>

ጦርነቱ አይቀሬ ነበር! (አብርሀ ደስታ)

ጦርነቱ አይቀሬ ነበር!

አብርሀ ደስታ


ጥያቄ
“ጦርነት ይኖራል ብለህ አስበህ ነበር?”
 
መልስ
ጦርነቱ አይቀሬ ነበር፤ በአምስት ምክንያቶች!
 
1. አብዮታዊ ዴሞክራሲ
የኢህአዴግ መንግስት አይዲዮሎጂ፣ ውስጣዊ አሰራር፣ የስልጣን ትርክት ወዘተ የሚያሳየው በፈቃደኝነት ከስልጣን እንደማይለቅ፡ በሐይል ከለቀቀ ደግሞ እስከ እርስበርስ ጦርነት የሚደርስ ግጭት እንደሚኖር የታወቀ ነበር። በ2004 ዓም በአንድ መፅሔት በፃፍኩት ላይ ህወሓት ከአዲስ አበባ በሐይል ከተባረረ ወደ መቀለ እንደሚሄድና ግጭት እንደሚኖር ያትታል።
ተቃውሞ የጀመርኩበት ምክንያትም የግል ፀብ ወይ ቂም ስላለኝ ሳይሆን ወደ ጦርነት ሳንገባ ኢህአዴግ በሰላማዊ መንገድ  በህዝብ ድምፅ ተሸንፎ ጠመንጃ ሳይሆን ሐሳብ ይዞ ለሚመጣው ፓርቲ ስልጣን የሚያስረክብበት ዕድል (Peaceful Transfer of Power) እንዲኖር ለማገዝ ነው። ግልፅ ዓላማዬ “የትግራይ ህዝብ 17 ዓመት ሙሉ የደማበት ይበቃዋል። ካሁን በኋላ መንግስት በተቀየረ ቁጥር ጦርነትና ደም መፋሰስ ይቁም፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ይኑር። ወደ ጦርነት እንዳንመለስ ህዝባዊ መንግስት ይኑረን” የሚል ነበር።
ኢህአዴግ ተፈጥሮው አልፈቀደምና አማራጭ ሐሳብ የሚያቀርቡ መሪዎች እያሰረ፣ ፓርቲዎች እያዳከመ፣ ሰላማዊ ትግል ገድሎ፣ በመጨረሻ ብቻውን ቀርቶ፣ ግዜ ደርሶ ሲፈርስ ወደ ፈራሁት ወደ እርስበርስ ጦርነት ገባን።
ስልጣን ጠቅልለው በሚይዙ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አይዲዮሎጂ የሚመራ ፓርቲ የሚተዳደር ሀገርና ህዝብ መጨረሻው ጦርነት ነው። ስለዚህ ጦርነቱ አይቀሬ ነበር። ጦርነት ሚቀርበት ዕድል የመንግስት ለውጥ በምርጫ ቢመጣ ነበር። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሀገራዊና ህዝባዊ ሐላፊነት ቢሰማቸው ኖሮ ስልጣን ለህዝብ ማስረከብ ነበር። ይህም ለዓመታት ተናግረናል!
2. የኢህአዴግ ውህደት
ኢህአዴግ በአንፃራዊነት ሰላማዊ በሆነ ህዝባዊ ዓመፅ ሲሸነፍ ትልቅ ዕድል ነበር።  ግን በውስጣቸው አለመግባባት ተፈጠረ። መፍታት ይገባ ነበረ። የውህደት ሐሳብ መጣ። ውህደት በሚደግፉና በማይደግፉ ድርጅቶች ለሁለት ተከፈሉ።
በአብዮታዊ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ሲመራ የነበረ “አንድ” ድርጅት ለሁለት ሲከፈል መጨረሻው ጦርነት እንደሚሆን የታወቀ ነበረ። ለሁለት ሲከፈሉ ግዜ በመኃከላቸው ጦርነት ግድ ነው፤ ጦርነቱ አይቀሬ ነበረ።
