>

የፀጥታው ምክርቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ የያዘው አቋምና አዝማሚያ፣ እና አንድምታዎቹ...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

የፀጥታው ምክርቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ የያዘው አቋምና አዝማሚያ፣ እና አንድምታዎቹ…!!!
አሳፍ ሀይሉ

በመጀመሪያ አንድን ግልፅ አቋም ማድነቅ እፈልጋለሁ። የአሜሪካንን ግልፅና ጠንካራ አቋም። ሁሉም የፀጥታው ምክርቤት ሀገሮች የአሜሪካን ዓይነት ግልፅና የማያወላዳ አቋም ቢይዙ ኖሮ፣ በኢትዮጵያችን የሚሰማ የተኩስ ድምፅ አይኖርም ነበር የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ!
የሆነ ሆኖ ሁሉም የምክርቤቱ አባሎች በግጭቱ በፍጥነት መቆም፣ በወታደራዊ መንገድ መፍትሔ እንደማያገኝና፣ በፍጥነት ሠላማዊ ፖለቲካዊ የጋራ መፍትሔ ላይ መደረስ እንዳለበት የጋራ አቋም ወስደዋል።
የማዕከላዊው መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ላይ ከእንግዲህ በኋላ መስተጓጎልን መፍጠር እንደማይችል ሁሉም ጠንካራ አቋሙን ገልጿል።
የቀረውና ሁሉንም ያላስማማው ነገር እነዚህን የውሳኔ ሀሳቦች ማንና እንዴት ያስፈፅማቸው የሚለው ዞሮ ዞሮ በመጨረሻ የሚጠብቃቸው አስጨናቂም አወዛጋቢም ጉዳይ ይመስላል።
አሜሪካ በኢትዮጵያችን የተከሰተውን የሚሊዮኖችን ነፍስ አደጋ ላይ የጣለ ጦርነትና የጦር ወንጀሎች ለመግታት ቆራጥ የተባበረ እርምጃና ጣልቃገብነትን የመደገፍ አዝማሚያ ያላት ይመስላል።
ሌሎች ደግሞ ነገሩ በአፍሪካ ኅብረትና ከፍ ካለም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል በሂደት እየታየ እንዲከወን የሚል ጥንቃቄ የተሞላበት (እና ለግጭቱ መራዘም ጊዜ የሚሰጥ) አቋም ወደመያዙ ያጋደሉ ይመስላሉ።
በዚህ ውሳኔ-አልባ ሁኔታ መሐል ለእኔ የሚታየኝና፣ የሚያሳስበኝ ነገር ጉዳያችንና ጦርነታችን ያለመፍትሄ ሊቀጥል ነው ማለት ነው – የሚለው ጉዳይ ነው።
ይህ ማለት የፀጥታው ምክር ቤት ቆራጥ ውሳኔ ባለመወሰኑ የተነሳ በሰጠው ያልተወሰነ (ገደብና አርጩሜ የሌለው) ጊዜ ውስጥ፣ ተዋጊ ወገኖች የተሻለ ዓለማቀፋዊ የድርድር ብልጫ ለመያዝ ሲሉ የማያወላውል  ድል ለመጨበጥ ከባድ ፍልሚያ ውስጥ የሚሠማሩበት ዕድል (ማለትም ጦርነቱ ተባብሶና ተስፋፍቶ የሚቀጥልበት ዕድል) ከፍተኛ ሊሆን ነው ማለት ነው።
ከፀጥታው ምክርቤት አባላት አቋሞች ሁሉ ላይ እንደተረዳሁት፣ ሁኔታዎች አሁን ባሉበት አኳኋን፣ የተ.መ.ድ. የፀጥታው ምክርቤት አቋም ሁሉንም የተጨበጠ መፍትሔ የማግኘት ኃላፊነቱን አጠቃልሎ በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ለሚመራው የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ አደራዳሪ ቡድን የሰጠ ይመስላል።
ችግሩ ደሞ ኦባሳንጆ ያቀረቡት 5 ነጥብ ገና ምንም ማለት ነው። ገና የተግባር መፍትሔዎችን አልያዘም። በብዙ አቅም መደገፍ አለበት። እና ብዙ መሬት ላይ ያሉ ጉዳዮችን ማወቅና ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አለበት።
ገና ብዙ መብሰል የሚቀረው ነገር ነው ያቀረቡት ኦባሳንጆ። ይህ ነው የሚባል የማያወላዳና የተጨበጠ ነገር የለውም።
