>
5:18 pm - Friday June 16, 0856

እውን ክርስትና ለአገር ዕድገት እንቅፋት ሆኗል? (ከይኄይስ እውነቱ)

እውን ክርስትና ለአገር ዕድገት እንቅፋት ሆኗል?

ከይኄይስ እውነቱ

ይህን ርእሰ ጉዳይ ኢትዮጵያ-ጠል አገዛዞች ደጋግመው ሲያነሡት ሰምቼአለሁ፡፡ የእነርሱ ዓላማ ይገባኛል፡፡ ክርስቲያን ነን ከሚሉ በተለይም ከተዋሕዶ ልጆች ሲነሣ ግን ግራ ያጋባል፡፡ ልክ አማራ ነኝ ብሎ አማራውን በግብር አባቶቹ ወያኔዎች የሚያስፈጀውን ዐቢይ እንደሚደግፍ ሆዳም አማራ ማለት ነው፡፡ በቅንነት ያለ ዕውቀት የተነሣ ወይስ ሌላ ፍላጎትና ዓላማ (motive) ይኑረው ፈጣሪ አምላክ ይወቀው፡፡ በመሠረቱ ጥያቄው የሃይማኖትን በቊዔት (ፋይዳ) ቢመለከትም ይህ ጽሑፍ ወደዛ ዝርዝር ውስጥ የመግባት ዓላማ የለውም፡፡

ክርስትናን ወይም በተቋም ደረጃ አብዛኛውን ክርስቲያን ምእመን የምትወክለው የኢትዮጵያ ርትዕት (ኦርቶዶክስ) ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአገር ዕድገት እንቅፋት ነች የሚለው አመለካከት መነሻው (ከሮም 100 ዓመታት አስቀድሞ ክርስትናን የተቀበለችውን – ቀለም በጥብጣ፣ ብርእ ቀርፃ፣ ብራና ደምጣ፣ መጽሐፍ ጽፋና ደጕሳ ምእመኗን በሃይማኖት በምግባር ስታነፅ የነበረችውን ኢትዮጵያን) አረመኔዎች ናቸው ላሠልጥናቸው በሚል ቅጥፈት ሽፋን ቅኝ ለመግዛት የመጣው የፋሽት ወራሪ ጥልያን መሠረተ አስተሳሰብ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ምዕራባውያን የተባሉት በተለይም (the so-called ‘global empire/coroporatocracy)’ designed and led by the Western powers, especially that of the US Government, the international financial institutions (IBRD, IMF, WTO, etc) and international corporations የሚያራምዱትና በተግባርም የሚያስፈጽሙት አፍራሽ ተልእኮ ነው፡፡  በየአዳጊ አገሩ ደግሞ የዚህን ‹ኢምፓየር› ተልእኮ አስፈጻሚ የሆኑ ሕዝባቸውንና አገራቸውን እንዲሁም ብሔራዊ ምሥጢራትን የሚሸጡ ቅጥረኛ አምባገነን አገዛዞችና ገዥዎች አሉ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ አለመታደል ሆኖ ላለፉት ሠላሳ አንድ ዓመታት የጐሣ ፖለቲካና ሥርዓት ያሠለጠኑት አገዛዞች ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ቢያንስ አገር የሚወድና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር ገዥ ቢኖርን እንኳ ከሕዝብ ጋር የ‹ዓለም አቀፍ ጉልበተኞቹን› ተጽእኖ መቀነስ ይቻል ነበር፡፡ እውነተኛው ችግር ያለው ግን ኢትዮጵያዊ አጀንዳ የሌላቸው ጊዜ የሰጣቸው ሀገር-በቀል ጉልበተኞቹ ጋር ነው፡፡

ክርስትና ኢትዮጵያን ጎድቷታል የሚል አስተሳሰብ ክርስትናን እና ክርስቲያናዊ እሤቶችን ካለመረዳት የሚመነጭ ይመስላል፡፡ ክርስትና አንድ ሕዝብን ወይም አገርን ይጎዳል ስንል በሌላ አነጋገር የሚታየውንና የማይታዩትን ዓለማት ካለመኖር ወደመኖር አምጥቶ የፈጠረ/ያስገኘ፣ በመግቦቱና በጥባቆቱ በሥርዓት የሚያስተዳድር አምላክ አለ ብለን የምናምነው እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱሳት መጻሕፍት አማካይነት የሰው ልጆች ዐረፍተ ዘመናቸው እስኪገታ ድረስ በአካለ ሥጋ ለሚኖሩት ሕይወት መመሪያ እንዲሆናቸው የተጻፈላቸው ቅዱስ ቃል እና ራሱ ባለቤቱ ከኀጢአት በስተቀር ለበጎ ሥራ ሁሉ አብነት ሆኖ በተግባር ያሳየው ሕይወት ወይም አምላካዊ ዕቅድ ከንቱ ነው ወደሚል ድምዳሜ የሚያደርስ ይሆናል፡፡  

