የፋሽስት መቅሰፍቱ ቢትወድድ መንገሻ ጀምበሬ –
ታሪክን ወደኋላ
ቢትወድድ መንገሻ ጀምበሬ ግንቦት 13 ቀን 1884 ዓ.ም በሜጫ ጉታ አውራጃ አካባቢ ተወለዱ። የደጃዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬ አባት ጀምበሬ እምሩ የሜጫ፣ የዴንሳ ፣ የጉታ ፣ የአገው ምድር ባላባት በመሆን ለብዙ ዘመናት አካባቢውን አሥተዳድረዋል፡፡ ቢትወድድ መንገሻ ጀምበሬ ቤተሰቦች ከአባታቸው እስከ ቅድመ አያቶቻቸው ድረስ ሁሉም የደጃዝማች ማዕረግ የነበራቸው ነበሩ። ቢትወድድ መንገሻ ብልህ ፣ አስተዋይ ፣ በልጅነት ዘመናቸው በአልሞ ተኳሽነታቸው ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ፣ በበገና ድርደራ እና በፈረስ ግልቢያ የሚታወቁ ነበሩ፡፡ ለአደንና ውኃ ዋናም ልዩ ፍቅር ያላቸው ትልቅ አርበኛ ነበሩ፡፡
ቢትወድድ መንገሻ ጀምበሬ በተወለዱ በዘጠኝ ዓመታቸው አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ከአያታቸው ደጃዝማች እምሩ ቤት ኾነው የቤተ ክህነት ትምሕርት እየተከታተሉ አደጉ፡፡ ከዚያ በኋላም አያታቸው ደጃዝማች እምሩ ሲሞቱ ከአጎታቸው ደጃአዝማች ሽፈራው እምሩ ጋር በመሆን የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየወሰዱ አደጉ፡፡ በእድገት ዘመናቸው ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬን ጀግንነት የተመለከቱት ደጃዝማች ሽፈራው እምሩ ከሚያሥተዳድሩት ግዛት በመቀነስ ቆላ አቦሌ የሚባለውን ግዛት ሰጧቸው፡፡
ከዚያ በኋላም በተወለዱ በ 32 ዓመታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ በማግኘታቸው የቡሬ ዳሞት አውራጃንና ሰከላ አካባቢዎችን ማሥተዳደር ጀመሩ፡፡ በመልካም ፀባያቸው ፣ በአስተዋይነታቸው እና ለሀገራቸው ባላቸው ልዩ ክብር ምሥጉን ሆኑ፡፡ በሚያሥተዳድሩት አካባቢ የፀጥታው ችግር የሌለበት ፣ በትንሹም በትልቁም የሚወደድ ባሕርይ እንዳላቸው በመታወቁ ሜጫን እንዲያሥተዳድሩ ትልቅ ኃላፊነት ተሰጧቸዋል፡፡ በወቅቱ እሳቸው በሚያሥተዳድሩት ግዛት ፍርድ የሚያጓድል፣ ድሃን የሚበድል፣ መንገደኛን የሚዘርፍና በአጠቃላይ ሕገ ወጥ ተግባር የሚፈጽም ሰው ሲኖር በፍጥነት ፍርድ በመስጠት የሚታወቁ ናቸው፡፡
በ 1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያን ወራሪ ጦር በመጣ ጊዜ በግዛታቸው ማለትም በሜጫ አውራጃ አካባቢ የሚገኘውን ጦር አስከትለው ከራስ እምሩ ጋር በትግራይ በኩል በመዝመት ለእናት ሀገር የሚከፈለውን መስዋትእነት ከፍለዋል፡፡ በወቅቱ በነበረው ጦርነት አርበኞች ከፍተኛ ጀብዱ ቢፈጽሙም ድሉ መርዝ በሚያዘንቡ አውሮፕላኖች በሚታገዘው የጣሊያን ጦር ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞችም ትግራይን ለቀው ወደ ኋላ በማፈግፈግና እንደገና በየአካባቢው የሚገኘውን የጎበዝ አለቃ እያስተባበሩ ጠንካራ ውጊያ በማድርግ የጠላትን ጦር ድል የተቀዳጁ አርበኛ ነበሩ፡፡ ከትግራዩ ጦርነት በተጨማሪ የጎጃም አርበኞች የጣሊያን ወራሪዎችን በአራት አቅጣጫ ተከፋፈለው ሲፋለሙ ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ አገው ምድርን፣ ሠከላን፣ ሜጫን፣ ጉታን፣ አቸፈርን፣ አለፋ ጣቁሳ መርተው ነበር።
ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ቢቸናን ፣ ራስ ኃይሉ ደብረ ማርቆስንና ሞጣን እንዲሁም ራስ በዛብህ ዳሞት አካባቢን በማካለል የጠላት ጦርን እረፍት ነሱት፡፡ ቢትወድድ መንገሻ ጀምበሬ ከደጃዝማች በላይ ዘለቀና ከሌሎች የውስጥ አርበኞች ጋር በመሆን የጋራ ጠላትን የተዋጉና በሀገር ጉዳይ እጅግ ከፍተኛ መናበብ ነበራቸው። በውጊያ ወቅትም በየመካከላቸው መረጃ ይለዋወጡ እንደነበረም ስለ እሳቸው የተጻፈ መረጃ ያመላክታል፡፡ ከሌሎች አርበኞች ጋር በመሆን ለፈጸሙት ጀብድ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የእንደራሴነት ማዕረግ ተሾመዋል።
በጀግንነታቸው ጠላት እጅግ የሚፈራቸው ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ በአንድ ወቅት በባሕር ዳር አካባቢ በወራሪው ኃይል ተማርከው የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ከጠላት መንጋጋ መውጣት መቻላቸውን ታሪካቸው ያስረድተዋል፡፡ በ 1929 ዓ.ም ጣሊያናዊዉ ካፒቴን ኮርቦ ባህርዳርን ያስተዳድር በነበረበት ጊዜ ቢትወድድ መንገሻ ጀምበሬ፣ ደጃዝማች ስብሀቱ ይግዛውን የይልማና ዴንሳ ጦር አዝማች ፣ ፊታዉራሪ መኮነን ዋሴና ሌሎችም ወደ ባህርዳር ካስጠራ በሗላ ፣ ደጃዝማች ስብሀቱ ይግዛውን ከነልጃቸዉና ፊታዉራሪ መኮነን ዉቤን ሲሰቅሏቸዉ፣ ቢትወድድ መንገሻ ጀምበሬን ግን እዚያዉ ባህርዳር ከተማ እንዳይለቁ በሚል የቁም እስረኛ አደረጋቸዉ።
በዚህ ወቅት የሰከላ፣ የፋግታ፣ የሜጫ፣ የአገዉ ምድርና የ አቸፈር ህዝብ በደብቅ ተሰብስበዉ የጣሊያንን ጦር ለማጥቃት ይነጋገሩ ነበር።
በመጨረሻም በስብሰባዉ ቢትወድድ መንገሻ ጀምበሬን የጦር መሪ አድርገዉ ለመዋጋት ወስነዉ ሽማግሌዎቹ ሄደው እንዲነግሩት ተደረገ። ቢትወድድ መንገሻ ጀምበሬም በሀሳቡ ተስማምተው ካፒቴን ኮርቦን ስላመመኝ ሄጀ ፀበል እንድጠመቅ ፍቀድልኝ በማለት ካነጋገሩት በሗላ በዋስ አስፈቅደው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ከዚያም ውስጥ ለውስጥ ጦራቸዉን ካደራጁ በኋላ በግልፅ ሸፈቱ። ከድሉ ከተመለሱ በኋላ በቀዳማዊ ዐፄ ሀይለሥላሴ ተጠርተዉ የቢትወደድነት ማዕረግ ተሰጣቸው። በመቀጠልም የጎጃም ክፍለሀገር ምክትል ገዥ ሆነው እያስተዳደሩ እያለ ወደ አዲስአበባ ተዛውረው የህግ መወሰኛ ምክርቤት ሀላፊ ሆነው ሲሰሩ ቆዩ። ከዚያም የወለጋ ክፍለሀገር ገዥ ሆነው በመስራት ላይ እያሉ ባደረባቸው ህመም ምክኒያት በ 1942 ዓ.ም በተወለዱ በ 58 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን የአርበኝነት ውለታቸውን ለማዘከርም በዳንግላ ከተማ አንድ ሁለተኛ ደረጃ እና አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስማቸው ተሰይመውላቸዋል።
ክብርና ሞገስ ለጀግኖች አርበኞቻችን