>

አንዳንድ ወፍ-በረር ሃሳቦች በቴዎድሮስ ካሣሁን "አርማሽ" ላይ! (አሳፍ ሀይሉ)

አንዳንድ ወፍ-በረር ሃሳቦች በቴዎድሮስ ካሣሁን “አርማሽ” ላይ!
አሳፍ ሀይሉ

ከጥቂት ዓመታት በፊት አንዱ ኮሜዲያን በሸራተን መድረክ ዜማው መላቅጡ የጠፋበትን ኃይልዬ ታደሰን ሲተች፦ “በዛሬው ዕለት ኃይልዬ ታደሰ በሸራተን መድረክ ላይ ወጥቶ ግጥሙን አንብቦ ተመለሰ” በማለት አስቆን ነበር። ኃይልዬም አምኖ ይቅርታ ጠይቋል መሠለኝ “ጉንፋን” ምናምን ብሎ ምክንያቱን።
ሰሞኑን ከሰው ተሻምቼ ያደመጥኩት የቴዎድሮስ ካሣሁን ዘፈንም የኃይልዬን ቀልድ ነው ያስታወሰኝ። ግጥሙ ልብ የሚነካ፣ ብዙ የጊዜያችንን አሳዛኝ እውነት የሚናገር፣ የቁጭት ድባብ ያጠላበት እንጉርጉሮ ነው። ዜማው ግን …??
ሥራው የፋኑ ፋኖን የጀግንነት መንፈስ ይዞ፣ ነገር ግን የአንቺሆዬ ለእኔን የመብከንከን ስሜት የሚያንፀባርቅ፣ የአምባሰልንና የትዝታን አስተካዥ ስሜቶችም የተላበሰ፣ አሁን በኢትዮጵያችን ላይ እየሆኑ ባሉት ነገሮች ሁሉ የመከፋትን፣ የማዘንን፣ ያለፈውን የድሮውን አብሮነትና የአባቶች አደራ የመናፈቅን፣ ወዘተ. ከትንሽ የተስፋ ጭላንጭልና መፅናኛ ጋር አደባልቆ የያዘ ወቅቱን ያገናዘበ ሥራ ነው።
ዜማው ግን… ያንን ኃይልዬ በጉንፋን ይቅርታ የጠየቀበትን ቃና-የለሽ ዜማ ነው የመሰለኝ። “ቴዎድሮስ ካሣሁን ልብ የሚነካ ግጥሙን አነበበ” ቢባል ነው የሚቀለው። ዜማው ወጥነት የለውም። ከዚህም ከዚያም የተዘረፈ፣ የተቀነጫጨበ፣ ለዛቢስ ድሪንቶ ዜማ ነው። የሚስብ ነገርም፣ ከመልዕክቱ በቀር የሚታወስ ጣዕምም የለውም።
የጥላሁን ገሠሠን አንዱን ዜማ ወስዶ በባክግራውንድ ሳውንድ እንዳይሆኑ አበሻቅጦ አስገብቶታል። ደግሞ ከሌላ የጥላሁን የሚገርም የአውዳመት ዘፈን ላይ የሆነች “አሲዮ አሲዮ.. አና(?) ቤሌማ” የሚል ድምፅና ዜማ ወስዶ ደንጉሮበታል። ከዚህም ከዚያም የተመነተፉ የተለያዩ ዜማዎች ደግሞ “የሕዝብ” ተብለው ቀርበዋል።
ብቻ ባጠቃላይ የቴዎድሮስ ካሣሁንን “አርማሽ. .” ዜማ ያገኘሁት አንዴ ቴዎድሮስ ታደሰ የአሁን ጊዜ ዘፈኖችን እንዴት እንደሚያያቸው ሲጠየቅ፦ “ከዚህም፣ ከህንድም፣ ከአውሮፓም፣ ከዚያኛውም፣ ከዚህኛውም እየተዘገኑ የተደበላለቁበት መላቅጡ የጠፋበት ዝብርቅርቅ ያለ ዜማ ነው በየሄድኩበት የሚያጋጥመኝ” በማለት እንደገለፀው ባለ መልኩ ነው።
ቴዎድሮስ ካሣሁን በሙያው ምላጭ ነው። አንድ ሥራ መቼ መውጣት እንዳለበት፣ ወይም ምን፣ ለማን፣ በምን ቶን መናገርና መወደድ እንዳለበት ያውቃል። በአቋሙም ሳተና ሀገር ያወቀለት ሀገር ወዳድ ነው። ሲያስፈልግም ደፋር ነው።
ግጥሙም አንደኛ ነው። የሚያነሳቸው የትውልዱ አጀንዳዎች ቀላል አይደሉም። ደራሲያቸውም ራሱ ነው። ብስለቱንና ያለውን መረዳት ያሳያል። ይሄንን ነጠላ ግጥም ጨምሮ እንደ መፅሐፍ ማለት ናቸው ግጥሞቹ።
በበኩሌ ግን ከዚህ በፊት ያወጣውን የመጨረሻ አልበሙን ጨምሮ፣ ይሄኛው ነጠላ ዜማም፣ የሚጎድለው ከፍ ያለ የሙዚቃ ዝግጅት፣ ወይም የሙዚቃ መርቀቅና ቅንብር፣ ወጥነትና የጣዕም ማጣት ጉዳይ እጅግ ጎልቶ ታይቶኛል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የቴዎድሮስ ሙዚቃዎች ይበልጥ በስታንዳርዳቸው ማሻቀብና መራቀቅ ሲገባቸው፣ እየወረዱብኝ ነው የመጡት። የኮንሰርት፣ የመድረክ ዘፈኖች ዓይነት እየሆኑብኝ። ከመድረኩ ስትወርድ ብቻህን ሆነህ የማታንጎራጉራቸው፣ ግጥም-ብቻ፣ መልዕክት ብቻ እየሆኑብኝ መጥተዋል።
የሆነ ሆኖ የቴዎድሮስ ሙዚቃዎች እንደ ሀገራዊ ባህላዊ የአማርኛ የአዝማሪ ሙዚቃዎች ሁሉ፣ የህዝብን ብሶት ማውጫ፣ ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችን ማንሻ፣ እና ከፍ ሲልም ህዝብን መቀስቀሻ ሆነው እያገለገሉ ናቸው።
ምናልባትም የቴዲ አፍሮን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሙዚቃ ደረጃቸው እየወረደ ሆነ ተብሎ የመጣ “ተራነትን” (intentional ordinariness) የተላበሱ ዘፈኖች ከደቡብ አፍሪካ ሕዝባዊ ዘፈኖች ጋር ብናነፃፅራቸው ብዙም የምንሳሳት አይመስለኝም።
እንደዚህ ያሉት ዘፈኖች ከህዝቡ እንዳይርቁ ስለሚፈለግ ብዙ በሙዚቃ ቅንብራቸው ያልተራቀቁ ሆነው፣ በዜማና በግጥሞቻቸው ሕዝባዊነትን የተላበሱ ናቸው። በሚያነሷቸው ደፋርና አንኳር ሀገራዊ መልዕክቶች ይታወቃሉ፣ ይስፋፋሉ፣ ይወደዳሉ።
እና የቴዲን ዘፈኖች የአፓርታይድን ዘረኛ አገዛዝ በደቡብ አፍሪካ ለመታገል እንደዋሉት ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ኖሯቸው ነገርግን ከmusical valueዋቸው ይልቅ፣ ለሕዝቡ ትግል በሚያበረክቱት አስተዋፅዖ (ወይም በinstrumental valueዋቸው) አንፃር ተወዳጅ ሆነው እንደሚወጡት የደቡባዊ አፍሪካ የሕዝብ ዜማዎች አድርገን ብንቆጥራቸው የምንሳሳት አይመስለኝም።