በእርግጥ የማስማማት ጥረት መሐል ላይ ያለ አካል ከዚህ በበለጠ ጥልቀት ስለ ተደራዳሪ ወገኖች አቋምና አስተያየቱን ለመስጠት እንደሚቸገርም፣ እንደማይፈልግም ግልጽ ነውና ለጊዜው በዚሁ እንለፈው።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ቆራጥና የማያወላዳ የወሳኝነት ሚና ለመጫወት ያለመፈለግ ነገር በፀጥታው ምክርቤት አባላት ሁሉ ላይ ይስተዋላል ብዬአለሁ።
ይህ በአንድ በኩል የአሜሪካንና ምዕራባውያንንና፣ የእነ ራሺያና ቻይናን የጎራ መከፋፈል አስቀርቶ በጋራ ችግሩን ለመፍታት ከመፈለግ የመነጨ የድርድር አቋም እንደሆነ ግልፅ ነው።
በሌላ በኩል የሚሞተውና የሚራበው፣ ወደመቀመቅ የሚገባው በሚሊየን የሚቆጠር የሀገራችን ህዝብ ጉዳይ ቢያሳስባቸውም፣ እንደ ተናጠል ሀገራት ካየናቸው የኛ መባላት ጉዳይ እነርሱን በግልም ሆነ በጋራ የሚደቅንባቸው ይህ ነው የሚባል (ቅርብ የሆነ) ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ስጋት የለም። በመሆኑም ቢያንስ ለጊዜው ነገሩን ከሩቅ ሆነው መፍትሄ የሚሉትን በማቅረብና ጫና በማሳደር ላይ የተመሠረተ አቋምን ማራመድ የመረጡ ይመስላሉ።
ሌላውና እጅግ ወሳኝ ምክንያት ሆኖ ያገኘሁት የእኛ የከዚህ ቀደም ሀገራዊ ታሪካዊ precedent ነው። በ1983 አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ አድራጊና ፈጣሪ ሆና ኢትዮጵያንና ኤርትራን እንደገነጣጠለችው የመሠለ ክስተትና የታሪክ ተከሳሽነት ውስጥ ደፍረው እጃቸውን ማስገባት እንዳልፈለጉ ያሳያል።
በመጨረሻም የጣልቃገብነትን መዘዞች የመፍራትም ነገር አለ። ባለፉት ዓመታት፣ እስከ ቅርቡ የአፍጋኒስታን ቀውስ ድረስ የተፈጠረውን ብንመለከት፣ በአፍጋኒስታን፣ ሶርያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ኮንጎ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ወዘተ ሀገሮች ውስጥ የተደረጉ የሀይል ጣልቃገብነቶች ለሀገሮቹ ያመጡት ጤናማና ዘላቂ መፍትሔ እንደሌለ ሁሉም የተረዱት ይመስሉኛል።
ያንንም በመረዳት፣ ተመሣሣይ ስህተት የሚያስመዘግቡበትን አዲስ የሀይል ቤተሙከራ በኢትዮጵያ ምድር መክፈት (መጀመር) እንዳልፈለጉም የሚያመላክት ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አሰቃቂ የጦርነት ፍጅትና የእርስበርስ ጭፍጭፍ፣ ያለ ዳኛና ተቆጪ፣ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ ሊቀጥል ነው ማለት ነው።
በዚህ በኩል ሁለት ሳይነሱ መታለፍ የሌለባቸው ነገሮች አሉ። አንደኛው የኤርትራ ወታደራዊ ጣልቃገብነት ጉዳይ ነው። ሁለተኛው የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ጉዳይ ነው።
የኤርትራን ሠራዊት በተመለከተ ከእንግዲህ የኤርትራ ሠራዊትና ወታደራዊ ቁሳቁሱ በኢትዮጵያ ጦርነት እጁን የማስገባት ሙከራ ቢያደርግ፣ በአሜሪካ (እና ምናልባትም በኔቶ አጋሮቿ ጭምር የተደገፈ) የተናጠል ወታደራዊ እርምጃ ሰለባ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እጅግ ሰፊ እንደሆነ ነው ከአንዳንድ የምክርቤቱ ተሰብሳቢዎች ሀገራት አቋምና አኳኋን የተገነዘብኩት።
ሁለተኛው የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት የተመለከተው የፀጥታው ምክርቤት ጠንካራ አቋም ጉዳይ ነው። ይህ የምክርቤቱ አቋም “No more another Eritrea under Ethiopian skies” የሚል መልዕክት ያለው ይመስላል።
ይህ ከሆነ እነ ኦነግና ህወኅት ከትግራይና ከኦሮሚያ ነፃ አውጪነት ዓላማና እንቅስቃሴ ወጥተው ከማዕከላዊው መንግሥት ተቀናቃኝ የሆነ የጋራ ሀገራዊ የፖለቲካና አስተዳደር ግቦችን ያነገቡ፣ እና አሁን ከያዟቸው አጭርና ውሱን ትልሞች የገዘፉ መጠነሰፊ ሀገራዊ ዓላማዎችን አነግበው ለመንቀሳቀስ ሊገደዱ ነው ማለት ነው።
በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት በኩልም በጠብመንጃ እንደማያሸንፍና መፍትሄ እንደማያመጣ በማያወላዳ ቃል የተነገረው በመሆኑ፣ ሁሉንም በራሴ አምሳል ደፍጥጬ እገዛለሁ ከሚለው የጠቅላይ አድራጊ ፈጣሪነት ወጥቶ ከተቀናቃኞቹ የተለየ፣ እና ብዙ ድጋፍ የሚያስገኝለትን ሀገራዊ የፖለቲካና አስተዳደር ፖሊሲዎች ይዞ ለተፎካካሪ ፓርቲነት፣ ወይም ከገዢነት ሥልጣኑ ፎቀቅ ብሎ ከሌሎች ጋር መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን ቁመናና አቋም ይዞ መገኘት ይጠበቅበታል ማለት ነው።
በተረፈ ግን በፀጥታው ምክርቤት በተሰነዘሩ አቋሞች ሁሉ በአማራው ላይ በተለየ የተነጣጠረ አቋም አለመያዙ አስገርሞኛል። ቀድሞም መሆን የነበረበትና ተገቢነቱን ቀደም ብዬም በእንግሊዝኛ ጭምር ለአሜሪካ ኤምባሲ ስፅፍበትም የነበረ፣ በግሌም የማምንበት አቋም ነው ይህ። በሀገር ደረጃ እንጂ ተነጥሎ አማራ ጉራጌ የሚል አካሄድ ተገቢነት ስላልነበረው። ስለሌለውም።
ነገር ግን ሁሉም የምክርቤቱ አባላት በአፍ ወለምታ ካልሆነ በቀር በዚህ ደረጃ የችግሩም የመፍትሔውም ዋነኛ አካል አድርጎ አማራውን (ወይም አማራውን እየመራው ያለውን የፖለቲካ አካል) ለመጥቀስም፣ ለማሳተፍም፣ ከበረከቱም ሆነ ከእርግማኑ ለማቋደስም ያልፈለጉበት የጋራ ምክንያት ምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። በተለይ ቀደም ብለው ከተያዙና ከተራመዱ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ አቋሞቾ አንፃር እንግዳ ሆኖብኛል።
ባጠቃላይ የፀጥታው ምክርቤት ያካሄደውን አስቸኳይ ውይይት፣ በሀገራችን መጪ ጊዜና ሁኔታዎች ላይ ከሚያመጣው ፋይዳ አንፃር የታዘብኩትና የተገነዘብኩት ዋና ጭብጥ ይኸው ነው።
ፈጣሪ መጪውን ጊዜ ወደልቦናችን ተመልሰን እንደ አስታራቂ፣ መካሪ ሽማግሌ በሁሉም የፀጥታው ምክርቤት አባላት የተመከርነውን ቅንና ከልብ የመነጨ ለሕዝባችንና ላገራችን የሚጠቅም በጎ ምክሮችና ግሳፄዎች ተቀብለን የምንተገብርበት ልቦና ይስጠን ብሎ መመኘት በራሱ እንደ ትልቅ ምርቃት የሚቆጠር ይመስለኛል።
የምክርቤቱን ውይይት እየተመለከትኩ ኢትዮጵያ ዕድለኛ እንደሆነች ነው የገባኝ። በጣት ድምፅ ብልጫ መቀመቅ ውስጥ ሊከተን የሚችል እጅግ ግዙፍ አቅም ያለው ዓለማቀፍ አካልና፣ ኃያላንም አጋዥም አባላቱ በምን ዓይነት የኃላፊነትና የአክብሮት ስሜት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከገባበት ማጥ ለማውጣት ሲጨነቁና ሲደክሙ ማየት የሀገራችንን ዕድለኝነትና የታሪክ ሀብታምነት ያመለክታል።
ይህ ዓይነቱ በሁሉም በኩል የተስተዋለው፣ ወዳጅነት ያልተለየው የአክብሮትና ወገናዊ የተቆርቋሪነት ስሜት ሁሌ ይገኛል ብሎ መገመት ግን ከፍ ያለ ስህተት ላይ ይጥላል። ቂልነትም ነው።
የተሰጠንና ያለንን መልካም ዕድል፣ እና ወዳጃዊ ገፀበረከት ለራሳችን ጥቅም ማዋሉን ካላወቅንበት መጨረሻችን አስከፊ ነው። ይህን አውቀን፣ ጀንበር በላያችን ሳለች እንወቅበት እያልኩ አበቃለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ወዳጆቿን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ። 
___________________________
ውይይቱን በቀጥታ መከታተል ለምትሹ፦
Filed in: Amharic