እስክንድር ነጋ፣ የህሊና እስረኛ፣ ቂልንጦ፣ አዲስ አበባ
1.1 ውስጥ ውስጡን የተሰጠው ምክር
ሽንፈት ባለበት ሁሉ፣ መላ ምቶች አሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ብዙውን ጊዜ፣ ሽንፈትን ለመቀበል ከመቸገር የሚመነጨ ችግር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ማለት እውነተኛ ሴራዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ አሉ፡፡ አበው፣ “የወደቀ ምሳር ይበዛበታል” እንዳሉት፣ በሽንፈት አዙሪት የተጠለፈ ኃይል ከውስም ከውጭም ጠላት ስለሚበዛበት፣ ሴራዎች ይጎነጎኑበታል፡፡ የዐቢይ መንግሥት ተመሳሳይ ወጥመድ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ገብቷል ማለት ባይቻልም፣ በሽንፈት አዙሪት ውስጥ ስለተጠመደ፣ ሴራዎች ቢጎነጎኑበት የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡
ጠ/ሚ/ሩ ባለፉው ሰሞን በፌስቡካቸው ላይ ባለቀቁት ፅሁፍ፣ “በጥቅም የተገዙ የህወሓት ወኪሎች በውስጣችን (መንግሥት ውስጥ ) አሉ” በማለት፣ ለሚመሩት ጦር ሽንፈት ሴራና አሻጥር ቦታ አለው ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመውናል፡፡ ነገሩን በዚህ አልቋጩትም፡፡ ሴራው ዓለም አቀፍ ሰንሰለት አለው ብለው እንደሚያምኑ ህዳር 2/2/14 በተላለፈው የ “አዲስ ወግ” ዝግጅት ላይ ሲያበስሩን ደግሞ፣ “አዲስ አበባ ስለተከበበች፣ ነገሩ (ጦርነቱ) እልቋልና፣ ከሀገር ሸሹ የሚል መካሪዎችአሉ” ብለውናል፡፡
ይህ ምን ማለት ነው? በአንድ በኩል፣ በአደባባይ እንዳምንሰማው፣ የተለያዩ ሀገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ማሳሰቢያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ባሌላ በኩል፣ ጠ/ሚ/ሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ከሀገር እንዲወጡ ውስጥ ውስጡን እየተመከሩ ይገኛሉ ማለት ነው፡፡
እንደ ጠ/ሚ/ሩ አባባል፣ ምክሩ ሲሰጥ ሁለት መከራከሪያዎች ቀርበዋል፡፡ አንዱ፣ ቀደም ብሎ በጨረፍታ እንደተጠቀሰው፣ ጦርነቱ በህወሓት አሸናፊነት ስለተጠናቀቀ፣ ከዚህ በኋላ በእነ ዐቢይ በኩል የሚደረግ ውጊያ፣ ከ “አልሞት ባይ ተጋዳይነት” ያለፈ ትርጉም የለውም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው፣ “አንዳንድ ኃይሎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ስለሚካሄድ፣ ቶሎ ቶሎ እንውጣ እያሉ ነው” የሚል ነው፡፡
1.2 ተጨባጭ እውነታዎች ሲፈተሹ