የብልፅግናና የህወሓት መሪዎች ለህዝብ ደሕንነትና ለሀገር አንድነት ቢያስቡ ኖሮ ጦርነቱን ለማስቀረበት ሳይከፋፈሉ ለመወሃድ ወይም ላለመዋሃድ ይስማሙ ነበረ።  ለምሳሌ የብልፅግና ሰዎች ውህደቱን ከፈለጉ ህወሓትን ማሳመን ይገባቸው ነበር። ማሳመን ካልቻሉ ውህደቱን ማዘግየት ይችሉ ነበር። ከሰላም አንፃር ውህደት ጥሩ ነው፤ ለሁለት ከመከፈል ግን አለመዋሃድ ይሻል ነበር። ህወሓቶችም ላለመወሃድ ማሳመን ካልሆነ ግን መወሃድ ይገባቸው ነበር፤ ለህዝብ ደሕንነት ሲባል አቋም Compromise ይደረጋል።
ለሁለት ሲከፈሉ ግዜ ጦርነት አይቀሬ ነበር። ወይ ተዋሃዱ፣ ወይ አትወሓዱ፤ ግን አትከፋፈሉ ስንል የነበረው በምክንያት ነው።
3. የሕገ መንግስት ትርጉም
ምርጫ በኮሮና ምክንያት የተራዘመ ግዜ ሀገራዊ ምክክር ያስፈልግ ነበር። መንግስት ግን ወደ “ህገ መንግስት ትርጉም” ነበር የሮጠው። ከሀገር አንድነትና ከህዝቦች ደሕንነት አንፃር ከፍተኛ ስሕተት ነበር የተፈፀመው። ፖለቲካዊ ቀውስ ባለበት ሀገር “ሕጋዊ አካሄድ”  ብቻ መፍትሔ እንደማይሆን ደጋግሜ ፅፌ ነበር። ወደ ጦርነት እየገባን እንደሆነም ፅፌ ነበር። ውይይት ቀርቶ ወደ ሕገመንግስት ትርጉም ሲኬድ ጦርነት እንደማይቀር ግልፅ ነበር። ያኔም በተደጋጋሚ ፅፍያለሁ። ሰሚ አላገኘሁም!
4. የትግራይ ምርጫ
የትግራይ ምርጫ “ምርጫ” ሳይሆን የጦርነት ትንኮሳ ነበረ። አንድ ክልል ሕጋዊው ሀገራዊ ምርጫ ቦርድ ሳይፈቅድለት ምርጫ ካደረገ የጦርነት ቅስቀሳ ነው። ስለዚህ ለሀገርና ለህዝብ ሰላም የሚያስብ አካል ማድረግ ያለበት መጀመርያ ምርጫው እንዲራዘም ማግባባት ወይ መደራደር፤ ተደራድሮ ምርጫውን ማራዘም የማይቻል ከሆነ ደግሞ ምርጫውን መቀበል፤ ዕውቅና መስጠት ተገቢ ነበር። ምርጫውን በድርድር ማስቀረት አልተቻለም፤ ዕውቅናም አልተሰጠው፣ መጨረሻ ጦርነቱ አይቀሬ ነበር።
መጀመርያ ምርጫ ለብቻ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ፃፍኩኝ፤ ቀጥሎም የተናጠል ምርጫ ጉዳት እንዳለው አስረዳሁኝ (ጉዳቱ ምንድነው? ስትሉኝ የነበራችሁ የትግራይ ልጆች ሆይ! አሁንስ ጉዳቱ ተገለጠላች?)። ምርጫው እንደሚካሄድ ያረጋገጥኩ ግዜ ምርጫውን ደገፍኩ፣ ተቀበልኩ፣ ዕውቅና ሰጠሁ። ጦርነት ምናስቀርበት መንገድ ይሄ ነበር።
5. የኤርትራ ግንኙነት
ከኤርትራ ጋር ሰላም መፍጠሩ አስፈላጊ ነበር። ግን በህወሓትና በሻዕብያ መካከል ያለው የቆየ ፀብ ሳይፈታ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የፖለቲካ ልዩነት እንዳለ እየታወቀ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶር ዐብይ ከኤርትራው ፕረዚዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በህወሓቶች ዘንድ እንደ ጦርነት ትንኮሳ አይታይም ወይ?
መደረግ የነበረበት፦ ህወሓቶችም የስምምነቱ አካል ማድረግ!
በነዚህና ሌሎች መሠረታዊ ምክንያቶች ጦርነቱ አይቀሬ ነበር። ይህን ያህን ከባድና መጥፎ፣ በሰላማዊ ዜጎች ዒላማ የሚደረጉበት ጦርነት ይሆናል ብዬ ግን አላሰብኩም ነበረ።
ሰላም!
Filed in: Amharic