>

የቱለማ ኦሮሞ እና የኦዳ ነቤ የገዳ ስርዓት....!!! --( ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ)

የቱለማ ኦሮሞ እና የኦዳ ነቤ የገዳ ስርዓት….!!!

——
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

 በኦሮሞ ህዝብ የአሰፋፈር ትውፊት መሠረት በመካከለኛው ኦሮሚያ የሚኖረው የኦሮሞ ነገድ “ቱለማ” ይባላል፡፡ ቱለማ በጥንታዊነታቸው ከሚጠቀሱ የኦሮሞ ነገዶች አንዱ ሲሆን በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በስፋት ከሚታወቁት መካከልም ነው፡፡ ለቱለማ መታወቅ ትልቁን ሚና የተጫወተው ደግሞ “መጫና ቱለማ” የሚባለው ታሪካዊ ማህበር ነው፡፡
 የኦሮሞ ህዝብ ትውፊት እንደሚለው የቱለማ አባት “ራያ” ይባላል፡፡ ከራያ የተወለደው ሌላኛው ልጅ “መጫ” ተብሎ ይታወቃል፡፡ ቱለማ ለአባቱ አንጋፋ ልጅ ሲሆን መጫ ደግሞ ሁለተኛ ልጅ ነው፡፡ ራያ እነዚህን ልጆች የወለደው በፊንፊኔ ግርጌ በሚገኘው “ገላን ደንጎራ” የተባለ አምባ አካባቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡
 በጥንቱ የኦሮሞ የውርሥ ደንብ መሠረት አባቱን የሚወርሠው አንጋፋ ልጅ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ራያ ሲያርፍ ቱለማ አባቱን ተክቶ በገላን ደንጎራ አካባቢ ኑሮውን መመሥረቱ ይነገራል፡፡ መጫ ደግሞ ወደ ምዕራብ ተጉዞ ቆሪቻ በተባለ አካባቢ እንደሰፈረ ምንጮቻችን ያስረዳሉ፡፡ በዛሬው ዘመን በሸዋ፣ በወለጋ፣ በጎጃም (ወንበራ)፣ በኢሉባቦር እና በጅማ የሚኖሩት ኦሮሞዎች ቱለማ እና መጫ ከሚባሉት የጥንቱ የራያ ልጆች የተራቡ መሆናቸውም ይወሳል፡፡
መጫ እና ቱለማ ለረጅም ዘመን በአንድ የገዳ ማዕከል ስር ይተዳደሩ ነበር፡፡ በሂደት ግን የቱለማ ነገድ የገዳ ማዕከሉን በአዲስ ሁኔታ በኦዳ ነቤ የመሠረተ ሲሆን መጫ ደግሞ ከአምቦ ከተማ በስተምዕራብ ባለው “ኦዳ ቢሲል” ሌላ የገዳ ማዕከል አቋቁሟል፡፡
 እንግዲህ ታዋቂውን የመጫ እና ቱለማ ማኅበር የመሠረቱት ከነዚህ ሁለት ታላላቅ  ነገዶች የተወለዱ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ እነ ኮሎኔል ዓለሙ ቂጤሳ፣ ጄኔራል ዳዊት አብዲ፣ መቶ አለቃ ማሞ መዘምር እና ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽ የመጫ ተወላጆች ሲሆኑ ኃይለማሪያም ገመዳ፣ ጄኔራል ታደሰ ብሩ እና በቀለ ነዺን የመሳሰሉት ደግሞ የቱለማ ተወላጆች ነበሩ፡፡
*****
 የቱለማ ኦሮሞ ዳጪ፣ በቾ እና ጂሌ የሚባሉ ሶስት ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በዳጪ ስር የሚካተቱት በዛሬው ሰሜን ሸዋ ዞን (ሰላሌ)፣ በምሥራቅ ሸዋ (ቢሾፍቱ ዙሪያ) እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩት ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ በቾ ደግሞ ዛሬ “ደቡብ ምዕራብ ሸዋ” በሚባለው ዞን ባሉት በርካታ ወረዳዎችና በምዕራብ ሸዋ ዞን ምሥራቃዊ ክፍል የሚኖሩትን ኦሮሞዎች ያካትታል፡፡ ጂሌ በደቡብ ምሥራቅ ሸዋ (መቂ፣ ወንጂ፣ ቆቃ፣ አዳማ፣ ሞጆ፣ ወለንጪቲ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ቤልቡላ ወዘተ) የሚኖሩ ኦሮሞዎች የሚካተቱበት ነው፡፡