በኢትዮጵያ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሲሰጥ የቆየውና አሁንም የቀጠለው ጥንታዊውና ባህላዊው የአብነት ትምህርት ለሀገር-በቀል ዕውቀትና ጥበብ፣ ሥነ-ጥበብና ኪነ-ጥበብ መሠረት መሆኑን እና ትምህርት ቤቶቹም ቀደምት አድባረ-ዕውቀት (ዩኒቨርስቲዎች) መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የአብነት ትምህርት ይዘት በዋናነት ሃይማኖታዊ ቢሆንም በሥነጽሑፍ የተላለፉት ቅርሶች የፍልስፍና፣ የሥነ ፈለክ፣ የሥነ ከዋክብት፣ ሥነ ሥዕል፣ ሥነ ሕይወት (ሰው፣ ዕፅዋትና እንስሳትን) ጥናትን የሚመለከቱ መሆናቸው፤ ምንም እንኳን እነዚህን ሀገር-በቀል ዕውቀቶች ወደ ዘመናዊው ትምህርት ለማሸጋገር በገዢዎችም ሆነ በተከታታይ ትውልድ የተደረጉ ሙከራዎች አናሳ ቢሆኑም ዕውቀቶቹ ለዘመናዊው ትምህርት ታላቅ ፋይዳ ያላቸው መሆኑ ጥርጥር የለውም፤ ሊቃውንቱ ዘመናዊው ትምህርት ሲጀመር በቋንቋ÷በግብረገብ ትምህርቶች በመምህራንነት፤ ፍትሐ ነገሥቱን በመተርጐም በዓለማዊው ዳኝነት፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሲቋቋሙም በተለያየ ኃላፊነት በማገልገል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፤ ለሕሙማን ባህላዊ ሕክምና በመስጠት ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን እና ለወደፊቱም በነዚህና በሌሎችም መስኮች ትውልድን ለማነፅና ለአገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ጽኑ እምነት አለ፡፡ 

አሁን በአካለ ሥጋ የተለዩን ታላቁ የቤተክርስቲያናችን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎርዮስ ቀዳማዊ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ባሳተሙት የምርምር መጽሐፋቸው በቤተክርስቲያኒቱ በኩል ክርስትና ላገር ለወገን ያደረገውን አስተዋጽኦ በተዋቡና ቅልብጭ ባሉ አባባሎች እንዲህ ገልጸውታል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሙሉ ትምህርት፣ ፍጹም ቋንቋ ከነፊደሉ፣ ሕግ ከነልዕልናው፣ ሥነ ጽሑፍ ከነጠባዩ ከነሙያው፣ ኪነ ጥበብ በየዓይነቱ፣ ሥነ ጥበብ በየመልኩ፣ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ፣ እምነት ከነፍልስፍናው፣ ነፃነት ከነክብሩ፣ አንድነት ከነጀግንነቱ፣ አገር ከነድንበሩ ከነፍቅሩ፣ ስም ከነምልክቱ ‹‹ከነትርጕሙ›› ለአገራችን ያበረከተቻቸው ሥጦታዎች መሆናቸውን እና ትውልዱ ጀግንነትን፣ አገር ወዳድነትን፣ ለታሪክ÷ ለባህልና ለሃይማኖት ተቆርቋሪነትን ይዞ እንዲያድግ በማስተማርና በማበረታታት ከፍተኛ ድርሻ አላት›› ሲሉ የሕይወት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ቀድሞም ሆነ አሁን አገራችንን በመልካም ስም ሲያስነሱና ለሕዝባችን የኩራት ምንጭ የሆኑ የዘመናዊው ትምህርት ሊቃውንት ባመዛኙ በአብነት ትምህርት ውስጥ ያለፉ የክርስትና መልካም ፍሬዎች ናቸው፡፡ ነፍሳቸውን በገነት በመንግሥተ ሰማያት ያኑርልንና እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደ ማርያም፣ ፕሮፌሰር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ዶ/ር ዕጓለ ገብረ ዮሐንሰ ወዘተ. የአገር መኩሪያ የክርስትና ፍሬዎች ነበሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ በቤተክርስቲያን የአብነት ትምህርት ውስጥ ባያልፉም (ቢያንስ ‹በየኔታዎቻችን› ሥር ተቀምጠው ፊደል ከመቊጠር ጀምሮ ዳዊት እስከ መድገም መድረስ የቀደመው ሥርዓት ነበር) አገራችን የክርስትናው መዓዛና ፍሬዎች የሆኑ በርካታ ምሁራን ነበሯት፤ቊጥራቸው ቢመናመንም ዛሬም አሉ፡፡ አንዳንዶች በአስደንጋጭ ዝምታ የተቀመጡ፤ ሌሎች ደግሞ ሰሚ ያጡ፡፡

