>

ደቡብ ምዕራብ ክልል - ከሽኩቻው ባሻገር... !!! (ወንድወሰን ተክሉ)

ደቡብ ምዕራብ ክልል – ከሽኩቻው ባሻገር… !!!

ወንድወሰን ተክሉ

በ1980 ዓም የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት (የደርግ) ባካሄደው ጥናት ውጤት፣ በኋላም በ1985 ዓም የሽግግር መንግሥት ላይ በተዘረዘረው መሠረት የካፋ እና ኢሉባቡር ክፍለሀገሮች ውስጥ የነበሩ ማንነቶችን በወረዳ እና አውራጃ እያደራጀ መቀመጫውን መቱ፣ ጅማ እና ሚዛን ተፈሪ (ያሁኑ ሚዛን አማን) ላይ ያደረጉ የአስተዳደር ማዕከሎች ነበሯቸው – ያሁኖቹ የደቡብ ምዕራብ ክልል ወገኖቻችን፡፡ የህወሓት/ኢሕአዴግ አስተዳደር በመጀመሪያ ‹ክልል 11› ተብሎ መቀመጫውን ሚዛን ላይ አድርጎ ቢቆይም ከሸካቾ ዞን (አሁን ሸካ) 3 ወረዳዎችን ወደ ጋምቤላ እና ኦሮሚያ ሸኝቶ የቀሩትን ወገኖች ከሌሎች 4 ክልሎች ጋር ተጨፍልቆ ‹ደቡብ ክልል› ተብሎ እስከ ዛሬ ለቆየው ‹የክልሉ ዋና ከተማ ርቀት› ውዝግብ ዳረገን፡፡ ሁሉን ዐዋቂው መንግሥታችን 5 ክልሎችን ጨፍልቆ ‹አንድ ናችሁ! አንድ ሁኑ!› ቢልም ሐዋሳን ለ26 ዓመት ሲገነባ ቆይቶ የሲዳማ ዞን ፖለቲከኞች ባደራጁት ሤራ ከዛሬዋ ገነት ከያኔዋ አቧራማ ከተማ (1989 አቧራዋን በጋሪ ላይ ሆኜ ጠጥቻለሁ፤) ‹ውጡልኝ!!› ተባሉ፤ እነሆ የቀድሞዎቹ 5 ክልሎችም ለ26 ዓመታት ያጠራቀሙትን የሽኩቻ እና የሤራ ስንቅ ተጠቅመው 11 ክልል እንጂ 5 መሆን አይበቃንም አሉ፡፡
የሲዳማ ማንነት በክልል መጠሪያነት መጠቀሱ የሚየያኮራቸው ፖለቲከኞች ባለፉት 2 ዓመታት ለሕዝቡ ምን እንዳስገኙለት ባላውቅም የክልሉ ዋና ከተማ ዙሪያ በመሆናቸው አላግባብ የተጠቀሙትን የሥራ ዕድል የሚውጥ መዋቅር እና በጀት ግን መፍጠር እንዳልቻሉ የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ የደቡብ ክልል መንግሥት ቢሮዎች ሠራተኞች ‹በሲዳማነታችን ወደ ክልላችን እንዛወር፤› ብለው ቢያመለክቱም የሚቀበላቸው መዋቅር እና በጀት አላገኙም፡፡ የደቡብ ምዕራብ ክልል ሲቋቋም እንዲህ ያለ ጫና ውስጥ እንዳይገባ የሚያደርግ በጎ ዕድል ያለው ሲሆን ከዞኖቹ ከ700 ኪሜ በላይ ርቀው መጥተው በየቢሮው የመቀጠር ዕድል ስለላልነበረ የተፈጠረ አጋጣሚ ነው፡፡ የቀሩት ዞኖች ደግሞ ከወልቂጤ እስከ ጂንካ፣ ከሳጃ (የም) እስከ ዲላ (ጌዲኦ) የተበተኑ በመሆናቸው ቢያንስ 2 ተጨማሪ ክልሎችን በቅርቡ እንደምናዋልድ በግልጽ ይታያል፡፡ ይህ በሰላም በተቋጨ እንጂ የባሰው ፈተና ገና የሚቀረን ወቅት ላይ ነን፤ እንደ ሀገር፡፡