ባጠቃላይ የቴዎድሮስ አርማሽ (ቀናበል) ዘፈን በያንጀዳንዳችን ልብ ውስጥ የሚመላለሰውን ኢትዮጵያዊ ትካዜና ቁጭት፣ ከተስፋና አሁንም ዕድሉ አለን ከሚል የአይበገሬነት ስሜት ጋር ይዞ የወጣ ለራስ የተዘፈነ እንጉርጉሮ ያህል አድርጌ ወስጄዋለሁ።
በአጠቃላይ ግሩም ነው። ከባትሽ፣ ላትሽ፣ ፀጉርሽ፣ ወገብሽ… ርዕሶች ወጥቶ ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይን አንስቶ መገኘት በራሱ አርቲስቱን የሚያስደንቀው ልዩ መገለጫው ነው።
በእርግጥ በቅርብ ጊዜያት ብዙ ያገራችን ዘፋኞች ሀገራዊ ጉዳዮችን እያነሱ እያሸቀነቀኑ አጋጥመውኛል። እነ ኃይሌ ሩትስ፣ ሮፍናን፣ ልጅ ሚካኤልን ከአዲሱ ትውልድ ሊጠቀሱ የሚገባቸው ይመስሉኛል።
የራሱን ወኔ የታጠቀው ፋሲል ደመወዝ ደግሞ አለ። ለስለስ ባለ በረቀቀ ዜማ ሀገሯን የምታነሳሳው እጅጋየሁ ሽባባውም አለች። ቆየት ያሉትን  እነ ጥላሁንን፣ ንዋይን፣ ፀሐዬን፣ ጌታቸው ካሣን፣ አለማየሁን፣ ማህሙድን፣ አስቴርን፣ ወዘተ ካነሳሳን ዝርዝሩ ብዙና ሰፊ ነው።
ለእኔ ቴዎድሮስ ካሣሁንን ከእነ ማን ጋር እንደምመድበው  ለማወቅ ይቸግረኛል። ከሽሽግ ቸኮል ጋር የሚዘፍንን፣ ስለ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሚያዜምን፣ ስለ አብዮቱ ሰቆቃ የሚናገርን፣ ስለ ፍቅር እስከ መቃብር የሚያዜምን፣ ስለ አፄ ቴዎድሮስ የሚያቀነቅንን፣ እና መዓት ግጥሞችና ዜማዎችን የሚያመነጭን እንደ ቴዎድሮስ ካሣሁን የመሠለን ዘርፈ-ብዙ ሰው ሥራዎች በአንድ ካታጎሪና የዕድሜ ክልል መገደቡ የሚከብድ ይመስለኛል። ከፋሲል ደሞዝና ከንዋይ ደበበ መሐል አድርጌ ባስቀምጠው ለእኔ ቅር አይለኝም።
ቴዎድሮስ በሀገራዊ ጉዳይም የተፈናቀለ ወገኑን በመርዳት። ወላጅ ላጡ ህፃናት በጎ በማድረግና ስለ ባንዲራችን ክብር በመቆም። የማይለቅ ኢትዮጵያዊ ቸርነቱን ያስመሰከረ ልባም አርቲስትም በመሆኑ ጭምር አርዓያነት ባለው ስብዕናውም ከልብ መከበር የሚገባው የትውልዱ መሪ ይመስለኛል።
ለማንኛውም ሙሉውን አልበም በጉጉት ከሚጠብቁት ከሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መካከል ነኝ።  እንደ ከዚህ በፊቶቹ ጊዜያት ለምን የኮንሰርት አዳራሽ ይከለከላል ብዬ በሀይለቃል ከመፃፍ ተገላግዬ፣ ከምስጋና ጋር ይበል፣ ያብብ፣ ይርቀቅ ብዬ መርቄው ስሰናበተው ደስ እያለኝ ነው።
ሀገራችንን ከባችበት የመከራ እንጦርጦስ ያውጣልን ብዬ ተሰናበትኩ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።
Filed in: Amharic