>

አበራ ገንዳ - ጋንጋ የአሰብ ወደብ ኢምንት ማስታወሻ  (በሠሎሞን ለማ ገመቹ)

አበራ ገንዳ – ጋንጋ

የአሰብ ወደብ ኢምንት ማስታወሻ

    በሠሎሞን ለማ ገመቹ.

ዓመታትን ወደኋላ፡፡ በዚያ ብዙ ቤተሰብ ነበር፡፡ ‹‹ነበር እንዲህ ቅርብ ነበር?›› ያሉት ማን ነበሩ? ርግጥ ነው እሳቸውም ያው ‹‹ነበር›› ሆነዋል፡፡ ‹‹ላይፍ ኢዝ ዎዝ ነገር ነው…›› ብላለች ሞልቃቂት፡፡ ሕይወቷ እንደ ውል አልባ ልቃቂት ምስቅልቅሉ ሳይወጣ በፊት የአስብና የምፅዋ ደማቅ ሆቴሎች ልዕልት ነበረች፡፡ ‹‹ዋ! ሁሉም ነገር ያልፋል!…›› አሉ የጥቁር ደሙ አባ መሐሪ? ሞልቃቂት በውበትና በቅብጠት ዓለም ውስጥ አልፋለች፡፡ አባ መሐሪ በወንድነትና በታላቅ የበቀል ሸለቆ ውስጥ በእሳት አለንጋ እየተገረፉ ዘመናቸውን ተሸግረዋል፡፡ ሁለቱም ኖረው፣ ኖረው አልፈዋል፡፡
የሞልቃቂት አልማዝ ውበት ምን ነበር? የቱን ያህል ነበር? ቁንጅናዋ የማረከው፣ ትክለ-ሰውነቷ ያንበረከከው፣ የምርጫዋን ልኬት ያወቀ፣ ወንድነቱን ያበደራት፣ ቀኑን ደማቅ፣ ሌሊቱ ባለ ማራኪ ሕልም ያረገላት፣ በደረጃ ምደባ ፈተናዋ የወደቀ፣ በአጨዋወት ስልቱ በመርቀቁ ልዩ አባ-ወራ መስሎ የኖረ፣ በእሷነቷም ይሁን በገንዘቧ ማዘዝም ይሁን በፈቃዷ መተዳደር የሆነለት… አንደቋመጠባት የቀረ፣ ተ‹‹ተደናጊሬን›› የተደናገረ… የተቁለጨለጨባት፣ ያስሟጠጠችበትና የተሳሳቀችበት፣ ያናናቀችውና የተጠቃቀሰችበት፣ የተወራረደባትና ብዙ ብዙ የወረደባት… እሱ ብቻ… በአሰብ የነበረ፣ ምፅዋ ላይ የሰከረና የከሰረ… ያውቀዋል፡፡
አልማዝ ሞልቃቂት ብቻ አልነበረችም፡፡ በአሰብ አያሌ ተፈጥሮ ከለጋነት ዕድሜ ጋር ምትኃተኛ የውበት ሥዕል የሳለባቸው፣ ቀለመ ደማቆች፣ ትክለ-መልካሞች፣ ትንፋሸ-አረቄዎች፣ ጆኒ ዎከሮች፣ አካለ ላባዎች፣ ዓይነ-ሌባዎች፣ ከንፈረ-ስሶች፣ ተረከዘ-መልካሞች፣ ባለ ሽንጥና ዳሌዎች፣ አማላይ ኩንስንሶች፣ ጠብ-ርግፍ ባዮች፣ ከንፈር አስመጣጭ፣ በስሜት ንዝረት ከአሰብ ሙቀትና ግለት ጋር አቅበጥባጭ ቆነጃጅት ነበሩ፡፡ የዛኑ ያህል በአሰብ እጅግ ብዙ ጎበዛዝትም በጎዳናዎቿና በሆቴሎቿ ተሽቀርቅረውባታል፡፡ ‹‹እንዳማሩ አይሞቱ…›› ነው ‹‹እንዳማሩ አይኖሩ›› ሆኖ ነው እንጂ ነገሩ!? አሰብ ምፅዋ…ማ፤ ትውስታው የትየለሌ ነው፡፡ ነበር?
