ስለወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ
ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ….!!!
የብልጽግና መንግሥት ሥልጣን ከያዘበት ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮም ሆነ በቅርቡ “አዲስ መንግስት” “አዲስ ምዕራፍ” እየተባለ ከሚነገርለት ከመስከረም 24/2014 ዓ.ም. በኋላ ባለው ጊዜ መንግስት ሊሠራቸው የሚገቡ ዋንኛ ተግባሮችን ሲያከናውን አልታየም፡፡ እነዚህም የሃገርን ሉዓላዊነት ማፅናት፣ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ማስፈን እና የሃገርን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሕይወት ማረጋጋት ናቸው፡፡ ብልጽግና ከነዚህ አንዱንም መንግሥታዊ ኃላፊነት በተገቢ ሁኔታ ለመወጣት አልቻለም፡፡ በአሁኑ ወቅት የኦህዴድ/ብልፅግና የኢትዮጵያን መንግሥት የከሸፈ መንግስት (Failed State) እንዲሆን ማድረጉን መደበቅ የማይቻልበት እውነታ ላይ ተደርሷል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሃገሪቱ የተለያዩ ማዕዘኖች ሲከናወን የቆየው በተለይም አማራው ላይ እየደረሰ ያለው የዘር ፍጅት፣ አሁንም “በአዲሱ ምዕራፍ” በእጅጉ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው።
ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከትግራይ ወደ አፋር በተለይም በስፋት ወደ አማራ ክልል እንዲዛመት የተደረገበት የሰሜኑ ጦርነቱ አንደኛው ምክንያት የኦህዴድ/ብልጽግና አስተዳደር በሚከተለው የተረኝነት ፓለቲካ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይወዳደረኛል የሚለውን የአማራ ክልል ህዝብ በሁለንተናዊ መልኩ እንዲደቅና እንዲዳከም ለማድረግ እየሠራ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ጦርነቱ ከትግራይ ወደ አማራ ክልል ከተዛመተበት ካለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ እስካሁን ባሉት ጥቂት ወሮች ብቻ ክልሉ ከ20,000 በላይ መንግሥታዊ እና የግል የኦኮኖሚና የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት ወድመውበታል፡፡ ገበሬው በጦርነት ላይ በመሆኑ ብዙ ማሳዎች ጦም በማደራቸው ክልሉ በምርት እጥረት እንዲቸገር መደረጉም ሌላው የኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና የእቅድ አካል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በጦርነቱ ምክንያት በአማራ ክልል ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር የተጋለጠ ሲሆን አንድ ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ ከቀዬው ተፈናቅሎ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡
በቅርቡ በአማራ ክልል ከህወሓት ወረራ ያልተላቀቁትን ወረዳዎች ሳይጨምር ተይዘው በተለቀቁ 46 ወረዳዎች ብቻ የህወሓት ጦር በወረራው ያደረሰው ጉዳት 280 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት የአማራ ክልል የኢኮኖሚ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡ ይኸ የገንዘብ መጠን የክልሉን የአምስትና የስድስት ዓመታት በጀት ሊሸፍን የሚችል ነበር፡፡ በአፋር ክልልም የደረሰውን ጥፋት ለጊዜዉ በአሃዝ ለማቅረብ መረጃ ባይገኝም፣ በክልሉ የሚካሄደውን ጦርነት የሚከታተሉ በሰው ኃይል፣ በንብረትና እና በመሠረተ ልማት እጅግ ከባድ ጥፋት እንደደረሰ እየገለፁ ነው፡፡
