>

የኢህአዴግ የሥልጣን አሞሮች... --- ከገነት ዘውዴ እስከ አዳነች አቤቤ! አሳፍ ሀይሉ

የኢህአዴግ የሥልጣን አሞሮች…
— ከገነት ዘውዴ እስከ አዳነች አቤቤ!
አሳፍ ሀይሉ

ሲጀመር። ‹‹ፖሊሲያችንን እስካፈጸመ ድረስ ገበሬንም አምጥተን ትምህርት ሚኒስትር እናደርጋለን›› ሲል ነበር “መሃይምነት ይለምልም!” የሚል የፓርቲውን መፈክር በድፍረት የተናገረው። መለስ ዜናዊ።
ወደ ሥልጣን በወጣ ማግሥት የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሰብስቦ – ‹‹ማንም ሰው የትኛውንም ዓይነት ሹመት መወጣት ይችላል!›› ሲል በቴሌቪዥን ተደመጠ አብይ አህመድ።
ኢትዮጵያ በወጉ ብስለትንና አንጋፋ የሙያ ልምድን በተላበሱ ሰዎቿ እንዳትመራ አወላግዶ የሚያስኬዳት በፊት ለፊትና በድፍረት እየታወጀ የሚቀጥል ኃይለኛ ፀረ-ዕውቀት፣ ፀረ-ሙያ፣ ፀረ-ፕሮፌሽናሊዝም የመንግሥት ፖሊሲ አለ፡፡
በተቋማት ደረጃ ብዙ ነገራችን እንዳልነበር ሆኖ የወደመውም በዚህ ዓይነቱ ኢህአዴጋዊ የአላዋቂዎች ፍልስፍና ሳቢያ ነው፡፡ በመንግሥት አመራር ውስጥ ሙያዊ ህይወት ገደል መግባቱ የብዙ ሀገራዊ ውድቀታችን ምንጭ ነው፡፡
ዛሬ አንድ ትልቅ ፕሮፌሽንን የሚጠይቅ ተቋምን መምራት ያለበት ትክክለኛው በዘርፉ የተካነው ሰው ቀርቶ – ሌላ የኢህአዴግ ዲግሪዎች የተለጣጠፈለት ለሙያው ባዕድ የሆነ ተላላፊ የፓርቲ አስፈጻሚ ወንበሩ ላይ በጊዜያዊነት ጉብ ይላል፡፡
ጉብ ብሎም ለዘለቄታው ቢቀጥል እኮ የሆነ በቆይታ ሊማርና ሊያዳብር የሚችለው ስትራቴጂክ ዕውቀትና ልምድ፣ ራዕይና ክህሎት እኮ ይኖራል መቼም ሰው እስከሆነ ድረስ፡፡ ይሄ ግን በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ አይታሰብም፡፡
በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ ሥልጣን እንደ ጉልቻ ከአንዱ አላዋቂ ወደ ሌላው ያለማቋረጥ ይሽከረከራል፡፡ በዓለም ታሪክ እጅግ አሳፋሪ ሆኖ መገኘት ምንም መስሎ በማይሰማው በኢህአዴግ ዘመን ነው የህግ ሙያ የሌለው ሰው – የፍትህ ሚኒስትር ተደርጎ ተሾሞ ያየነው፡፡
የፕሮፌሽናሊዝም ሞት የሀገራችን የመንግሥት ሥርዓት ክሽፈት አንዱ ማሳያው ነው፡፡ በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ ሙያ እና የሙያዊ ዕውቀት አስፈላጊነት ገደል ገብቷል፡፡
በበረሃ ትግል (ጦርነት) ለበርካታ ዓመታት በመሠማራታቸው የተነሳ ከምንም ዓይነት የረባ ዘመናዊ ትምህርትም ሆነ ሙያዊ ዕውቀት ርቀው የቆዩት የህወኀት አባላትና መሪዎች – የሀገሪቱን ሥልጣን ለመቆጣጠር ሲሉ – የግድ ‹‹ሙያን›› እና ‹‹ሙያዊ ህይወትን›› እንደ አላስፈላጊ መሥፈርት አድርገው ወደ መቁጠር ዞሩ። እስካሁንም የቀጠለው ይሄው መመሪያ ነው፡፡
