>

"ከአፄ ኢዬአስ እስከ ዐቢይ አህመድ ....!!!" (እስክንድር ነጋ፣ የህሊና እስረኛ፣ ቂልንጦ፣ ኢዲስ አበባ)

“ከአፄ ኢዬአስ እስከ ዐቢይ አህመድ ….!!!”

እስክንድር ነጋ፣ የህሊና እስረኛ፣ ቂልንጦ፣ ኢዲስ አበባ

 

1.1—-የ360 ዙር ታሪካችን
ዘመነ መሳፍነት በአፄ ኢዬአስ የንግሥና ዘመን እንደተከሰተ የታክ መፃህፍት ይነግሩናል፡፡ አፄው በየግዜው በውስጥ የሚነሱባቸውን አመፆች በራሳቸው ሠራዊት መቋቋም ተስኗቸው፣ በትግራዩ ስሁል ሚካኤል ጦር ላይ ጥገኛ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ፍቅራቸው ግን አልዘለቀም።  በመጨረሻ፣ አፄው በትግራዮ መሥፍን ትዕዛዝ በሻሽ ታንቀው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይህ ወቅት፣ ከአክሱም ውድቀት በኋላ ትግራይ በኢትዮጰያ ፖለቲካ ማንሰራራት የጀመረችበት ግዜ ለመሆን የበቃም ነበር፡፡
 ይኸው፣ የኢትዮጵያ ታሪክ የሶስት መቶ ስልሳ ዙር ያጠናቀቀ ይመስል፣ ታሪክ ራሱን ደግሞ፣ አፄ ኢዬአስ የነበሩበት ቦታ ላይ ተመልሶ ይገኛል፡፡ እነ ዐቢይ አህመድ፣ ባህር ዳር  ላይ ሆነው ጥቅምት 19/2012 ባወጡት መግለጫ፣ “ህወሓትን በፌድራሉ መከላከያ ኃይል ብቻ ማሸነፍ አይቻልም” ብለው እቅጩን ነገረውናል፡፡ ልክ እንደ ኢዮአስ ግዜ፣ የፌድራሉ መከላከያ በትግራይ ኃይል የተበለጠበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡
 ሀገራችን እዚህ ቦታ ላይ እንዴት ደረሰች? የሚለውን ጥያቄ አስመልክተው፣ ጠ/ሚ/ሩ፣ ቅዳሜ፣ጥቅምት 21/2014 ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አንድ ፅሁፍ ለቀው፣ በመገናኛ ብዙሃን ተነቦላቸዋል፡፡ ከጠ/ሚ/ሩ ፅሁፍ ጥቂት ሰዓታት በፊት፣ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ፣ መከላከያ ከደሴና ከኮምቦልቻ “ስትራቴጂካዊ ማፈግፈግ” ማድረጉን ማብሰራቸው የጠ/ሚ/ሩ ፅሁፍ በጉጉት እንዲደመጥ አድርጓል፡፡
ነገሩ በዚህ አላበቃም። በነጋታው ደግሞ፣ ጠ/ሚ/ሩ የፌስቡክ ሰለባ ሆነው፣ ፅሁፋቸው፣ “ግጭት ቀስቃሽ ነው” ተብለው ከገፃቸው ላይ ተሰርዞባቸዋል።
1.2—-ማን ነው የተዳከመው?
