>
5:26 pm - Tuesday September 17, 6796

የቴዲ አፍሮን "አርማሽ/ቀና በል"ን  በወፍ በርር ስቃኘው...!!!   (እንዳለጌታ ከበደ)

የቴዲ አፍሮን “አርማሽ/ቀና በል”ን  በወፍ በርር ስቃኘው…!!!

                              (እንዳለጌታ ከበደ)

“አርማሽ/ቀና በል” ልብ የሚነካ ራሮታዊ ዘፈን ነው። “ዕንባ ዕንባ ይለኛል ይተናነቀኛል…” የሚያስብል ነው። አሁናዊነትም:የተለዬነትም: አለው። እያነባ ያጽናናል። እያባባ ያንጻል። ወደ ቀልብ አድርሶ ይመልሳል።
 ዘፈኑ ነፍስ የምታሰማው የጥሪ ደወልም መስሎ ተሰምቶኛል። “ኧረ እንደምን?” ቢሉ የዘፈኑ ወካይ ተራኪ ቁዘማና ትካዜ ውስጥ ሆኖ እናቱን የሚጣራ የተማጽኖ ድምጽ አለውና። ባይተዋር: ተስፋውን አምጦ ለመውለድ እየሻተ: ምጡ ሲረዝምበት የሚያሰማው እንጉርጉሮ!
የዘፈኑ ገጸ ባህርይ “እገሌ/ እገሊት ሆይ  ና/ ነይ ድረስላት/ ድረሺላት!” ብሎ ከጥንቱም ሆነ አሁን ካሉት የጠራው ስመጥር ‘ታዳጊ/ተዋጊ’ የለም። “ይህችን ሀገር ማን ነው የሚታደጋት?” ብሎም አልጠየቀም። “አለሁልሽ:  እየመጣሁልሽ ነው!” የሚል ራስን እንደ መሲህ የሚያስቆጥር ደወልም አይደለም። ራሷ ናት የተጠራችው። እናቲቱ። ይህ ደግሞ እስከዛሬ ከማውቀው አገርኛ ዘፈን የተገላበጠ ያደርገዋል። በፊት የነበረው “መጣሁልሽ እናቴ” ነበረ። አሁን ቴዲ መጣና “ነይ!” አላት። ጠሪና ተጠሪ ተለዋወጠ። ጠባቂዋ ተጠባቂ ሆነች።
“እኔስ እስካይሽ ጨነቀኝ
ሀገሬ መምጫሽ ናፈቀኝ።”
ጠሪው በመናፈቅ ብዛት ልቡ ዝሏል። ሆኖም ተስፋ አልቆረጠም። በውንም በሕልምም እናት አገሩ እየመጣች ታውከዋለች። “ነይ! ነይ!” የሚላት እንድታጽናናው ነው። የተለየችውም በልጅነቱ ነው – በአፍላነት ዘመኑ። የተለያትም በመንፈስ እንጂ በአካል አይደለም። እያለች የለችም። ከሚያውቃት ከሚያስባት ስለተለየችበት በኢትዮጵያ ተደናግጧል። መንፈሷ ተራቁቷል። አድባር አውጋሩ ተጣልቷታል።
“…የቦረቅኩበት በልጅነቴ
የያኔው መልክሽ ብቅ ሲል ፊቴ
እየመለሰኝ ወደትላንቱ ….”
ስንኞቹ እንደሚገልጹት ኢትዮጵያ መልኳ ተለውጧል። ተስፋዋ የሻገተ ወይም የዛገ መስሎ ታይቷል። ጠላቶቿ ይዘባበቱባት ይዘዋል። ተራራ ስሟ ተንዷል። ለዚህም ነው የዘፈኑ ተራኪ መባዘኑ:መኳተኑ: “በልጅነቴ የማውቅሽ ኢትዮጵያዬ ሆይ የት ነሽ?” ብሎ መጣራቱ። በልጅነቱ ውስጥ ተስላና ተቀርጻ የቆየችው ኢትዮጵያ አርማዋ ቅዱስ ነበር – አይነኬ አይደፈሬ። “ምኩራቧ የተፈራ የነጻነት ቤት።” ሲያድግ ግን አጣት። እደግመዋለሁ! እያለች የለችም። እናም እየጠበቃት ነው – “ባክሽ ኢትዮጵያ ነይ ቶሎ!” እያለ።
እንደዘፈኑ ይዘት ሀገር የምትታወከው: ሀገር የምታቃስተው: ሀገር ከልጆቿ የምትርቀው ቅያሜ ሲያድርባት ነው። በዘፈኑ ውስጥ “ነይ! ነይ!” ተብላ የምትጠራዋ ኢትዮጵያ “የሄደችው” ልጆቿ የዘረኝነት ዘር በልባቸው ስላበቀሉ ነው። ይህም ዋጋ እንዳስከፈላትና/ እያስከፈላት እንደሆነ  ይናገራል።
“..አይበቃም ወይ ማሳል
በዘር ጉንፋን ታመን…”
“…ዘር ያበቀለው ታጭዷል መከራ
የኢትዮጵያዊነት አሁን ነው ተራው…”