በርግጥ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ባገልጋዮችም ሆነ በምእመናን በኩል መንፈሳዊነቱ ተዳክሞ፣ ስንፍና በዝቶ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ የሚል አስተሳሰብ ነግሦ፣ ከሁሉም በላይ ከሃዲና አልቦ እግዚአብሔር የሚሉ ጨካኝና አረመኔ ገዥዎች ክርስትናን ለማጥፋት ያልቆፈሩት ጉድጓድ ያልፈነቀሉት ደንጊያ የለም፡፡ በተለይም ኢሕአዴግ በተባለውና አሁንም ስም ቀይሮ በቀጠለው የአጋንንት ቡድን አለን የምንለውና አገራችን እና አብዛኛው ሕዝቧ እንደ ድርና ማግ የተሸመኑበትን ክርስቲያናዊ መሠረት ያላቸው ማኅበራዊ እሤቶቻችን ተሸርሽረው አስጊ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ሆነዋል፡፡ 

መርዛሙ ጐሠኝነት ከቤተመንግሥቱ አልፎ ቤተክህነቱን ተብትቦት የሰማያዊ መንግሥት እንደራሴዎች አዕይንተ እግዚአብሔር የተባሉ ካህናት/መነኮሳት እና የአንድ የክርስቶስ ዘር የሆኑ ምእመናን በጐሣ ተቧድነው በፈጠሩት መለያየት እምነት የሌላቸው ወይም በኑፋቄ የተበከሉ የአገዛዙ ባለሥልጣናት፣ ሰላዮችና ካድሬዎች ቤተክርስቲያንን የወንበዴዎች ዋሻ አድርገዋታል፡፡ በዚህም ምክንያት እውነት፣ ፍቅር፣ ቅንነት፣ ትህትና፣ ቸርነት፣ ትጋት፣ መከባበር፣ራስን መግዛት፣ እኩልነት፣ ትዕግሥት፣ አንድነት፣ ኅብረት፣መተማመን፣ መደማመጥ፣ መተባበር፣ የመሳሰሉት ክርስቲያናዊ እሤቶች ጠፍተው ነውሩ ሁሉ ክብር የሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ በቅርቡ አገዛዞች ባለሥልጣናት፣ ካድሬዎቻቸው፣ አድርባይ ደጋፊዎቻቸው እና በግብር ከፋዩ ገንዘብ የውሸት ፋብሪካዎች የሆኑት ‹የመንግሥትና በመንግሥት ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ተለጣፊ መገናኛ ብዙኃኖች› ሐሰትና ቅጥፈት ‹የመንግሥት› ዋና መገለጫ ከመሆን አልፎ የሕዝብ ባህል እንዲሆን  እያደረጉ ነው፡፡ ዘረኝነት፣ አድሎ፣ ንቅዘት፣ ዝርፊያ፣ ሌብነት፣ ወዘተ. ሥር የሰደዱ የማኅበረሰብን አብሮነት ያናጉ የሞራል ልሽቀት መገለጫዎች ሆነዋል፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዕውቀት፣ የምርምርና ጥናት እንዲሁም የልህቀት ማዕከላት ሳይሆኑ በለጋ ዕድሜአቸው ጐሠኛነትን እንደ ወተት እየተጋቱ ያደጉ ወጣቶች ርስ በርሳቸው ቡድን ለይተው የሚናረቱበት ጋጠ ወጦች ማፍሪያ ከሆኑ ከርመዋል፡፡