ጌዲኦ ለብቻው ተቆርጦ በመልክአምድር ተለይቶ፣ ከደቡብ ኦሞ እስከ ወላይታ ድረስ ሰፊ ዝምድና እና የጋራ እሴት ቢኖርም የፖለቲከኞቹ ጥቁር መነጽር የሚያሳየው ልዩነትን ብቻ መሆኑ (ከኢትዮጵያ ተገንጥለው ሀገር የሚሆኑ ይመስላሉ ሲደሰኩሩ፤)፣ በእያንዳንዱ ዞን እና ወረዳዎች ውስጥ ጭምር ገና ብዙ የሚያነጋግሩ አጀንዳዎች በይደር መቆየታቸው፣ አንዳንድ ዞኖች ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ ክልል የመሆን እንጂ ከሌላ ጋር የመተባበር ፍላጎት እና ምቹ ሁኔታ ማጣታቸው፣ … ወዘተ የዘር ፖለቲካችን የሚያመጣብን በሽታ ገና እንደሚያቆስለን ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ አዲሱ ደቡብ ምዕራብ ክልል በአንጻራዊነት ጥሩ ነገሮች ተሳክተውለት ሕግን በተከተለ መንገድ ወደ ልደቱ እየገሰገሰ ነው፡፡
የአዲሱ ክልል ምሥረታ ሀሳብ ገና ከጥንቱ ከልደቱ ከ1987 ዓም ጀምሮ ሲነሣ የቆየ ሲሆን በ1994 ዓም በአቶ መለስ ዜናዊ ተጽዕኖ (አፈሩ ይቅለላቸው) እንዳሁኑ እንዲደራጁ በፓርቲ ደረጃ ተወስኖላቸው ነበረ፡፡ ነገር ግን የክልል ምንነት የተወሳሰበበት ጊዜ ስለነበረ የዋና ከተማ ሽሚያ አጣልቷቸው ለሕዝብ አገልግሎት ብለው የለፉትን ሰዎች ድካም ሽኩቻው አተነነው፡፡ ዛሬም እነሆ ይኸው ሽኩቻ በደንብ ተጠናክሮ መጥቶ አራት ከተሞች ላይ የክልሉን መንግሥት መቀመጫ አዳራጃለሁ ብለዋል፡፡ ይህ ቢሳካም ባይሳካም ኅዳር 13 ለክልል ምሥረታ ቀጠሮ የተያዘ ቢመስልም የዞኑ ፖለቲከኞች ግን ‹‹ጠንካራው ዝሆን እኔ ነኝ!›› በሚል የጫካ ፉክክር ውስጥ ናቸው፡፡
አራቱ_ዕጩ_ከተሞች ቴፒ (ከሸካ ዞን)፣ ሚዛን አማን (ከቤንች ሸኮ ዞን)፣ ቦንጋ (ከካፋ ዞን) እና ተርጫ (ከዳውሮ ዞን) ሲሆኑ የምዕራብ ኦሞ ዞኗ ‹ጀሙ› እና የኮንታ ልዩ ወረዳዋ ‹አመያ በግልጽ የተነገራቸው ድርሻ የለም፡፡ የዚህ ሁሉ ፍትጊያ ምክንያት አለመተማመን ነው፤ ‹ዋና ከተማው እኛ ጋር ካልሆነ እና ወደፊት ክልሉ ቢፈርስ በሕዝባችን ሀብት ያለማነውን ከተማ ጥለን መሄድ ትልቅ ኪሣራ ነው!!› የሚለው ጉልሁ እና ተገቢው ምክንያት ነው፡፡
#የዳውሮ ሕዝብ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ዋና ከተማውን ጅማ አድርጎ ከተማዋ በኢሕአዴግ አደረጃጀት ኦሮሚያ ውስጥ ስትቀር ከጅማ እንዲወጣ ተገደደ፤ በኋላ ደግሞ ሰሜን ኦሞ አስተዳደር አካባቢ እና ክልል 8 (ካልተሳሳትኩ) ተብሎ በቋንቋ እና ባህል ከተዛመዱት የዳሞት ወገኖቹ ጋር ሆኖ አርባምንጭን እና ወላይታ ሶዶን አልምቶ ወዳሁኑ ሐዋሳ ተሸኘ፤ ለ26 ዓመት ያለማውን ሐዋሳ ትቶ ወደ አዲሱ ክልል ሲመጣ ተጨማሪ ስህተት እንዳይሠሩ ቢፈሩ እውነታቸውን ነው፤ 500ሺህ ሕዝብ ይዞ እንደ ውሃ ላይ ኩበት ሲንገዋለሉ መክረም ያሳዝናል፡፡ ሌሎቹ ዞኖች እንደ ዳውሮ ባይሆኑም ትናንሹን ምክንያታቸውን እያጋነኑ ዋና ከተማውን ወደራሳቸው መጎተታቸው ‹ብልጥ ከሌላው ስህተት ይማራል፤› ነውና ይሁን፡፡
ፖለቲከኞቹ እንዳሻቸው የሚቆምሩበት አጀንዳ ግን ይህን ያህል የሚያጣላ አይመስለኝም፡፡
– ለሥራ ዕድሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫነታቸው ሳይዘነጋ፣
– የሀብት ፍትሐዊ ክፍፍሉ ሕገመንግሥታዊ መሆኑ ተሰምሮበት፣
– የክልል ባለሥልጣን መሆን ማለት በክልሉ ውስጥ ላሉ መላው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ኃላፊነት እንዳለበት ሳይረሳ፣
– በግልም ሆነ በቡድን ሤራቸው ውስጥ በወገንተኝነት የሚስሠራ አድልዎ ለግለሰቦች ኪስ ማደለቢያ የተቆመረ ካልሆነ በቀር ለደሃው የተራበ አንጀት ጠብ የማይል በመሆኑ፣
… ወዘተ የክልል መቀመጫነትን ይህን ያህል ገመድ ባይጓተቱበት ጥሩ ነበረ፡፡
የሕገ መንግሥቱን ረቂቅ እንዳየሁትም ወሳኝ የፍትሐዊነት ስጋቶችን ለመቅረፍ ሞክሯል፡፡ 3.2 ሚሊዮን ሕዝብ እና 13 ነገዶችን ያቀፈው አዲሱ ክልል ኅዳር 13/ 2014 ዓም ሲመሠረት በክልል ዋና ከተማነት ምን ቢያደርግ ይሳካለታል;!
የክልሉን መንግሥት አካላት በኮሚቴ ደረጃ በአራት ከተሞች ሊደለድሉ መስማማታቸው ተነግሯል። በነዚህ ከተሞች እንዴት እንደሚያደራጅ ከምክርቤቱ ምሥረታ በኋላ ባሉት ቀናት በአዋጅ ስለሚጸድቅ ከወዲሁ ነጻ እና የግል ሀሳቤን መግለጽ ፈለኩ፡፡
1. የሕግ_አውጪው_ምክርቤቶች፡- አንድ ከተማ ላይ እንደሚሆን ተገልጧል፤ ይህ የክልሉን ምክርቤት ጽ/ቤት እና የብሔረሰቦች ምክርቤት እንደሚያካትት ግልጽ ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ተዛማጅ አገልግሎት የሚሰጡትን የባህል፣ ስፖርት፣ ቱሪዝም እና መሰል ጉዳዮችን በአስፈጻሚነት፣ በተቆጣጣሪነት እና በምርምር ማዕከልነት የሚመሩ ተጨማሪ የክልል መሥሪያ ቤቶች አንድ ላይ ቢሆኑ ጥሩ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ በዚያውም የዳውሮ እና ኮንታ አካባቢዎች ወደፊት የኢትዮጵያ ቀደምት ጥበቦች የሚገለጡበት አካባቢ ስለሚሆን እነዚህ የመንግሥት አካላት ተርጫ ከተማ ላይ ቢሆኑ ጥሩ ይመስለኛል፡፡
2. የሕግ_አስፈጻሚ_አካላት፡- ይህ የክልሉን ፕሬዚዳንት፣ የገዢውን ፓርቲ ጽ/ቤት፣ የፌደራል መንግሥት የአስፈጻሚ አካላት ቅርንጫፎች፣ ክልል ነክ የመያድ እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ያካትታል፡፡ ዋናው የዝሆኖቹ ፉክክር ይህንን የመንግሥት አካላት ቡድን ወደራሱ ዞን ከተማ ለመውሰድ ሲሆን የክልላዊ ሀብትን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀም ተቋማት ከመያዙ አንጻር ሽኩቻው ትርጉም ያለው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ቦንጋ እና ሚዛን ከተሞች በዚህ ጉዳይ የሞት ሽረት ትግል ገጥመው እየተፎካከሩ መሆናቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ እንደ መፍትሔ ግን የካቢኔ አባላት የሆኑትን ተቋማት ብቻ ከፕሬዚዳንቱ እና የፓርቲ ጽ/ቤቱ ጋር በዚህ ከተማ ማስቀመጥ እና ቀጥታ የሥራ ትስስር የሌላቸውን እንዲሁም አንድን ባለጉዳይ እንዳይንገላታ በቴክኖሎጂ ሊተሳሰሩ የሚችሉትን ቢሮዎች ሌላ ቦታ ማስቀመጥ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በዕውቀት እና በቅንነት ላይ የተመሠረተ ድርድር እና ምክክር ከተደረገ ይህን የተቋማት ቡድን ቦንጋ ላይ ማድረግ ጥሩ ነው ብዬ አሰብኩ፤ በዚያውም ላለፉት ወራት ቦንጋ አካባቢ ሲጎነጎን የነበረው ሤራ የሕዝብን እና የሀገርን ሀብት አለፍ ሲልም የክቡሩን የሰው ልጅ ሕይወት ሲቀጥፍ የነበረ በመሆኑ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስቀጥል ነው፡፡ የቦንጋ ከተማ ያለባትን የመሬት መንሸራተት ችግር በአስተማማኝ ደረጃ መፍትሔ የሚሰጥ የከተማ ፕላን አዘጋጅቶ የሕዝብን ሕይወት መጠበቅ ደግሞ የዞኑ አስተዳደር ግዴታ ይሆናል፡፡
3. ሦስተኛው የመንግሥት አካል የሆነው #የሕግ_ተርጓሚ ክፍል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ከክልል ፖሊስ እና የዓቃቤ ሕግ ክፍሎች ጋር ወደ ሚዛን ከተማ ቢሄድ ከተማዋ የተተርፈረፈ ምቹ ሁኔታዎች አሏት፡፡ ከክልሉ አስፈጻሚ አካላት ውስጥ የካቢኔ አባላት ያልሆኑትን ጨምሮ ተጨማሪ ተቋማትን ወደ ሚዛን መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ (ተጨማሪ ሐተታ ከታች አለ፤)
4. አራተኛው የቴፒ ከተማ በአዲሱ ክልል ካሉት ከተሞች ሁሉ ለክልል ዋና ከተማነት ምቹ እና ዝግጁ ነበረች፡፡ በሸካ ዞን ላይ የሚቆምሩ የፌደራል እና የክልል ፖለቲከኞች ከ1985 ዓም ጀምሮ የቀውስ ማዕከል አድርገዋት ዕድገቷ ተገትቶ መቆየቱ ብዙ ነገርን አጉድሎባታል፡፡ ከዚህ የተነሣ የክልሉ ካቢኔ አባለት ያልሆኑትን ቢሮዎች እና ተጨማሪ ተቋማትን ተቀብላ ብታስተናግድ እና የስብሰባ ማዕከል ብትደረግ ሁለገብ ተመራጭነት ይኖራታል፡፡ ደቡብ ሱዳንን፣ ኡጋንዳን እና ሩዋንዳን የሚመለከቱ የንግድ መስመሮች መተላለፊያ፣ የባቡር እና ከፍተኛ አውራ ጎዳና ደረቅ ወደብ፣ የቡና፣ ሻይ እና ቅመማቅመም ምርምር እና ቁጥጥር ማዕከልነቷ፣ ወዘተ ከተጠናከረ ከተማዋ በአዲሱ ክልል ውስጥ የራሷን ክልላዊ ድርሻ በኮከብነት ትወጣለች፡፡
ተጨማሪ_ሐተታ፡-