አማራው በኢትዮጵያዊነት ላይ ባለው የፀና እምነት እና ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ቀጣይነት በታማኝነት የመቆም ታሪካዊ ተልዕኮውን ለመድገም የሚችል ማህረሰብ ነው፡፡ይህ አባባል የአፋርንም ህዝብ ይመለከታል፡፡ ይሁንና አማራው ላለፉት 30 ዓመታት በተገቢ አመራር እጦት ምክንያት ይህን ተልዕኮውን እንዳይወጣ ሆኗል፡፡ የአካባቢው ህዝብ ክልሉን ከወረራ፣ እና ሃገሪቱን ከብተና ለመከላከል በከፍተኛ ስሜት ለዘመቻ ቢንቀሳቀስም፣ በተረኝነት ፖለቲካ የሚመራው የብልጽግና መንግሥት በተነሳሳው ሃገራዊ ስሜቱ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እየተቸለሰበት ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል በደባ እና በሸፍጥ እንዲዳከም፣ የማያስፈልግ መስዋእትነት እንዲከፍል እየተደረገ ስለመሆኑም ያለፉት የሶስት እና የአራት ወራት የሠራዊቱ ክንውን ያመለክታል፡፡ የሕዝባዊ ኃይሉ ሠራዊት ማለትም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያና ፋኖ ከትቶ ከገባበት 2014 ዓ.ም. መስከረም ወር መጨረሻ አንስቶ እስካሁን ባለው ጊዜ የማጥቃት የዘመቻ ስምሪት ትዕዛዝ ተሰጥቶ ቢሆን ኑሮ በህወሓት ወራሪ ኃይል ከተያዙ የአማራ ክልል ወረዳዎች ጨርሶ ማስወጣት ይቻል ነበር፡፡
ስልታዊ ማፈግፈግ በሚል ቅጥ አምባሩ የማይታወቅ ለወያኔ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ወታደራዊ ስትራቴጂ ሳቢያ መከላከያው በትዕዛዝ ሳይዋጋ በማፈግፈጉ ሰሜን እና ደቡብ ወሎን ህወሓት እንዲረከብ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የአማራው ሕዝባዊ ኃይል፣ የአፋር ልዩ ኃይል እና መከላከያ ባደረጉት ከፍተኛ መስዕዋትነት የህወሓት የሩጫ ዘመቻ እንዲገታና መውጫ መንገዱ እየታጠረ እንዲሄድ መደረጉ በመገናኛ ብዙኃን ተገልጿል፡፡
ይሁንና ላለፉት ሰላሳ አምስት ቀናት “ከፌደራል መንግሥት ትእዛዝ አልተላለፈም፤” በሚል ከሰሜን ሸዋ ውጭ በጎንደር እና በወሎ ያለው የመከላከያ እና የህዝባዊ ኃይል ሠራዊት የማጥቃት ስምሪት እንዳልተሰጠው መረዳት ተችሏል፡፡ ለቀጣዩም ጦርነቱን ወደ ትግራይ ክልል በመውሰድ የህወሓትን ወታደራዊ አቅም ከጥቅም ውጭ ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ጦርነቱ ሊያበቃ የሚችልበት ሁኔታ አይታወቅም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሁኔታ ግን የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት እነዚህን ግቦች ለማሟላት ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡ ለዚህ ማስረጃ ጦርነቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በህወሓት የበላይነት እየተመራ በነበረበት ሁኔታ መንግሥት በናይጀሪያ የቀድሞው ፕሬዚዳት ኦባሳንጆ አማካይነት ድርድር እንዲጀመር ፍላጎት ማሳየቱ ነው፡፡ ጦርነቱን የፌድራል መንግሥቱ በባለቤትነት ሊያካሂደው ሲገባ፣ ዋንኛ ሓላፊነት ለአማራ እና አፋር ክልሎች አሳልፎ መስጠቱ የፌደራል መንግሥቱን ክሽፈት ያሳያል፡፡
“በአሁኑ ጊዜ ያለው ሠራዊት መቶ ዓመታት በኢትዮጵያ ተገንብቶ የማያውቅ ነው” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አነጋገር በጦርነቱ ሂደት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሲያመጣ አልታየም፡፡ መንግሥት የአየር ኃይል እና የሜካናይዝድ ክፍል ጦር አቅሙን በመጠቀም ትግራይ ድረስ ገብቶ የህወሓትን ከባድ መሣሪያዎች፣ የጦርነት ግብዓት የሚያከማችባቸውን ቦታዎች፣ ለውጊያ አገልግሎት የሚጠቀምባቸውን ተቋማት አለብዙ ችግር ከጥቅም ውጭ ማድረግ ሲችል ይህም አመርቂ በሆነ ሁኔታ እየተከናወነ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ መቀሌ የሚገኙ አንዳንድ ወታደራዊ ነክ ተቋማት በአየር መደብደብ የጀመሩት ህወሓት ገፍቶ መጥቶ ደሴን እና ኮምቦልቻን ለመቆጣጠር ሲቃረብ ነው፡፡
