>

የዋሽንግተን ፉከራ እና የአፍሪካ ቀንድ ቀያይ መስመሮች!   (እስሌማን አባይ)

 የዋሽንግተን ፉከራ እና የአፍሪካ ቀንድ ቀያይ መስመሮች!!!!! 
እስሌማን አባይ

የአፍሪካ ቀንድ በጅቡቲ የሚገኙትን ጨምሮ የ16 አገራት የጦር ሰፈሮች መገኛ ነው። አምስቱ በሶማሊያ ይገኛሉ። ሁለቱ የኤምሬትስ ሲሆኑ በሶማሊላንድ፣ በሞቃዲሾ ደግሞ የቱርኩ አለ። የአሜሪካውም ባዶግሌ ላይ የተገነባው ነው። የእንግሊዙ በባይዶዋ፤ የኳታርና የሳዑዲ ጦር ሰፈሮችም  እየተገነቡ የሚገኙ ናቸው፡፡
በኤርትራም ሁለት ወሳኝ ወታደራዊ ካምፖች አሉ። አንደኛው የእስራኤል ያውም በወሳኙ ባብ አል-ማንዴብ በር ላይ፤ ሌላኛው የኤምሬትስ ሲሆን የሩሲያም እየተገነባ ነው፤ ሊገነባ የው የሚሉ መረጃዎች እየተሰሙ ይገኛል፡፡
ጅቡቲ ሕዝቧ 1 ሚሊዮን አይሞላም። ጠቅላላ አመታዊ ምርቷም ከ 1ቢሊዮን ዶላር በታች ነው። ይሁንና ስትራቴጂክ አቀማመጧ በዓለማችን ቁልፍ የባህር ጎዳና በሆነው ”ባብ ኤል-ማንደብ ስትሪት ላይ ሰየማትና ሀያላን ወታደራዊ ሰፈራቸውን ለመመስረት የሚ ተፈላጊ አገር አደረጋት።
የአሜሪካ፣ የጀርመን፣ የቻይና፣ የጃፓን፣ የጣሊያንና ስፔን ጦር ሰፈሮች በጂቡቲ ይገኛሉ። የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያም እየተገነቡ ናቸው። በተጨማሪም ፈረንሳይ 1 የባህር ኃይል ጣቢያና ሁለት ጄት ማረፊያዎች በጅቡቲ ያሏት ናት።
የንፁህ ውሃ ችግር ያለባት ጅቡቲ ከኢትዮጵያ በየቀኑ 100,000 ኪዩቢክ ሜትር ንፁህ ውሃ ይደርሳታል። የማስተላለፊያ መሠረተ ልማቱ በቻይና የገንዘብ ድጋፍ 300 ሚሊዮን ዶላር ፈጅቶ 2017 ላይ ስራ የጀመረ ነው። ጅቡቲም የውሃ ጥሟን ከኢትዮጵያ በሚላክላት ንፁህ ውሃ ትቆርጣለች፡፡ ለኃይል ማስተላለፊያ ከህዳሴ ግድቡ እስከ ጅቡቲ በተዘረጋው መስመርም ኢትዮጵያ ዋናዋ የጂቡቲ የኤሌትሪክ ምንጭ ትሆን ዘንድ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
በኦጋዴን 2014 ላይ ለተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ኢትዮጵያና ጂቡቲ የ765 ኪ.ሜ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመዘርጋት (በኢትዮጵያ 700 ኪ.ሜ፣ በጅቡቲ 65 ኪ.ሜ) መፈራረማቸው ይታወቃል፡፡ ጋዙ በጅቡቲ ወደቦች በኩል ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን በ4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው ደግሞ በቻይናው ፖሊ-ጂሲኤል ግሩፕ ነው፡፡
የጅቡቲው ዱራሌ ወደብ በዱባዩ DP World እንዲተዳደርም ስምምነት ተጠናቋል፡፡ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ድርሻ እንድታገኝ በማድረግ ኢትዮጵያንም የወደብ ባለቤት የሚያደርግ ፊርማ የተቀመጠለትም ነው፡፡
በቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒን 2017 ላይ የተከፈተው የቻይና ወታደራዊ ካምፕ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካ ጉልህ አንድምታ ያለው ነው። ቻይና ከግዛቷ ውጭ የገነባችው ትልቁ ወታደራዊ ካምፕ ይኸው በጂቡቲ የሚገኘው ነው። ጅቡቲ 100 ሚሊዮን ዶላር የክራይ ክፍያ ከቻይና ታገኛለች። (ቻይና በ590 ሚሊዮን ዶላር የጂቡቲውን የወደብ ወጪ የሸፈነችም ናት)። በጦር ሰፈሩ ምንም እንኳ በይፋ ባይገለፅም አንዳንድ ተቋማት 10ሺ የቻይና ወታደሮች እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በጂቡቲ ሉሚናር ከሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡ አሜሪካ በጂቡቲ 2001 የከፈተችው የሉሚናር ጦር ሰፈሯ 2000 ገደማ ወታደሮች ናቸው የሚገኙበት።
የቻይናው ወታደራዊ ካምፕ ተዋጊ ጄት ተሸካሚዎችና አራት የኑክሌር ሰርጓጅ መርከቦችን ጨምሮ በግዙፍነቱ በቀጣናው ተስተካካይ የሌለው ባለ 124 ሜትር ሁለት የጦር መርከቦች ማረፊያም ነው። በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ ዋናዋ ተዋናይ ቻይና ናት። የቀንዱ አገራትን 80 % የጋራ ንግድ ድርሻ የሚይዝ ትስስር ፈጥራለች። የኢትዮጵያም ቁጥር 1 የንግድ አጋር ናት።
በቅርቡ ምዕራባዊያን ከቤይጂንግ ሁለት መልክ ያለው ትግል ከፍተዋል። አንዱ በቀጥታ ከቻይና ጋር። ሁለተኛው ደግሞ የቻይናን አጋሮች በመጠምዘዝ ቤይጂንግን በተዘዋዋሪ መፋለም…። ለዚህ አላማቸው ማሳኪያነት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የጀመሩትን ጣልቃ ገብነት #ቻይና በይፋ ተቃውማዋለች!!!!
በተጨማሪም ኢትዮጵያና ቻይና የ road and belt ፕሮጄክት #የጋራ_ደህንነት ስምምነት ከወር በፊት ተፈራርመዋል። የደህንነት መረጃ መለዋወጥና የሽብር ድርጊቶችን መመከት የስምምነቱ አላማ ነው። ከአመታት በፊት ቻይና ወታደራዊ አታሼዋን በአዲስ አበባ ሰይማለች። ይህም በአፍሪካ በጣም ጥቂት ውሳኔ መሆኑ የሁለቱን ትብብር ያሳያል የተባለለት ነው። አለማቀፍ ተንታኞችም ቻይና በአፍሪካ ከምጣኔ ሐብት ትብብር በይፋ ወታደራዊ መዳፏን ማንቀሳቀስ ልትጀምር ነው እያሉ ይገኛል። በተለይም ሺ ጂንፒንግ ከቀናት በፊት የምዕራባዊያንን አድማ ለማምከን ያፀደቁት ፀረ-ማዕቀብ ህግ ቤይጂንግ ብረት-ለበስ አቋም ለመጀመሯ ዋና ማሳያ ሆኗል።ምዕራባዊያን እንደተኩላ ተቧድነው  ቻይና ላይ እየጮኹ ይገኛል። እሷም እንደፀናች ቀጥላለች። አፍሪካ ደግሞ ተተኳሪ ስትሆን፤ ማዕከሏ ደግሞ አዲስ አበባ የመሆኗን ጉዳይ ሰሞነኛው የአሜሪካ ከሩሲያና ቻይና ባደረገቻቸው ውዝግቦች ገሃድ ሆኗል።