ከሁሉም በላይ አድርባይነት አገር የሚያጠፋ መዳኛ የሌለው ደዌ ሆኗል፡፡ በዚህ ጎራ ውስጥ አገዛዞችን በጭፍን ደግፈው የሕዝብን ሰቈቃ የሚያራዝሙ ራስ አታላዮች ታጭቀውበታል፡፡ እነዚህ ጉዶች ሐሳዊ በሆነ የእምነትና የኢትዮጵያዊነት ካባ ተሸፍነው አገርንና ወገንን የሚያደሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ልባቸው የሚያውቀውን ሕሊናቸው ግን ሊያዳምጥ የማይፈልገውን እውነት ሲነግሯቸው ‹እውነቱ ምንድን ነው?› የሚል ጲላጦሳዊ የፌዝ ጥያቄ ሲያነሱ ይደመጣሉ፡፡ ህልው ሆኖ አሁን ላይ ያለው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ (status quo) በጭራሽ እንዲነካባቸው አለመፈለግ ዓይነተኛ መለያቸው ነው፡፡ አገር እየታመሰና ሕዝብ እያለቀም ቢሆን እነሱ አሁን የሚገኙበት የኑሮም ሆነ የሥራ ሁናቴ ዋስትና የሚሰጥ የተደላደለ ጥጋት (safe haven/comfort zone) ነው ብለው ስለሚያስቡ እንዲነካባቸው አይፈልጉም፡፡ በዚህም ምክንያት አገርን እያጠፋ ላለ የኦነግ/ኦሕዴድ አገዛዝ ሽንጣቸውን ገትረው ጥብቅና ሲቆሙ ይታያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላት የሆነውን ወያኔ የሚቃወሙበት ምን የሞራል ልዕልና አላቸው? እነሱ ለሆዳቸው ሲሉ ያደሩለት አገዛዝና ‹አመራር› የወያኔ አስተሳሰብ ወራሽ ብቻ ሳይሆን፣ አስጠባቂና አስቀጣይ፤ በጥፋትም ረገድ ሬከርዱን በሦስት ዓመት ተኩል ያስከነዳ የልቡሳነ ሥጋ አጋንንት ስብስብ ነው፡፡  አድርባዮች ይህንን አጥተውት አይደለም፡፡ ዳተኝነታቸውም ሆነ ድርጊታቸው ካለማወቅ፣ ከየዋሕነትም ወይም ከሞኝነት የመነጨ አይደለም፡፡ እነዚህን ወገኖች ለማሳመን መድከም አያስፈልግም፡፡ የያዙት የተሳሳት መንገድ በክርክር የሚቃና አይመስልም፡፡ ምናልባት ጊዜ የሚያመጣው መፍትሄ እንዲባንኑ ያደርጋቸው እንደሆነ ማየት ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ ሐተታ የተሰጠበትን አሳብ ለመቋጨት ከፍ ብሎ ለአብነት ያህል የተጠቀሱት አገራዊ ሕማሞች ያልተጻፈ ሕግና ሥርዓት በሆኑበት የሕዝብን ደኅንነት፣ የአገርን ዕድገትና ልማት ከቶውንም ማሰብ አይቻልም፡፡ ያልዘሩትን ማጨድ ይሆናልና፡፡ በሌላ አነጋገር ከክርስትናው እሤቶች መለየት ጤናማ አገርና ሕዝብ እንዳይኖር ያደርጋል፤ አድርጓልም፡፡ 

ሐቁ ከፍ ብለን የገለጽነው ሆኖ ሳለ ጥፋታችንን፣ ድክመታችንን፣ ውድቀታችንን በክርስትና ማሳበብ የስንፍና ጥግ/ድንቁርና ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በክርስትና አስተምሕሮና እሤቶች ምክንያት ሥልጣኔ፣ ዕድገትና ልማት እንደተገታ ማሳበብ ዕብደትና ድንቊርና ነው፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት ባመዛኙ ከክርስትናው በተግባር ተፋትተው ቢገኙም ምዕራባውያን ለሥልጣኔአቸው መሠረቱ ክርስትና እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ዛሬ በአውሮጳ የሚገኙ ስመ ጥር ዩኒቨርስቲዎች (ለአብነት ያህል የእንግሊዙ ኦክስፎርድ፣ የፈረንሳዩ ሶ ቦርን) በአንድ ወቅት ገዳማት ነበሩ፡፡