ግን በጊዜ ዓለም ውስጥ ዕንኳን በአሰብ ጥፍት ቅርት… ባለው፣ ‹‹ዛሬ ይመጣል ነገ…››  እያሉ ተስፈኞች ብዙ ተስፋ እየሰነቁ… በተስፋ እንደማለሉ ዕልም ጭልጥ ብለው፣ ጃጅተው፣ ጎብጠው፣ አህህ! አሄሄ… እያሉም ታመው፣ ደክመው በቀሩበት፤ በሌላውም አካባቢና ሥፍራ ቢሆን ያው የነበረው በነበረበት አልቀጠለም፡፡ በውል ያልያዙት፣ መሠረቱን ያላጠነከሩት፣ ከመግባባት ይልቅ እየተጯጯሁ የተደናቆሩበት፣ እየተጠላለፉ ተደጋግፈናል የሚሉበት፣ እየተሳሳቁ ያሸመቁበት፣ አንዱ ‹‹እናሸንፋለን!›› ሲል ከአንጀቱ ሌላው ግራ ክንዱን ብቻ እያነዘረ… በልቡ ‹‹እናሾፋለን!?›› እያለ የሴራ ገመዱን ሲገምድ፣ ሲቋጥርና ሲፈታ… በኖረበት፤ ዕንኳንስ ሊሆን ይችላል ብለው ያሉት ተጨባጩና መኖር የቻለውም ነገር ቢሆን በነበረበት  ሊቀጥል አልቻለም፡፡ የሳቀው እንደሳቀ አልዘለቀም፡፡ ያዘነም በኃዘኑ ኩሬ ውስጥ እንደሰጠመ አልቀረም፡፡ በውበቱና በአፍላነቱ የሚመካው ሁሉ እስከወዲያኛው በነበረበት አልኖረም፡፡ የሕይወት አዚሙ አንዴ ሲደፋው፣ አንዴ ሲያቀናው ቆይቶ ኖሯል ተብሎ ያልኖረ፣ ከተስፋው የሕይወቱ አዝመራ ላይ አንድ እፍኝ እህል ያልዘገነ፣ አንድ መዳፍ ውሃ ያልተጎነጨ… እንደወጣ የቀረ፣ አንደ ጀገነ… የመነነ፤ በአሰብ ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ የኢትዮጵያ ምስቅልቅል ዓለም ጥቂት አይደለም፡፡
እናም በትውስታ ዐምድነቱ፣ በነበረ ሕይወትነቱ፣ ባለፈ ኑሮ ጓዝነቱ…. የአበራ ገንዳ – ጋንጋ  የትዝታ ዕንጉርጉሮ መዝገብ፤ ከሰፊውና ከግዑዙ የአሰብ ትዝታ ዶሴ ክምችት ውስጥ ተስቦ ከወጣ ወዲህ፤ አንድ ብቻውን መገለጥ ሲጀምረ… ብዙ! እጅግ በጣም ብዙ የኑሮ ነው የሕይወት ዕንቆቅልሽ አለበት፡፡ በመኖር የተኖረ፡፡ ባይኖርም ዛሬ አብሬ ካልኖርኩ እያለ ያስቸገረ፡፡ በችግርና በስቃይም ብቻ ሳይሆን እንደው በደፈናው ‹‹ያ ያሳለፍነው›› የወጣትነት፣ የጉልምስና፣ የልጅነት፣ የጉርምስና ‹‹ዘመን›› እንዴት ነበር? የሚያሰኘው አንዱ፤ የአበራ ገንዳ አሰብ ጥቂት የትዝታ ማኅደር ነው፡፡
