
 6. ካለፈው የሊቢያ እድገት ጋር ዛሬ በነቢብም ሆነ በገቢር የሚታየው እጅጉን የሾቀ ነው፡፡ በምንም ተአምር በፊት ከነበረው ጋር ማወዳደር አይቻልም፡፡
 7. የነዳጅ ሀብቷ የግጭት እና እልቂት ምንጭ ከመሆኑ ባሻግር ብሔራዊ ስሜት ለሌላቸው፣ከአፍንጫቸው አርቀው በማያስቡ የሀገራቸውን አንድነት በካዱ የከንቱ ከንቱዎች ታጣቂ ሀይሎች  መዳፍ ስር ወድቋል
 8. የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በእጅጉ ወድቋል፣የገንዘብ ግሽፈት ብርቅ አይደለም፣የሀገሪቱ ሀብት እየተዘረፈ ወደ ውጭ ሀገር ይላካል፡፡ የህገወጥ ስደተኞች ቁጥር እጅጉን ጨምሯል ወዘተ ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡

በነገራችን ላይ በውጭ ሀገራት ( በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ መንግስታት ማለቴ ነው) ድጋፍ የሚተማመኑ ወይም ጥገኛ ወይም ታዛዥ የሆኑ የሊቢያ ባለስክጣናት ቁጥር እጅጉን ጨምሮ ይገኛል፡፡ ባዶ ቤት ቁንጫ ይፈላበታል እንዲሉ፡፡ በትናንሽ ጭንቅላቶች እና ድፍን ቅሎች በምትመራ ሀገር ውስጥ የውጭ ሀገር ሰዎች ፍላጎት ማስፈጸሟ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌዋ ሊቢያ ናት፡፡ እባካችሁን ሳይመሽብን በፍጥነት አውቀን እንታረም፡፡ የሊቢያ ተፈላሚ ሀይሎች ፍላጎት ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ግልጽና ጥርት ያለ አቋም የላቸውም፡፡ በሊቢያ ምድር ነፍጥ አንሰተው ርሰበርስ የሚፋለሙት ወንድማማቾች የተለያዩ አለማና ፍላጎት ነው ያላቸው፡፡ ብዙዎቹ ርሰበርስ የሚፋለሙት የተፈጥሮ ነዳጅ ዘይት ጉድጓዶችን ለመቆጣጠር እንደሆነ ይነገራል እንጂ ያቺን በተፈጥሮ የታደለች ሀገር በአንድነት አድርጎ ወደ እድገት ጎዳና ለመውሰድ እንዳልሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

   እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ በብይነ መንግስታቱ ድርጅት አነሳሽነት በሊቢያ ምድር እንደ አሽን የፈሉትን ደመኛ ቡድኖች ለማሸማገል በርካታ ጥረቶች ስለመደረጋቸው ከአለም የመገናኛ አውታሮች ሰርክ አዲስ የምንሰማው ዜና ይመስለኛል፡፡ ይህን ተከትሎ በጦር አውድማ የሚፋለሙትን የሊቢያ የጦር አበጋዞችን ወክለው የሚነጋገሩ ልኡካኖች ነበሩ ወይም አሉ፡፡ አንዳንድ ግዜ በብይነ መንግስታቱ ተወካዮች ተመልካችነት፣ አንዳንድ ግዜ ሀያልን ሀገራት አስተናጋጅነት፣በጎረቤት ሀገራት ሽምግልና፣በአፍሪካ ህብረት አመሃኝነት  ወዘተ ወዘተ በሁለቱ ካምፖች መሪዎች መሃከል ከ12 ግዜያት በላይ ንግግሮች፣ውይይቶች በሶስት አህጉራት ውስጥ መስኮብን ይጨምራል መደረጋቸው ይሰማል፡፡ ሆኖም ገን ይሁንና በሽማግሌዎች ወይም አደራዳሪዎች የተደረገው ጥረት አሁን ድረስ ፍሬ ያለው ውጤት ሊያስገኝ አልተቻለውም፡፡ አዲስ ዘመናዊ፣ዲሞክራቲክ የሆነ ህገመንግስት ገና በሊቢያ ተጽፎ አልጸደቀም፡፡ አሁን ድረስ ፕሬዜዴታዊም ሆነ ፓርሊሜንታ የምርጫ ውድድር በዲሞክራሲያዊ መንገድ አልተካሄደም፡፡

በሌላ በኩል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 21 2021 የተቃዋሚው ሀይል የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ማድረጉ ተስፋ ሰጪ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ የውስጥና የውጭ ተመልካቾች በነበረው የፖለቲካ ሀይሎች ንግግርና ውይይት በተመለከተ ተስፋ ሰንቀው እንደነበር ማታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡

  ለአብነት ያህል በሞሮኮዋ ከተማ ቡዙኒካ (Bouznika) በብይነ መንግስታቱ ተመልካችነት የሊቢያ ብረት አንጋቾች ፊትአውራሪዎች በአደረጉት ውይይት የመንግስት ስልጣንን በእኩል ደረጃ ለመከፋፈል በተወሰነ መልኩ መግባባት ላይ እንደደረሱ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡

በስዊዝ በምትገኘው ሞንትሪየክስ (Montrreux)  በአደረጉት ውይይት ደግሞ የሊቢያን ውድቀት መፍትሔ በሚገኝበት መንገድ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰውም ነበር፡፡

በግብጽ በምትገኘው አንዲት ከተማ ውስጥ ደግሞ(ሁርገሃዳ ትሰኛለች) (Hurghada) ስላም ለማስፈን፣የብሔራዊ ጦር ሀይሉን እንደገና ስለማደራጀት ( ከሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች የተወጣጣ የጦር ሀይል ስለሚመሰረትበት ሁኔታ ማለቴ ነው) የሊቢያ ተፋላሚ ሀይሎች ቁጭ ብለው ተነጋግረው ነበር፡፡ 

ሆኖም ግን ይሁንና የሊቢያ የፖለቲካ ሀይሎች አጠቃላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያላቸው እርቀት ሰፊ ነው፡፡  በተመሳሳይ መልኩ ሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎች የሚያስማማ የፖለቲካ መሰረት የለውም ማለት አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ በመጀመሪያና በዋነኝነት መገንዘብ ያለብን ቁምነገር ቢኖር ሁለቱም በሊቢያ የሚገኙት ዋነኞቹ ሀይሎች ያላቸው የወታደራዊ ሀይል ለአሸናፊነት የሚያበቃቸው አይደለም፡፡ ይህም ማለት አንደኛው የወታደራዊ የበላይነት በመቀዳጀት ሌላኛውን ተቀናቃኙን ማሸነፍ አይቻለውም፡፡ በወታደራዊ ሀይል በመጠቀም ማሸነፍ አዳጋች ነው፡፡ ምክንያቱም ጦርነቱ የርስበርስ ጦርነት ስለሆነ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ሊቢያ ዛሬ በተለያዩ ሁለት ፓርቲዎችና የተለያዩ ሀላፊነት ባላቸው ፓርቲዎች ቁጥጥር ስር ወድቃለች፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሁለቱም የፖለቲካ ሀይሎች በኢኮኖሚ ራሳቸውን የቻሉ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል አብዛኞቹ የነዳጅ ጉድጓዶች፣የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧዎችና የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች በቁጥጥር ስር የወደቁት ቱብሩክ (Tobruk)ግዛትን በያዘው የታጣቂ ሀይል ቡድን ስር ነው፡፡ ስለሆነም በሊቢያ ምድር ጤናማ የምጣኔ ሀብት እድገት ለማምጣት ወይም ሊቢያን ከኢኮኖሚ ድቀት መንቅሎ ለማውጣት ሁሉም የተፋላሚ ወገኖች ተስማምተው አንድ ማእከላዊ ጠንካራ መንግስት መመስረት አለባቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የሊቢያ ነዳጅ ሀብት በተለያዩ የጦር አበጋዞች ቁጥጥር ስር ወድቋል፡፡ ማእከላዊውን ሊቢያ የተቆጣጠረው የትሪፖሊ መንግስት የሀሪቱን የነዳጅ ሀብት መቆጣጠር እስካልቻለ ድረስ የሊቢያ የኢኮኖሚ ችግር የሚፈታ አይመስለኝም፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ የሊቢያ ህዝብ በተለይም በሁለቱ ትላልቅ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ( በትሪፖሊ እና ቤንጋዚ ከተሞች ውስጥ ነዋሪ የሆኑት) በሊቢያ ምድር በሚካሄደው የርስበርስ ጦርነት፣የጸጥተ መደፍረስ ምክንያት ተሰላችቷል፡፡ ሁለቱም ሀይሎች ወደ ድርድር፣ወደ ሰላማዊ መፈትሔ እንዲመጡ፣ የሊቢያ አንድነት እንዲጠበቅ በአደባባይ በይፋ በነሀሴ 2013 ዓ.ም. ድምጹን አሰምቷል፡፡ ህዝቡ ጦርነት አያዋጣም በማለት መጠየቅ ከጀመረ ቆይቷል፡፡