በአንድ መስክ ለአንቱታ ደረጃ ከደረሰ የዘርፉ ባለሙያ፣ አሊያም በሙያው ዘርፍ የዳበረ የዕውቀትና የሥራ ልምድ ከተላበሰ አንጋፋ ዜጋ ይልቅ – በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ – ከምንም ነገር በላይ የፓርቲው አባልነትና ጋሻ-ጃግሬነት፣ ታማኝነትና አደግዳጊነት ትልቁ የሥልጣንና የመሪነት መስፈርት እንዲሆን ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሥርዓት መንኮታኮት “ሀ” ብሎ የጀመረው በዚህ ዓይነቱ የክሽፈት እንድርድሮሽ ነው፡፡
በእርግጥ ይህ የጨዋ ድፍረት የተጀመረው በእርግጥ ዛሬ ላይ አይደለም፡፡ ሥልጣን በአምቻ-ጋብቻ ከሚገኝበት ከፊውዳሉ ዘመን ጀምሮ፣ ቆራጥ ነው፣ አብዮታዊ ነው፣ ተራማጅ ነው፣ ወዘተ የሚል ቅፅል እየተለጠፈ “ሥልጣን የሰፊው ህዝብ ነው” በሚል ሽፋን ለበታች ወታደርና አብዮት ጠባቂ እስከሚታደልበት እስከ ወታደራዊው ሶሻሊስታዊ መንግሥት ክሩ የሚመዘዝ ችግር ነው።
በኢህአዴግ ዘመን የሀገራችንን ተቋማት ያውሸለሸላቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ቦታ ማጣቱ ብቻ ሳይሆን – ኢትዮጵያን የሚመራው መንግሥት የዕውቀት-ፀር እና የሙያ-ፀር ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ ነው፡፡
በዘመነ ኢህአዴግ ትልልቅ ሀገራዊ ፋይዳዎችን ሊያበረክቱ ይችሉ የነበሩ ግዙፍ ሀገራዊ ተቋማት ተውሸልሽለው የቀሩት በየዘርፉ በሳል የህይወት ልምድና ዕውቀትን ባካበቱ አንጋፋ ኢትዮጵያውያን የሚመራ ተቋም እንዳይኖር በመደረጉ ነው፡፡
ህወኀት-ኢህአዴግ ሀገርንና ተቋማትን በባዕድ ዘዋሪ ሰዎች መምራትን – ከፍተኛው ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡
ይህን ረዥም ትንታኔና ጊዜ የሚፈጅ አብይ ርዕሰ ጉዳይ ለጊዜው ተወት አድርገን የዘመኑን ኢህአዴጋዊ ዘዋሪዎች ሥልጣን ለማየት የፓርቲው የሥልጣን አሞሮች – እንዴት እንደ ፌንጣ ወይ እንደ ጉሬዛ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የማይገናኝ ቦታ እየዘለሉ እንደሚኖሩ መመልከት በቂ ነው።
ለምሳሌ ይህን ኢህአዴጋዊ የሹመት መመሪያ በዚህች ሁለት ዓመት ብቻ በሀገራችን ከተስተናገዱ ተሿሚዎች ቀበላሉ አይቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለ ሀገሪቱ የሥልጣን አሞሮች ከዚህ የተሻለ ማሳያ ማስረጃም የለም፡፡ ጥቂቶቹን እንያቸው፡-
አዳነች አቤቤ
=========
መጀመሪያ የጉምሩክ ባለሥልጣን ነበረች፣ ቀጥሎ ጠቅላይ አቃቤ ህግ (ማለትም የፍትህ ሚኒስትር) ሆነች፣ አሁን ደሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ፡፡ (እግዚአብሔር ያሳየን!) ጉምሩክን ለመምራት ስለ ጉምሩኩ ዝርዝርና አጠቃላይ አሠራር ጥልቅ ግንዛቤው ያለው ሰው – ኬሪሩን (ማለትም ሙያዊ ህይወቱን) በዚያ ዘርፍ ያሰማራ ሰው አያስፈልግም ለመሆኑ?