ጠ/ሚ/ሩ በጦር ግንባር ያለውን ሁኔታ የገለፁበት መንገድ፣ ገራሚ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ መከላከያ ከደሴና ከኮምቦልቻ አፈግፍጎ የወጣ ቢሆንም፣ “ሠራዊታችን በምድርና አየር እንዳይነሳ እያደረገ እየመታው ነው”  ብለዋል፡፡
ይህን እንዴት እንቀበለው? እርግጥ፣ እንደ ጦር መሪነታቸው፣ የሠራዊታቸውን ሞራል ሁሌም ከፍ ለማድረግ መጣር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግን፣ ይህን ኃላፊነት ሲወጡ፣ ተዓማኒነታቸው ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ሚዛን የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አባባላቸው፣ የጦሩን ሞራል ለመጠገን እየጣረ ካለ መሪ ይልቅ፣ መሬት ላይ ካለው እውነታ የራቅ መሪ አስመስሏቸዋል፡፡ በዚህ ግዜ አደገኛ ገፅታ ነው።
 ቀጣዩን የህወሓት እንቅስቃሴ አስመልክተው ያሉትም አለ፡፡ በአሁኑ ግዜ፣ “የመጨረሻ አቅሙን እየተጠቀመ ነው” ብለውናል፡፡ ዓላማውንም፣ “(በአየር ድብደባ) የወደመበትን ከባድ መሣሪያ በመተካት ወደ ፊት መግፋት እንደሆነ” ነግረውናል፡፡
ግን፣ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ ማን ነው ወደፊት መግፋት የሚችለወ? ከባድ መሳሪያው የወደመበት? ወይስ በእጁ ያለው? በዐቢይ አባባል፣ ነገሩ የታገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ በዚህ የነፍስ ግቢ፣ የነፍስ ውጪ ግዜ፣ እያዳንዷ ቃላቸው ትመዘናለች። ጠቅላይ አዛዡ ጥንቃቄ አላደረጉም፡፡
 በሌላ በኩል ደግሞ፣ “በቀጣይ ተመሳሳይ ጥቃት መሰንዘሩ አይቀርም” በማለትም፣ “ተዳክሟል” በሚሉት ህወሓት ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ጠቆም አድርገውናል፡፡ የት ጋር ነው ጠ/ሚ/ሩ ያሉት? ህወሓት ተዳክሟልን? ወይስ ከደሴና ኮምቦልቻም ባሻገር ጥቃት የመሰንዘር አቅም አለው? ግልፅ  አይደለም፡፡
እንደ አጋጣሚ ሆኖ፣ በዚያው ምሽት መግለጫ የሰጡት የህወሓቱ የጦር አዛዝ ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ፣ ነገሮችን ጥርት አድርገው አስቅምጠውላቸዋል፡፡ ጄኔራሉ፣ “ጦርነቱ አልቋል” በማለት፣ የፍልሚያውን ዋንጫ በእጃቸው ለማስገባት ወደ አዲስ አበባ እንደሚገሰግሱ ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጠውላቸዋል፡፡ እንደ ፃድቃን አባባል፣ የደሴና ኮምቦልቻ መያዝ፣ በ1983 አምቦ ላይ ከደርግ ጋር ከተደረገው የመጨረሻ ፍልሚያ የሚስተካከል ነው፡፡
ጦር ሜዳ ላይ ያለው እውነታ ምንም ይሁን ምን ግን፣ ዐቢይ ተስፋ እንዳልቆረጡና ለቀጣይ ፍልሚያ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ለእነ ፃድቃን ግልፅ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል፡፡
1.3—–ቀጣዩ ፍልሚያና የጠ/ሚ/ሩ ስጋቶች
ሆኖም፣ በዚያ ቀጣይ ፍልሚያ ጠ/ሚ/ሩ ስጋቶች እንዳሏቸው አልሸሸጉንም፡፡ በቀዳሚነት፣ “በመካከላችን የህወሓት ወኪሎች አሉ” ብለው አስደንግጠውናል፡፡ ነገሩ በማበራዊ ሚዲያ ላይ በተደጋጋሚ ሲባል የከረመ ቢሆንም፣ ከእሳቸው አንዳበት ሲሰማ የሚፈጥረው የተለየ ስሜት አለ፡፡ ሥልጣን ከያዙ ሶስት ዓመታት በኋላ ይህን ሊሉን ባልተገባ፡፡  ምን ሲሰሩ ቆዩ? ይህ በጦር ሜዳ ለምን እየተሸነፉ እንደሆነ አንድ መጠቆሚያ ነው፡፡ እነ ዐቢይ ሰፈር የብቃት ችግር አለ።
 እዚህም ጋር እንደ አጋጣሚ ሆኖ፣ የጠ/ሚ/ሩን ጥርጣሬ የሚያጠናክር ፍንጭ ከጃል መሮው ሸኔ ወዲያው ተሰምቷል።  ሸኔ፣ “ከሚሴን ተቆጣጥሬያለሁ” ብሎ ባወጣው መግለጫ፣ የመከላከያ አባላትን መማረኩን፣ ከእነዚህ መካከል የኦሮሞና የደቡብ ወታደሮችን “በእንክብካቤ” እያስተናገዳቸው መሆኑን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ጠ/ሚ/ሩ፣ ከጥቅም ጋር ተሳስሮ በህወሓት በከል አለ ካሉት አደጋ ይልቅ፣ ከብሄር ጋር ተሳስሮ በሸኔ በኩል ያለው አደጋ ከፍ ያለ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
 ይህን አደጋ ከመከላከል አኳያ፣ በአንድ በኩል፣ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን ሁሉ በጅምላ ላለመፈረጅ፣ በሌላ በኩል፣ አደጋ እንዳለ ተቀብሎ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ ቀላል አይደለም፡፡ እነ ዐቢይ ከባድ ችግር ተደቅኖባቸዋል፡፡ ይህን ችግር ለማለፍ ጥበቡ አላቸው ለማለት እቸገራለሁ።
1.4—-ተጠያቄነትን ማስፈን 
ከችግሮቹ ባሻገር፣ ዐቢይ አሉ የሚሏቸውን መፍትሄዎችንም አልነፈጉንም፡፡ በዚህም መሰረት፣ “የምንጠይቅ ብቻ ከሆነ፣ የድላችን ግዜ ይራዘማል” ሲሉ መክረዋል፡፡  ትክክል ናቸው፡፡ ወሬ ብቻ ኢትዮጵያን አያድናትም፡፡
ግን፣ ማን ነው ጠያቂ ብቻ የሆነው? ህዝቡ? በፍፁም እንዳልሆነ ይታወቃል። “ዝም ብሉ”  እየተባለ፣ “ትግራይ ለምን ተለቀቀች?” ብሎ የጠየቀም የሞገተም የለም በሚያስብል ደረጃ ነው ነገሮች እስካሁን ያሉት፡፡ ኮረም፣ አላማጣ፣ ላሊበላ፣ ወልዲያ ሲለቀቁም እንደዚያው፡፡ ደሴም፣ ኮምቦልቻም፣ ከሚሴም በህወሓት ሲያዙ የተለወጠ ነገር የለም፡፡
እኔ እንደሚመስለኝ፣ የጠያቂ መብዛት አይደለም  ጠ/ሚ/ሩን ያሳሰባቸው፡፡ ሀገር እፈረሰች ነውና፣ ጠያቂ ይበዛል የሚል ፍራቻ አላቸው፡፡ አስቀድመው ማጥቃታቸው ነው፡፡ ጠ/ሚ/ሩ በጃቸውም አልበጃቸውም ግን፣ ጠያቂዎች አሁን አስፈላጊ ናቸው፡፡ ሀገሪቷ ባለቤት አላት፡፡ ያ ባለቤት ህዝቡ ነው፡፡ ነገሮች ሲበላሹ እየተመለከተ ዝም ሊል የሚችልበት አግባብ የለውም፡፡ እየወደመ ያለው ቤቱ ነው፡፡
