>

ስለ ብሔራዊ መታወቂያ (ከይኄይስ እውነቱ)

ስለ ብሔራዊ መታወቂያ

ከይኄይስ እውነቱ


የወሳኝ ኵነት ምዝገባና ብሔራዊ መታወቂያ ዓዋጅ ቊጥር 760/2004 (እንደተሻሻለ) ከወጣ ዘጠኝ ዓመታትን አስቈጥሯል፡፡ ወያኔ የሠለጠነበትን ስድስቱን ዓመታት ብናነሳ እንኳን ሦስት ዓመታት አሉን፡፡ አንድ ሕግ ሲወጣ (ከጊዜው እጅግ ካልቀደመ በቀር) ሕጉን ለማስፈጸም የሚረዱ ተቋማዊ፣ አስተዳደራዊ፣ የፋይናንስና ሌሎችም ዝግጅቶች አስቀድሞ መደረግ እንዳለባቸው ይታሰባል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት በዘፈቀደ በሚመሩበት እና ከሥርዓት ይልቅ የባለሥልጣናት ፈቃድ ወሳኝ በሆነበት አገዛዝ ውስጥ ይህንን መጠበቅ ከንቱ ይመስለኛል፡፡ ግብር ለመክፈል ግብር ከፋዩ የሚጉላላበትና የሚሽቆጠቆጥበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ በዘር ቋጠሮ እና በፖለቲካ ታማኝነት የተመለመሉ ካድሬዎች በተሰገሰጉባቸው ተቋማት ውስጥ ቅን እና የተፋጠነ አገልግሎት መጠበቅም የማይታሰብ ነው፡፡ ከካድሬዎቹ በተረፈው ቦታ ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥበት መንግሥታዊ ተቋም ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሠራተኞች ደግሞ አልቅሰው ከገቡ በኋላ ተገልጋዩን ሕዝብ ሲያስለቅሱ ማየቱ የሰርክ እውነታ ነው፡፡ ጎበዝ፤ ካድሬዎቹም ሆኑ ሌሎቹ በትውውቅና በንቅዘትም ተቀጣሪ የሆኑ ሠራተኞች ክፍያቸውን የሚያገኙት ከግብር ከፋዩ ሕዝብ መሆኑን የሚያስተውሉት አይመስልም፡፡ ከችሎታ/ብቃት ማነስ የከፋው ችግር የቅንነትና የአገልጋይነት መንፈስ መጥፋት ይመስለኛል፡፡ ይህ ትዝብት የሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ተብለው የተቋቋሙ አብዛኛው ተቋማት የሚጋሩት የጋራ ጠባይ ቢሆንም የአገልግሎት አሰጣጡ ብልሽት በወረዳ እና ክፍለ-ከተማ አስተዳደሮች እጅጉን የከፋ ሆኖ ይታያል፡፡ 

እዚህ ላይ የጎላውን ደንቡን፣ ልማዱን ወይም መደበኛ ሁናቴውን (the general rule) ለመናገር እንጂ ከእሳት እንደምትተርፈው ባቄላ አልፎ አልፎ በጎና ቅን አገልጋዮች መኖራቸውን ዘንግቼ አይደለም፡፡ እነዚህን እንደ ልዩ ሁናቴ (exception) የምናያቸውና መደበኛ አሠራሩን የማይወክሉ በመሆናቸው እንጂ፡፡

