>

ህገመንግስቱ በግዜው አለመሻሻሉ የኢትዮጵያን የመከራ ዘመን ያራዝመዋልን ? (ደረጀ መላኩ -የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ህገመንግስቱ በግዜው አለመሻሻሉ የኢትዮጵያን የመከራ ዘመን ያራዝመዋልን ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)


ከማርክሲስት ርእዮትዓለም በተቃረነ መልኩ በጎሳና ቋንቋ ላይ መሰረቱን ያደረገው  የኢትዮጵያው ህግመንግስት አንዱን ለመሸለም(ለመጥቀም) ሌላውን ደግሞ ለመጉዳት ተዘጋጅቷል የሚል እምነትና ድምዳሜ ላይ የደረሱ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ቁጥራቸው የትዬሌሌ እንደሆነ የህገመንግስት ምሁራን በጥናቶቻቸው የደረሱበት ጉዳይ ነው፡፡ ጥንታዊ፣ ወደ ታሪክ ማህደር ውስጥ የተዶለ ማንነት በብዙ የህይወት አውድ ነጋ ጠባ ሲታይ ወይም ሰርክ አዲስ የህይወት መመሪያ ሲሆን በጎሳዎች ወይም በነገዶች ማሃከል ጥላቻ ይነግሳል፡፡ በሌላ አነጋገር አሁን በሰለጠነው ዘመን እንደ ጥንቱ እንደጠዋቱ በጎሳ አስተሳሰብ መመራት ልዩነትን እንጂ አንድነትን አያመጣም፡፡ እኛ እና እነርሱ እየተባባልን ግዜያችንን የምናጠፋ ከሆነ ከግጭት ውስጥ ለመውጣት ሊያዳግተን ይቻለዋል፡፡ ግጭቶች ይስፋፋሉ፡፡ ሰላምና ደህንነት ይርቀናል፡፡ ማህበራዊ ሀብታችን ይሸረሸራል፡፡ በብሔራዊ አስተሳሰብ ለመኖር ዳገት ይሆንብናል ( ብሔራዊ አስተሳሰብ ይሸረሸራል፡፡) ለትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትና ሌሎች አክራሪ ብሔርተኞች ጥቅም እንዲያመች  ተደርጎ የተዘጋጀው ሕገመንግስቱ ጫፉ ላይ ሁለት ስለት እንዳለው ጎራዴ የሚቆጠር ነው፡፡ ይህ ባለሁለት ስለት ጫፍ አንዳለው ጎራዴ የሚመሰለው ህገመንግስት እውነተኛ የፌዴራል ስርአትን ዴሞክራሲን ምሉሄበኩልሄ በሆነ ሁኔታ ማስፈን አልተቻለውም፡፡ አሁን ያለው ህገመንግሰት በወቅቱ በገዜው በምሁራን የሚከለስበት፣የሚሻሻልበት መንገድ እንዲፈለግ ስማጸን በትህትና ነው፡፡ ህገመንግስቱን ለመሻሻ ል ካልተመከረበት መዘዙ ብዙ መሆኑ እጅጉን ያሳስበኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም   የማይመከረውን ግን ሊሆን የሚችለውን የመለያየት ሁኔታ ያፍጥነዋል፡፡ ግን ኦኮ እኛ እንኳን ተለያይተን በአንዲት ሉአላዊት ሀገር ጥላ ስር ሆነን ወደ የእድገት ጎዳና ለመጓዝ ያልቻልን አሳዛኝ ሰዎች ነን፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ምሁራን የዩጎዝላቪያ እጣ ፈንታ እንዳይደርሰብን በሚል ያዘጋጁትን  ጠቃሚ ምክረ ሃሳባቸውን በተለያዩ ግዜያት እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ የእኛ የኢትዮጵያውያን ጉዳይ ግን ከዩጎዝላቪያ ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ ነው፡፡ የእኛ ጉዳይ አስፈሪና አደገኛ ነው፡፡ በአውሮፓ ምድር ባልካን ባህር አካባቢ ትገኝ የነበረው ዩጎዝላቪያ   ከመፈረካከሷ በፊት  በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ ጥንካሬ ከኢትዮጵያ በእጅጉ የተሻለች ነበረች፡፡ ወደ ትንንሽ ሀገር ከተከፋፈለች በኋላም ቢሆን የባህር በር ያለቸው አዳዲስ ሀገራት ተፈጥረው መኖር ችለዋል፡፡( መኖር ከተባለ ማለቴ ነው፡፡) የእኛ ነገር ግን ለየቅል ነው፡፡ ህይወት ጎምዛዛ ትሆንብናለች፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ገበሬ ጨለማ ውስጥ የሚዳክር ሲሆን፣ገና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ብርቅ የሆነበት ነው፡፡ እባካችሁን እምቡር እምቡር ማለቱን ትተን ስለ ኢትዮጵያ እንሰብ፣እንወያይ፣እንነጋገር፡፡