እሱ ደግሞ በራሱ ሌላው የትውስታ ዳና ወይም ፋና ወይም ‹‹ፈለግ›› ሊሆን የሚችል ነው፡፡  እንዲያም ሲባል ‹‹ጋንጋ›› የአበራ-ገንዳ ቁራኛ ነው፡፡ ጋንጋም ይሁን አበራ-ገንዳ፣ ካምቦ ሱዳንም ይሁን ሌላው ሌላው…. መንደርና ሠፈር፤ አንዱ በአንዱ ውስጥ ነው፡፡ አንዱ የሌላኛው ባለቀለም ጥለት ነው፡፡ የቀለሙ ዓይትም ብዙ ነው፡፡ ሁሉም ደግሞ በአሰብ ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የባሕር በር፣ ስለ ሃገራችን በሃገራችን፣ በወገናችን ለወገናችን የሆነና የተባለ፣ ስለ ሃበሻ የታላቅነት ሕልም ፍቺ ሲባል በተደከመ ወሰን-አልባ ድካም፣ ብዙዎች የሚባሉ የሃገር ልጆች በአዕምሯቸው የያዙትን የዕድገትና የሥልጣኔ ፍሬን የመቋደስ፣ የስኬቱንም ምርት ወደ ትውልድ የማድረስ… ሸክም ተሸክመው ሽቅብ ቁልቁል ያሉበት ነው፡፡
አሰብ ዝም ብሎ አሰብ አይደለም፡፡ አልነበረምም፡፡ አሰብ ከቢር፣ አሰብ ሰቂር…. ብለን ብቻ በቀላሉ ልናልፈውም አይቻለንም፡፡ ከላይ እስከ ታች አሰብ፣ መርሳ-ፋጡማ፣ መርሳ ጉልጉብ፣ ካምቦ ሱዳን፣ ምፅዋ፣ ዳህላክ፣ ከአንድ ሺኅ ኪሎ ሜትር በላይ ወሰን የነበረውና በጥልቁና በስፋቱ የተዘረጋው…. የባብኤል መንደብ ቁልፍ የውሃ መስመር… የቀይ-ባሕር ዳርቻ፣ አዱሊስ፣ ኪሎማ… ወደብ ክበብ፣ ራሺያ ክበብ፣ ጨረቃ ጉዞ ሆቴል፣ ኒኖ ዲዛረዲ…  ትዝታው ትልቅ ነው፡፡ ትውስታው ጠሊቅ ነበር፡፡
 ትልቅ ነው፣ ጠሊቅ ነው… ሲባል አሰብ እንደው በነጠላው ባለ ብዙ ሕይወታዊ ትዝታ ባለቤት በመሆኑ ብቻም አይደለም፡፡ ትውስታው ዛሬንም የማኖር፣ የአሁንን የቀዘቀዘ ስሜት በነበረ የትውሰታ ግለት የማሞቅ፣ መንፈስን የማኩራት… አንዳች አቅም ያለውም ስለሆነ ጭምር ነው፡፡ ‹‹ሰው በምግብና በመጠጥ ብቻ አይኖርም›› ተብሎ የተፃፈው፣ ተብሎም የተነገረው፣ እየተባለም የሚሰበከው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ለኃይማኖታዊ አስተምህሮ ስርፀት ሲባል ብቻም አይደለም፡፡በትላንት የትዝታና የትውስታ ስንቅ ዛሬን ልጠውልግ የምትለውን ተስፋ በጨዋታ በጨዋታ… ማለምለም ስለሚቻል ነው፡፡ የትላንትን እያሰቡ ትካዜን መርሳት፣ ለነገ ማቀድ፣ ለዕለቱ መራመድ የሚያስችል አንዳች ሞራላዊ አቅም ስለሚያስገኝ ነው፡፡
ደግሞም ትዝታ የታሪክ አብነት፣ አክሊልና ዘውድም ነው፡፡ በራሱ ወግ ማዕረግ አለው፡፡ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለወገን፣ ለሃገር፣ በአጠቃላይ ለብዙኃን ሕልውና ሲባል አንድ የተበረከተ አስተዋፅዖም አለበት፡፡ አንድ ገጽታው ዋዛ ፈዛዛ ቢመስልም ዕንኳ ሌላው ክፍሉና ግዛቱ ሃገራዊና ማኅበረሰባዊ፣ ከፍ ሲልም ሰው የመሆን ያለመሆን ፈተና የተፈተኑበት፣ መራሩንና ወሰን-አልባውን ትግል የታገሉበትም ነው፡፡ አሰብ ላይ፡፡ በዚያ የቀይ ባሕር ሰፊ ዳርቻ… ከአርባ ዓመታት በፊትና በፊት ጀምሮ፤ እስከ አርባኛው ዘመን ማክተሚያ የመጨረሻ ወር መባቻ ድረስ ሰው ከመልከዓ-ምድሩ ጋር፣ ከዱር ከቤት እንስሳቱ፣ ከአዕዋፋቱ፣ ጸጥ ረጭ ካለውና ከሚወብቀው… ተፈጥሮ፣ በውሃው ውስጥ ከሚኖሩት ፍጥረታት፣ በአየሩና በአሸዋው፣ እሳተ ገሞራ… ከፈጠራቸው ሻካራና ጠጣር አለቶች ስር… ከሚርመሰመሱትና ከሚያሸምቁት ነፍሳት ጋር፤ የሰው ልጅ በአንድነትና በፍቅር ስሜት ብቻም ሳይሆን በሽኩቻና በርክቻም… ሰው ለመሆን ጥሯል፡፡ ተጣጥሯል፡፡ ታላቂቱን ኢትዮጵያን ለመመሥረት በየሙያው ዘርፉ ላብና ወዙን ሲያንጠባጥብና ሲያስመጥጥ… ኢትዮጵያዊው ሰው ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ደሙን፣ ሥጋ አጥንቱን ገብሯል፡፡
አበራ ገንዳ – ጋንጋ የአሰብ ከቢር፣ የአሰብ ሰቂር… አንድ ትዝታ የሚሆነው ከፍ ሲል በተገለጸውና በሌላውም መሰል ምክንያት ነው፡፡ በዚያ መመዘኛ ይህ ወግ ወይም አጭር የትውስታ ማጫሪያ ጥሁፍ… የአንድ የእናት ኢትዮጵያ ታሪክ ጥግ ማመልከቻም ነው፡፡ አሰብ፣ አበራ ገንዳ፣ ጋንጋ፣ ሠላሳኛ፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ ማጣሪያ አውታር፣ ብርቱዎቹ የነዳጅ ማጣሪያው ወዝ-አደሮች እነ ጋሽ ይመርና ይማም…፣ የባሕር ኃይላችን ባልደረቦች፣ የአየር መከላከያ ምድብ ጥንቁቅ ወታደሮች፣ የንግድ መርከብ ሠራተኞች፣ ሌሎቹ ሸቃላዮች፣ ካምፕ ጠባቂዋና ተወዳጇ ውሻ ‹‹ጃክሰን››… ከአሰብ ወደብ ዳርቻ እስከ ‹‹መርሳ ፋጡማ›› እጅግ ከልቧ የምታፈቅራቸውን የአየር መቃወሚያ ከፍል ባልደረቦች ላለመለየት ብላ … በቀይ ባሕር ላይ ያለማቋረጥ ከሰባት ኪሎ ሜትር… በላይ የዋኘችው ዋና፣ የመቶ አለቃ ኢዶሳና የ‹‹ጃክሰን›› አዝናኝ ገጠመኝ ጉዳይ፣ በሰባት ብር የሚቆረጠው ሥጋ፣ ከስልሳ እስከ ሰማኒያ ብር ድረስ እየተሸመተ የሚንቆረቆረው ውስኪ፣ ደራይ ጂን… ከዚያ ወዲያ ደስታ ተድላው፣ ውሻን እንደ በግ ተሸክሞ በስካር መንፈስ ወደ ቤት ማዝገሙ… ሌላ ሌላውም ትዝታና የነበረ ጨዋታና ኑሮ፤ አበራ ገንዳ – ጋንጋ አሰብ ቀረ ድሮ፡፡ በጤናና በፍቅር ያሰንብትልኝ የተከበራችሁ አንባቢያን፡፡
 (በሳምንታዊዋ ግዮን መፅሔት ለንባብ የቀረበ)
Filed in: Amharic