መቼ ይሆን የቀበሌ/ወረዳ አስተዳደሮች በጸጕረ ልውጦች ሳይሆን በአካባቢው ነዋሪዎችና የሕዝቡን ፍላጎትና ችግር በሚረዱ አመራሮችና ሠራተኞች የሚመራው? ባላፉት ሠላሳ አንድ ዓመታት እኔ ከዐርባ ዓመታት በላይ በኖርሁበት ቀበሌ/ወረዳ ውስጥ በእነዚህ የከተማ ነዋሪዎች አስተዳደር ውስጥ አመራርም ሆነ ተራ ሠራተኛ ሆነው ሲፈራረቁ የነበሩትን አንዳቸውንም አላውቃቸውም፡፡ ነባር ነዋሪውም ባጠቃላይ አያውቃቸውም፡፡ ይኸው ጉዳይ አሁን የበለጠ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ዛሬ እነዚህ የከተማ አስተዳደሮች ክረምት ከበጋ ነዋሪዎችን ከሕግ ውጭ ቤታቸውን በማፍረስና በማፈናቀል በተጠመዱ፣ በጥላቻ በተሞሉና አዲስ አበባ የነዋሪዎቹ/አዲስ አበቤዎች አይደለችም በሚሉ ተረኛ ጐሠኞች እየተሞሉ ነው፡፡ አዲስ አበባን በብቃት ሊመሩና ሊያስተዳድሩ የሚችሉ ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዝናት የመጡ ነዋሪዎች እያሏት አሁንም በውሸት ምርጫ ሽፋን የጸጕረ ልውጦች የ‹ሞግዚት› አስተዳደር ቀጥሏል፡፡ ታዲያ የትኛው ነዋሪ ነው ፍትሕና መልካም አስተዳደር የሚጠብቀው? 

የተነሣሁበትን ጉዳይ አልዘነጋሁትም፡፡ ብሔራዊ መታወቂያ መያዝ የዜጎች መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም (በሕግ የተቀመጡ መሥፈርቶች መሟላታቸውን እያረጋገጠ) ይህንኑ ለዜጎች መስጠት ግዴታው ነው፡፡ የጐሣ ሥርዓቱና ፖለቲካው የቀጠለ ቢሆንም፣ ዲጂታል በተባለው ብሔራዊ መታወቂያ ላይ ጐሣ አለመጻፉ በበጎ መልኩ ባየውም (‹ብሔራዊ› ብሎ የጐሣ ማንነት ማስቀመጡም እርስ በርሱ ተቃራኒ መሆኑ አሳስቧቸው አይመስለኝም) ፣ ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ከሚያካትታቸው መረጃዎች ውስጥ ይኸው የጐሣ ማንነት መካተቱ እና በመረጃ ቋት ውስጥ መያዙ ያለው አገዛዝ ጤናማ ያለመሆኑን እና የወያኔ ቅጥያ መሆኑን አመልካች ነው፡፡ በርእሳችን ዐውድ አነሣነው እንጂ የወያኔን የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› በደም የተገኘ የህልውናችን መሠረት ነው ብለው የሚያምኑት የዐቢይ ኦሕዴድም ሆነ አሁን በአሽከርነት የሰበሰባቸው የወያኔ የእጅ ሥራዎች የሆኑት ጭፍሮች የጐሣ ፖለቲካና ሥርዓትን እያስቀጠሉ ባለበት ሁናቴ ስለ መታወቂያ ነጥሎ መናገሩ  ብዙ ትርጕም ላይሰጥ ይችላል፡፡

ይህ አስተያየት አቅራቢ በታዘባቸው የኮልፌ-ቀራንዮ እና የቂርቆስ ክ/ከተሞች አንዳንድ ወረዳዎች ውስጥ የዲጂታል መታወቂያ አሰጣጡ ሂደት እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ በተለይም ነዋሪው ወረፋ ይዞ እና አስፈላጊውን ፎርማሊቲ አሟልቶ ምዝገባውን ካጠናቀቀ በኋላ መታወቂያውን ለመውሰድ የሚቀጠርበት ጊዜ አንድ ሳምንት ቢሆንም በተግባር ከአንድ እስከ ሁለት ወራት የሚወስድበት ምክንያት በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ኅትመቱ የሚካሄደው በማዕከልም ቢሆን፣ ዛሬ ቴክኖሎጂው ባደገበት ዘመን ስካን ተደርጎ እና ተጠናቅቆ ከነዝርዝር መረጃው የሚላክን ዲጂታል መረጃ ባጭር ጊዜ ውስጥ አትሞ ማከፋፈል ያለተቻለበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል ሕዝብን ማጉላላቱን ባስቸኳይ አቁሞ አፋጣኝ መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል እላለሁ፡፡

Filed in: Amharic