 እርግጥ፣ ጠ/ሚ/ሩ እንዳሉት፣ የቤቱን ውድመት ማስቆም የሚችለው ጠያቂ በመሆን ብቻ አይደለም፡፡ ከተሞች አናት በአናት እየተለቀቁ ባለበት ሁኔታ ግን፣ ሽንፈቱ እንዴት እንደተከሰተ፣ ለምን እንደተከሰተ፣ በምንስ መንገድ ማስተካከል እንደሚቻል ጠይቆ፣ ተጠያቂነትን ከማስፈን የገዘፈ ተግባር ሊኖር አይችልም፡፡ ተጠያቂነት መንግስት በሩን ዘግቶ ብቻውን የሚፈፅመው ተግባር አይደለም፡፡ እንደ ጥፋቱ ክብደት፣ ህዝብ ጣልቃ ሊገባበትም የሚችል ጉዳይ ነው፡፡
1.5—–አስገራሚው መዘናጋት
የተጠያቂነቱ ጉዳይ ይበልጥ የሚያገዝፈው ደግሞ፣ ጠ/ሚ/ሩ፣ “የጠላት የጥንካሬ ምንጭ የእኛ ድክመትና መዘናጋት ነው” ያሉት ነው፡፡ ይህን የሚሉን፣ ደሴና ኮምቦልቻ በመያዛቸው በመሆኑ፣ ቀደም ብሎ መከላከያ መቀሌን ለቅቆ ከወጣ በኋላ እንደ ማዘዣ ጣቢያው የመረጣቸው ኮረምና አላማጣ በህወሓት ከተያዙ በኋላ መዘናጋት ነበር ማለት ነው፡፡
 ይባስ ብሎ፣ የወልዲያና የላሊበላ መያዝም መንግሥታቸውና የጦር አዛዣቸውን ከእንቅልፋቸው አልቀሰቀሳቸውም፡፡ ደሴና ኮምቦልቻ ሲያዙ ነው ጠ/ሚ/ሩ የበታቾቻቸውን ለመቀስቀስ የተነሱት፡፡ ማን ነበር “ ጉድ ሳይሰማ  መስከረም አይጠባም” ያለው? ይኸው በጠ/ሚ/ሩ በኩል አባባሉ ተፈፃሚ ሆኖለታል! ገራሚ ነው፤ በእጅጉ ገራሚ፡፡
1.6—–መደማመጥና ተግባር
የጠ/ሚ/ሩ ፅሁፍ፣ ሙሉ ለሙሉ እንከን ብቻ የሚወጣለት አይደለም፡፡ ጥሩ ፀሃፊ ናቸው፡፡ ፖለቲካቸውን አለመወደዴ መክሊታቸውን እንድክድ አያደርገኝም፡፡ ፖለቲካ ባይጠልፋቸው ኖሮ፣ ጥሩ ፀሃፊ ወይም አነቃቂ (Inspirational speaker) ይወጣቸው ነበር፡፡  በፅሁፎቻቸው አንዳንድ ጥሩ ሃሳቦች ይገኛሉ፡፡ ይኸኛውም የተለየ አይደለም፡፡
 ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር ለመወጣት፣ “መደማመጥና መተግበር አለብን” ብለዋል፡፡ እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉም ተናጋሪ የሆነበት ሀገር ከሆነች ሰነባብታለች፡፡ እኔ ሳውቃት ሁሌም እንደዚያ ሆና ነው፡፡ ምን አልባት የአፄዎቹ ዘመን ሁሉም አድማጭ የነበረበት ግዜ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከአንድ ፅንፍ ወደሌላኛው ሄደናል። መሃሉን ፈልገን ማግኘት አለብን፡፡ ሀገራችን ከእጃችን እያመለጠችን ነው፡፡ የአፄ ኢዮአስን መንገድ ጀምረነዋል፡፡ መቋጫው ላይ ግን  አልደረስንም። አፈር ቧጠንም ቢሆን፣ የአፄው መጨረሻ ላይ መድረስ የለብንም፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያ ይጠብቅ ን ይባርክ፣ ይጠብቅ!

Filed in: Amharic