ሃገራቸውን እና አካባቢያቸውን ከወራሪው የህወሓት ኃይል ለመታደግ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ወጣቶች ሰልጥነው ለጦርነት ዝግጁ ቢጠባበቁም የጦርነት ስምሪት ትዕዛዝ አለመሰጠቱ የአማራውን ሕዝባዊ ኃይል በጥርጣሬ የመመልከት አዝማሚያ እንዳለ ያመላክታል፡፡
ይህም ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወጥቶ ወደ አማራ ክልል በተዛመተበት ጊዜ በመከላከያ፣ በአማራ ልዩ ኃይል እና በፋኖ ተይዘው የነበሩ ስትራቴጅክ እና ወታደራዊ ገዥ ቦታዎችን አለምንም ጦርነት ተከታታይነት ባለው መልኩ “አፈግፍጉ” በሚል ትዕዛዝ እንዲለቀቁ ማስደረጉ መንግሥት የመረረ ትግል ላለማድረጉ ማስረጃ ነው፡፡
መንግሥት ጦርነቱን የእውነት ጦርነት ለማድረግ ያለመፈለጉ በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ ይታመናል፡፡ እነዚህም አንደኛው ኦህዴድ/ብልፅግና ከህወሓት ጋር ያለው ግጭት የስልጣን ግብግብ እንጂ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ያለመሆኑ፣ ሁለተኛው ኦህዴድ/ብልፅግና መንግስት ከህወሓት ይልቅ የታጠቀ እና የተደራጀ የአማራ ኃይል ለኦሮሙማ የፖለቲካ ግብ ስትራቴጂያዊ ጠላት ሊሆን ይችላል ብሎ ማመኑ ናቸው፡፡ የአማራው ልዩ ኃይል በተለይም ፋኖው ትጥቅ እና ስንቅ እንዳይቀርብለት፣ በከፊል የቀረበለትም ህዝባዊ ኃይል ቢኖር የጦርነት ስምሪት ሳይሰጠው እንዲሰላችና ቤተሰቡን እና እርሻውን እንዲያማትር መደረጉ አማራው በወያኔ ላይ ድል እንዳይቀዳጅ የመፈለግ ስሜት እንዳለ ያመላክታል፡፡
በኦህዴድ/ብልጽግና እና በህወሓት መካከል ያለው ግጭት የስልጣን ሽኩቻ እንጅ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት አለመሆኑ በብልጽግና መንግሥት በኩል ለድርድር የቀረቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጤን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እንደሚታወሰው ህወሓት አሸባሪ የሚል ስያሜ እንዲሰጠው የተደረገው በፓርላማ ሁኖ እያለ፣ ፓርላማው ይህን የአሸባሪነት ስያሜ ሳያነሳ “ህወሓት እውቅና ከሰጠው” የብልጽና መንግሥት ከህወሓት ጋር ለመደራደር ዝግጁ እንደሆነ ካቀረባቸው ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች ዋነኛ ቅድመ ሁኔታ ማድረጉ ምስክር ነው፡፡
እንዴት ነው ሽብርተኛ የተባለ ድርጅት ለመንግሥት እውቅና እንዲሰጥ የሚጠየቀው? የጦርነቱ ዋነኛ ምክንያት የእውቅና እጦት ከሆነ፣ ጦርነቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልል ሳይዛመት ሠራዊቱ ትግራይ ውስጥ እያለ ማቅረብ በተገባ ነበር፡፡ በአማራው እና በአፋር ክልሎች ላይ እጅግ ግዙፍ ጥፋት ከደረሰ በኋላ፣ በአማራው እና በአፋር ሕዝባዊ ኃይል እንደሁም በመከላከያ ተጋድሎ ህወሓት ከወረራቸው አካባቢዎች የሚወጣበት ቀዳዳ እያጣ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ፣ ጦርነት እንዲያቆም እና ለፌደራል መንግሥቱ እውቅና እንዲሰጥ የሚሉ ጥያቄዎችን በቅድመ ሁኔታነት ማንሳት ፖለቲካዊ ስህተት ነው፡፡ አሁን የተያዘው የመከላከል ጦርነት ወደ አጥቂነት ደረጃ ሳይሸጋገር ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች አለአግባብ የያዘውን ቦታ ሳይለቅ ጦርነት ይቁም፣ ህወሓት ለብልጽግና መንግሥት እዉቅና ይስጥ መባሉ ድርድሩ ከአገር ጥቅም ይልቅ ስልጣንን ያስቀደመ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚካሄድ ድርድር ኢህአዴግ ቁጥር አንድን ከኢህአዴግ ቁጥር ሁለት ጋር የማስታረቅ አካሄድ ነው፡፡