 ሊቢያ የኮሎኔል ጋዳፊ መንግስት ከወደቀ በኋላ አሳዛኝ የሀገር ምሳሌ ሆነች እንጂ አላለፈላትም፡፡ ያቺ በነዳጅ ሀብት የበለጸገችው ሀገር በኢኮኖሚ ድቀት እየተሰቃየች ያለችው በውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ብቻ ሳይሆን በውጥ በርስበርስ ጦርነት ምክንያት እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልብ እንድንል እማጸናለሁ፡፡

እንደ መደምደሚያ

የዛሬውን ጽሁፌን የምቋጨው በአልጄሪያ ምድር የተካሄደውን የርስበርስ ጦርነት ዳፋ በማስታወስ ይሆናል፡፡ ከላይ ከሊቢያ ውደቀት

ወደኋላ መመልከት

እ አ አ በ1991 ማለቂያ ወር ጀምሮ በአኀጉረ አፍሪካ አካል የሆነቺው አልጄሪያ ውስጥ በመንግሥትና በዓማፂያን ኃይሎች መሐከል ዓለምን ያስደመመ ጦርነትና በርካታ ንፁሐን ዜጎችን ሰለባ ያደረገ እንደነበር በታሪክ ተዘግቧል ። 

ጦርነቱ የፈጀውም ዕድሜውም ቀላል የሚባል አልነበረም ።

የአገሪቱን የውስጥ ውስብስብ የፖለቲካ ችግር ይዞም በተጨማሪ ምክንያት የውጪ መንግሥታትም ጣልቃ ገብነት መኖሩን ሳንረሳም ይሁን ።

ለአቅመ ዜና ማዳመጥ የደረሰ የዛን ዘመን ሰው ሁሉ እግዚኦ ሲል ያልዋለበት ቀኖችም እንዳልነበርም ይታወሰኛል ።

በየከተማው ፣ መንደሩና ገጠሩ የተቀሉትን ሚስኪኖች ቤት ይቁጠረው ።

ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ጦቢያ ሬዲዮን ሥራ ከመሄዱ በፊት ከፍቶ ያዳመጠ ፣ ከረፈደሞ በምሣውም ሰዓት ፣ ያልተመቸውም በማታው ዜና ያንን ተከታታይ የንፁሐን ፍጅትና ዕልቂት እንደ ሰበር ዜና ሳይሆን መደበኛ ዜና ሆኖ ማድመጡ እጅጉን የሰውን ልጅ ሠይጣን እንደሰረረውና ደም ማፍሰስን ሥራዬ ብሎ የተያያዘው የዕለት ተዕለት ምግባር ይመስል ነበር ።

አሁን ግን ያን ሁሉ ሦስት አሥር ዓመታት በላይ ተጉዞ ፣ በኛው ምድርም ሰበር ዜና እያሉ ካለፉት ዘጠኝም በለው አሥር ወሮቾም በዋናነት ይዞ የሚደመጠው የጦርነት መዘዝን ደግሜ ውጤቱን ሳስበው ፣ ለሌሎች አገሮችም የኛው የማያባራው ፍጅትና ዕልቂትም እንዳለፍነው የሰማነው የአልጄሪያ ፍጅት ዘመን ዜና ሆኖ የአገራችን ስም በሌሎች አገሮች ሚዲያ ነጋ ጠባ እንዳይናኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን፡፡ ሰላም፣ ነግግርና መደማመጥ እንዲኖር ሁላችንም መተባበር አለብን፡፡ በሀገራችን ያሉ የፖለቲካ ሀይሎች ሁሉ ወደ ጠረቤዛ ዙሪያ ተሰባስበው መነጋገር እንዳለባቸው ሁላችንም ሃሳብ ማቅረብ አለብን፡፡ …ጉዟችን ወዴት ነው የሚለውን ጉዳይ ግን ሁላችንም ልናስብበትና ልንመክርበት የሚያሻን ትልቅ ፈተና መሆኑን አበክረን መረዳትን ይጠይቃል ። የያዝነው 2014 ዓ.ም.የሰላም፣የፍቅር፣እኩልነት፣የፍትህና የአንድነት አመት እንዲሆን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰለጠነ መንገድ መነጋገር አለብን፡፡

 

Filed in: Amharic