>

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሪፖርት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት አግኝቷል....!!! (ዶክተር ዳንኤል በቀለ)

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሪፖርት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት አግኝቷል….!!!

ዶክተር ዳንኤል በቀለ


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ጋር በጣምራ በትግራይ ግጭት ላይ ያካሄዱት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሪፖርት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘቱን ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ እንደገለጹት፤የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ጋር በጣምራ በትግራይ ግጭት ተፈጸሙ በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ አድርገው ይፋ ሪፖርቱን በቅርቡ ይፋ አድርገዋል፡፡ ሪፖርቱንም 16 አገራት፤ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ኃላፊዎችና የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገሮች ጭምር ተቀብለውታል።

‹‹ሪፖርቱንም የተከታተሉት ሀገራት በጥናቱ የተሳተፉ ሁለቱን ተቋማትን ገለልተኛና ታዓማኒ ሪፖርት በማቅረባቸው አመስግነዋል፤የሪፖርቱን ምክር ሃሳብም በግጭቱ የተሳተፉ ወገኖች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በትግራይ ግጭት ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ጋር በጣምራ ያካሂዱታል ሲባል ብዙ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር የኮሚሽኑን የገለልተኛና የነጻነት ጥያቄዎችን አቀርበውና ተገቢ እንዳልሆነ ኮንነው እንደነበር አውስተው፤ ሪፖርቱ ይፋ እንደሆነም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና 16 አገራት ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎችና የጸጥታው ምክር ቤት አባል የሆኑ አገሮችም የሁለቱን ተቋማት የጣምራ ሪፖርቱን ተቀብለው በግጭቱ የተሳተፉ ወገኖችም ምክረ ሃሳቦችን እንዲተገብሩት ጥሪ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡አገራቱና ተቋማቱ ስለ ጣምራ ሪፖርቱ ገለልተኛነት፣በሙያ ብቃትና ትክክለኛነት መመስከራቸውን ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

በትግራይ የተካሄደው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሪፖርትም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነጻና ገለልተኛ መሆኑን ማረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት በጣምራ ያካሄዱት ምርመራ ያስፈለገበት አንዱ ዓላማ በትግራይ ግጭት ምን እንደተፈጸመ ለማጣራትና ለመርመር መሆኑን ዶክተር ዳንኤል አመልክተው፤በዓለም መገናኛ ብዙኃን መንግሥት ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል የሚሉና መሰል የተዛቡ መረጃዎችን ሪፖርቱ ያጋለጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ወገኖች በማይካድራ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ብለው ይሞግታሉ፤በሌላ ወገን ትግራይ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ብለው የሚከራከሩም አሉ ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ የጣምራ ሪፖርቱ ምርመራውን ያካሄደው ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ህግ አንጻር በመሆኑ ከዚህ ህግ ማዕቀፍ አንጻር ሲመዘን በማይካድራም ሆነ በትግራይ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንጂ የዘር ማጥፋት አለመሆኑን የምርመራ ሪፖርቱ አረጋግጧል ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ግጭቱ ከተጀመረ አንስቶ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማትና ግለሰቦች ጭምር መንግሥት ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀሙን ሲዘግቡ እንደነበሩ አውስተው፤በዕርዳታ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙም መንግሥት ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል የሚለው ውንጀላና የሀሰት መረጃ ትክክል አለመሆኑን ሪፖርቱ ማጋለጡንና እንቅፋት የመፍጠሩ ሥራም በአንድ ወገን ሳይሆን በግጭቱ የተሳተፉ በሁሉም ወገኖች የተፈጸመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ አባባል እንዲሁም በግጭት ውስጥ የሚሳተፉትን ወገኖች የሚደግፉ አክቲቪስቶች፣አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ስለ ግጭቱ የተለያዩ ዘገባዎችን ሲያሰራጩ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት እውነቱን ለማወቅ ችግር ነበር፡፡ ነጻና ገለልተኛ ምርመራ ማድረግ ያስፈለገው እውነተኛውን ነገር እውነተኛ ካልሆነው ለመለየትም ጭምር ነው። የምርመራ ሪፖርቱም ትክክለኛውን እውነት ነው ያረጋገጠው ብለዋል፡፡

ጌትነት ምህረቴ

Filed in: Amharic