ይኸ አካሄድ ደግሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከአሁኑ ይበልጥ በባሰ ሁኔታ የሚያወሳስበው ይሆናል እንጂ ሊያረጋጋው አይችልምና ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል እንላለን፡፡ እርግጥ ጦርነት እና ድርድር አብረው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው፡፡ ይሁንና ድርድር የሚጀመርበት ጊዜ የፖለቲካ ችግርን ከመፍታት አንፃር ወሳኝነት ያለው ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ባልደራስ አመለካከት ድርድሩ መጀመር ያለበት ህወሓት በኃይል ከያዘው አካባቢ በኃይል እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” እንዲሉ በድርድሩም ሂደት ውስጥም ቢሆን ጉዳት የደረሰባቸው የአማራ እና የአፋር ክልሎች ከፌደራል መንግሥቱ እኩል የድርድሩ ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል፡፡
የብልጽግና መንግሥት ለድርድር በኦፊሴል የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች
1ኛ/ ጦርነት ማቆም
2ኛ/ ህወሓት ከወረራቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ለቆ መውጣት
3ኛ/ ህወሓት ለብልጽግና መንግሥት እውቅና እንዲሰጥ የሚሉ ናቸው፡፡
እነዚህን የብልጽግና መንግሥት ድርድርን አስመልክቶ ያቀረባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ባልደራስ አግባብነት ያላቸው ናቸው ብሎ አያምንም፡፡ አሁን በመንግሥት በኩል የተያዘውን የመከላከል የጦርነት አካሄድ ወደ ማጥቃት በማሸጋገር በትግራይ ውስጥ ያለውን የህወሓት ጦርነት ማደራጀት ተቋማት ከጥቅም ውጭ በማድረግ ጦርነቱን ማቆም ሲቻል፣ ጦርነቱ ይቁም የሚል ድፍን ያለ ቅድመ ሁኔታ ማቅረብ ስህተት ነው፡፡ ህወሓት ከወረራቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች ኃይሉ እየደከመ ባለበት በአሁኑ ጊዜ በወታደራዊ የማጥቃት እርምጃ ጠራርጎ ማውጣት ሲቻል፣ በድርድር ለቆ ይውጣ የሚል ቅድመ ሁኔታ ህወሓት ተዋጊ ኃይሉን ሳይመታ አስወጥቶ ለሌላ ዙር ጦርነት ጊዜ የሚገዛበት ስለሆነ፣ የተሳሳተ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ድርድርን እንደጊዜ መግዣ በማድረግ የሚታወቅ እና የለየለት ሽብርተኛ እንደሆነ የሚታወቀውን ህወሓትን እውቅና እንዲሰጥ መጠየቅ፣ ህወሓትን ከሽብርተኛነት ወደ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ለመቀየር የሚደረግ ዳርዳርታ ነው፡፡
የኦህዴደ/ብልጽግና መንግሥት የሚከተለውን በመከላከል ላይ የተመሰረተ የጦር ስትራቴጂ ወደ ማጥቃት ሳያሸጋግርና የማጥቃቱ የዘመቻ ውጤት ሳይታወቅ ወያኔ አለአግባብ የያዛቸውን ቦታዎች እንደያዘ “ጦርነቱ ይቁም ህወሓት ለብልጽግና መንግሥት እውቅና ይስጥ” መባሉ የድርድሩ መንፈስ ከሀገር ጥቅም ይልቅ ስልጣንን ያስቀደመ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ጦርነቱ እስካሁን የተመራበት መንገድ መሰረታዊ ድክመቶች ያሉበት፣ ጦርነቱን የሚያራዝምና ተጨማሪ ጥፋት የሚያስከትል መንገድ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በመከላከል እንጂ በማጥቃት ላይ ያላተኮረ የጦርነት ስትራቴጅ ለድል አያበቃም፡፡ የአማራ ህዝባዊ ኃይል ብአዴን ብልጽግና በጥርጣሬ መመልከቱ እና ስንቅ እና ትጥቅ በተገቢው መልኩ በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ በፌደራል መንግስቱ ላይ ጫና ከማሳረፍ ይልቅ ስልጣንን የሚያስቀድም የውስጣዊ መከፋፈል ፖለቲካ መከተሉ አካባቢውን ለበለጠ ጥቃት እና ጥፋት ዳርጎታል፡፡ በዚህ የትንቅንቅ ወቅት የብአዴን ብልፅግና “በግሉ የታጠቀ ሁሉ መሳሪያ ያስመዝግብ” የሚል መመሪያ ማውጣቱ ደግሞ የክልሉ አመራር ውደቀት ተጨማሪ ማመላከቻ ነው፡፡
