>

ሁለቱም ተመሳሳይ ንግግር በአንደዜ ተናገሩ - አንዱን አወዳሽ አንዱን ከሳሽ ሆንን - ለምን...??? (ዘመድኩን በቀለ)

ሁለቱም ተመሳሳይ ንግግር በአንደዜ ተናገሩ – አንዱን አወዳሽ አንዱን ከሳሽ ሆንን – ለምን…???
ዘመድኩን በቀለ

*… ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው። አንዱ ጂንካ ጫካ፣ አንዱ በሻሻ ጫካ የተወሉዱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። 
* …ሁለቱም በሃይማኖት አንድ ናቸው – ጴንጤ። ሁለቱም ወታደር ነበሩ። ሻአቢያን ለመዋጋት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የዘመቱ ወታደሮች ነበሩ። አንደኛው የሬድዮ ኦፕሬተር ሆኖ ኮሎኔል ማዕረግ የደረሰ፣ የታሪኩን ዲሽታ ጊናን ማዕረግ አላውቅም። ሁለቱም በቤተ እምነታቸው ፓስተሮች የተቀቡ ናቸው። ዐቢይ በፓስተሪት ብርቱካን፣ ታሪኩ በፓስተር ኢዩ ጩፋ። 
… ሁለቱም ተመሳሳይ ንግግር በአንደዜ ተናገሩ። ዐቢይ አሕመድ ተነሥ፣ ታጠቅ፣ ዝመት አይባልም። የክልል መሪዎች በደንብ አስቡበት ብሎ መመሪያ ሰጠ። ፓምፕ ላይ ዝመቱ፣ ትራክተር ላይ ዝመቱ እንጂ ለኢትዮጵያ ተነሥ ታጠቅ ዝመት ማለት፣ ወያኔን መዋጋት አስፈላጊ አይደለም ብሎ ተናገረ። እሱ ይሄን ሲናገር ወያኔ ደሴ አፍንጫ ላይ ቆማ በመድፍ እየደበደበች ነበር። በሁለተኛው ቀን ኮምቦልቻ፣ በሦስተኛው ቀን ሰሜን ሸዋ ገባች።
… ታሪኩ ዲሽታ ጊናም የጠቅላዩን ቃል ሰፋ አድርጎ በመድረኩ ላይ ሰበከ። ተናገረ። ደሰኮረ። የወያኔን ዕርቅ እምቢ ባይነትን ሳይረዳ ዕርቅ ይሻለናል። ወጣቶች አይሙቱ፣ ሽማግሌዎች ቄጤማ ለምለም ሳር ቀጥፋችሁ፣ ድንጋይ በትከሻችሁ ተሸክማችሁ አስታርቁን አለ። ይሄን ነው የተናገረው። ንግግሩ የወያኔን ባህሪ ካለማወቅ ከመሆኑ በቀር ትክክል ነበር። አንድ ጳጳስ ወይም ሼክ መናገር ያለበትን ቃል ነበር ታሪኩ የተናገረው።
…ዐቢይ አሕመድም፣ ታሪኩ ዲሽታጊናም ሁለቱም በኢትዮጵያውያን ዘንድ በብርቱ ተወቀሱ፣ ተከሰሱም። ዐቢይ አሕመድ ወደ ባህርዳር በረረ። በክልል መሪዎች፣ በዐማራ ምሁራን ፊት ቆሞ ማሩኝ፣ ይቅር በሉኝ። እኔ እንደዚያ ያልኩት ዐማራ መወረሩን አጥቼው አይደለም። የውጩ ጫና ሲበዛብኝ ቢጨንቀኝ ጊዜ ነው እንዲያ ብዬ መናገሬ ብሎ እጅ ነሥቶ ይቅርታ ጠየቀ። ለቴሌቭዥን፣ ለራዲዮም ሳይቀርብ ይቅርታው በውስጥ አለቀ። ከዚያ እንደወጣ እስከ አሁን የከተተ ባይኖርም በየክልሉ ሁሉ ግን ክተት በሚዲያ አሳወጀ።
…ዲሽታ ጊና ግን ደነገጠ፣ አደናበሩት። ከቤቱ እንዳይወጣ እንዲደበቅ ሁላ አደረጉት። ዘመድ ወገን የሌለው ገበሬ የገበሬ ልጁ ታሪኩን አስጨነቁት፣ ልጁ መሳሳቱን እያወቁ፣ ለጦርነት ቅስቀሳ በተጠራ መድረክ ላይ ተጋብዞ ለመድረኩ የማይመጥን ንግግር ማድረጉን እያወቁ ወረዱበት። እንደ ንጉሥ በታየበት ከተማ ላይ እንደወንጀለኛ ከቤቱ ሳይወጣ ተደብቆ፣ ተሸሽጎ ጥፍሩ ውስጥ ተደብቆ እንዲቀመጥ አደረጉት። ለዐቢይ አሕመድ የሰጡትን ዕድል ለዲሽታ ጊና ነፈጉት።
…በመጨረሻም ዲሽታ ጊናን አንበርክከው ይቅርታ አስጠየቁት። ደም እንባ አስነቡት። በቃ ወደ ጂንካ ጫካዬ እመለሳለሁ። ትኬትም ቆርጫለሁ። ገንዘብ ኖሮህ ሰው ካጣህ ምን ዋጋ አለው አለ ዲሽታ ጊና። ሰው በሚርመሰመስበት ከተማ ሰው አስራቡት። ዲሽታ ጊናን እንዲህ በል አስብለው የሰው ልብ መሞከሪያ የህዝብ ሙቀት መለኪያ ያደረጉት ቁማርተኞቹ ባሉበት ሃገር ዲሽታ ጊናም፣ የዲሽታ ጊና ረጋሚዎችም ግን ኦሌሳንጎ ኦቦሳንጆን እነ ዐቢይና ሽመልስ ወደ መቀሌ ለሽምግልና ከወያኔ ዘንድ እንደላኩ አልሰሙም ነበር።
… ሃጫሉ ሁንዴሳን ገድለው አስገድለው የሚታሰረውን አስረው፣ የሚገደለውን ገድለው ቁማሩን የበሉት ቁማርተኞች ታሪኩ ዲሽታ ጊናንም በጥይት  ባይገድሉትም በሴራ ተብትበው በህዝብ ምላስ አስገደሉት። ብቻውንም አስቀሩት። ከማማ ላይ ፈጥፍጠው አፈረጡት። በእንብርክክ አስኬዱት። አስለቀሱት። ብቸኛም አደረጉት። አሁን እሱም እዚህ ከተማ ውስጥ ደፍተውት እንደሃጫሉ ቁማር ከሚቆምሩበት ወደ ጂንካ ወደ ጫካዬ እመለሳለሁ ማለቱ ደግ አደረገ። አበጀ። ፍጠን ታሪኩ። ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ተሸሸግ።
…መፍትሄው። የታሪኩን ይቅርታ መቀበል ነው። ለዐቢይ አሕመድ የተሰጠው ይቅርታ ታሪኩ ዲሽታ ጊናን መንፈግ አግባብ አይደለም። ዐቢይ አሕመድ ባህርዳር ድረስ ሄዶ ከካሜራ ጀርባ ለሥልጣኑ ሲል ነው ብአዴናውያንን ይቅርታ የጠየቀው። ህዝብን ሳይሆን የፌክ የህዝብ ወኪሎችን ነው ይቅርታ የጠየቀው። ታሪኩ ግን ለእንጀራው ሲል ነው በአደባባይ በግንባሩ ተደፍቶ ሚልዮኖች እያዩት፣ ዐቢይ አሕመድም እያየው፣ ሽመልስ አብዲሳም እያየው፣ ብፁዓንም ሼክ ፓስተሮችም እያዩት፣ ትግሬም ዐማራም እያየው ይቅርታ የጠየቀው። እናም ዐማሮች ሆይ የታሪኩን ይቅርታ ተቀበሉት። ከአባትህ ገዳይ ጋር የመታረቅ ከፍ ያለ ስብዕና ያለህ ዐማራ ሆይ ይሄን አንድ ምስኪን ሰው ይቅር ማለት አያቅትህምና ይቅርታውን ተቀበለው። ለሰይጣን ምህረት የለመነች የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልጆች የታሪኩንም ይቅርታ ተቀበሉት።
• የኦባሳንጆን ውጤት ግን በጥንቃቄ ጠብቁት።
• ወጥር ዐማራ  ‼
• ፍርዱን ለእናንተ !! ህዝብን በጓዳ በማጀት ሳይሆን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት ማን ነበር?
Filed in: Amharic