>

በቡድን መድፈር፣ ዝርፊያና ድብደባ፡ የሕወሐት ጥቃትና ጭፍጨፋ ሰለባ አማራዎች ምሥክርነት (ጌታቸው ሽፈራው)

በቡድን መድፈር፣ ዝርፊያና ድብደባ፡ የሕወሐት ጥቃትና ጭፍጨፋ ሰለባ አማራዎች ምሥክርነት
ጌታቸው ሽፈራው

 

(የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ሪፖርት)
ሴቶች በአፈሙዝ ተገድደው በቡድን ተደፍረዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ድብደባና ሰቆቃ ደርሶባቸዋል፤
የሕወሐት ታጣቂዎች የጤና ተቋማትን ከዘረፉና ካወደሙ በኋላ የመድኃኒት እና የሕክምና አገልግሎት ተቋርጧል፤
ጦርነቱ ወደ አማራ ክልል ከተሻገረ ወዲህ ዘግናኝ የመብት ጥሰትና ጭፍጨፋ ተፈጽሟል፤
የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ) በአማራ ክልል፣ ነፋስ መውጫ አካባቢ ወረራ በፈጸመበት እና ጥቃት ባደረሰበት ነሐሴ አጋማሽ 2013 ዓ.ም 16 የከተማው ሴቶች በወራሪው መደፈራቸውን ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ከጭፍጨፋ የተረፉት ሴቶች በጠመንጃ አፈሙዝ ተገድደው በሕወሐት ታጣቂዎች በቡድን ተደፍረዋል፣ ንብረቶቻቸው ተዘርፈዋል፣ እጅግ የከፋ አካላዊ ድብደባና ሰቆቃ ደርሶባቸዋል፡፡ አምነስቲ መረጃ ሲሰበስብ ቃለ-መጠይቅ ካደረገላቸው 16 የአስገድዶ መደፈር ሰለባ ሴቶች ውስጥ 14ቱ በቡድን የተደፈሩ ናቸው፡፡ የሕወሐት ታጣቂዎች በነፋስ መውጫ የሚገኙ የጤና ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በመዝረፍ የተረፋቸውን አውድመውታል፡፡
አማራና አፋርን በኃይል ለማጥቃት በማሰብ ባካሄደው ወረራ፣ ከነሐሴ 6-15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የጋይንት ወረዳ ማዕከል የሆነችውን ነፋስ መውጫን በወረረባቸው ቀናት ጥቃትና ውድመት ፈጽሟል፡፡ በእነዚህ 9 የወረራ ቀናት ውስጥ 70 የሚሆኑ ሴቶች በሕወሐት ታጣቂዎች መደፈራቸውን መናገራቸውን የአማራ ክልል መንግስት ባለሥልጣናት ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቀዋል፡፡
‹‹የጥቃቱ ሰለባዎች በሰጡን ምስክርነት የሕወሐት ታጣቂዎች ድርጊት አስጨናቂና እጅግ አውሬያዊ መሆኑን ገልጸው በጦር ወንጀል የሚመደብ ብሎም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (despicable acts by TPLF fighters that amount to war crimes, and potentially crimes against humanity) ነው፡፡ ታጣቂዎቹ የሰው ልጅን የሰብዓዊነትና የሞራል ልዕልና ያጨቀየ ተግባር ነው የፈጸሙት›› የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሐፊ አግነስ ካላማርድ
ዋና ጸሐፊዋ አግነስ ‹‹የሕወሐት ታጣቂዎች እየፈጸሙ ካሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል፣ የዓለም-አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋት ያፈነገጠ ተግባር፣ አስገድዶ መድፈር እና ጾታን መሠረት ያደረጉ አስከፊ ጥቃቶችን በአፋጣኝ እንዲያቆሙ፡፡ በእንደዚህ ያለ ወንጀል ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ትዕግስት እንደማይኖርና ተሳታፊዎች ሁሉም ተጠያቂ እንዲሆኑ ያሰማራቸው አካል (ሕወሐት) አካልም ሊገነዘበው ይገባል›› በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡
የሕወሐት የቡድን የመድፈር ወንጀል እና የአካል ጥቃት
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቡድን አስገድዶ መደፈር እና ጾታን መሠረት ያደረገ አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸውን 16 የንፋስ መውጫ ሰለባዎች ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ የቪዲዮ መደወያ መተግበሪያ በመጠቀም ቃለ-መጠይቅ አድርጎላቸዋል፡፡
በተጨማሪም የንፋስ መውጫ ሆስፒታል ኃላፊን፣ በደረሰው ጥቃት ዙሪያ እና ከጥቃቱ ማግስት ስለተፈጠረው የስነ-ልቦና ቀውስ መረጃው ያላቸውን የአካባቢውን እና የክልሉን የሥራ ኃላፊዎች በማነጋገር መረጃ ሰብስቧል፡፡
በዚህም የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ዴስክ ኦፊሰር እንደገለጹት፣ 71 ሴቶች አካባቢውን ወርረውት በነበሩ የሕወሐት ታጣቂዎች ተገደው ተደፍረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፌደራል ፍትሕ ሚኒስቴር ቁጥራቸው ወደ 73 ከፍ እንደሚል አሳውቋል፡፡
  ጥቃቱ ሰለባ ሴቶች ለአምነስቲ እንደገለጹት፣ ነሐሴ 6/2013 ዓ.ም የሕወሐት ታጣቂዎች ከተማውን እንደተቆጣጠሩ ነው አስገድዶ መድፈር የጀመሩት፡፡ በሚናገሩት የትግርኛ ቋንቋ ተጽዕኖ በሚታወቅበት አነጋገር፣ አማራን አዋራጅ ስድቦቻቸው እና በግልጽም ሕወሐት መሆናቸውን በመናገራቸውማንነታቸውን መለየት ችለዋል፡፡
በዕምነት የተባለች የ45 ዓመቷ የንፋስ መውጫ ከተማ የጥቃቱ ሰለባ፣ 4 የሕወሐት ታጣቂዎች ነሐሴ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በምሽት ወደቤቷ እንደመጡ፣ ቡና እንድታፈላላቸው ካስገደዷት በኋላ፣ 3ቱ አስገድደው በቡድን እንደደፈሯት ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተናግራለች፡፡
‹‹አዝማሚያቸውን በፍጥነት ስለተረዳሁ፣ ሴቶች ልጆቼን እንዳይደፍሩብኝ በፍጥነት ከቤት እንዲሸሹ አደረኳቸው፡፡ ሆኖም የሕወሐት ታጣቂዎች ልጆቼን መልሼ እንዳመጣቸው አስጨነቁኝ፡፡ እኔም እንደማላመጣላቸው ነገርኳቸው፡፡ ከዚያ መሳደብ ጀመሩ፡፡ ‹‹አማራ አህያ ነው››፣ ‹‹አማራ የማይረባ ነው›› እያሉ ይሳደቡ ነበር፡፡ ሆኖም ከመካከላቸው አንዱ ስድቡን እንዲያቆሙ ይከለክላቸው ነበር፡፡ ‹‹ይች እናት ናት፣ ልናጠቃት አይገባም›› ይላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እሱን አባረው ቀሩት 3ቱ እየተፈራረቁ አስገድደው የመድፈር ወንጀል ፈጸሙብኝ››
የ30 ዓመቷ የንፋስ መውጫ ከተማ ምግብ ቤት ባለቤት የሆነችው ሌላኛዋ ሰለባ ገበያነሽ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል የተናገረችው፡  ‹‹የፈጸሙብኝን ለእናንተ ለመናገር እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ አስገድደው ደፍረውኛል፡፡ ልጆቼ እያለቀሱ ከፊታቸው ለሦስት ደፍረውኛል፡፡ ትልቁ ልጄ 10 ዓመቱ ሲሆን ትንሹ 9 ዓመቱ ነው፤ የሕወሐት ታጣቂዎች ሲደፍሩኝ እየተመለከቱ ያለቅሱ ነበር፡፡ ታጣቂዎች ማድረግ የፈለጉትን ሁሉ አድርገው ሄዱ፡፡ ከባድ ድብደባም ፈጽመውብኛል፡፡ ከቤቴ ሽሮዬን እና በርበሬዬ ሳይቀር ዘርፈውኛል፡፡ በጥፊ እና በእርግጫ ደብድበውኛል፡፡ አፈሙዝ ደግነውም እንደሚገድሉኝ አስፈራርተውኛል››
 የ28 ዓመቷ ሐመልማል እንጀራ በመሸጥ ትተዳደራለች፡፡ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም 4 የሕወሐት ታጣቂዎች ሴት ልጇ ፊት በቡድን አስገድደው እንደደፈሯት ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተናግራለች፡
‹‹የ 2 እና የ10 ዓመት ሴት ልጆች አሉኝ፡፡ ልጆቼን እንዳይገድሉብኝ በከፋ ሰቆቃ ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ ‹እኔን እንዳሻችሁ ግደሉኝ፣ ልጆቼን አትንኩብኝ› እያልኩ አለቅስ ነበር፡፡ ትንሿ በወቅቱ ተኝታ የነበረ ቢሆንም፣ ትልቋ ልጄ የሚሆነውን ትከታተል ነበር፡፡ እሷ ያየችውን እና የደረሰባትን ጭንቀት ለመናገር አቅም አጣለሁ፡፡
 ከሠውነት ዝቅ የሚያደርጉ የጥላቻ ስድብ ጥቃቶች
በቡድን ከመድፈርና ከድብደባ በተጨማሪ የሕወሐት ታጣቂዎች ዘር-ተኮር የማዋረጃ ስድቦችን እንደተጠቀሙ፣ በተለይም ‹‹አማራ አህያ ነው›› እና ‹‹አማራ ስግብግብ ነው›› የሚሉ ይገኙበታል፡፡ አንዳንዶቹ በግልጽ ሴቶቹን የሚደፍሩት የፌደራል መከላከያ ሠራዊት የትግራይ ሴቶችን ስለደፈረ ለበቀል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በ 4 የሕወሐት ታጣቂወች የተደፈረችው ሐመልማል ለአምነስቲ ስትናገር፡
‹‹ቀድሞ አስገድዶ የደፈረኝ ዋናው መሪያቸው ነው፡፡ ‹አማራ አህያ ነው፣ አማራ ትግራይን ጨፍጭፏል፣ መከላከያ ሚስቴን ስለደፈረብኝ ነው አንችን የምደፍርሽ› ይል ነበር፡፡
መስከረም፣ በ3 የሕወሐት ታጣቂዎች በቡድን የተደፈረችው፣ በመሣሪያ ሰደፍ የተደበደበችው የ30 ዓመቷ ወጣት ለአምነስቲ የተናገረችው፡ ‹‹ይሰድቡኝ ነበር፤ ‹አንች አህያ አማራ፣ ከዚህም በላይ ብናደርግሽ ትችይዋለሽ› እያሉ ነው የደፈሩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ እራሴን ስለሳትኩ የሆነውን አላውቅም፡፡››
አስገድደው ከደፈሩ በኋላ ዝርፊያ መፈጸም
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳረጋገጠው፣ ከአስገድዶ መድፈር በመቀጠል የሕወሐት ታጣቂዎች በየቤቱ ዝርፊያ ፈጽመዋል፡፡ በትንንሽ ንግድ እና የቀን ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ እና ከእጅ-ወደ-አፍ ሕይወት ውስጥ ያሉ የጥቃቱ ሰለባዎች የቤት አስቤዛ፣ ጌጣጌጥ፣ ጥሬ ገንዘብና ስልኮቻቸውን ተዘርፈዋል፡፡
በትንሽ ንግድ የምትተዳደረው መስከረም ለአምነስቲ የተናገረችው የሚከተለውን ነው፡፡ ‹‹ምግብ ወደምሸጥባት ቤት 4 ሆነው ገብተው ምግቡንም፣ መጠጡንም ከወሰዱብኝ በኋላ ሁለቱ አስገድደው ደፈሩኝ፡፡ የጣት ቀለበቴን እና የአንገት ሐብሌን እና የእጅ አምባሬን አውልቀው ወሰዱት፡፡›› ፍረሕይወት ከነሐሴ 6-14 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት በተደጋጋሚ በሕወሐት ታጣቂዎች በቡድን አስገድዶ መደፈር የተፈጸመባት ናት፡፡ ገንዘቧን እና ስልኳንም ዘርፈዋታል፡፡
ነሐሴ 6 ቀን 2013 ዓ.ም በሕወሐት የመደፈር ጥቃት ሰለባ ስትሆን፣ ሱቋን ዘርፈውና አውድመው ጌጣጌጦቿን ነጥቀዋታል፡፡  ‹‹ንብረቴን በሙሉ ዘርፈውኛል፡፡ ቢራ ጠጥተው ሲጠግቡ 4 ሳጥን ቢራ እና 2 ሳጥን ለስላሳ መጠጥ ሰባብረውብኛል፡፡ የወርቅ አንገት ሐብል ከላዬ ላይ በጥሰው ወስደዋል፡፡ አልጋ ልብስ እና አንሶላ ሳይቀር ገፍፈው ወስደዋል፡፡ ባዶዬን ስለቀረሁ ምንም መተዳደሪያ የለኝም፡፡››
የፈጠረው የጤና ቀውስ
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጥናቱ ቃለ-መጠይቅ ካደረገላቸው ከ16ቱ የጥቃቱ ሰለባዎች ውስጥ 15ቱ በከፋ አካላዊ፣ የጤና እና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የጀርባ ሕመም፣ ደም የቀላቀለ ሽንት፣ የመንቀሳቀስ ችግር፣ ድብታ እና ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ሕወሐት የጤና ተቋማቱን በማውደሙ የተነሳ፣ ከሁለቱ የጥቃቱ ሰለባዎች ውጪ ማናቸውም የጤና ምርመራና ክትትል ማድረግ አልቻሉም፡፡ በተለይ ድኅረ-መደፈር የጤና ክትትል፣ በአስገድዶ መደፈር የሚመጣን እርግዝና መከላከያ፣ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ምርመራ፣ የግብረ-ስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎች፣ አካላዊ ጉዳት ሕክምና እና የስነ-ዐዕምሮ ክብካቤ ማግኘት አልቻሉም፡፡ እንዲህ መሠል የጤና ግልጋሎት የሚሰጥ አንድ ግብረሰናይ ድርጅት ለአምነስቲ እንደተናገረው፣ ችግሩ ወዳለባቸው ቦታዎች ተንቀሳቅሶ እርዳታ ለማድረግ መንግስት በተራድዖ ተቋማት ላይ የነበረው አቋም እክል ፈጥሮበት ነበር፡፡
ከሰለባዎቹ ውስጥ አንዷ በዕምነት ስትሆን፣ በአስገድዶ መደፈር ሳቢያ ጀርባዋ ላይ እንደሚያማት ገልጻ፣ ‹‹በአምላክ ቸርነት ብቻ ነው ከዚህ በኋላ የምድነው›› በማለት ሰቆቃዋን ትገልጻለች፡፡
የ20 ዓመቷ የቤት ውስጥ ሠራተኛዋ ሠላማዊት፣ ነሐሴ 6 ላይ 3 የሕወሐት ታጣቂዎች አስገድደው በቡድን የደፈሯት ሲሆን ላልተፈለገ እርግዝና ተዳርጋለች፡፡ ምንም የሕክምና አገልግሎትም ማግኘት አልቻለችም፡፡  አብዛኞቹ የዚህ አሰቃቂ ጥቃት ሰለባዎች ጭንቀት እና አስጊ የሆነ የመደበት ስሜት ውስጥ ገኛሉ፡፡
ከትቃቱ ማግስት አንስቶ ለ54ቱ የጥቃት ሰለባዎች የዕለት ድጋፍ ማድረጉን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኃላፊዎች ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የምክር አገልግሎት እና የቴና ተቋማቱን መልሶ የማደራጀትና ሥራ የማስጀመር ተግባራትም እየተከናወኑ ነው፡፡
ተጎጂዎችን በተገቢው መንገድ ለማቋቋምና ለመደገፍ የኢትዮጵያ መንግስትም ፈጣን እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ እንደ መጀመሪያ አፋጣኝ እርምጃ፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታና ድጋፍ ተደራሽነት ያልተቋረጠ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡
Filed in: Amharic