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በውስጥ እና ውጭ ተግዳሮቶች (ጫናዎች) ውስጥ የወደቀ እንደሆነ ምንም የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ ከአይምሮዬ ጓዳ ጋር  ስመክር የመጣል ሃሳብ መንግስት በከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ስለወደቀ አንዳንድ ለውጦችን የሚያደርግበትን ግዜ አራዝሞት ይሆን ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ በሌላኛው የአይምሮዬ ጓዳዬ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያን ለመከራ የዳረጋትን ህገመንግስት ማሻሻል ለምን ዳገት ሆነበትም ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ እርግጥ ነው ይገባኛል፡፡ ይህ ህገመንግስት እንዳለ፣ሳይሻሻል እንዲቀመጥ የሚፈልጉ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም፡፡ ህገመንግስቱም በአንድ ለሊት፣ለተወሰኑ ቡድኖች ጥቅም ሲባል ብቻ መሻሻል አለበት በሚል ድምዳሜ ላይ የምደርስ ተላላ ሰውም አይደለሁም፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለውም ማእከላዊ መንግስትም ቢሆን ህገመንግስቱን ለማሻሻል ስለፈለገ ብቻ የሚሳካለትም አይመስለኝም፡፡ የመንግስት አካል የሆኑም ሆነ ሌሎች በጎሳ አኳያ የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችና ተከታዮቻቸው ህገመንግስቱ ስለሚሻሻልበት ሁኔታ የሚደማ ልብ ያላቸው አይደሉም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ አሁን በምንገኝበት አስጨናቂ ግዜ ህገመንግስቱን ለማሻሻል ጊዜ ያገኘ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ በከባድ ችግር ውስጥ ስለተዶለች መጀመሪያ የገጠማትን ችግር ለማስወገድ የቆረጠ ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበት አደጋ ያጋለጣት የጎሳ ፖለቲካ አደረጃጀት የሚፈቅደው ህገመንግስት ነው የሚሉ ምሁራን በርካታ ናቸው፡፡ ለማናቸውም አሁን ባለው ተጨባጭ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መንግስት ተግዳሮት አጋጥሞታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የገጠመው ተግዳሮቶች የሚከተሉት ይመስሉኛል፡-

1.አለም አቀፍ ተጽእኖ በተለይም በምእራቡ አለምና በተባበረችው አሜሪካ

2.በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጄክት ምክንያት ከግብጽና ሱዳን የገጠመን ተቃውሞና ሴራ

3.አሸባሪው የወያኔ ቡድን የፈጸመውን ወረራ ድል ለመንሳት የምናደርገው ህልውናን የማስከበር ጦርነት

4.በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተከሰቱ ሰብዓዊ ቀውሶች (humanitarian crisis)

5.የመሰረታዊ ምግቦች ዋጋ ጣራ መንካት

6.በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ስራፈት መሆናቸው እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ አንዳንድ ተስፋን የሚፈነጥቁ ተግባራት ከመንግስት አኳያ ገቢራዊ ሆነዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ለብሔራዊ እርቅ ዝግጁ ነኝ መባሉ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡( የአደራዳሪው ገለልተኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡) ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳን የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን (ጥቂት ቢሆኑም መልካም ጅማሮ ነው ብዬ አስባለሁ) የብልጽግና ፓርቲ ስልጣን መስጠቱ ፓርቲውን ያጠነክረዋል፡፡ ወደ ዴሞክራሲያዊ ጎዳናም ይወስደዋል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ከዚህ አኳያ መንግስት ሊመሰገን ይገባዋል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የብልጽግና ፓርቲ በጣም አጣዳፊና አሳሳቢ የሆኑትን የጎሳ ፖለቲካ ተቋማትን በፍጥነት ማሻሻል፣ መከለስ ከፊቱ የተደቀነ ከባድ ስራ ነው፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያን ህገመንግስት የሚሻሻልበትን የሰለጠነ መንገድ ለመፈለግ በታሪከ ፊት ቆሟል፡፡ መንግስት ህገመንግስቱን በተመለከተ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለመፍጠር መንፈሳዊ ወኔ ቢታጠቅ ለፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን መፍትሔ ለመሻት ግማሹ መንገድ ሊጀመር ይቻለዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

 • ህገመንግሰቱ በልማት አኳያ ስለነበረው ውጤት
 • ህገመንግስቱ ለዲሞክራሲ ማበብ እንቅፋት ስለመሆኑ
 • ማህበራዊ ትስስርን በተመለከተ
 • የአናሳዎች መብት
 • ሉአላዊነት እና
 • የግዛት አንድነትን በተመለከተ  ወዘተ ብሔራዊ ውይይት በቅንነትና በእውነት መሰረት ላይ መደረግ አለበት፡፡ የተጠቀሱት ነጥቦች በሰለጠነ መንገድ፣በሰከነ መንፈስ ውይይት ከተደረገባቸው ህገመንግስቱን ለማሻሻል እዳው ገብስ ይሆናል ብዬ አስባለሁ

እንዴት አሁን ያለንበት አጣብቂኝ ውስጥ ደረስን ?

ከጥንታዊት የአክሱም ስረወመንግስት የንግድ ግንኙነት ጀምሮ የዛግዌ ስረወመንግስትን ጨምሮ በማናቸውም ዘመነ መንግስት የብዙ ነገዶች ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ሰለሞናዊ ስርወ መንግስት ተከትሎ ከፊል የፌዴራል ስርዓት እውን እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡በግዜው በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ተጠሪነታቸው ለኢትዮጵያ ንጉሰነገስት( King of Kings (Emperor) የሆኑ ንጉሶች ነበሩ፡፡

በነገራችን ላይ ከዘመናዊነት እሳቤ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ አሃዳዊ እና ጠንካራ ማእከለዊ መንግስት ያቆጠቆጠው እንደ አውሮፓውኑ 1920 ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሆነ ማእከላዊ መንግስት እድገትና ግስጋሴ አንዳይኖረው የፋሺስት ጣሊያን ወረራ አደናቅፎታል፡፡ ( ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ አመታት ታሪክ ያለው አሃዳዊ የሆነ የመንግስት ታሪክ እንዳላት ልብ ይሏልል፡፡) ፋሺስት ጣሊያን በኢትዮጵያ የጎሳ መርዝ ዘር በኢትዮጵያ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ከመዝራቷ እና ከመከፋፈሏ ባሻግር ኢትዮጵያን በአምስት የጎሳ ክልሎች ከፋፍላ ነበር፡፡ እነኚህም ኤርትራ እና ትግራይን አንድ ላይ ያደረገ ግዛት፣አማራ፣ሐረር፣ኦሮሞ/ሲዳሞ፣ እና የሶማሊያ ግዛት ነበሩ፡፡ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በጎሳና ቋንቋ መሰረት ላይ ሆና እንድትከፋፈል በማድረጓ የኢትዮጵያን አንድነት ለማላላት ጥርጊያ መንገድ የከፈተች ሀገር ናት፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ጥንስሱ የተጀመረው በፋሺስት ጣሊያን የወረራ ዘመን ነበር፡፡እንደ ደጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1960 የተጀመረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ  ከኢትዮጵያ ታሪክ ተጻራሪ በሆነ መልኩ በአንድ ለሊት ከጎሳ ቡድንነት ወደ ‹‹ሀገርነት›› ጥያቄ መቀየሩ የታሪካችን አንዱ አሳዛኝ ገጽታችን ነው፡፡ በነገራችን ላይ የ1960ዎቹ የተማሪዎች አንቅስቃሴ ውስጥ ለኢትዮጵየና አንድነት ሲሉ መስእዋት ሆነው ያለፉ አንደነበሩ የአሁኑ ትውልድ ማወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ በተማሪው አንቅስቃሴ ውስጥ ሰርገው የገቡት የጎሳ ፖለቲከኞች ግን የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግር ግን ብዙም አላላመጡትም ነበር፡፡ አልተረዱትም ነበር፡፡ ወይም አልፈለጉም ነበር፡፡

በግዜው የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪ የነበረው ዋለልኝ ‹‹ ብሔራዊ ጭቆና እንደነበር›› ከተነገረ በኋላ ጨቋኙም የነበረው አማራ እንደነበር ጽሁፍ አቅርቧል፡፡ የዋለልኝን ትርክት በዋነኝነት የተቀበለው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡ የወያኔ ቡድን በበኩሉ የተገንጣይነት አላማውን ለማሳካት ይረዳው ዘንድ በታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ ስህተቶችን የአማራው ብሔር ነው በማለት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በመላዋ ኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥ የጥላቻ መርዝ ሲረጩ ቆይተዋል፡፡ ዛሬ በአንድ አንድ  የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰዎች በማንነታቸው ብቻ የሚገደሉት ወያኔ በረጨው መርዝ የሰከሩ ጎሰኞች በሚከፍቱት ጥቃት ምክንያት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት የጥላቻ ትርክት የጥንታዊቷን የኢትዮጵያ ታሪክ ከህዝቡ ትኩረት እንዳይሰጠው የሚያደርግ፣ የሀገሪቱን አንድነት ሊያናጋ የሚያስችል ነው፡፡ ወያኔ እራሱን የሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶችን ወይም ብሔሮች አዳኝ አድርጎ እንዲቆጠርም በብዙ ባዝኖ የነበረ እኩይና መሰሪ ድርጅትም ነበር፡፡ በመጨረሻም ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመከፋፈል እንዲያስችላት የዘራችውን የጎሳ ፖለቲካ መርዝ፣ ወያኔ ቋንቋና ጎሳን መሰረት ያደረገውን መከፋፈል ፖሊሲ ተቋማዊ ያደረገ እኩይ ቡድን እንደሆነ አንባቢውን አስታውሳለሁ፡፡

ጎሰኝነት ለዲሞክራሲ ጽንሰሃሳብና ፌዴራሊዝም ትኩረት የሚሰጥ አይደለም

ኢትዮጵያን ጎሳና ቋንቋ ላይ መሰረት ባደረጉ ክልሎች መከፋፈል ከእኩልነት መንፈስ ጋር የሚቃረን ስለመሆኑ በርካታ የህግ ሰዎች የሄሱት ጉዳይ ነው፡፡ ጎሳንና ቋንቋን መሰረት አድርጎ አንዲት ሀገርን መከፋፈል፡-

 • የአንድን ሀገር ዜጎችን ( የጎሳው አባል ያልሆኑትን ማለቴ ነው) ወይም መድበል ፓርቲ አስተሳሰብን ችላ ሚል ነው
 • የዜጎችን እኩልንት ችላ ያለ ነው
 • የግለሰብ ነጻነትንም የሚነፍግ ነው፡፡

የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ሊጎመራ የሚቻለው የዜግነት መንፈስ ሲሰርጽ ነው፡፡ በአንዲት ሀገር የሚኖሩ ዜጎች ህብረትና አንድነት ከሌላቸው ዲሞክራሲን ለማስፈን ዳገት ይሆንባቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ የክልላዊ መንግስታት ስልጣን ቁጥጥር ስር የወደቀው በጎሳው አባላት ብቻ ነው፡፡ የጎሳው ኤሊቶች ለዲሞክራሲ ስርዓት ልባቸው የሚደማ አይደለም፡፡ ቆሜለታለሁ ከሚሉት ማህበረሰብ ውጭ ሌላውን ወገንም ከማናቸውም ሁኔታ ( ፖለቲካዋ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አውድም) የሚያገሉ ናቸው፡፡