ዘፈኑ ውስጥ ሌላው ጎልቶ የሚሰማው ቃል መስከረም ነው። ይህች “የአስራ ሶስት ወራት ጸጋ!” ተብሎ የሚዘፈንላት አገራችን በወርሃ ሐምሌም: በወርሃ የካቲትም: በወርሃ ግንቦትም አትመሰል። አንዳቸውንም አትወክል።  ሐምሌ በዘውዱ ስርአት ገናና ነበር – ንጉሡ ተወልደውበታልና።  የካቲት ደግሞ በደርግ ዘመን ገናና ነበር – ደርግ የዘውዱን ስርዓት የገረሰሰበትና አብዮቱ የፈነዳበት ወር ነውና። ግንቦት ደግሞ በኢሕአዴግ ተዘካሪ ነው – የደርግን አገዛዝ ናድኩበት የሚለው ወር ነውና። ይህ አንዱን ወር መርጦ ገናና የማድረግ አባዜ የቅርብ ዘመን ገዢዎቻችን አባዜ ነው።
ኢትዮጵያ “የትኛው ወር አንቺን ይገልጽሻል?” ብትባል ግን መስከረምን የምትመርጥ ይመስለኛል። መስከረምን የምትመርጥበት ምክንያት ልጆቿ በውበትና በተስፋ ሲሰክሩ ስለምታይ ነው ብዬም አስባለሁ።
ቴዲ አፍሮ መስከረምን መምረጡ ተገቢ ነው የሚል ስሜትና የፈጠረብኝም ለዚሁ ነው። የአደባባይም የቤትም በዓላት የሚበዙባት: ዘመድ ወዳጅ የሚጠያየቅባት።
ቴዲ ልጃገረዶች “አበባ አየሽ ወይ?” ብለው ከሚዘፍኑት የልጃገረዶች ጨወታ ውስጥ “እናቴን ጥሯት መድኃኒቴን/ እሷን ካጣችሁ መቀነቷን…” የሚለው ስንኝ የመሰለ በዘፈኑ ውስጥ ማስገባቱም ሆን ብሎ እንደሆነ ያስታውቃል። “መጥታ ታብሰው ዕንባዬን/ሀገሬን ጥሯት አርማዬን”
መስከረም ለኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ብቻ ሳትሆን የሃይማኖታዊና የባሕላዊ በዓላት ወር ናት። ለእኔ መስከረም ተፈጥሮዋ እንደሚመሰክረው ልጃገረድ ናት። አደይ የፈካውና ወንዙ የጎደለው እንዲሁም ዘመን የተሸጋገረው ለእሷ ክብር ይመስላታል። ውብ ናት። ወንዶች የሚጋደሉባት: ድምጻውያን የሚያንጎራጉሩላት: ተፈጥሮ የሚያረግድላት!
እና ድምጻዊው እናቱን/ አገሩን የመሰለው በመስከረም ወር ነው – እንድትመጣለት የፈለገውም በዚህች ወር።
“…ዓመት አውዳመት ድገመን ሲሉ
ልጆች በቀዬው ችቦ እያበሩ
መስቀል ፋሲካው ዒድ እንቁጣጣሽ
አውዳመት አይሆን አንቺ ካልመጣሽ
ዘመን አድሰሽ በፍቅር ቀለም
ብቅ በይ ኢትዮጵያ ሁኚና መስከረም..”
….
የ”ቀና በል” ተራኪ ተስፈኛ ነው – ቀን ጠባቂ: ያ ቀን እስኪመጣ አንገታችንን ከምንደፋ: ከምንወድቅ: ዘምመን ከምንገኝ ቀና ብለን እንጠብቃት የሚል። ኢትዮጵያ እንድትመጣ ልጆቿ ከዘረኝነት መንፈስ ተላቀው ታጥበውና ታጥነው መጠበቅ እንዳለባቸውም አምኗል። (በነገራችን ላይ ዘፈኑ ለእናትየውና ለልጇ የተዘፈነና ሁለት ዘፈኖች የተጣመሩበት መስሎ ተሰምቶኛል። “አርማሽ” ለእናቲቱ ነው። “ቀና በል” ደግሞ ለልጅየው።)
በስተመጨረሻም ነይ ነይ የሚለው ሆድ የሚያባባ ዜማውን ለውጦ በሞቅታ ልጆቿን ያነቃቃል – እንዲህ እያለ።
“…ዘመን አድሰሽ  ……. አስዮ
በፍቅር ቀለም ……. ቤሌማ
ብቅ በይ ኢትዮጵያ  ……. አስዮ
ሆነሽ መስከረም……. ቤሌማ…”
ሳጠቃልለው  ቴዲ አፍሮ በአዲሱ “ቀና በል/አርማሽ” ዘፈኑ ነገረኝ ወይም ነገረልኝ ያልኩት እውነት ይህን ይመስላል። የምንጠብቃትን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እንዴት ልንጠብቃት እንደሚገባም ይነግረናል።
Filed in: Amharic