ጉምሩክ ባለሥልጣንን በወጉ ሳይመራስ እንዴት ወደ ፍትህ ሚኒስቴር? ፍትህን በሚገባ ሳያስከብርስ እሱን እርግፍ አድርጎ ወደ ከንቲባነት? ከኢኮኖሚ ወደ ህግ፣ ከህግ ወደ አስተዳደር፣ ከአስተዳደር ወደ ብሄር ፖለቲካ፡፡ መገለባበጥ ነው እንደጉድ፡፡
/በነገራችን ላይ፦ ይሄ የአዳነች አቤቤ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የምናወራው ስለእሷ አይደለም፡፡ አጠቃላይ ኢህአዴግን ስለተጣባው የመገለባበጥ አባዜ ነው፡፡/
ጉልቻው ያለማቋረጥ ይቀያየራል፡፡ ተቋማት ተቋማቱን የሚያውቅም፣ በትክክል እንደቃሉ ‹‹የሚመራ››ም መሪ የላቸውም፡፡
በሀገራችን በዘርፉ ሙያው ያካበተ ልምድና ዕውቀት ያለው መሪ ሳይሆን ያለው – ከአውቶብስ እንደሚወርዱና እንደሚሳፈሩ መንገደኞች – በፍጥነት ከአንዱ ተቋም ወደሌላ የማይገናኝ ተቋም እየተንቀዠቀዠ የሚሳፈር – የሥልጣን መንገደኛ ነው ያለው፡፡
አሞሮቹ በሀገሪቱ ሥልጣኖች ዙሪያ ሥጋ እንዳዩ አሞሮች እያንዣበቡ ይኖራሉ፡፡ ያገኙትንና የደረሳቸውን ሥልጣን እያነሱ መብረራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ድጋሚ ደግሞ ያርፉና ሌላ የሥልጣን ሥጋ ይወረወርላቸዋል፡፡ እንዲያ እንዲያ እያሉ የሥልጣን አሞሮቹ ዓላማ-የለሽ የሥልጣን በረራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ሀገር፣ ተቋም፣ ሙያ (ፕሮፌሽናሊዝም)፣ የማይቋረጥና በፅናት የሚተጋ ሀገራዊ ራዕይ፣ ዕውቀትና ባለዕውቀቶች – በእነዚህ ሁሉ የፓርቲው የሥልጣን ሻሞዎች ውስጥ – አንዳች ቦታ የላቸውም፡፡ ስለዚህ አሳዛኛ ነገር ነው የምናወራው፡፡ እንጂ ስለ አንዲት አዳነች አቤቤ አይደለም፡፡ ስለ ሁሉም ነው፡፡ ስለ ሁሉም የሥርዓቱ እውነተኛ ገፅታ። ነው፡፡
ለማ መገርሳ
========
በመጀመሪያ ወታደር ነበር፣ ቀጥሎ የደህንነት ሹም ሆነ፣ ቀጥሎ የኦሮሚያ ፕሬዚደንት ሆነ፣ ቀጥሎ የፌዴሬሽን ምክርቤት አባል፣ ቀጥሎ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ አሁን ከጨዋታ ውጪ፡፡
አብይ (አብዮት) አህመድ
================
መጀመሪያ ወታደር፣ ቀጥሎ የደህንነት ሹም (የኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር) ፣ ቀጥሎ የሳይንስና የመረጃ ዳይሬክተር፣ ቀጥሎ የቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የአጋሮ ተመራጭ የፓርላማ አባል፣ ቀጥሎ የኦሮሚያ ክልል ቤቶችና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የኦህዴድ ሊቀመንበር፣ ቀጥሎ የኢህአዴግ ሊቀመንበር፣ ቀጥሎ ደሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡
ሽፈራው ሽጉጤ
==========
መጀመሪያ መምህር ነበር፣ ከዚያ ከሲቪል ሰርቪስ በአካውንቲንግ ሲመረቅ ኦዲተር ሆነ፣ ቀጥሎ የደቡብ ክልል ፕሬዚደንት፣ ቀጥሎ የትምህርት ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ከጨዋታ ውጪ፡፡
ደመቀ መኮንን ሀሰን
=============
መጀመሪያ የባዮሎጂ መምህር ነበር። ቀጥሎ የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት ሆነ። ቀጥሎ የፓርላማ አባል ሆነ። ቀጥሎ የትምህርት ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የብአዴን ሊቀመንበር፣ ቀጥሎ ለ7 ዓመት ደሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡
አምባቸው መኮንን
============
መጀመሪያ ታጋይ ነበር። ከዚያ በርቀት ትምህርት ሃይስኩልን አጠናቀቀ። ቀጥሎ ከሲቪል ሰርቪስ፣ ቀጥሎ ከደቡብ ኮሪያና ከእንግሊዝ ዲግሪዎችን አገኘ። ቀጠለና የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር፣ ቀጥሎ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነ።