አሁን የሰፈነው ነጻነት አልባ አወቃቀር ግለሰቦችን የሚመዝነው በጎሳቸው ማንነት ነው፡፡ ሰዎችን ወይም ግለሰቦችን በጎሳቸው ማንነት ብቻ ( በስልጣን ላይ ያለው ኤሊት ጎሳ አባል ካለሆኑ) ከፖለቲካ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወታቸው እንዲገለሉ ያደርጓቸዋል፡፡ መሪዎች የሚመረጡት የጎሳው አባል መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ፣በስሜት እንጂ በምክንያትና ችሎታ ላይ ተመስርቶ አልነበረም፡፡ በጎሳ አባላቶቻቸው የተመረጡ መሪዎች ተጠሪነታቸው ለበቀሉበት ጎሳ ብቻ ነው፡፡ ለሌሎች በጎሳ ክልሉ ነዋሪ ለሆኑ ዜጎች የሚደማ ልብ የላቸውም፡፡

በጎሳ አጥር በታጠረ ክልል የሚኖሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆች፣ ከአካባቢው ተወላጆች በቁጥር አነስተኛ የሆኑት የዲሞክራሲ መብታቸው እንደሚገፈፍ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡( ሕይወታቸውን በሚነካ ማናቸውም ነገር ለመወሰን ወይም መሳተፍ አይችሉም፡፡ እነርሱ ባይተዋር ናቸው፡፡) ለአብነት ያህል ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖር የሌላ አካባቢ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብቱን የተነጠቀ ነው፡፡ ምክንያቱም የጎሳ ፖለቲካ አድሏዊነት የሰፈነበት በመሆኑ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የዲሞክራሲ ስርዓት እውን የሚሆነው ዜጎች በስርዓቱ ላይ እምነት ሲያድርባቸው፣ተሳታፊ ሲሆኑ እና ጥያቄ ማቅረብ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጎች በእኩልነት በሚያገልግልበት መንፈስ መከለስ ያለበት ይመስለኛል፡፡ በሁሉም ክልሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በእኩልነት መንፈስ መከበር አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የሚገኝ አንድ ክልል በበላያነት የተያዘው በአንድ ጎሳ ወይም ነገድ ሲሆን፣ሌሎች በጎሳ በታጠረ ክልል የሚኖሩ አናሳ ቁጥር ያላቸው ጎሳዎች ወይም ነገዶች መብታቸው ወይም ማንነታቸው ይጣሳል፡፡ ለአብነት ያህል በኦሮሚያ ከልል የሚኖሩ የጉራጌ ወይም የአማራ ተወላጆች መብቶቻቸው በየግዜው መጣሱ የአደባባ ሚስጥር ነው፡፡ በሌሎችም ክልሎች ነገሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሌላ አብነት መጥቀስ ቢያስፈልግ በቤኒሻንጉል ክልል የስልጣኑ ባለቤቶች የአካባቢው ተወላጆች የስልጣኑ ባለቤት የሆነው ቡድን ወይም የጎሳ አባል ከትምህርት ፖሊሲ አንጻር ትኩረት የሚሰጠው የጎሳ አባላቱን ቋንቋ ላይ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች በክልሉ የሚኖሩ ዜጎች ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚማሩበትን መንገድ ሲያመቻቹ አይስተዋልም፡፡ለብዝሃ ባህል ትኩረት የሚሰጥ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ የጎሳ ክልል የፖለቲካ አንድነት እውን ለማድረግ የማይጠቅም ከመሆኑ ባሻግር በአጠቃላይ ህዝቡ ዘንድ ግራ መጋባትን የሚፈጥር እና የዲሞክራሲ ሃሳብን የሚያቀጭጭ ነው፡፡

ዴሞክራሲ የሚያብበው የባህል ብዝሃነት ሲያብብ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ዴሞክራሲ በሰፈነበት ሀገር እኩልነት፣ሰላም፣ብልጽግና እና ማህበራዊ ፍትህ መስፈኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ነገዶች በሚኖሩባቸው ሀገራት፣በርካታ ቋንቋዎች የሚነገርባቸው ሀገራት፣የተለያዩ ባህሎች በሚገኙባቸው ሀገራት፣በመጠነ ሰፊ ፖለቲካዊ ቀውስ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ለተዘፈቁ ሀገራት ወደ ተሻለ ተራማጅ አስተሳሰብ፣ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ በአጅጉ ሊረዳ እንደሚችል በርካታ የፖለቲካ ሰዎች ከጻፉት የጥናትና ምርምር ወረቀታቸው ላይ ማየት ይቻላል፡፡ በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ መሰረቱን ጎሳ እና ቋንቋ ላይ ያደረገ የፌዴራል ስርዓት ለዲሞክራሲ ስርዓት መጎምራት እንዳማይበጅ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው ኢትዮጵያ ሀገራችን ናት፡፡ ባለፉት ሰላሳ አመታት የሰፈነው የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ምሉሄበኩልሄ በሆነ ሁኔታ እውን እንዳይሆን ጋሬጣ ፈጥሯል፡፡ በጎሳ ክልል ውስጥ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ዜጎች ባይተዋር ናቸው፡፡ አነርሱ በጎሳ ክልል ተወካይ የላቸውም፡፡የጎሳ ክልል መብት የሚሰጠው ለጎሳው ክልል ተወላጆች ብቻ ነው፡፡በአንድ ጎሳ ክልል ሉአላዊነቱ ለጎሳው ተወላጆች ብቻ ነው፡፡ በአንድ የጎሳ ክልል ውስጥ ኑሮ እያዳፋ ያመጣቸው (ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው) የሌላ አካባቢ ተወላጆች የመረጡት የፖለቲካ ተወካይ የላቸውም፡፡ ይህም ማለት በክልሉ ምክር ቤት የፖለቲካ ስልጣን የያዘ ተወካይ የላቸውም ማት ነው፡፡ ለአብነት ያህል በሀረሬ ክልል የፖለቲካ ስልጣኑ ባለቤት የሀረሬ እና ኦሮሞ የፖለቲካ ኤሊቶች ናቸው፡፡ በሀረር ከተማና ዙሪያ የሚኖሩ የአማራና ጉራጌ ተወላጆች፣የወላይታ ተወላጆች ወዘተ ዘወተ በሀረር የፖለቲካ ስልጣን የያዘ ተወካይ የላቸውም፡፡በሶማሌ ክልል የፖለቲካ ስልጣን ባለቤቶች የሶማሌ ፖለቲካ ኤሊቶች እንጂ የኦሮሞና አማራ ወይም ሌሎች ኢትዮጵያውያን አይደለም፡፡ በአዲሱ የሲዳሞ ክልል የፖለቲካ ስልጣን ባለቤቶች የሲዳማ ኤሊቶች አንጂ የወላይታ፣ጋሞ ወዘተ ተወላጅ የሆኑ ኤሊቶች አይደሉም፡፡ በቤንሻንጉል ክልል የፖለቲካው ስልጣን ባለቤቶች የክልሉ ተወላጅ ኤሊቶች ብቻ ናቸው፡፡ 

