>

የአሜሪካና ምዕራባውያን ጫናና መፈንቅለ መንግሥት በግርማዊነታቸው መንግሥት ላይ!! [መስፍን ማሞ ተሰማ] 

የአሜሪካና ምዕራባውያን ጫናና መፈንቅለ መንግሥት በግርማዊነታቸው መንግሥት ላይ!!

[መስፍን ማሞ ተሰማ] 

ንጉሠ ነገሥቱ [ ግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ] ርዳታ ለመጠየቅ [ኢትዮጵያን በግብርናና በኢንዱስትሪ ለማልማት] የተለያዩ የአሜሪካንና የአውሮፓ ሀገሮችን ከግንቦት 10 ቀን እስከ ሐምሌ 28 ቀን1946 ዓ/ም ከሁለት ወር በላይ ለሆነ ጊዜ ጎብኝተው ለትምህርትና መከላከያ ከሚውሉ ጥቃቅን ርዳታዎች በስተቀር [ ይህንን ነጥብ ልብ ማለት ያስፈልጋል ] ባዷቸውን ተመለሱ። ብዙም ሳይቆዩ ከመስከረም 25 ቀን 1947 ዓ/ም አስከ ህዳር 28 ቀን 1947 ዓ/ም በዘጠኝ የአውሮፓ ሀገሮች በመዘዋወር የልማት ገንዘብ ፍለጋ ከሁለት ወር በለሠይ ጉብኝት ቢያደርጉም አሁንም ለልማት የሚውል ርዳታ ሳያገኙ ቀሩ።
በእነዚህ ሁለት ጉዞዎች አሜሪካንና አውሮፓን ጎብኝተው ከምዕራቡ ዓለም ምንም ርዳታ በማጣታቸው ወደ ምሥራቅ ሀገሮች ሄደው ርዳታ ለማግኘት ከወዳጃቸው ከዩጎዝላቪያው መሪ ከፕሬዚዳንት ማርሻል ብሮንዝ ቲቶ ጋር ሲመክሩ ቆዩ። በነሐሴ ወር 1951 ዓ/ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስሊዎስ የፓትሪያርክ ሹመት ላይ ለመገኘት ወደ ግብፅ እንደሄዱ ሳይታሰብ በዚያው ጉዞ ድንገት ሶቪየት ኅብረት ሞስኮ መግባታቸው ተሰማ።
ሞስኮ በገቡ በሶስተኛው ቀን ለልማት ሥራዎች ሁሉ የሚያስፈልግ እና በረጅም ጊዜ የሚከፈል አራት መቶ ሚሊዮን ሩብልስ አግኝተው ተመለሱ። [ ይህ የርዳታ ገንዘብ በዚህ ወቅት የምንዛሪ መጠን ከአምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰማኒያ ሺህ ዪኤስ ዶላር በላይ ሲሆን ዶላሩ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ደግሞ ከሁለት መቶ ስልሳ ስድስት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ መሆኑን ልብ ይሏል ] ለልማት የሚያውሉትን መጠነ ሰፊ የርዳታ ገንዘብ አግኝተው ነሐሴ 18 ቀን 1951 ዓ/ም ኢትዮጵያ እንደተመለሱ በአራተኛው ቀን ነሐሴ 22 ቀን 1951 ዓ/ም ማታ እና በ14ኛው ቀን መስከረም 7 ቀን 1952 ዓ/ም ከቀኑ በስምንት ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለልማት ታጥቆ እንዲነሳ በሬዲዮ ሰፊ ንግግር አሰሙ።
ንጉሠ ነገሥቱ ከምዕራቡ ዓለም የተነፈጉትን ለልማት ሥራዎች(ና) ለጭሰኞች መሬት እየሰጡ ለማስፈር  የሚውል የገንዘብ ርዳታ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ተቀናቃኝ ከነበረችው ከኮሚኒስቷ ሶቪየት ኅብረት በማግኘታቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ በየዘርፉ በሚገኙ የልማት ሥራዎች ላይ ለሥራ ታጥቀው እንዲነሱ የሚቀሰቅስ ሰፊ ንግግር