ቻይና ምዕራባዊያኑን ረፍት በነሳው የbelt and road initiative በኩል አህጉራትን አስተሳስራለች። ተሳስራበታለችም። ይህ #BRI በስያሜው የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ሆኖ ቢታወቅም የባቡር መስመር ብቻ አይደለም። ከኢኮኖሚም በላይ ነው። ቻይና ከኢኮኖሚ ኃያልነት ወደ ሁለገብ የአለም ሀያልነት ለመሻገር የጀመረችው ስራ መሆኑን እነ አሜሪካ ከረፈደም አውቀውታል። ቻይና የቤልት ኤንድ ሮድ ጉዳይ የብሔራዊ ደህንነቴ ጉዳይ ነው በማለት #ህግ አፅድቃለች። ይህን የሚገዳደር ለሆነ ተግባር የቻይና ጦር እንዲሳተፍ ያስገድደዋል ማለት ነው።
ይህን ግስጋሴ ለመግታት በድሮው የጫና አካሄድ የሞከሩት ምዕራባዊያኑ ሐሳባቸው አልሰመረም። እንደውም የቻይናን ተፅዕኖ ከፍ አደረገው። ይህን ተከትሎ build back better በተባለ ፕሮጀክት እስከ 20 ትሪሊዮን ዶላር በመመደብ አሜሪካ የምዕራብ አጋሮቿ ጋር እንቅስቃሴ ጀምራለች። ከዚህ ጎን ለጎን አሜሪካ እንደ ኢትዮጵያ ቀውስ በገጠማቸው አገራት ላይ እጇን ከመስደድ አልተቆጠበችም። ቻይናም ጥቅሟን ታሳቢ ያደረገ ምላሽ በመስጠት ላይ ናት። የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር መስመር ቁልፍ የ BRI አካል ነው። የቻይና ደህንት ጉዳይ ነው ማለት ነው። እዚህ አካባቢ እንኳን ትህነግ የአሜሪካ እጅ ከገባም ጉዳዩ #የቻይና ጭምር ነው ማለት ነው።
ሌላው ደግሞ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ወዳጅ እየቀነሰች የቻይና አጋሮች እየበዙ ናቸው። ባለፈው አመት የቻይናና ኤርትራ ውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች ተገናኝተው ነበር። ትልልቅ ፊርማ አኑረዋል። ይህ ርምጃ ለምዕራባዊያኑ ስጋት ሆኗል። ሌላ የቻይና ጦር ሰፈር በኤርትራ ሊገነባ ነው በማለት። ሩሲያም በኤርትራ ወደብና ጦር ሰፈር የመገንባት ሀሳቧ እያደገ ነው የመጣው። በ2017 ይህው ተዘግቦ ነበር። ከሱዳን አብዮት በኋላ ወሬው ጠፍቶ ነበር። ካርቱም ሩሲያን ትታ ወደ አሜሪካ መጓዟ የሩሲያን አማራጭ ኤርትራ ላይ ያደርጋል። ቱርክ በተመሳሳይ በሶማሊያ ካላት ጦር ሰፈር በተጨማሪ ወደ ኤርትራም ታማትራለች። ህንድም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የድርሻየን ልጠቀም ካለች ሰነባብታለች።
ታዲያ ቻይና በሰፊው በተሰናሰለችው የአፍሪካ አህጉር፣ እያንዳንዱን አገር በመሰረተ ልማቷ ባስተሳሰረችው የአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ጎን የተሰለፉት ቱርክ ህንድ ሩሲያ በጉጉት በሚፈልጉት ቀጣና ውስጥ ኢትዮጵያ ወሳኝ አገር ናት።
#እንደ መደምደሚያ፦ ዋሽንግተን ወደ #ኢትዮጵያ ጦር ልታዘምት ነው የሚለው ሰሞነኛ አጀንዳ ታዲያ ከኢትዮጵያ ባሻገር የነዚህ ሁሉ አገራት ጭምር ጉዳይ ነው። ለዚህ የአሜሪካ ፉከራ በዋናነት ስትራቴጂክ ባላንጣዋ ከሆኑት ሌሎች ሃያላን ጋር የተጠና አፋጣኝ ትብብር ማድረግ ጠቃሚውና አዋጭ የቤት ስራችን ይሆናል ማለት ነው። ለዚህ ተግባር የምናባክነው ደቂቃ ሊኖር አይገባም!!
Filed in: Amharic