ሁለትቱ መከራከሪያዎች ሴራዎች ናቸው? ወይስ ተጨባጭ እውነታዎች አላቸው? እንፈትሻቸው፡፡ “ነገሩ (ጦርነቱ) አልቆለታል” ከሚለው እንነሳ፡፡ ይህ አባባል መጀመሪያ የተሰማው፣ መከላከያ ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላ ጀኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤና ጄኔራል ታደሰ ወረደ በሰጧቸው ቃለምልልስ ነበር፡፡ ከአራት ወራት በፊት ነበር፡፡ ጥያቄው፣ አባባልቸው እውነት ከሆነ፣ አዲስ አበባ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ለምን አልተያዘችም? የሚል ነው። በተጨማሪም፣ ባለቀለት ጦርነት፣ ህወሓት እንዴት ከደብረታቦርና ጉና ሊለቅ ቻለ? የሚለውም አለ።
የህወሓት አመራሮች ትንሽ አጋነዋል፡፡ ጦርነቱ እንኳን ትግራይ እንደትለቀቀች ይቅርና፣ ደሴና ከምቦልቻ ከተያዙ በኋላም ወደፊትና ወደኃላ እንደሚመላለስ በሚሌ ዙሪያ በተደረገው ውጊያ ታይቷል፡፡ ከጦርነቱ ማለቅ ይልቅ፣ ህወሓት ወታደራዊ የበላይነቱን መያዙ ነው እውነታው የሚያመላክተው፡፡ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ በአፋርና በሸዋ በያዛቸው መሬቶች ለበላይነቱ ተጨባጭ ምስክሮች ናቸው፡፡ ሊስተባበሉ አይችሉም፡፡ ይህን የበላይነት ይዞም፣ አዲስ አበባን አልሞ ወደፊት እየገሰገሰ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በባዶ አልሰጋም፡፡
ግን፣ ህወሓት ሚሌን ይዞ የአዲስ አበባ ጅቡቲን መንገድ ቢዘጋ እንኳን፣ ጦርነቱ መቶ በመቶ አልቆለታል ማለት አይደለም፡፡ አዲስ አበባም ቢደርስ እንደዚያው፡፡ ምንአልባት ለዚህ እውነታ ትልቁ ምሳሌ፣ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የስታሊን ግራንድ ውጊያ (The battle for Stalingrad) ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ 1983 አይደለም። በተለይ፣ሚሌ ላይ በነበረው ውጊያ እንኳን በኢትዮጵያ አየር ኃይል እጅ ያሉት ተዋጊ ድሮኖች (combat drones) ገና ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይእንዳልዋሉ በፈረንጆቹ አካባቢ የሚነገረው እውነት ከሆነ፣ በሊቢያ እንደታየው፣ በሙሉ ኃይላቸው ሊንቀሳቀሱ የኃይል ሚዛኑን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ የሰከነ አመራር ካለ፣ የኃይል ሚዛኑ እንደድንገት ሊቀየር ይችላል።
ሌላም አለ፡፡ ህወሓት አራት ኪሎ ያለውን የምኒልክ ቤተ መንግሥት ቢይዝ እንኳን፣ ጦርነቱ ያልቃል ማለት አይደለም፡፡ ጎንደርና ጎጃምን መያዝ ቀላል አይሆንም፡፡ ጎንደርን መያዝ አዲስ አበባን ለመያዝ ከሚደረግ ውጊያ የከረረ ሊሆን ይችላል፡፡ በደርግ ጊዜ፣ የአዲስ አበባ መያዝ የጦርነቱ መጨረሻ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ግዜ፣ የአዲስ አበባ መያዝ ወይ ለጦርነቱ መቀጠል ፣ ወይ ለአዲስ ጦርነት መከሰት መነሻ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡
በሱዳን የተደረገው መፈንቅለ መንግስት በኢትዮጵያ ሊደገም ይችላልን? ለሚለው የፈረንጆቹ አባባል፣ “በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ነን፣ ሊሞከር አይችልም” ብለው ጠ/ሚ/ሩ ያቀረቡት ምክንያት፣ ሚዛን አይደፋም፡፡ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከሥልጣናቸው የወረዱት የግብፁ ፕሬዚዳንት ሞርሲ በሀገሪቷ ታሪክ በህዝብ የተመረጡ ብቸኛው ፕሬዚዳንት ነበሩ። ከብዙ በጥቂቱ፣ በኢራን፣በቺሊ፣በናይጀሪያ፣ በሱዳን፣ በአልጀሪያ፣ ወዘተ ተመሳሳይ ድርጊቶች ተፈፅመዋል፡፡ ብዙውን ግዜ፣ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዘው ሁኔታ፣ የመንግሥት መዳከምና ሀገር ወደ ሥርዓት አልባ ምስቅልቅል የምትገባበት አደጋ መከሰት ነው፡፡ እርግጥ፣ በእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታም ቢሆን፣ ወታደሮች በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት የሚያስችላቸው ህጋዊ፣ ፖለቲካዊና ሞራላዊዊ ድጋፍ አላቸው ወይ? ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ ይገባልም፡፡
ብልፅግና ሀገሪቷን በጦር ሜዳውም፣ በዲፕሎማሲውም፣ በኢኮኖሚውም ምስቅልቅሏን እያወጣት ባለበት በዚህ ግዜ ግን፣ ፈረንጆቹ ሃሳቡን ያነሱት ሴራ ለመጎንጎን ነው ብቻ ብሎ በእርግጠኝነት ለመደምደም አይቻልም፡፡ ጠ/ሚ/ሩ፣ ሀገሪቷ ወታደራዊ ጣልቃ ገብተን የማይጋብዝ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን የማረጋገጥ ኃላፊነት አላባቸው፡፡ ፈረንጆቹን ለቀቅ አድርገው እዚያው ላይ ቢያተኩሩ ለሁላችንም ይበጃል፡፡
1.3 “ሁለተኛ ሀገር የለንም”
በጣም ያነጋገረው የጠ/ሚ/ሩ አባባል ግን፣ ስለ ኮ/ል መንግሥቱ የሰጡት አስተያየት ነበር፡፡ “አዲስ ታሪክ ባንሰራ፣ከ1983ቱ ታሪክ ልንማር እንደምንችል አልተገነዘብንም” ያሉት ጠ/ሚ/ሩ፣ “ኮ/ል መንግስቱ ከሀገር የወጡበት ጉዳይ ቢጠና፣ የማጭበርበር ውጤት (መሆኑ እንደሚደረስበት) ጥርጣሬ የለኝም” ብለው ደምድመዋል፡፡
እንደ ጠ/ሚ/ሩ ትንታኔ ከሆነ፣ በ1983 “ጦርነቱ አልቆለታል፣ አመራሩ ሊሸሽ ነው” የሚል ወሬ የተጋጋለው፣ ህወሓት ከአዲስ አበባ ገና በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እያለ ነበር፡፡ ይህ ወሬ በመንግስት አመራር አባላት መካከል አለመተማመንና መከፋፈልን መፈጠሩን፣ ይህን ታሪክ ለመድገም አሁንም ተመሳሳይ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን አስጠንቅቀዋል፡፡
በዚህ ድባብ፣ ኮ/ል መንግስቱ ከሀገር ሲወጡ፣ “ህወሓት ወደ አዲስ አበባ ስተት ብሎ በዎክ ገብቷል” ብለዋል፡፡ ይህ ታሪክ በእሳቸው እደማይደገም እፅእኖት ሰጥተውታል፡፡ “እኛ ሁለተኛ ሀገር የለንም፡፡ አየር ሲቀያየር የሚቀያየር ነገር የለንም” በማለት፣ ምንም መጣ ምንም፣ ከሀገር እንደማይወጡ ቃል ገብተዋል፡፡