የክልል መንግሥት ሲባል በባለሥልጣኖች ክፋት ላይ የተንጠለጠለ ስግብግብነት እያስቸገረ እንጂ የፌደራሊዝም መርሕ ‹አለመማከል – ዲሴንትራላይዜሽን› በመሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶች ወደ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች በበቂ ደረጃ መውረድ አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በክልል በጀት የሚተዳደሩ እና ከክልሉ ካቢኔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው ተቋማትን በሚዛን እና ቴፒ ብቻ ሳይሆን በጀሙ እና አመያ ጭምር አድርገው ፍትሐዊነትን ቢለማመዱ ጥሩ ነበረ፡፡ በሥልጣን ላይ ያሉትን የሌሎች ዞኖች አመራሮች የቤት መሥሪያ ቦታ ሰጥተው ለማማለል መሞከራቸውንም ስንሰማ አካሄዳቸው ከወዲሁ ጅላጅል እና ክፉ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡
ይህንን በተመለከተ ባያያዝኳቸው ፎቶዎች እንደምናየው የ2011ዱ የደቡብ ክልል የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ብዛት 18 የካቢኔ አባላት (አሁን ወደ 22 አድገዋል፤) እና ከ60 በላይ ክልላዊ ተቋማትን ያካተተ ነው፡፡ በዛ ላይ ደግሞ በክልል በጀት የሚንቀሳቀሱ የልማት ድርጅቶች እና ማዕከላት አሉ፤ ለምሳሌ አንድ ክልላዊ ስቴድየም፣ ክልላዊ የሚዲያ ድርጅት፣ የሥልጠና እና አገልግሎት ቅርንጫፎች፣ ወዘተ፡፡ እነዚህን ተቋማት በፍትሐዊነት መርሕ በሚዛን፣ ቴፒ፣ ጀሙ እና አመያ መቀመጥ የሚችሉትን አይቶ በትስስራቸው፣ በሥራ ቅልጥፍና እና ተዛማጅ ተፈጥሯዊ ስነምህዳራቸውን አገናዝቦ መመደብ በመርገም ውስጥ የሚገኝን በረከት ማፈላለጊያ ብልሃት ነው፤ በተቃራኒው ደግሞ 78ቱንም ቢሮዎች እኔ ከተማ ካልሆኑ ብሎ ማሰብ (መሞከር አይደለም!) በበረከት ውስጥ የሚጠራ እርግማን ይሆናል፡፡ የቦንጋዎቹ ዝሆኖች በጣም ስግብግብ በመሆናቸው ግን አብዛኞቹን እያመካኙ ለመጠቅለል መቋመጣቸው አይቀርም፤ በሕዝብ ስም ሲምሉ እና ሲገዘቱ ለካፋ ሕዝብ የሚጠቅሙ ይመስላሉ፡፡ የክልሉን ወገኖቻችንን ‹እግዜራቸው› ይርዳቸው፡፡
መውጫ፡-
ከ2012 ዓም ጀምሮ በደቡብ ክልል መበተን ጉዳይ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ እንድሳተፍ ዕጩ እየተደረኩ ብመደብም ከያቅጣጫው ያሉ ዝሆኖች እየፈሩኝ ከየታጨሁበት ኮሚቴ ያሰወግዱኛል፡፡ በ80ዎቹ ሽማግሌዎች ውስጥ በፌደራል ደረጃ ተወስኖ፣ በደቡብ ምዕራብ ክልል ምሥረታ ላይ በአደራጆቹ ዞኖች ከሸካ ተጠቁሜ ስብሰባዎች ላይ ጭምር እንድገኝ ጥሪ ከደረሰኝኝ በኋላ ፈሪዎቹ ጉግማንጉጎች ከሩቁ ያስወግዱኛል፡፡ ምኔ እንደሚያስፈራቸው እንጃ ግን ልናዘዝ፤ ‹‹አይዟችሁ! ሥልጣን አልፈልግም፣ ለሕዝብ የሚጠቅም ወይም በምክንያት ላይ የተመሠረተ ሀሳብ ሳቀርብ የምትጠሉኝ ከሆነ ደግሞ መጀመሪያውኑ እኮ እኔም አብሪያችሁ ለመሥራት አልፈልግም፤ ሳልጠይቅ ተሹሜ አገልግዬ፣ ስታሳድዱኝ ትቼላችሁ የወጣሁት የድሮው ወንድምስሻ ነኝ፤ አትፍሩኝ፤ አልፈልጋችሁም!!››
Filed in: Amharic