በኢትዮጵያ የመገንጠል መብትን የሚፈቀድው አንቀጽ የአናሳዎችን መብት ያስከበረ ነበርን ?

በኢትዮጵያ ህገመንግስት የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ መብት የሚሰጠው አንቀጽ 39 ኢትዮጵያን በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ ልዩ ሀገር ያደርጋታል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አንቀጽ 39 የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል ድረስ የሚሰጠውን መብት ማለቴ ነው፡፡ አናሳ ቁጥር ላላቸው ነገዶች የሚሰጠው መብት ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ለአብነት ያህል በሶማሌ ክልል ወይም ኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ እና የክልሎቹ ተወላጆች ያልሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ያላቸው መብት አልተጠቀሰም፡፡ እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር 1999ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅት የመገንጠል ጥያቄ ለማቅረብ ጫፍ በደረሱበት ግዜ ሳይቀር በሁለቱም ክልሎች ስለሚኖሩ በቁጥር አነስተኛ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን  መጻኢ እድል በተመለከተ የሁለቱም ነጻአውጪ ድርጅቶች የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች የሚደማ ልብ አልነበራቸውም፡፡

በነገራችን ላይ በብይነ መንግስታቱ ውሳኔ ቁጥር A/49/752 መሰረት የራስን እድል በራስ መወሰን መብት የሚሰጠው በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ውስጥ ፍዳቸውን ሲያዩ ለነበሩ ህዝቦች ነው፡፡ በማናቸውም የአለም ሀገራት ህገመንግስት ውስጥ እንዲህ አይነት የመገንጠልን መብት የሚፈቅድ አንቀጽ የለም፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ኤሊቶች ይህን ሃሳብ በመውሰድ ሌሎች በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ነገዶች በመጨቆን ነው የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን የተነሱት፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ልሂቃን እወክለዋለሁ የሚሉት ነገድ ወይም ጎሳ የራሱን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚለው መብት መከበር አለበት በማለት ሲነሱ፡፡ በራሳቸው የጎሳ ክልል ለሚኖሩ ሌሎች የአካባቢው ተወላጅ ላልሆኑ ጎሳዎች ብሔር ወይም ነገዶች መብት መከበር ቅንጣት ታህል የሚደማ ልብ የላቸውም፡፡ ምንም እንኳን የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል መብታቸን መከበር አለበት የሚሉ አክራሪ ብሔርተኞች እንደ አሽን ቢፈሉም፣በጎሳ ክልሎች የሚኖሩ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የሌላ አካባቢ ተወላጆችና በጎሳው ክልል የሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ነባር የጎሳው አባላት ያላቸውን መብት በተመለከተ አያውቁም ወይም ማወቅ ወይም መስማት አይፈልጉም፡፡ ይህ ደግሞ ከብሔርተኝነት ፍልስፍና አኳያ ፍጹም ተጻራሪ ሃሳብ ነው፡፡

