>

«ትኋን ውጣ ቁንጫ ግባ . . . !!!» (ወንድወሰን ውቤ)

«ትኋን ውጣ ቁንጫ ግባ . . . !!!»

ወንድወሰን ውቤ

ለምን እንዲህ እንደሚባል የትመጣውን ለማያውቅ ሰው ነፍሳትን በማበላለጥ የተጠመድን ሊመስለው ይችላል። አባባሉ ግን የራሱ ታሪካዊ ዳራ አለው።
¶ ትኋን የተባሉ ፖርቱጋሎች(ፈረንጆች) ናቸው። ትኋን ብርሃን እያለ አያጠቃም፣ አይናከስ።  መብራት አጥፍቶ የተኛን ሰው ግን ነክሶ ደሙን ይመጣል። ፖርቱጋሎችም በአህመድ ግራኝን ወረራ በክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ስሜት ለዕርዳታ መጡ። ወረራው በግራኝ ሞት ከተቋጨ በኋላ ግን ነገር አመጡ። ለከፈልነው መሥዋዕትነት የኢትዮጵያ ምድር ሲሦው ይሰጠን፣ ኢትዮጵያ ትኮትልክ፣ እና መሰል ጥያቄዎችን አነሡ። ዐፄ ገላውዴዎስ ደግሞ በመከራችን ደርሳችሁልናል፣ ለመከራችሁ እንደርሳለን፣ ወታደሮቻችሁ ለከፈሉት መሥዋዕትነትም በወርቅና በብር እንከፍላለን እንጂ ከሀገራችን ከፍለን፣ ከአፈራችን ዘግነን እንሰጥ ዘንድ አይቻለንም አሉ።  ከሐዋርያት እምነታችን ዝንፍ፣ ከተዋሕዶ ሃይማኖታችን ነቅነቅ የለም ብለው ጸኑ።
   የንጉሡን ጽኑ አቋም ያዩት ጀሱይዊት ሚሲዮናውያን ከኢትዮጵያውያን ጋር ተጋብተውና ተላምደው ከሚኖሩ ወታደሮች ጋር እየኖሩና እነርሱን እናገለግላለን በሚል ሽፋን ካቶሊክነትን ቀስ በቀስ ማስፋፋት ጀመሩ። ትኋን ሰላም ነው ብሎ የተኛን ሰው እንዲያጠቃ እነርሱም እንዲሁ የተዘናጉትን ኢትዮጵያውያን ውስጥ ለውስጥ ሲሸረሽሩ ቆይተው በሱስንዮስ ዘመን ካቶሊክነት የመንግሥት ሃይማኖት ተደርጎ ታወጀ።
    ይህን ያልተቀበሉ ኦርቶዶክሳውያን ደንገተኛ አደጋ እየጣሉ ካቶሊካውያንን ማጥቃት ጀመሩ። በዐርበኞቹ ሽምቅ ውጊያ የተደናገጡት ፖርቱጋሎች ተዋጊዎቹን መያዝ ቢያቅታቸው «ቁንጫ» የሚል ስያሜ አወጡላቸው። ቁንጫ ሊያጠቃህ ሲፈልግ እስኪመሽ ወይም እስክትተኛ አይጠብቅም። በተመጨው ሰዓት ይናከስና ሊይዙት ሲሞክሩ ተፈናጥሮ ያመልጣል።
   በዚያ የኩትልክና ዘመን ኢትዮጵያውያን የመስቀል ዕለት በፖርቱጋልና በካቶሊካዊው ኃይል ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለመክፈት «ትኋን ውጣ ቁንጫ ግባ፤» የሚለውን ቃል እንደ ምሥጢራዊ መግባቢያ ቃል ተጠቅመውበት ነበር።  ፈረንጅ(ትኋን) ውጣ ሐበሻ(ቁንጫ) ግባ፣ ካቶሊክን ከቤተ መንግሥት አስወጣ፣ ኦርቶዶሳውያን ወደ ቤተ መንግሥት ግቡ፣ ወደ ንግሥና ተመለሱ። የሚል መልእክት ተላልፎበታል።

   ዛሬም ትኋናዊ ጠባይን ውጣ ማለት ይገባል። ሀገራችን የኛ ናት፤ ኢትዮጵያውያን ነገድ አልባ ኅብረት ፈጥረን በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ላይ ማዘዝ መናዘዝ የሚሹትን ውጡ ማለት ይገባናል። እርስ በእርስ የሚያናክሰንን ትኋናዊ ጠባይ ይገሥጽልንማ። ፈረንጅኛ መልክ ባይኖራቸውም ፈረንጅኛ ሐሳብ ይዘው ኢትዮጵያን ማየት የማይሹት ሁሉ ሐሳባቸው ከንቱ የሚሆንበትን ጊዜ ያምታልን። ዘመኑ አድብተን የምንጠቃቃበት ሳይሆን ፊት ለፊት ተነጋግረን ለሀገር የሚበጀውን የምናደርግበት፣ የሀገራዊ እርቅ፣ የሰላም ዘመን እናድርገው።

መልካም በዓለ መስቀል፤

Filed in: Amharic