አጀብ ነው! ጠ/ሚ/ሩ ጥሩ አልተመኙም ማለት አይቻልም፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር ተሳስሮ፣ በዚህ ጉዳይ የታሪክ ጠባሳ አለን፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስት ውድቀት ከ1966 ይልቅ፣ ከማይጨው ውጊያ በኋላ ሀገር ጥለው የሸሹ ግዜ ነበር ብዬ አምናለኹ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ንጉሥ ተዋግቶ ሲያሸንፍ፣ ወይ ተሸንፎ ሲሞት ነው የምናውቀው፡፡ ሌላ ሁሉ ሊሸሽ ይችላል፤ ንጉሥ ግን አይሸሽም።የአፄ ኃይለ ሥላሤ ሽሽት፣ ይህን ማንነታችንን ገርስሶታል፡፡ ከሽሽቱ በኋላ፣ አፄው ተቀባይነት ሊኖራቸው የሚችልበት ሁኔታ የነበራቸውን ህዝባዊ መሰረት አጡ፡፡ የተማሪውን ንቅናቄ ከፈጠሩት ምክንያቶች መካከል አንዱ ይህ ነበር።
የአፄው ሽሽት በኮ/ል መንግሥቱ መደገሙና አለመደገሙ፣ በታሪክ ፅሃፊዎች ዘንድ ገና አመርቂ ጥናት አልተደረገበትም፡፡ የኮ/ል መንግሥቱ ቃል ግን በጋዜጦች፣ መፅሔቶችና መፅሃፍት ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ኮለኔሉን አሳፍራ የነበረችው አውሮፕላንን ያባረሩት ፓይለት ምስክርነት እንደዚያው በጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ ይገኛል፡፡ ከመንግሥቱ ጎን የማይለዩት አጃቢያቸውም በዚምባቡዌ ከተመለሱ በኋላ ቃለ ምልልስ ተደርጎላቸው ለታሪክ ቁጭ ብሏል፡፡ ሌሎች ብዙ ያልተነኩ ምንጮች ደግሞ አሉ፡፡ ጠ/ሚ/ሩ እንዳሉት፣ ጉዳይ መጠናቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ታሪካችንን ማወቅ አለብን፡፡ አለበለዚያ፣ ስህተቱን እየደገምን እንኖራለን፡፡
1.5 ወደ ውስጥ መመልከት
ኮ/ል መንግሥቱ ከሀገር ከመውጣታቸው ትንሽ ግዜ በፊት፣ ዕጣ ፋንታቸው በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተነስቶ ነበር፡፡ የስብሰባው መሪ ራሳቸው ኮ/ል መንግስቱ ሲሆኑ፣ ታዳሚው ከፍተኛ የመንግሥትና የፓርቲ ባለሥልጣናት፣ የኃይማኖት መሪዎችና የታወቁ ሰዎች ነበሩ፡፡ በዚያ መድረክ ላይ ነበር አቡነ ገብርኤል የተባሉ የኦርቶዶክስ ጳጳስ፣ ኮ/ል መንግሥቱ የአፄ ቴዎድሮስን ፅዋ እንደሚጨልጡ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ምጥ ላይ እያለች በሽሽት ወደ ውጭ ሀገር ይሄዳሉ ብለው እንደማያምኑ የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያ በሱማሌ ተወርራ በነበረበት ግዜ ፣ ኮ/ል መንግሥቱ “አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀረን ድረስ እንዋጋለን” ብለው በተደጋጋሚ ያሰሙት የነበሩትን መፈክር ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡ አቡኑ ይህን አባባል አስበው የሰጡት አስተያየት ሳይሆን አይቀርም። መንግስቱ ለአቡነ ምላሽ ሳይሰጧቸው ነበር ያለፉት፡፡