ክርስትና በአፍም በመጣፍም ከዚያም አልፎ በሕይወት መሥዋዕትነት (ሰማዕትነት) በተገለጠበት ባለፉት 2ሺህ ዓመታት  የሰው ልጅ አእምሮና ግዕዛን ከሌላቸው እንስሳትና አራዊት አንሶ የመገኘቱ ዋና ምሥጢር በተቃራኒው በስም ክርስቲያን ነኝ እያለ ከክርስትናው ፍጹም የተፋታ ሕይወት መምራቱ ነው ብንል እውነት ነው፡፡ ከአእምሮው ጋር ላለ፣ ከኅሊናው ጋር ላልተፋታ አስተዋይ ሰው ክርስትናና አስተምሕሮቱ እንዲሁም ሕይወቱንም በመኖር የሚያዳብራቸው ዘላቂ እሤቶች ሊደርስባቸው የሚያስባቸው/የሚፈልጋቸው ልዕለ ሃሳቦች (ideals) እንደሆኑ ለመገንዘብ አያዳግተውም፡፡ 

ሃሳባችንን ሚዛናዊ ለማድረግ አገራችን ኢትዮጵያ ክርስትናን በ1ኛው መቶ ክ/ዘመን፣ በሥርዓት የተደራጀ አገልግሎቱን በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ያለአንዳች ደም መፋሰስ (ከነገሥታቱ ወደ ሕዝቡ ወርዶ) በቀደምትነት ተቀብላ ስታስተምር ስትሰብክ ብትኖርም በየጊዜው በውስጥም ሆነ በውጭ በተነሡ አጽራረ ቤተክርስቲያኖች (የክርስትና ጠላቶች – ያለፉትን ሦስት ዓመት ተኩል ሳንዘነጋ) አማካይነት በደረሰባት ዐውዳሚ ፈተና በምግባርና ትሩፋት የበለጸጉ አበውና እመው፣ በርካታ ሊቃውንቷን፣ አገልጋዮቿን፣ በእምነት የጸኑ ምእመኖቿን፣ መጻሕፍቷን፣ ቅርሷን አጥታለች፡፡ ክርስትና ፈተና ሲገጥመው ቤተክርስቲያን ስትጎዳ መላው አገር ይጎዳል፡፡ በግራኝ አሕመድ የጥፋት ዘመን እንደሆነው፡፡ ባንፃሩም በየዘመናቱ የተፈጸሙት ጥፋቶች የክርስቲያኑን ሕዝብ መንፈሳዊ ጥንካሬ በእጅጉ ጎድተውታል፡፡ በዚህም ምክንያት ቊጥሩ ቀላል የማይባል ምእመን በዕውቀትና ሥነምግባር ላይ ከተመሠረት እምነት ይልቅ በዘልማድ የሚመላለስ፣የበዓል ክርስቲያኖችም ተሰባስበውባት ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁናቴ ክርስትናውንም ሆነ አገርን በእጅጉ አስከፍሏል፤ አሁንም እያስከፈለ ነው፡፡ በጊዜአችን የምናስተውለው ሃይማኖትን በዘር/ጐሣ የመለወጥ ቀሊልነትም የዚሁ በድቡሽት ላይ የመመሥረት ውጤት ነው፡፡ ክርስትናን በቅጡ ሳይረዳ ክርስቲያን በሆነው ሕዝብ ዘንድ ያለው መሠረታዊ ጥፋት ኃላፊነቱን ሁሉ እንደ ሕፃን ልጅ ለእግዚአብሔር ትቶ አገዛዞችና ገዥዎች የሚያደርሱበትን ግፍና ጭቆናን ከእግዚአብሔር እንደታዘዘበት መዓት በመቊጠር ጭቆናን እና ጨቋኝን ተሸክሞ ለመዝለቅ የሚያሳየው ጠባይ፣ እምነቱን ሰበብ አድርጎ በአገር ጉዳይ ከመሳተፍ ማፈግፈጉ፣ ደሀ ሲበደል ፍርድ ሲጓደል ዝም ብሎ የመመልከቱ ጉዳይ በእጅጉ ጎድቶናል፡፡ በዚህም ምክንያት አገር ወንበዴ፣ ሽብርተኛና ዘረኛ ገዥዎች  እየተፈራረቁባት ለዜጎች ምድራዊ ሲዖል ለመሆን በቅታለች፡፡ ይሄ የተሳሳተ አመለካከት ግን ከክርስትና አስተምሕሮትና እሤቶች ጋር ዝምድና የለውም፡፡ 

