>

ጠ/ሚ/ አብይ አህመድ ለፓርላማው በሰሜን ኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ጦርነት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠየቁ....!!! (ተስፋለም ወልደየስ)

ጠ/ሚ/ አብይ አህመድ ለፓርላማው በሰሜን ኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ጦርነት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠየቁ….!!!

በተስፋለም ወልደየስ

 

በሰሜን   ኢትዮጵያ ባሉ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበላቸው። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲን ወክለው የተወካዮች ምክር ቤትን የተቀላቀሉ አራት የፓርላማ አባላት ናቸው።

የፓርላማ አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲጠሩላቸው የሚጠይቀውን ደብዳቤ ለተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ያስገቡት ባለፈው አርብ ጥቅምት 12፤ 2014 መሆኑን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃል ምላሽ እንዲሰጡባቸው ከተጠየቁ ጉዳዮች መካከል፤ የኢፌዲሪ መንግስት “በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በምን ያህል ጊዜ የማጠናቀቅ” እቅድ እንዳለው ነው።

የፌደራል መንግስት ጦርነቱን ካጠናቀቀ በኋላ “በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎችን በምን ያህል ጊዜ ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያብራሩላቸው እንደሚፈልጉ የኢዜማ የፓርላማ ተመራጮች በደብዳቤያቸው በተጨማሪነት ጠይቀዋል። አራቱ የፓርላማ አባላት የጦርነቱን “ዘለቄታዊ መፍትሔ” የተመለከተ ጥያቄም በደብዳቤያቸው አንስተዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት “በሀገር ህልውና ላይ የተደቀነ አደጋ” ሲሉ የጠሩት የፓርላማ አባላቱ፤ ይህንን “ለመከላከል እና ለማክሸፍ” ጥረት እየተደረገ እንዳለ እንደሚረዱ በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል። ሆኖም ይህን መሰል አደጋ “በድጋሚ እንዳይከሰት እና ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲሰጠው” በመንግስት በኩል ምን አይነት “ጥንቃቄ” እየተደረገ እንደሚገኝ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ማግኘት እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው የፓርላማ አባላቱ ባለ አንድ ገጽ ደብዳቤ ላይ አጽንኦት ተሰጥቶት የተነሳው ሌላው ጉዳይ፤ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሚወጡ መረጃዎች ስርጭት ነው። የፓርላማ አባላቱ፤ ፓርቲያቸው ከሁለት ወር በፊት የሰሜኑን ጦርነት በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ያነሳውን የ“አንድ ወጥ የእዝ ሰንሰለት” አካሄድ፤ በመረጃ ስርጭት ላይም እንዲተገበር እንደሚሹ ጥቆማ ሰጥተዋል።

“ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሚወጡ መረጃዎችን አንድ ወጥ እና ከአንድ ማዕከል የሚወጡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት ይስተዋላል” ሲሉ በደብዳቤያቸው የተቹት የፓርላማ አባላቱ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ በመንግስት በኩል የታቀደ ነገር ካለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል። መንግስት “በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚሰራጩ የተለያዩ የሀሰት እና አደናጋሪ መረጃዎችን ለመቆጣጠር” እያከናወነ ስላለው ስራም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያስረዱ ጥያቄ አቅርበዋል።

የኢዜማ የፓርላማ ተመራጮች ለእነዚህ ጥያቄዎቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የቃል ምላሽ እንዲሰጡ የጠየቁት፤ የምክር ቤቱን የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብን በመጥቀስ ነው። በ2008 ዓ.ም. የወጣው የተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወር አንድ ጊዜ የቃል መልስ የሚሰጥበት የአንድ ሰዓት የጥያቄ ጊዜ ይኖረዋል” ሲል ይደነግጋል።

በደንቡ መሰረት ማንኛውም የቃል መልስ የሚፈልግ ጥያቄ የሚያቀርብ የምክር ቤት አባል ጥያቄውን ከአስር ቀን በፊት ለአፈ-ጉባኤው በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት። ሆኖም “ለህዝብ ጠቀሜታ ያለው አስቸኳይ ጥያቄ” በሚቀርብበት ጊዜ፤ ከአስር ቀን ባነሰ ማስታወቂያ፣ በአፈ ጉባኤው ፍቃድ ለምክር ቤቱ ሊቀርብ እንደሚችል ደንቡ ያስቀምጣል። የኢዜማ የፓርላማ አባላት “የአስቸኳይ ጥያቄ” አቀራረብን ቢከተሉም በአፈ ጉባኤው ጽህፈት ቤት በኩል እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙ ምንጮች ገልጸዋል።

ከሶስት ሳምንት በፊት መስከረም 24 የምስረታ ጉባኤውን ባደረገው በስድስተኛው ፓርላማ፤ ኢዜማን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአጠቃላይ የያዟቸው የፓርላማ መቀመጫዎች 11 ናቸው። ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ በአምስት መቀመጫዎች አብላጫ ቦታ የያዘው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ነው። በገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባላት በተሞላው ስድስተኛው ፓርላማ፤ ከአስራ አንዱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በተጨማሪ አራት የግል ዕጩዎች መቀመጫዎች ማግኘታቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

Filed in: Amharic