የአስቸኳይጊዜአዋጅ ቁጥር 5 /2014
የኢፊድሪ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች
በሃገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን ኣደጋ ለመከላከል የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
መንግሥት የሃገርን ህልውና፣ ሉዐላዊነት እና የግዛት አንድነት ከውስጥም ሆነ ከውጭ
ጠላቶች የመጠበቅ የሕግም ሆነ የሞራል ኃላፊነት እና ግዴታ አለበት
ይህንን በመገንዘብ፤ የሽብርተኛው ሕውሃት እና የሽብር ግብረአበሮቹ እንቅስቃሴ በሃገር ህልውና እና
ሉዐላዊነት ላይ ጉልህ እና ድርስ አደጋ የደቀነ በመሆኑ፤ ሽብርተኛው ሕውሃት እና የሽብር ግብረአበሮቹ ለዕኩይ አላማቸው መሳካት በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ እየፈፀሙ ያሉት ግድያ፣ ዝርፍያ እና ሌሎችም ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላባቸው ኢሰብዐዊ ጥቃቶች እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ከግምት በማስገባት፤
ከቀጥተኛ እና መደበኛ የውግያ አውድ በተጨማሪም የሽብርተኛው ሕውሃት እና የሽብር ግብረአበሮቹን ተልዕኮ ያነገቡ ግለሰቦች ከሰላማዊ ዜጎች ጋር በመመሳሰል በህዝብ እና በሃገር ላይ የደቀኑትን ከፍተኛ እና ተጨባጭ የደህንነት ስጋት በመረዳት፤ ሽብርተኛው ሕውሃት ኢትዮጵያን የማዳከም እና ብሎም የማፍረስ ምኞት ካላቸው የውጭ ሃይሎች ጋር በከፍተኛ ቅንጅት እየሰራ እንደሆ በመገንዘብ ፤ ከላይ የተገለፁት የሃገር ህልውና ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም አዳጋች በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ እና ተግባራዊ ማድረግ አደጋውን ለመቀልበስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል::
ክፍል አንድ
ጠቅላላ
1. አጭር ርእስ
ይህ አዋጅ “የሃገርን ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ
አዋጅ ቁጥር 5/2014 ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል::
2. ትርጓሜ
ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም ሲባል፣
1. “የሕግ አስከባሪ አካል” ማለት የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ የመረጃና
ደህንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልል ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት ማለት ነው።
2. “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ” ማለት የዚህን አዋጅ አፈጻጸም
ለመከታተል እና በበላይነት ለመመራት በዚህ አዋጅ አንቀጽ 7 መሠረት የተቋቋመ
የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ ነው።
3. “የጦር መሳሪያ” ማለት በጦር መሳሪያ አስተዳደር ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር
1177/2012 ትርጉም የተሰጣቸውን አነስተኛ፣ ቀላል እና ሌሎችንም የጦር መሳሪያ
አይነቶች እና ጉዳት አድራሽ ዕቃዎች ያጠቃልላል።
4. “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ማለት ነው።
5. በዚህ አዋጅ በወንድ አነጋገር የተገለፀው ሴትንም ይጨምራል።
3. የተፈፃሚነት ወሰን
1.ይህ አዋጅ በመላው ኢትዮጵያ ተፈፃሚ ይሆናል።
2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የአደጋው
መጠን እና አካባቢያዊ አድማስ እየቀነሰ በሄደ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ
የተፈፃሚነት ወሰን በዚያው ልክ እየጠበበ ሊሄድ የሚችል ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጅ መምሪያ ዕዙ አዋጁ ተፈፃሚነት በከፊልም ሆነ በሙሉ ቀሪ የሚሆንባቸውን
አካባቢዎች በመመሪያ ይወስናል፣ ይህንኑ ለሕዝብ ያሳውቃል።
ክፍል ሁለት
በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የማይፈቀዱ ተግባራት
4. በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ የሃገርን ህልውና እና ሉዐላዊነት፣ እንዲሁም
የሰላማዊ ዜጎችን ደህነንት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን፦
1. በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል መከላከያ ኃይልን ወይም የትኛውንም ሌላ
የጸጥታ አካል በማሰማራት ሰላምና ፀጥታ እንዲያስክብሩ ትዕዛዝ ሊሰጥ
ይችላል፤
2. እድሜያቸው ለወታደራዊ አገልግሎት የደረሱ እና የጦር መሳርያ የታጠቁ
ዜጎች ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ፣ ወታደራዊ ግዳጅ እንዲቀበሉ፣ ወይም
ይህን ማድረግ የማይችሉ ሲሆን በአማራጭ ትጥቃቸውን ለመንግስት
እንዲያስረክቡ ሊያዝ ይችላል፤
3. የሰዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን ይችላል፤
4. ማናቸውም የህዝብ የመገናኛ እና የህዝብ መጓጓዥ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም
እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል፤
5. ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ
ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ
አዋጅ ተፈፃሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ
ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ይችላል፤
6. ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ
ማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅት ንብረት የሆነን ማናውንም ቤት፣ ህንፃ፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማንኛውንም ሰው ለማስቆም፣
ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ ይችላል፤ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ
የጦር መሳሪያዎችን መውረስ ይችላል ፤
7. ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት
እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ
እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቀቁ ለማዘዝ ይችላል፣
8. ከፍተኛ የፀጥት ችግር እና ስጋት በተፈጠረባቸው የሃገሪቱ ክፍሎች የአካባቢ
አመራር መዋቅርን በከፊልም ሆነ በሙሉ፣ ማገድ፣ መለወጥ እና በሲቪልም
ሆነ በወታደራዊ አመራር መተካት ይችላል፤