ስለሆነም ጦርነቱ በድል እንዲጠናቀቅ ከተፈለገ፣ በአማራው ክልል የሚካሄደው የእስካሁኑ የጦርነቱ ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ አመራር በአስቸኳይ መታረም አለበት፡፡ የእርማቱ እርምጃ ውጤት ሊያገስኝ ከማይችል ጠባብ የስልጣን አመለካከት ተላቆ ሕዝባዊነትን መላበስ ይኖርበታል፡፡ የአማራ ክልል መደበኛ የሆነ መንግሥታዊ መዋቅር ብቻውን ውጤት አላስገኘም፡፡ በመሆኑም በየአካባቢው ህዝቡ እምነት የሚጥልባቸው እና ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች፣ የልዩ ኃይሉ፣ የፋኖው እና የሚሊሻ ኃይሎች አመራሮች፣ ከቀድሞ ሠራዊት የተወጣጡ ወታደራዊ ባለሙያዎች፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች እንዲሁም ከአጎብዳጅነት የፀዱ የአማራ ብልፅግና አባላት ያሉበት የቀውስ እና የሕልውና የዘመቻ ወቅት ፖለቲካዊ አመራር የሚሰጥ የጋራ አካል ሊቋቋም ይገባል፡፡
ይኸ የቀውስ ጊዜ አመራር ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመቀናጀት፡-
1. የፌደራል መንግሥቱ ወደ ግንባር ለዘመተው ኃይል አለምንም ማመንታት በቂ ስንቅ እና ትጥቅ የሚቀርብበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል፡፡ መከላከያ ኃይሉንም ከአሻጥር የፀዳ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡
2. የአማራ ክልልን የክተት ጥሪ ውጤታማ ለማድረግ ለአማራ ክልል ልዩ የጦርነት ጊዜ የበጀት ድጋፍ የሚገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ፓርላማው በዚህ ጉዳይ በአስቸኳይ ተሰብስቦ መወሰን ይኖርበታል፡፡ ሌሎች ክልሎችም የፋይናንስ እና የስንቅ አቅርቦት ሊያበረክቱ ይገባል፡፡
3. ሌለው የጦርነት ገፈት ቀማሽ የሆነው የአፋር ክልል በመሆኑ፣ በክልሉ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት ለመቋቋም እንዲቻል የፌደራል መንግሥቱ ለአፋር ክልልም ልዩ የጦርነት ጊዜ በጀት ሊመድብ ይገባል፡፡
4. በአማራ ክልል በወያኔ በተከፈተው ወረራ የተጎዳው ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ከፍተኛ ችግር ላይ በመሆኑ፣ ከሃገር አቀፍ እና ከዓለም አቀፍ አካላት እርዳታ የሚገኝበትን ሁኔታ በማመቻቸትና በቅርብ በመከታተል መሰናክሎችን ማስወገድ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
5.የህወሓትን የወረራ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አቅጣጫዎች የኦነግ ታጣቂ ኃይል ለከፈተው ጦርነትም ተገቢ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መታቀድ ያለበት የዘመቻ ስምሪት ይህ አሸባሪ ኃይል በሚንቀሳቀስባቸው የአማራ እና የኦሮሞ አካባቢዎች በሙሉ እንዲሸፍን ተደርጎ በመገደል፣ በመፈናቀል እና በከፍተኛ ስጋት ላይ የወደቀውን የአማራ ህዝብ መታደግ የግድ ይላል፡፡ የአማራ ህዝብ እንደ ቄራ ከብት በሚታረድባቸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ የተጠናከረ የአማራ ልዩ ኃይል እንዲዘምት የፌደራል መንግሥቱ ፈቃድ ሊሰጥ ይገባል፡፡ የኦህዴድ/ብልጽግና መንግሥት ከተረኝነት የኦሮሙማ ፖለቲካ የፀዳ መሆን አለመሆኑ ለዚህ ጥያቄ በሚሰጠው ምላሽ የሚመዘን ይሆናል፡፡