አደረጉ። ከዚህ ሁኔታ በሁዋላም ከምሥራቅ ሀገሮች ጋር የተደረገው ግንኙነት የምዕራቡን ኃያላን መንግሥታት ስላስቆጣቸው በየአቅጣጫው በኢትዮጵያ ላይ ጫናቸውን ያሳድሩ ጀመር። [እዚህ ላይ በኛ ዘመን ኢትዮጵያ በቀንደኛነት ከአሜሪካ ከእንግሊዝ ከፈረንሳይና ከተመድ የገጠማትን ጫናና ጣልቃ ገብነት ልብ ማለት ያስፈልጋል ] በተለይ በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ኮሎኔል ፒንክ የኦጋዴን ሶማሌዎችን በታላቋ ሶማሌ የህልም እንጀራ የመመገብ ፕሮፓጋንዳ ኦሮሞዎችንም እንዲጨምር ለማድረግ እንቅስቃሴውን አጠናከረ። በደጋው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ለሚኖሩ የኦሮሞ አርሶ አደሮች “ኃይለ ሥላሴ ከኮሚኒስቷ ሶቪየት ኅብረት ያመጣው ብድር እናንተን ጭሰኞችን ባለዕዳ ለማድረግ አማራውን ለማበልፀግ እና ከቀድሞውም በበለጠ ለአማራው ባለርስቶች ተገዥ እንድትሆኑ ለማድረግ ነውና ተነሱ” የሚል ፕሮፓጋንዳ ይነዛ ጀመር።
ፕሮፓጋንዳው በዚህ መልክ እየተነዛ እያለም ንጉሠ ነገሥቱ በዘመነ መንግሥታቸው ረጅምና ታሪካዊ የሆነውንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ልማት ታጥቆ እንዲነሣ በመድረግ ላይ ያተኮረ ንግግር በሬዲዮ አስተላለፉ። ንግግሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ ከሰራ በጓዳው፣ ደጁ፣ ጓሮው፣ ሜዳው ሸለቆው ጋራውና ሸንተረሩየሚገኘው ሀብት ተዝቆ የማያልቅ መሆኑን በመጥቀስ በዋዛ ፈዛዛ ጊዜውን ሳያባክን በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ የሚቀሰቅስ ነበር። ያ የንጉሠ ነገሥቱ ንግግር ለዚያን ጊዜም ሆነ ለአሁኑ እና ለወደፊቱም ትውልድ ጭምር ኢትዮጰያውያን ከድኅነት ተላቀው በብልፅግና መኖር የሚችሉበትን መንገድ የሚያመላክት ነው። [በምዕራባውያን በተቀነባበረ  ከፍተኛ አሻጥሮችና ሁዋላም በ1953 ዓ/ም በአሜሪካውያን ድጋፍ በነግርማሜ ነዋይ የተሞከረውና በርካታ የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት የልማት ውጥን ደጋፊ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በወንድማማቾቹ ግርማሜና ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ የተረሸኑበት መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎ የልማት ውጥኑም እንዲከሽፍ ተደርጓል።]
* ሕይወቴ – ለአገሬ ኢትየቀጵያና ለወገኖቼ ኢትዮጵያውያን ዕድገት የነበረኝ የሥራ ጥማት –  ቅፅ አንድ (ከ1917 እስከ 1967 ዓ/ም) ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ – ገፅ ብዛት 636 * [ ከላይ ባቀረብኩት ፅሁፍ ውስጥ በቅንፍ የተቀመጡት ከመፅሀፉ በቀጥታ ቃል በቃል የተወሰዱ ሳይሆኑ ነገር ግን የመፅሀፉን መልዕክት የጠበቁ ጭማሮዎች ናቸው – መማተ ]
Filed in: Amharic