 ዳጪ፣ በቾ እና ጂሌ የሚባሉት የቱለማ ኦሮሞ ቅርንጫፎች በብዙ ጎሳዎችና ንዑስ ጎሳዎች የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ ከቱለማ ኦሮሞ ጎሳዎች መካከል ገላን፣ ሶዶ (ሰዴን ሶዶ)፣ አቦ (ቶርበን አቦ)፣ ሜታ፣ አድኣ፣ ወረ-ጃርሶ፣ ጊምቢቹ፣ ኤካ፣ ጉለሌ፣ ያያ፣ ሊበን፣ ጋዱላ፣ ገረሱ፣ ዱለቻ፣ አቡኑ፣ ቡያማ፣ አመያ፣ አሙማ እና አከዩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
==ኦዳ ነቤ እና ቱለማ==
 የቱለማ ኦሮሞ በጣም አንጋፋ መሆኑን የሚመሰክረው ትልቅ አብነት ነገዱ ከጥንታዊው “ኦዳ ነቤ” ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑ ነው፡፡ የኦሮሞ ሽማግሌዎች እንደሚሉት ጥንታዊው የገዳ ስርዓት በመካከለኛው ዘመን የተከሰቱትን ታላላቅ ለውጦች ባገናዘበ መልኩ ተሐድሶ እንዲካሄድበት ተወስኖ ነበር፡፡ የገዳ ማዕከሉም ጥንት ከነበረበት “ፉጉግ” የተሰኘ ቀበሌ ተነቅሎ ለሁሉም የኦሮሞ ነገዶች አማካይ ወደሆነ ስፍራ እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ ፉጉግን የተካው ማዕከል ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ የገዳ ጉባኤዎችን የሚያስተናግደው ታዋቂው “ኦዳ ነቤ” ነው፡፡
 የትውፊት ምንጮቻችን እንደሚሉት ኦዳ ነቤ የተሻሻሉት የኦሮሞ “ሄራ” (ህገ-መንግሥት) እና “ሴራ” (ዝርዝር የመተዳደሪያ ህጎች) የታወጀበት ስፍራ ነው፡፡ ያኔ ከታወጁት ህጎች መካከል ብዙዎቹ በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በጥንት ዘመናት የገዳ ስርዓት ስምንት ዑደቶች (cycles) የነበሩት መሆኑ ይነገራል፡፡ እነዚህ ዑደቶች ወደ አምስት ዝቅ የተደረጉት በኦዳ ነቤ በተካሄደው የተሐድሶ ንቅናቄ ዘመን እንደሆነም ይወሳል፡፡
 በዘመናችን ሕያው ሆነው የሚያገለግሉት ኦዳ ሮባ (በባሌ የሚገኝ)፣ ኦዳ ቢሲል (በምዕራብ ሸዋ ያለ)፣ ጉሚ ጋዮ (በቦረና የሚገኝ) እና ኦዳ ቡልቱም (በምዕራብ ሀረርጌ የሚገኝ) የተሰኙ የገዳ ማዕከላት የሚመሩበት “ሄራ” (ህገ-መንግሥት) በኦዳ ነቤ የተደነገገው ሁሉን አቀፍ የኦሮሞ “ሄራ” እንደሆነ የኦሮሞ ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡
==የገዳ ስርዓት በቱለማ==
 የገዳ ስርዓት አምስት ዑደቶች አሉት- ከላይ እንደገለጽኩት፡፡ እውነታው ሲታይ ግን ዑደቶቹ በቁጥር አስር ናቸው፡፡ ይህም የሆነው አባቶች በአምስቱ ዑደቶች እየተፈራረቁ ሀገሩን ከመሩ በኋላ ልጆቻቸው በተመሳሳይ ሁኔታ በአምስት ዑደቶች እየተፈራረቁ ስለሚያስተዳድሩ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በቱለማ ኦሮሞ ዘንድ አምስቱ ቀዳሚ (የአባቶች) የገዳ ዑደቶች ሜልባ፣ ሙደና፣ ኪሎሌ፣ ሚቺሌ እና ቢፎሌ ይባላሉ፡፡ አምስቱ ተከታይ (የልጆች) የገዳ ዑደቶች ደግሞ ሀርሙፋ፣ ሮበሌ፣ ቢርመጂ፣ ሙለታ እና ዱሎ ይባላሉ፡፡