ቀጥሎ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ዋና ዳይሬክተር፣ ቀጥሎ የአማራ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የጠቅላይ ሚኒስትር የመሠረተ ልማት አማካሪ፣ በመጨረሻም የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነ።
ታከለ ኡማ
=======
ሃይስኩልን ከአምቦ አጠናቅቆ፣ በመጀመሪያ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ፣ ቀጥሎ በኢንቫይሮመንታል ሳይንስ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል፣ ቀጥሎ የሱሉልታ ከንቲባ፣ ቀጥሎ የሆለታ ከንቲባ፣ ቀጥሎ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የአዲስ አበባ ከንቲባ፣ አሁን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር፡፡
ሽመልስ አብዲሳ
===========
ከጊንጪና ከአምቦ የመጀመሪያና ሃይስኩል ትምህርቱን አጠናቀቀ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍናና በሂውማንራይትስ፣ ከዩኒሳ በሊደርሺፕ ዲግሪዎችን አግኝቷል፡፡
ቀጥሎ የኦሮሚያ ፕሬዚደንት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነ። ቀጥሎ የኦሮሚያ ከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነ። ቀጥሎ ደሞ የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነ። ከዚያ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ቀጥሎ የኦህዴድና የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነ። አሁን ደሞ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት፡፡
አይሻ መሀመድ
==========
በሲቪል ኢንጂነሪንግና ሊደርሺፕ ዲግሪዎችን አግኝታለች፡፡ ቀጥሎ የአፋር ፓርቲ (አብዲፓ) አባልና አመራር ሆነች። ቀጥሎ የአፋር ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ ሆነች። ቀጥሎ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ደሞ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ለ10 ወር የመከላከያ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ደሞ ድጋሚ የከተማ ኮንስትራክሽንና ልማት ሚኒስትር፡፡
ሲራጅ ፈጌሳ
========
የደኢህዴን ምክትል ሊቀመንበር፣ ቀጥሎ የመከላከያ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ፣ ቀጥሎ የትራንስፖርት ሚኒስትር፡፡
ወርቅነህ ገበየሁ
===========
በህግ ተመርቋል፣ በተልዕኮ ተጨማሪ ዲግሪዎችን አግኝቷል፣ መጀመሪያ የፖሊስ ኮሚሽነር፣ ቀጥሎ ኮሚሽነርነቱን ትቶ የፓርላማ ተወዳዳሪ፣ ቀጥሎ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ ቀጥሎ የትራንስፖርት ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የተባበሩት መንግስታት አምባሳደር፣ ቀጥሎ የኢጋድ ዳይሬክተር፡፡
ተሾመ ቶጋ
=======
የኢኮኖሚክስ ምሩቅ ነው፡፡ መጀመሪያ የደኢህዴን አባልና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነ። ቀጥሎ በሶስት የአረብ ሀገሮች አምባሳደር ተደርጎ እየተሾመ ተሽከረከረ። ቀጥሎ የስፖርት ሚኒስትር ሆነ። ቀጥሎ የፓርላማ አፈጉባዔ፣ ቀጥሎ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር፣ አሁን ደሞ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር፡፡
ሞቱማ መቃሳ
=========
የኦህዴድ አባልና አመራር ነበር። ቀጥሎ የፓርላማ አባል ሆነ። ቀጥሎ ለአጭር ጊዜ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነ። ቀጥሎ ድጋሚ ወደ ፓርላማ አባልነቱ ተመለሰ፡፡
ተመስገን ጥሩነህ
===========