The UN Resolutions (A/49/752) grants self-determination rights to groups of people that have been colonized and other people that were subjected to “foreign domination.” Elites exploit such concepts to oppress and prosecute minorities of “ethnic other” while clamoring for self-determination. 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ‹‹ እንደ ብሔራዊ ጥያቄ ›› ሁሉ ‹‹ የራስን እድል በራስ የመወሰን ሃሳብ›› ከውጭ ሀገር፣ ከባእድ ሀገር የገባ ሃሳብ ነው፡፡ ይህ ሃሳብ ሀገር በቀል አይደለም፡፡ ወያኔ እራሱ ‹‹ራስ›› በሚለው ትርጉም አኳያ ግራ የተጋባ ይመስላል፡፡ በአጭሩ ትርጉሙን በሚገባ የተረዳ አይመስልም፡፡ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍሎች ወይም ክልሎች ይልቅ ወይም በተሻለ መልኩ የትግራይ ክልል በአንድ ብሔር ብቻ የተሞላ ይመስላል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እውነታው ለየቅል ነው፡፡ በትግራይ ምድር አብዛኛው ቁጥር የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችን ትግራዋይ ቢሆኑም፣ በትግራይ ምድር አገው፣ሳሆ (ኢሮብ)፣ እና ኩናማ የሚባሉ ነገዶች አሉ፡፡ እነኚህ የተጠቀሱት በቁጥር አነስተኛ የሆኑት ነገዶች ቢያንስ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት አላቸው፡፡ ሆኖምግን ይሁንና ፖለቲከኞች ይህን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ለራሳቸው ጠባብ አላማ ማስፈጸሚያ ነው ያደረጉት፡፡ በተለይም የጎሳ ፖለቲከኞች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን እንደ ፖለቲካ መጨቆኛ መሳሪያ አድርጎ ነው የተጠቀመበት፡፡ ይህ መራር ሃቅ ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲከኞች በገንዘብ፣ህግና ፖለቲካዊ ድጋፍ ያለቸው ሲሆን የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን ጥርጊያው መንገድ ተሰርቶላቸዋል፡፡ አለም ወደ አንድነት ወደ ህብረት በመጣበት በዚህ በሰለጠነው አለም 9ኝ የሚደርሱ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች ነን ያሉ አክራሪ ብሔርተኞች በዋሽንግተን ዲሲ ባደረጉት ስብስባ መዳረሻችን ኮንፌዴራሊስት ነው ብለው ስምምነት ላይ ደርሰናል ማለታቸው እጅጉን አስደንጋጭ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ክሀደትም ይመስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ በጎሳ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች መብት እከሉ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመብት ባለቤቶች የአካባቢው ተወላጆች ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች የአካባቢው ተወላጆች ያልሁኑ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በብሔራዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቀበሌ ደረጃ ሳይቀር የፖለቲካ መብታቸው የተገፈፈ ነው፡፡ አሁን በደረስንበት የሰለጠነ ዘመን የጎሳ ፖለቲካ መከተሉ አሳዛኝም አሳፈሪ ነው፡፡

ምንም እንኳን የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ እና የቡድን መብቶች በኢትዮጵያው ህገመንግስት ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም በአንድ የጎሳ ክልል የሚኖሩ፣የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊ ዜጎች፣ በጎሳ ኤሊቶች የተጠቀሱት መብቶቻቸው እንደሚገፈፍ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አንዴ አንድ የጎሳ ክልል ሉአላዊ ከሆነ በክልሉ ለዘመናት የኖሩ እና ከሌላኛው የኢትዮጵያ ክፍል መጥተው የሰፈሩ ገበሬዎች፣ነጋዴዎች፣የግልና የድርጅት ሰራተኞች በጎሳ ኤሊቶች አመሃኝነት መብታቸው መገፈፉ አይቀሬ ነው፡፡

 1. እውን የጎሳ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ጸጥታንና ዳር ድንበርን ለማስጠበቅ እረድቶ ያውቅ ነበርን  ?

የአፍሪካው ቀንድ ሀገራት በታሪክ፣ቋንቋ፣ሃይማኖት እና ባህል አኳያ ለዘመናት የቆየ ግንኙነት አላቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ  አካባቢው ስር በሰደደ ጥላቻ ውስጥ የተዘፈቀ ሲሆን፣ አሁን ድረስ ያልተፈታ በድንበር ይገባኛል ምክንያት ሀገራቱ የሚራኮቱበት የአፍሪካ ክፍል ነው፡፡ ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ዳር ድንበር የተሰመረ አይደለም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበር ሁለቱን ሀገራት ባስማማ መልኩ በአለም አቀፉ የድንበር ኮሚሽን አልተሰማራም፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በሯ የተዘጋባት አሳዛኝ ሀገር ከመሆኗ ባሻግር ለጥቃትም የተጋለጠች ናት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ጉዳይ ለኢትዮጵያ ወሳኝ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ሉአላዊነትን ከጎሳና ቋንቋ  ብቻ ጋር ማጣመር ለብሄራዊ ደህንነት ስጋት ነው፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2006 የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊያ አክራሪዎች ( እንደ አልሸባብ ከመሳሰሉት ጋር ማለቴ ነው) ጋር ጦርነት በገጠመበት ግዜ አንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ሶማሌ ዜጎች ወንድሞቻችን መሃከል አንዳንዶች ከአክራሪ ሶማሌ ተዋጊዎች ጋር አብረው ሊሰለፉ ይችላሉ ብለው ግምታቸውን ሰንዝረው ነበር፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጋምቤላ ክልል የተወለዱ ኢትዮጵያዊ የኑዌር ተወላጆች፣ ደቡብ ሱዳን ከተወለዱ የኑዌር ጎሳዎች እና በኢትዮጵያ የግዛት ክልል በተሰሩ የስደተኞች ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው ከሚኖሩትጋር በማበር፣የአኙዋክ ተወላጆች ላይ ጉዳት አድርሰው ነበር፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁም ነገር ቢኖር በጎሳ የታጠረ ክልል ለውጭ ወራሪ ሀይሎች ወይም ጠብ ያለሽ በዳቦ ለሚሉ ቡድኖች ጥቃት የተጋለጠ መሆኑን ነው፡፡ ለግዜውም ቢሆን ሱዳን እግሯን አንፈራንጣ በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ለመንፏለል ያበቃት፣የጎሳ ፖለቲካ በፈጠረብን መዘዝ እንጂ ኢትዮጵያ ለሱዳን አንሳ እንዳልሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በአጭሩ የጎሳ ፖለቲካ ለብሔራዊ ደህንነትና ዳርድንበር መጠበቅ እውን መሆን ደንቃራነቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሽብርተኛው የወያኔ ቡድን ኢትዮጵያ በጎሳ ፖለቲካ ተከፋፍላች ብሎ በማሰቡ ነበር በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈጸመው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የኢትዮጵያ ህዝብ የጎሳ ፖለቲካ ሳያደናቅፈው በአንድነት ሆኖ እየተፋለመው ይገኛል፡፡

 1. እውን የጎሳ ብሔርተኝነት ለእድገት እንቅፋት ነውን ?

የህዝብ ቁጥር መጨመር፣የወጣቶች ስራ እጥ መሆን፣ከባድ የምግብ እጥረት፣የአካባቢ ብክት፣የጸጥታ መደፍረስ እና ሌሎች ችግሮች የማህበረሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት እንቅፋቶች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ የስራ ፈጠራ እውን እንዲሆን ማበረታቻ ቢኖርም፣የኢነቨስትመንት መስፋፋት ተስፋ ሰጪ ሆኖ ቢታይም፣ ወዘተ ወዘተ የጎሳ ፖለቲካ ቅስቀሳ ከበረታ ሰብዓዊ ቀውስ መከሰቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ መረጋጋት ለማጣት አዳጋች ነው፡፡ 

ገለልተኛ የሲቪል ተቋማት ባልጎመሩበት  እና የሲቪል ማህበረሰቡ ተሳትፎ አናሳ በሆነበት ሀገር አንዳንድ ፖለቲከኞች ተስፋ የቆረጡ ወጣቶችን በማነሳሳት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማሳከት መንቀሳቀሳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲከኞች አጠቃላይ ማህበረሰባዊ እድገትን ማምጣት የሚችሉ አይደለም፡፡ እነርሱ ወክለነዋል ከሚሉት ነገድ ወይም ብሔር ውጭ ላሉትና በክልላቸው ለሚኖሩ ሌሎች ዜጎች የሚጨነቁ አይደለም፡፡ ( ወክለነዋል ለሚሉት ነገድ ወይም ብሔርን ወደ የላቀ የኑሮ እድገት ደረጃ ሲያሸጋግሩት አልታየም) በነገራችን ላይ የምጣኔ ሀብት እድገት በመጀመሪያ ቁርጠኝነት፣የሀብት ማንቀሳቀስ፣ማእከላዊ ፕላን( እቅድ)፣ እና ቅንጅትን ይጠይቃል፡፡ 

 1. በዘፈቀደ የሚሰመር ወሰን ማህበራዊ ግንኙነትን ያበላሻል

በዘፈቀደና ህጋዊ ባልሆነ ሁኔታ በጎሳ ክልሎች ማሀከል ያለውን ወሰን ማስመር ማለቂያ ወደሌለው የድንበር ይገባኛል እና ማንነት ጥያቄ ይወስደናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በክልሎች መሃከል ያለው ግንኙነት በአብዛኛው በፖለቲካዊ ውሳኔ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡በነገራችን ላይ የጎሳ ማንነት የፖለቲካ መሳሪያ በሚሆንበት ግዜ የባህላዊ ግንኙነት ይሰበራል፣ በነገዶች ግንኙነት መሃከል ሰፊ ክፍተቶች ይፈጠራሉ፡፡ የዚህ ውጤቱ ደግሞ አንዳንድ ቡድኖች የበላይነትን በመጎናጸፍ በቁጥር አነስተኛ የሆኑትን ነገዶች መብት ይገፋሉ ወይም በተራቸው ጨቋኝ ይሆናሉ፡፡ይጨቁናሉ፡፡ ሌላው መጨቆን የለብኝም በሚል ደግሞ ወደ ግጭት ውስጥ ይወድቃል፡፡ በሸካ መዠንገር፣በቴፒ ወዘተ በየግዜው የሚነሱት ግጭቶች እንደምሳሌ ሊነሱ ይችላሉ፡፡

ወሰንን ጎሳዊ ማድረግ ዋና ዋናዎቹን ብሔሮች ጨምሮ ሌሎች በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ነገዶችን በወሰን ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ለደም አፋሳሽ  ግጭቶች እንደዳረገ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ማህበራ እድገትን ያሳነሰ ሲሆን ፣ ማህበራዊ ግንኙነትን ያቀጨጨ እና ብሔራዊ ደህንነትን ችላ ያለ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መአት እየወረደ ግን የጥግራዩ አሸባሪ ቡድን እና ሌሎች አጋሮቹ የጎሳ ፖለቲካን የሙጥኝ ብለዋል፡፡ በነገራችን ላይ የጎሳ ፖለቲካ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነት የሚሸረሽር እንጂ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጅ አይደለም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ እውን የሆነው የርስበርስ ጦርነት በአሸባሪው ወያኔ ጸብ ጫሪነት የተቀጣጠለ ቢሆንም፣የጎሳ ፖለቲካ አስተዋጽኦ የትዬየሌሌ ነው፡፡ አሸባሪውን የወያኔ ቡድን መክተን ከመለስ ባሻግር በፍጥነት ከጎሳ ፖለቲካ የምነወጣበት መንገድ በህግ አዋቂዎች የሚመከርበት መንገድ እንዲፈለግ እንማጸናለን፡፡

ህገመንግስቱ በአሸናፊዎች የታዘዘ ወይንስ እውነተኛ የፖለቲካ መፍትሔ ?

የአሸባሪው ወያኔ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ባደረበት ጥላቻ ( በተለይም በአማራው ላይ ይብሳል) ምክንያት አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገመንግስት እንዳዘጋጀ በርካታ የፖለቲካና ህገመንግስት አጥኚዎች በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ ያስቀመጡት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ወታደራዊው መንግሰት በጦርነት አሸንፎ የማእከላዊ መንግስቱን ተቆጣጥሮ የነበረው የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ከአጋሮቹ ጋር አዘጋጅቶ ያጸደቀው ህገመንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ያሳተፈ ባለመሆኑ አሁን ለደረስንበት አሳዛኝ ሁኔታ አብቅቶናል፡፡ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሲዘጋጅ የአንድነት ሀይሎችን ያሳተፈ ባለመሆኑ በብዙዎች ባለሙያዎች የሚተች አቢይ ጉዳይ ነው፡፡

ወያኔ በመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ ብሔራዊ ጥያቄዎችን›› ለመመለስ ከቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት የቀዳውን የጎሳ ፌዴራሊዝም ገቢራዊ ለማድረግ ቢሞክርም የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት አላስቻለውም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ራሱ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያ ችግር ብቻ ሳይሆን ካንሰር ሆኗል፡፡ ይህ ህገመንግስት የህዝብ እንቅስቃሴን፣የባህልና ቋንቋ መደበላለቅን፣ የማህበራዊ ትሰስርን፣ ለብዙ አመታት በቆየ ግንኙነት የፈጠረውን የመግባቢያ ቋንቋን ወዘተ ወዘተ ችላ ያለ ነበር፡፡  

በአጠቃላይ የጎሳ ፖለቲካ እየጎመራ በሄደ ቁጥር ሙስና ስር ይሰዳል፣መድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲቀጭጭ ያደርጋል ብዬ እሰጋለሁ፡፡

ምን ይበጃል  ?

ለክልሎች ምሉሄ በኩልሄ ስልጣን የማይሰጥ ማእከላዊ መንግስትና የጎሳ ክልሎችን የፈጠረ ማእከላዊ መንግስት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ይበጃል ብዬ አላስብም፡፡ ስለሆነም እውነተኛ ፌዴሬሽን መኖሩ የሚያከራክር አይደለም፡፡ እውነተኛ ፌዴሬሽን ለመፍጠር ደግሞ በእኩልነትና ማህበራዊ ፍትህ ላይ የተመሰረተ የሲቪል ብሔርተኝነት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ የሲቪል ብሔርተኝነት ሀገሪቱን ባህል ያከበረ፣የግልና የቡድን መብቶችን ያከበረ መሆን እንዳለበት አዋቂዎች ይመክራሉ፡፡

በነገራችን ላይ እውነተኛ የፌዴራል ስርዓት እውን እንዳይሆን የሚፈልጉት በአብዛኛው የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑ ኤሊቶች እና ሌሎች የስልጣን ጥመኛ የሆኑ የፖለቲካ ቡድን መሪዎች እንደሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዜጎችም ሆኑ መሪዎች በጎሳዎች መሃከል ያሉትን ልዩነቶች በማቻቻል መቀበል አለባቸው፡፡ ይህም ማለት አንደኛው የበላይ ሌላኛው የበታች ይሁን ማለት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ የግዛት ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ሁሉ እኩል መብት መጎናጸፍ አለባቸው፡፡ ደካማ ተቋማት፣በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ጽንፍ መርገጥ፣ ለዲሞክራሲ መስፈን በምንም አይነት አይጠቅመንም፡፡ ከጎሳ ፖለቲካ ለመውጣት ጠንካራ የሲቪል ማህበራት፣የሰለጠነ  ውይይት፣ የማህበራዊ ሚዲያን በሰለጠነ መንገድ በአስተማሪነት መጠቀም አማራጭ የላቸውም፡፡

ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ባያፍራ ግዛት ውድቀት መማር አለባት፡፡ ኢትዮጵያ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ቡድኖችን አንድ ላይ መሰብሰብ ወይም ትልቅ ቁጥር ያለቸውን የባህል ማህበረሰቦችን ወደ ተለያዩ ክፍሎች መውሰድ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር የተለያዩ ቡድኖችን በአንድ አስተዳደር ክልል ውስጥ ከማድረግ ይልቅ በዛው ክልል የራስ ገዝ አሰተዳደር መፍቀዱ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ አንድን ትልቅ ብሔር( በቁጥር፣ባህል..ወዘተ ወዘተ ) ማለቴ ነው ወደ ተለያዩ ግዛቶች መከፋፈል ለአክራሪ ብሔርተኞች አመቺ ሊሆን ስለሚችል በአዋቂዎች ተጠንቶ ገቢራዊ ቢሆን መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

በጎሳ እና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ ክልላዊነት የድንበር ችግርን መፍታት ዳገት የሚሆንበት ፣በብሔርች ወይም ነገዶች መሃከል አጉል ፉክክር የሚፈጥር፣ግጭቶች በቀላሉ ሊፈጠሩበት የሚችል እንደሆነ በገቢርም በነቢብም የታየበት ነው፡፡

ምሉሄበኩክልሄ የሆነ ዴሞክራሲ ከጎሳ ፖለቲካ ለመውጣት ፍቱን መድሃኒት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በመጨረሻም ፕሬዜዴንታዊ ስርዓት ከአረጀው ካፈጀው የጎሳ ፖለቲካ ለመውጣት ሌላው አማራጭ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንዲሁም ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ህገመንግስቱን የሚተረጉምበት መንገድ በህግ አዋቂዎች ተጠንቶ ቢቀርብ አንዱ የመፍትሔ መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለማናቸውም ውሳኔው የሚጥመውን የሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሆነ እሰቲ በየአካባቢው የውይይት መድረክ የሚከፈትበት መንገድ ይፈለግ፡፡ አስከትሎም ህዝቡ  የጎሳ ፖለቲካን የሚፈቅደውን ህገመንግስት ስለማሻሻል በሚመለከት ያለውን ሃሳብ ለማዳመጥ በየአካባቢው የውይይት መድረኮች የሚከፈቱበት መንገድ ቢፈለግ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ፣ሰላም ለሀገራችን!

 

Filed in: Amharic