 እያንዳንዱ የገዳ ዑደት የስምንት ዓመት የጊዜ ርዝመት አለው፡፡ በመሆኑም ከላይ የዘረዘርናቸው የገዳ ዑደቶች በየስምንት ዓመቱ እየተተካኩ የመንግሥቱን በትረ-ስልጣን ይይዛሉ፡፡ በተመሳሳይ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች (ከ40-48 ዓመት የሆናቸው) ለአንድ የገዳ ዘመን ሀገሩን ይመራሉ፡፡ በየትኛውም እርከን ላይ ባለ የአስተዳደር ሥራ ላይ የሚሳተፉት የገዥው የገዳ ዑደት አባል የሆኑ ግለሰቦች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ለስምንት ዓመታት ሀገሩን ከመሩ በኋላ ስልጣናቸውን ያስረክባሉ፡፡
 በጥንቱ የገዳ ስርዓት ደንብ መሠረት የኦሮሞ ማኅበረሰብ አባል የሆነ ሰው የህይወት ዘመኑን የሚያሳልፈው ራሱ በሚፈልገው አቅጣጫ ብቻ አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው ከልደቱ እስከ ሞቱ ድረስ ባለው የሕይወት ዘመኑ በገዳ ደንብ የተጣሉበትን ማህበራዊ ግዴታዎችና ኃላፊነቶች እየተወጣ ነው የሚኖረው፡፡ እነዚህ ኃላፊነቶችና ግዴታዎች ሰውዬው ከሚያልፍባቸው የእድሜ ደረጃዎች ጋር ይቀያየራሉ፡፡
     በዚህ መሠረት በእድሜያቸው ከስምንት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች “ገሜ” ይባላሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ያሉት ልጆች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ሰውነታቸውን በሚያጎለብቱ ጨዋታዎች ላይ  (ዋና፣ ትግል፣ ዝላይ፣ ሩጫ ወዘተ..) በመሳተፍ ነው፡፡ ልጆቹ ከ8-16 ባለው የዕድሜ ክልል ሲገቡ “ደበሌ” ይባላሉ፡፡ በዚህኛው ዕድሜ ክልል ላይ የደረሱ ልጆች ከብቶችን ይጠብቃሉ፡፡ ቤተሰቦቻቸውንም በሥራ ይረዳሉ፡፡
    ከ16-24 ዓመት የሆናቸው ልጆች “ፎሌ” ይባላሉ፡፡ እነዚህ ልጆች የቤተሰቦቻቸውን ዋነኛ የመተዳደሪያ ሥራዎች (እርሻ፣ ቤት መሥራት፣ እንጨት መፍለጥ፣ ንግድ፣ የሸክላ ሥራ ወዘተ) ይሠራሉ፡፡ የጦር መሣሪያ አጠቃቀምና የውጊያ ልምምድም ያደርጋሉ፡፡ ከ24-32 ዓመት የሆናቸው ሰዎች “ኩሳ” ይባላሉ፡፡ በዚህ የዕድሜ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ዋነኛ ተግባሩ የጦር ኃይሉ አባል በመሆን ህዝቡንና ሀገሩን ከጥቃት መከላከል ነው፡፡
    ከ32-40 ዓመት የሆናቸው ሰዎች ደግሞ “ራባ ዶሪ” ይባላሉ፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ሁለት ዋነኛ ኃላፊነቶች አሉት፡፡ አንደኛው የአስተዳደርና የህግ ጉዳዮችን እንዲሁም የሀገሩንና የህዝቡን ባህልና ታሪክ ማጥናት ነው፡፡ ሰውዬው እግረ መንገዱን ከሥነ-መንግሥት ጉዳዮች ጋር እየተለማመደ ራሱን ለመሪነት ያዘጋጃል፡፡ “ራባ ዶሪ” የሆነ ሰው ሁለተኛ ተግባሩ ጋብቻ መፈጸምና የወደፊት መኖሪያውን መቀለስ ነው፡፡
 አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ከ40-48 ዓመት ባለው የዕድሜ እርከን ላይ ሲደርስ “ሉባ ሆነ” ይባላል፡፡ ሰውዬው በዚህ የዕድሜ ዘመኑ የሀገር አስተዳዳሪ ይሆናል፡፡ ይህ ሲባል ግን በዚህ ዕድሜ ላይ የደረሰ ማንኛውም ሰው “አባገዳ” ወይንም “ፕሬዚዳንት” ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ ዕድሜ ላይ ከደረሱት የማህበረሰቡ ክፍሎች መካከል “አባገዳ” ሆኖ የሚመረጠው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ ከአምስት እስከ አስር የሚደርሱ የገዳው የካቢኔ አባላትም ይመረጣሉ፡፡ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በተለያዩ እርከኖች (ቀበሌ፣ ወረዳ ወይም ዞን) እና በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ተመድበው ሀገሩን ያስተዳድራሉ፡፡
 ዕድሜው ከ48-56 ዓመት የሆነው ሰው “ጉላ” ይባላል፡፡ ሰውዬው በዚህኛው የእድሜ ዘመኑ ላይ ሲደርስ ስልጣኑንም ሆነ ሀገር የማስተዳደሩን ተግባር ለተከታዩ ገዳ አባላት (ዕድሜአቸው ከ40-48 ለሆነው) ያስረክብና ለራሱ ሌላ ኃላፊነት ይረከባል፡፡ በዚህ የዕድሜ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ኃላፊነት አዲሶቹን ሀገር መሪዎች ማማከር ነው፡፡
 ዕድሜው ከ56-64 ዓመት የሆነው ሰው “ዩባ” ይባላል፡፡ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሰው ዋነኛ ሥራው በማኅበረሰቡ አባላት መካከል የሚከሰቱ ውዝግቦችን በሽምግልና መፍታት ነው፡፡ በጋብቻ ጊዜ ሽማግሌ ሆነው የሚላኩትም በዚህ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ዕድሜው ከ64-72 ዓመት የሆነው ሰው ደግሞ “ዩባ ለመፋ” ይባላል፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ዋና ሥራው የማኅበረሰቡ የትውፊት፣ የባህልና የታሪክ ተራኪ ሆኖ ማገልገል ነው፡፡
 ዕድሜው ከ72-80 ዓመት የሆነው ሰው “ዩባ ሰደፋ” ይባላል፡፡ በዚህ ዕድሜ ላይ ያለ ሰው ዋና ሥራው በተለያዩ ማኅበራዊ ኩነቶችና በክብረ በዓሎች ላይ እየተገኘ ህዝቡንና ሀገሩን መመረቅ ነው፡፡ ሰውዬው ሰማኒያ ዓመት ሲሆነው “ገዳ-ሞጂ” ይባላል፡፡ አንድ ሰው በዚህ የዕድሜ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከማንኛውም ማኅበራዊ ግዴታዎች ነፃ ሆኖ የጡረታ ዘመኑን ይጀምራል፡፡
*****
 ከላይ የዘረዘርነው የቱለማ ኦሮሞ የሚተገብረውን የገዳ ስርዓት ደንብና ወግ ነው፡፡ ሆኖም በሌሎች የኦሮሞ ነገዶች ዘንድ የሚሠራበትም ወግና ደንብ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ የገዳ ዑደቶችና ዕድሜን መሠረት ያደረጉት የማኅበረሰቡ ቡድኖች በሚጠሩባቸው ስሞች ላይ ግን ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ በምዕራብ ሀረርጌ የሚኖሩት የኢቱ ኦሮሞዎች አምስቱን የአባቶች የገዳ ዑደቶች “በዻዻ”፣ “ቡልቱማ”፣ “መርዲዳ”፣ “ሆረታ”፣ “ፈደታ” በማለት ነው የሚጠሯቸው፡፡ አምስቱን የልጆች የገዳ ዑደቶች ደግሞ “ወበሰ”፣ “በሲራ”፣ “ዺቢሳ”፣ “ኑኩሳ”፣ “ዳኢሞ” ይሏቸዋል፡፡
——
አፈንዲ ሙተቂ፤ “ቦረና እና በሬንቱ” ከተሰኘው መጽሐፍ የተቀነጨበ፣ 2013፣ ገጽ 67-75
Filed in: Amharic