የቅርቡ ትውልድ ያለውን ብሔራዊ ሀብት በሚገባ ስለማያውቅ አባቶቻችን በብዙ ተጋድሎ ያቈዩለትን ነፃነት ከነሙሉ ክብሩና ኩራቱ ዛሬ ለጊዜያዊ ጥቅም (አገዛዞች ለሚጥሉለት ቅንጥብጣቢ ሹመት ሽልማት፣ በሥልጣንም ለሚገኘው የማይገባ ሀብትና ጥቅም) አሳልፎ እየሰጠ ነው፡፡ ዛሬ ቊጥሩ በቀላሉ የማይገመት ኢትዮጵያዊ ዘርፈ-ብዙ የሆነውን ብኲርናውን በብልጭልጭ ነገሮች ሽጦ በመንፈስ የነጮች ቅኝ ተገዥ ሆኗል፡፡ ነጮችን ለመምሰል መሞከርና የነሱን ርካሽ የሆነ ባህል መቀላወጥ የሥልጣኔ ምልክት አድርጎ እየቆጠረው ነው፡፡ ከውጭም ቢሆን ቢያንስ መልካም የሆኑትን ሲቀስም አይታይም፡፡ ዛሬ ብዙ ሙዐለ ሕፃናት ት/ቤቶች በመንፈስ ቅኝ በተገዙ ግለሰቦች ስለሚተዳደሩ ከመግባቢያ በዘለለ ሌላ ፋይዳ የሌለውን እንግሊዝኛ ቋንቋ እንደ ግብ እየቈጠሩት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ባብዛኛው ባደጉም ሆነ በአዳጊ አገሮች የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን ለባዕዳን አሳልፎ የሚሰጥ የለም፡፡ ምክንያቱም የጋራ ብሔራዊ ማንነት፣ የጋራ ብሔራዊ ሥነ-ልቦና እና የአገር ፍቅር የሚቀረፅበት ዋና ቦታ በመሆኑ፡፡ እኛስ? በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት አንድም ባልገባን የቅዠት/ተውሶ ርዕዮተ ዓለም ስንባዝን አንድም ባለቤት ያጣ አገር በመሆን ተቅበዝባዥ፣ የባከነ፣ የበታችነት ስሜት የሚያሰቃየውና የማንነት ቀውስ ውስጥ የሚገኝ ትውልድ እየቀፈቀፍን እንገኛለን፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ማዕርጋትን የተሸከሙ ‹የተማሩ ደናቁርት› እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ የ‹ሠለጠነና ዘመናዊ› ከሚባለው የምዕራቡ ዓለም ተምረናል÷ አልፎም በዩኒቨርስቲዎቻቸው እያስተማርን ነው የሚሉ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለጋ ወጣቶችን በመመልመል ኢትዮጵያን የቀደመ ታሪኳን፣ ባህሏንና ብሔራዊ ቅርሷን አጥብቀው እንዲጠሉ ጥላቻንና በቀልን በማስተማር ወገኑን ተወዳዳሪ በሌለው ጭካኔ የሚጨፈጭፍ ትውልድ እየፈጠሩ ነው፡፡ የአንድን ታላቅ አገር ርእሰ ከተማ ሕዝብ በጅምላ በማነወር እንደ ጉማሬ በአፋቸው ሲጸዳዱ አስተውለናል፡፡

ሻእቢያ የተባለው ዛሬ ኤርትራን ምድራዊ ሲዖል ያደረገው የተገንጣይ ቡድን ይህን ዕኩይ ተግባር (ሳኅል በርሃ ወስዶ ኤርትራውያን በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ሥር የሰደደ ጥላቻ እንዲኖራቸው ሲያስተምር/ሲያሠለጥን ዘመናትን አሳልፏል) ሲፈጽም ኖሯል፡፡ ኋላም ለመንፈስ ልጆቹ ለወያኔና ለኦነግ በማሠልጠን ትውልድና አገር የማጥፋቱ ዘመቻ ቀጥሏል፡፡ የዐቢይ ኦሕዴድም በማናቸውም መመዘኛ ኦነግ በመሆኑና ራሱም ስለነገረን ካለፉት ሦስት ዓመት ወዲህ ወገንን በማረድ፣ ሚሊዮኖችን በማፈናቀል፣ ለሰው ሠራሽ ረሃብ በመዳረግ፣ ብሔራዊ ቅርስን በማጥፋት፣ ከወያኔ የወረሰውን የጐሣ ሥርዓት በሕግም በመዋቅርም አጠናክሮ በመቀጠል (አዳዲስ ባንቱስታን ሀገር-አከል ‹ክልሎችን› በመፍጠር)፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲን በማበላሸት ኢትዮጵያን ወደ ‹በርባሮስ› እያወረዳት ነው፡፡ ‹ሰውየውን› አፉን ከፍቶ ፊቱን ጸፍቶ ‹አዲስ ምዕራፍ› ሲል ያናገረው ወዶ አይደለም፡፡ ይሄ በርግጥ ለኢትዮጵያ እንግዳ/‹አዲስ› ምዕራፍ ነው፡፡ የጥፋት ምዕራፍ፡፡ 

ኢትዮጵያ በዋናነት የምትመካበት መንፈሳዊ ሀብቷ ነው፤ የአብሮነታችን፣ የአንድነታችን፣ በባህልም ሆነ በብሔራዊ ሥነ ልቡና መልክ የሚገለጹ መልካም እሤቶቻችን ሁሉ ዋልታና ካስማ ነው፡፡

ባህላዊው የቤተክህነት ትምህርት (traditional church education) በመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ተወስኖ በመቅረቱ አገራዊ ዐውድን (ታሪክን፣ ባህልን፣ ብሔራዊ እሤቶችን፣ ወዘተ.) በዋጀ መልኩ ወደ ዘመናዊው ትምህርት ሊሸጋገር ባለመቻሉ ዛሬ ‹ዘመናዊ› የምንለው ትምህርት ሀገር-በቀል መሠረት የሌለው፣ አገራዊ ችግርን የማይፈታ ከባዕዳን የተወረሰ ባዕድ ሆኖብን ትውልዱ ከሁለት ያጣ ሆኖአል፡፡ ወይ ቅኝ እንደተገዙት አገሮች ለይቶለት የውጩን አልተከተለ ወይ ሀገር-በቀሉን ዕውቀት (indigenous knowledge) አልያዘ የውኃ ላይ ኩበት ሆኗል፡፡

ከሌሎች መልካሙን መቅሰም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ወደ ራሳችን ሀገር-በቀል ዕውቀታችን ካልተመለስን፣ በስም ክርስቲያን ነኝ የሚለው ሁሉ በዕውቀትና በሕይወት ላይ ወደተመሠረተው ክርስቲያናዊ ሕይወት ካልተመለሰ የዕብደትና ድንቊርናው ዘመን የማይቀጥልበት ምክንያት የለም፡፡ ዶሮን በቆቅ ለውጦ የራስ የሆነውን ሰዶ ማሳደዱ ይቀጥላል፡፡ ዛሬ እንቊው ክርስትናችን በ‹እሪያዎች› (ዛሬ ያሉትና ባለፉት  50 ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር የበቀሉት አረሞች /አገዛዞችና ገዢዎች/ ) ፊት በመቀመጡና ‹የእሪያዎቹን› ማስጠሎነት ወለል አድርጎ በማሳየቱ ራሳቸው ተዋርደው ኢትዮጵያን የምታህል ጥንታዊትና ታሪካዊት የተቀደሰች አገር የዓለሙ ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በመጨረሻ በማጠቃለያነት ላነሳ የምፈልገው መልካም ዕውቀት (የሰውን ልጅ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት የሚያበለጽግ ዕውቀት) ሁሉ ዓለምአቀፋዊ ገጽታ አለው፡፡ የሁሉም ሰው ልጅ ሀብት ነው፡፡ የሰው ልጅ በተለያየ መንገድ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ዕውቀትን መዝግቦ ማኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ (ትውፊትን ጨምሮ) አሁን እስካለንበት ዘመን ባለው ዕውቀት ሁላችን ተጠቃሚዎች ነን፡፡ የአስተዋጽኦው መጠን ይለያይ እንጂ ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚተላለፈው ዕውቀት ውስጥ በየትኛውም የዓለም አካባቢ የሚገኝ ሕዝብ በዚህ የዕውቀትና ጥበብ ባሕር ውስጥ የራሱ ድርሻና አሻራ አለው፡፡ ለሁሉም ዕውቀት ምንጭ አንድን አገር ወይም ሕዝብ ማድረግ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ የዕውቀት ልውውጥ፣ ውሰት፣ ትብብር፣ መቅዳት/መኮረጅ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ቅርፁ፣ ይዘቱ፣ ጥልቀትና ስፋቱ እንደ ታሪኩ፣ ባህሉ፣ እምነቱ፣ ልማዱ እንዲሁም እንደ አገሩ ተጨባጭ ሁኔታዎች ሊለያይ ይችላል፡፡ ፍልስምናዊ መሠረቱም እንደዚሁ ሊለያይ ይችላል፡፡

ባንፃሩም ሰይጣናዊ ዕውቀት አለ፡፡ ሆን ብሎ አንዱን ሀብታም ሌላውን ደሀ የሚያደርግ፤ ጉልበታሙ ደካማውን የሚያጠቃበት፤ አንዱን ጌታ ሌላውን ባርያ የሚያደርግ፤ ግፍና ጭቆናን የሚያሰፍን፤ በመብትና ነፃነት ሽፋን ፈጣሪና ተፈጥሮ ከሠራው ሥርዓት ውጭ የሚያደርግ (ለምሳሌ ግበረ ሰዶምና ግብረ ገሞራ)፤ የሰው ልጅን ወደ ጭራቅነት  የሚቀይር (ባለፉት ሦስት ተኩል የሰቈቃ ዓመታት እንዳየነውና አሁንም እንደቀጠለው) ፤ በቀለም በጐሣ ከፋፍሎ አድሎና ልዩነትን የሚፈጥር፤ ንቀትና ጥላቻን በማበረታታት የሰው ልጅን ለጅምላ እልቂት የሚዳርግ፤ ወዘተ. እንዲህ ዓይነቱ ‹ዕውቀት› ዕውቀት ከተባለ ከክርስትናው በተቃራኒ የቆመ ነው፡፡ ዓለማችንን የሰቈቃና ዋይታ መድረክ ያደረጋት እንዲህ ዓይነቱ አጋንንታዊ ‹ዕውቀት› ነው፡፡ በአመዛኙ ምዕራቡ ዓለም የሚመራበትና በዓለማችን የተዛባ ሥርዓት እንዲኖር ያደረገ ይህ ዲያቢሎሳዊ ‹ዕውቀት› ነው፡፡ በጽሑፋችን መግቢያ ላይ ያነሳነው (the so-called ‘global empire/coroporatocracy’) የሚባለውና ባጠቃላይ ከድህነት፣ ከበደልና ጭቆና የሚያተርፉ ‹ጌቶች› (lords of poverty) የሠለጠኑበትና ዕኩያን የሚመሩበት የጥፋት ‹ዕውቀትን› ይመለከታል፡፡

ፍላጎቱና ጊዜው ያለው ለማገናዘብ እንዲረዳው እነዚህን መጻሕፍት ፈልጎ መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፤

  • የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፤ ከዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ
  • የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ታሪክ፤ የከፍተኛ ትምህርት መቋቋምና መስፋፋት ጕዞ በኢትዮጵያ፤ ከዶ/ር አክሊሉ ሀብቴ
  • የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ፤ ከአቡነ ጎርጎርዮስ
  • የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፤ ከሊቀጠበብት አያሌው ታምሩ 
  • ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት፤ ከሊቀ ሥልጣናት ሀብተማርያም
  • የፕሮፌሰር መሥፍን ወልደ ማርያም የኋለኞቹ ሁለት መጻሕፍት (አድማጭ ያጣ ጩኸት እና ዛሬም እንደ ትናንት)
  • የኢትዮጵያ ተጠሪ ማነው፤ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
  • Republicans on the Throne, by Tekalign Gedamu
  • Confession of an Economic Hit Man, by John Perkins
  • Lords of Poverty, by Graham Hanccok
Filed in: Amharic