ተገደውም ሆነ በፈቃዳቸው፣ እንደ አቡኑ እምነት መንግሥቱ ከሀገር ባይወጡ ኖሮ፣ ታሪክ በተለየ አቅጣጫ ይጓዝ ነበር ወይ? ብለን እንደ ሀገር የምንጠይቅበት ግዜ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ፣ የታሪክ ተማራማሪዎች መልስ ይዘውልን እስኪመጡ ድረስ ግዜ የሚሰጥ አይችለም፡፡ መንግሥቱ ዝምባቡዌ ከገቡ 30 ዓመታት በኋላ፣ ታሪካችን ተመሳሳይ መንታ መንገድ ላይ ቆሞ፣ ውድ ሀገራችን ምጥ ላይ ትገኛለች፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎች ፣ ” ይህ ቢሆን ፣ ታሪክ እንዲህ ይሆን ነበር ” ብሎ እንደመናገር የሚጠሉት ነገር ያለ አይመስለኝም።ግምት ነው የሚሆንባቸው። ግምት ደግሞ ፣ “ግም” በሚሉት ፊደሎቹ የሚገለፅ ነው ይላሉ። ይህን ታሳቢ ያደረገ አስተያየት ነው የምሰጠው።
መንግስቱ ከሀገር የወጡት ግንቦት 13/1983 ነበር፡፡ በዚያን ዕለት፣ የመንግስት ጦር በአምቦ ከኢህአዴግ ጋር፣ በደቀመሃሪ ከሻዕቢያ ጋር ተፋጧል፡፡ ሁሉም ወገኖች ለዚያ ወሳኝ ፍልሚያ ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ሰነባብተዋል፡፡ የውጊያዎቹ ውጤት የሚወሰነው በእነዚያ ዝግጅቶች ነበር፡፡
በመንግስት በኩል ብቃትና ፅናት ያለው አመራር ቢኖር ኖሮ፣ የኮ/ል መንግስቱ በድንገት መሄድ፣ ሠራዊቱን ከማጥቀት ወደ መከላከል ቁመና ሊያወርደው ይችል ነበር እንጂ፣ ሙሉ ለሙሉ እንዲበተን ምክንያት ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ በደርግም ግዜ አሁን፣ በመንግሥት በኩል ያለው ክፍተት የአመራር ደክመት ነው፡፡ ይህ ወታደራዊ ሳይንስ ነው፡፡ መላምት አይደለም፡፡
ከዚህ እውነታ አኳያ፣ ዐቢይ ስለ ሴራ ከማውጣትና ከማውረድ ይልቅ፣ መንግሥታቸውን ቢፈትሹ ለእሳቸውም ለሀገርም ይበጃል፡፡ ጦርነቱ በወሬ ወደ ሸዋ አልገባም፡፡ ጦርነቱ ላለበት ሁኔታ ብዙ ተጠያቂዎች አሉ፡፡ በመላው ዓለም አንዳለው አሠራር፣ መጠየቅ ያለባቸው ጦርነቱ በሂደት ላይ እያለ ነው፡፡ ለግዜው በእነ ዐቢይ በኩል የተያዘው ፈሊጥ፣ ሽንፈታቸውን externalize ማድረጉ ላይ ነው፡፡ አያዋጣም። ችግራቸው በዋናነት በውስጣቸው ነው። ከመንግስታቸውም ሆነ ከሀገር ውጭ አይደለም፡፡ ይህ ማለት፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ችግር የለም ማለት አይደለም። ብዙ አሉ። ግን በሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ የሚቀመጡ ናቸው። ይህን ሳይቀበሉ፣ ራሳቸውንም ሀገሪቷንም ከዘፈቋት አዘቅጥ ውስጥ ማውጣት አይችሉም፡፡
በመጨረሻም፣ ይህን ፅሁፍ እያጠናቀቅኹ ባለበት ግዜ፣ ጠ/ሚ/ሩ ግንባር በአካል ተገኝተው ጦርነቱን በቀጥታ ለመምራት መወሰናቸውና፣ በነጋታውም ተግባራዊ እንዳደረጉት እየተዘገበ ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ በውሳኔያቸው ቢደሰቱም፣ እንዳንዶች ግን፣ ሰፊ ዝግጅት ተደርጎ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ሊጀመር ሲል ወደ ግንባር ማምራታቸው እንደ ድል ዜና ሽሚያ ቆጥረውባቸዋል፡፡
ድሉን ማንም ያምጣው ማንም ግን፣ በዚህ ጭልምልም ባለ ግዜ፣ ቢያንስ ቢያንስ የህወሓትን ግስጋሴ ማስቆም ከተቻለ ትልቅ ሀገራዊ እፎይታ ነው የሚያስገኘው፡፡ ለዘለቄታው ድል ግን፣ መንግስት ከውጭ ይልቅ ወደ ውስጥ ሳይመለከት የሚመጣ መፍትሄ የለም፡፡