6. እስካሁን የተያዘው የመከላከል የጦርት አመራር ሙሉ በሙሉ ተለውጦ በተለያየ ግንባሮች የማጥቃት እርምጃ እንዲወስድ፣ ለዚህ የማጥቃት እርምጃ የትጥቅ፣ የስንቅ፣ የመረጃ አቅርቦት፣ ወዘተ…ባልተቆራረጠ ሁኔታ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ የማጥቃት እርምጃው ዓላማ በአጭር ጊዜ የወያኔ ወራሪ ኃይልን ከአማራ እና አፋር ክልሎች ጠራርጎ በማስወጣትና ለወደፊቱም ወታደራዊ ስጋት ሊፈጥር የማይችልበት ደረጃ ላይ ማድረስ እና በዚህ ሂደት ህወሓት ትጥቁን እንዲፈታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
7. ሽብርተኛው ህወሓት እና ግብረአበሮቹ በአማራ ክልል ህዝብ ላይ እየፈፀሙ ያሉትን ወታደራዊ ጥቃት እና ዘረፋን በማክሸፍና በመታደግ ረገድ ድክመት ያሳዩ የአማራ ብልፅግና አመራሮች ተገምግመው ሓላፊነታቸውን እንዲለቁ እና ሕዝባዊ ተቆርቋሪነታቸውን በተግባር ባሳዩ የተሻሉ ሰዎች እንዲተኩ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው እርምጃ ነው፡፡
8. በተለይ በአማራ ክልል በርከት ያሉ የወያኔ የውስጥ ሴረኞች እንዳሉ የደሴ እና የኮምቦልቻ ጦርነቶች አሳይተዋል፡፡ በመሆኑም በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የውስጥ አሻጥረኞችን የማጥራቱ ሂደት ንፁሃን የትግራይ ተወላጆችን ለችግር በማይዳርግ መልኩ በጅምላ ሳይሆን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ሊከናወን ይገባል፡፡
9. በተለያዩ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉት የጦርነት መረጃዎች ወቅታዊነትን እና ታዓማኒነትን መሰረት በማድረግ ለህብረተሰቡ ማሰራጨትን በተመለከተ የሚታዩትን ድክመቶች ለማረም መንግሥት አበክሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡
10. የኢትዮጵያ በአካባቢ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶች እና ኢትዮጵያ እንድትዳከም የሚፈልጉ ምዕራባውያን አገሮች ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል በቁጥጥር ስር ለማድረግ የቀየሱት ስትራቴጂ በቅድሚያ አማራን ማዳከም እና መበታተን የሚል እንደነበር ይታወቃል፡፡ ህወሓት እና ኦነግ ይህን “የጨቋኝ አማራ” የሃሰት ትርክት የወረሱት ከጌቶቻቸው ታሪካዊ ጠላቶች እና ምዕራባውያን ነው፡፡ ስለሆነም ለኢትዮጵያ አገራዊ ጥቅም የቆሙ ኃይሎች አለም አቀፍ አጋሮቻቸውን ማበራከት እና ግንኙነታቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን በመደገፍ አጋርነታቸውን ያሳዩ ዓለም አቀፍ ኃያላን ሃገራትን ማለትም ሩሲያንና ቻይናን ለማመስገን በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ የሚመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሩሲያ እና በቻይና ኦፊሴላዊ ጉብኝት ሊያደርግ ይገባል፡፡ ይህ እርምጃ ለአሜሪካ የማስጠንቀቂያ ደወል በመሆን ኢትዮጵያን በሚመለከት የተሳሳተ የውጭ ፖሊሲዋን አካሄድ ሊያረግበው ይችላል፡፡
የኦህዴድ/ብልጽግና መንግሥት ከላይ የተዘረዘሩትን ምክረ ሃሳቦች ሳይቀበል ቀርቶ እስካሁን የተከተለውን በወያኔ ላይ የተለሳለሰ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አካሄድ ከቀጠለ፣ በኢትዮጵያ ህልውና እና ሉኣላዊነት ላይ በአጭር ጊዜ ሊጠገን የማይችል ጉዳት እንዳይደርስ ያሰጋል፡፡ ድርድር መደረጉ የማይቀር ቢሆንም ለድርድሩ የሚቀርቡ ቅድመ ሁኔታዎች ጠንከር ያሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህም ማለት ድርድሩ የማጥቃት ጦርነቱ ተገፍቶበት የሚገኙ ውጤቶችን በቅድሚያ የሚያሳጣ መሆን የለበትም፡፡
ድል ለኢትዮጵያ!
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ህዳር 08/2014 ዓ.ም