መጀመሪያ ወታደር ነበር። ቀጥሎ የብአዴን አባል ሆነ። ቀጥሎ በኮምፒውተር ሳይንስና ሊደርሺፕ ዲግሪዎች አገኘ፣ ቀጥሎ የአማራ ክልል የፀጥታ አማካሪ ሆነ። ቀጥሎ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ፣ ቀጥሎ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ፤ ቀጥሎ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነ።
ቀጥሎ የደህንነት ሹም (የኢንሳ ኃላፊና ዋና ዳይሬክተር)፣ ቀጥሎ የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣ ቀጥሎ የመከላከያ መረጃ መምሪያዎች ኃላፊ፣ ቀጥሎ የጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ፣ ቀጥሎ የአማራ ክልል ፕሬዚደንት፡፡
አባዱላ ገመዳ
=========
መጀመሪያ ወታደር ነበር። ሲጀምር የደርግ ወታደር፣ በወያኔ ሲማረክ ታጋይ፣ በመከላከያ ኃላፊነቶች እስከ ሜጀር ጄነራል ማዕረግ የደረሰ ወታደር። በመቀጠልም የኦህዴድ መሥራችና አመራር አባል ሆነ። ቀጥሎ ከቻይና ሚሊቴሪ ሊደርሺፕና በተልዕኮ በማኔጅመንት ዲግሪዎችን አገኘ።
ቀጥሎ ሜጀር ጄነራልነቱን ውድቅ አድርጎ በ”አቶ” በመተካት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ሆነ። ቀጥሎ የፓርላማ አፈጉባዔ፣ ቀጥሎ የጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ፣ አሁን የጠቅላይ ሚኒስቴር የፖሊሲ አማካሪና የደቡብ ሕዝቦች የበላይ ጠባቂ፡፡
ቴድሮስ አድሃኖም
===========
የህክምና ዲግሪ አግኝቷል፣ ቀጥሎ የህወሃት አባል፣ ቀጥሎ የትግራይ ጤና ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር፡፡
በታጋይነቱ ላይ እንደሌሎቹ ከሙያው ርቆ ብዙ ሳይረግጥ ከርሞ፣ በስተመጨረሻም በኢህአዴግ መንግሥት ሎቢ በታገዘና አንድ ግለሰብን ለስልጣን ለማብቃት ብዙ ሚሊዮን ብሮች በተከሰከሱበት የዲፕሎማሲ ዘመቻ ቢያንስ ለሙያው ወደሚቀርብ ዓለማቀፍ ሥልጣን በቅቷልና ተመስገን ነው፡፡
ብንለው፣ ብንለው የሥልጣን አሞሮቹ ያው ናቸው። የሚሽከረከሩበት ወንበር ተዘርዝሮ የሚያልቅም አይደለም። በቃኝ የለም። ይሄ ከሙያዬ ጋር አይዛመድም የለም። አላውቅም የለም። ምንተ-እፍረትና ይሉኝታም የለም።
ጥንብ ያየ አሞራ እዚያው ሲሽከረከር ውሎ እንደሚያድር። ሽሚያ ብቻ። የኢህአዴግ ተሽከርካሪ ባለሥልጣናት ታሪክ፣ የአሞሮች ሽሚያ ታሪክ ነው።
አሁንም ሥልጣኖች መገለባበጣቸው አላባራም፡፡ የሥልጣን አሞሮቹም አሁንም መሽከርከራቸውን አላቆሙም፡፡ ሙያዊ ህይወትና አንጋፋ ልምድ ዜሮ ገብተዋል፡፡ የሥልጣን ሥጋዎች እንደ ቅርጫ ለባለዕድለኞች ይበተናሉ፡፡
ሀገር በዕውቀት፣ በልምድ፣ በያንዳንዱ ሙያ ራሱ ሙያው ባፈራቸው ዕውቅ ፕሮፌሽናሎች የምትመራ መሆኗ ቀርቶ – የኢህአዴግ የሥልጣን አሞሮች መጫወቻ ከሆነች ቆየች፡፡ ከገነት ዘውዴ እስከ አዳነች አቤቤ፡፡ እና ገና ወደፊትም፡፡
የመንግሥት ተቋማት ተረኛ ተጓዦችን የሚጭኑና የሚያራግፉ የጊዜያዊ መንገደኛ ተርሚናሎች ሆነዋል፡፡ አሞሮቹም በያረፉበት ወንበር የቻሉትን ቀነጣጥበው፣ ዕድሜ-ልካቸውን ከሥልጣን ተጎራብተው፣ መብረራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እኛም ለጉድ የፈጠረን ዕድሜ-ልካችንን ወደነዚያው ተሽከርካሪ ሥልጣናት አንጋጠን ማላዘናችንን እንቀጥላለን፡፡
በእነዚያው የኢህአዴግ የሥልጣን አሞሮች፣ በእነዚያው ባሉበት የሚሽከረከሩ ፖሊሲዎች፣ በእነዚያው ተሽከርካሪ ሥልጣናት፣ በእነዚያው ተሽከርካሪ አጋፋሪዎች፣ በዚያው በምናውቀው የአፈናና የብሔርብሔረሰብ ቅርምት ውስጥ እየዳከርን፣ ምን ዓይነት የተለየ ለውጥ ነው የምንጠብቀው?
በበኩሌ አላውቅም። ተጨባጩ እውነታና ምኞታችን አይገናኝም። ፍላጎታችን አይገባኝም። በትክክል የገባው ሰውም አላጋጠመኝም። ሀገር የምትፈርሰው ግን እንዲህ እንደ አሁኑ፣ እንዲህ እንደ ዋዛ ሁሉም ሁሉን ነገር ለአሞሮቹ ጥሎ ነገርዓለሙን እርግፍ አድርጎ ሲተወው ነው። ነገሬን አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic