>
5:28 pm - Saturday October 10, 8618

ድሉ የማነው?  (ዘመድኩን በቀለ)

ድሉ የማነው? 

ዘመድኩን በቀለ

…ተወደደም ተጠላም ድሉ የዐማራ ገበሬ ነው። ድሉ የዐማራ ፋኖ ነው። ድሉ የዐማራ ሚኒሻ ነው። ድሉ የዐማራ ልዩ ኃይል ነው። ድሉ እስከዛሬ ሽሽ፣ አፈግፍግ እየተባለ ሲዋረድ፣ እየሸሸ ሲማረክ፣ በወያኔ ሲቀጠቀጥ የከረመውና አሁን በመጨረሻው ሰዓት የመዋጋት ፈቃድ ያገኘው የጀግናው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ነው። አዎ ቀድሞ ክተት ያወጀው ዐማራው ነው። ዐዋጅ መመሪያው የወጣውም ከባህርዳር ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ የዐማራ ገበሬን ወደ ዘመቻ ተከተሉት እንጂ የዐማራ ጦር ጠቅላይ ሚኒስትሩን አልተከተለም። ተከትሎም አልዘመተም። ዐማራ ክተት ዐውጆ የውጊያ ያለህ ብሎ በጦር ግምባር እያዛጋ፣ እያፋሸከ እየቋመጠ ከተቀመጠ እኮ ቆየ። ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመሩት ብሔራዊ ጦር እየፈረጠጠ ከመቀሌ ሞላሌ ድረስ ሲሸሽ የዐማራ ጦር በባዶ እጁ እየመከተ ለማስቆም ሲሞክር እኮ ነው የቆየው። አሁንም ቢሆን ወያኔን ወጥሮ የያዘው የዐማራ እና የዐፋር ኃይል ነው። ይሄን መካድ ነውር ነው።
…እስከዛሬ ፈርጣጭ የነበረውን ጦራቸውን እና የጦር መሪዎቻቸውን ሳይገመግሙ፣ ለምን ተሸነፍን ብለው ራሳቸውንም ካውንስሉንም ሳይጠይቁ፣ ብሔራዊ ጦሩን የውርደት ካባ ያከናነቡት እነ ጄ ብርሃኑ ጁላን እና እነ ጄ ባጫ ደበሌን አዝለው፣ እሹሩሩም ብለው አስቀምጠው አሁን በድግሱ መጨረሻ ላይ ደርሶ የድል አጥቢያ አርበኛ መሆን ፌር አይደለም። መጀመሪያ ግምገማ መች ተደረገና? ሙሉ ወሎ፣ ከፊል ጎንደር፣ ከፊል ሸዋ፣ አፋር በከፊል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በሚመሩት ብሔራዊ ጦር ሽሽት ምክንያት እኮ ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል። ዐማሮችና አፋሮች ታርደዋል። ከፎቶው በፊት ግምገማው ይቅደም።
…የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ቢሆንም ቅሉ እደግመዋለሁ ጠቅላይ ሚንስትሩን ተከትሎ የዘመተ የዐማራም፣ የአፋርም ኃይል የለም። ዐማራም አፋርም ክተት ብለው አውጀው፣ ገበሬው እርሻውን፣ ሠራተኞች፣ ወጣቶች፣ የዩኒቨርሲቱ ፕሮፌሰሮች ሳይቀሩ ከዘመቱ ቆዩ። ዐማራ ያጣው ተዋጊ ሳይሆን የመዋጋት ፈቃድ ነበር። አሁን እሱን ፈቃድ አግኝቷል። ውጤቱም እየታየ ነው። በአንድ ቀን የኮንክሪት ምሽግ የሚደረምስ ተአምረኛ ሃይል ነው ዐማራ ያለው። መጠበቅ ነው። ውጤቱ ደግሞ ድል ብቻ ነው። ማሸነፍ ብቻ ነው።
…እርግጥ ነው ጠቅላዩን ተከትለው አዛውንት ጡረተኛ አባቶች የወታደር ልብስ ለብሰው ፎቶ ተነሥተው ራሳቸውን አነቃቅተው ተመልሰዋል። አንዳንድ አርቲስቶችም ጠሚውን ተከትለው በየከተማው ፎቶ ተነሥተው ተመልሰዋል። የግንቦት 7 እና የኢዜማ አባላትም ደብረ ብርሃን ድረስ ሄደው ፎቶ ተነሥተው ተመልሰዋል። “ዘመቻ ምኒልክ” የሚል ባነር ጽፈው እነ አንዳርጋቸው ጽጌም የኦሮሞ ፅንፈኞችን አሳብደውበታል። ጠቅላዩም እኔ ያልወጠወጥኩት ወጥ አይጣፍጥም ስለሚሉ በአፋር ሰሞኑን፣ ትናንት ደግሞ በጋሸና ግንባር ተገኝተው ውጊያውን በጉጉት ጀምር እስኪባል ይጠብቅ የነበረውን ሥርዓት አክባሪ የዐማራ ኃይል አስጀምረው የሚፈለገው፣ የሚጠበቀውም ድል እንዲጀመር ምክንያት ሆነዋል።
…ሲሰሙት ይመራል፣ ያንገሸግሻልም። ነገር  ግን እውነቱ ይሄው ነው። የድል ሽሚያ ይቅር። አቢቹ ዘመተ ከተባለም የዐማራ ገበሬን ዐዋጅ ተከትሎ ዘመተ እንጂ ከአርቲስቶች በቀር አቢቹን ተከትሎ የዘመተ የዐማራና የአፋር ገበሬ የለም። ደግሞም አቢቹ ያወጀው የክተት ዐዋጅም የለም። አቢቹ ያለው እስከዛሬ ከቤተ መንግሥት ሆኜ የምመራው ጦር እየሸሸ ደብረ ብርሃን ድረስ ስለደረሰ ወያኔ ጉርምቦዬን አንቃ ሳትገለኝ እዚያው ግንባር ድረስ ሄጄ መመሪያ ልስጥ ብሎ ነው የሄደው። እንኳን መሪ አይጥም ጎሬዋ አቅራቢያ ሁከት ሲበዛባት፣ ጭስና እሳት ሲበዛባት ከጉድጓዷ መውጣቷ አይቀርም። የሆነውም እንደዚያ ነው። …ዐማራ ሆይ አሁን ፈቃድ አግኝተሃልና ጠላትህ እንዳያመልጥህ። የወረረህን አፈር ከደቼ አብላው። ያዋረደህን እንዳትለቀው። መቅደስህን ያረከሰውን፣ ሴቶችህን የደፈረውን፣ ከብቶችህን የጨፈጨፈውን አረመኔ እንዳትፋታው። በለው።
…ይህችን ስላልኩ ቅር የሚላችሁ ካላችሁ እያየሁ እጨምርላችኋለሁ !! እኔ የምበላውን ሳላይ አልጎርስም። ጎርሼም ሳላላምጥ አልውጥም። በመንጋ ሃሳብ አልመራም። ስድብ፣ ወሬ፣ እዬዬህን አልሰማም። እጠይቃለሁ። አንሳላስላለሁ። ትፈነዳለህ ጧ ትላለህ እንጂ በሃገሬ አንድነትም ላይ፣  በኢትዮጵያ ትንሣኤም ላይ አልደራደርም። ፈቃድ ካገኘ ዐማራ ለድል ሰከንድ አይፈጅበትም። በአፋር ተገኘ ለተባለው ድል “አንበሳው የአፋር ሚሊሻ” ሲል የከረመው መንጋ ለዐማራ ጊዜ ምነው ወገቤን አለ? ድሉን ለመከላከያ ከመከላከያም ለአቢይ አሕመድ ብቻ ጠቅልሎ መስጠት ይሄ የድል ዘረፋ ነው። አስተካክለህ መዝግብ ምድረ ሌባ ሁላ !! ቅኔ እንጂ ታሪክ አይዘረፍም።
• ነውረኞችን፣ በዚህ ሁሉ መቶ ሺዎች መሃል ገብቶ የከረፋ፣ ዓይን የሚያቆሽሽ ስድብ የሚሳደቡትን ወገብ ዛላቸውን ብዬ እቀስፋቸዋለሁ። ሌሎቻችሁ ግን የሚሰማችሁን በጨዋ ደንብ “ተንፒሱ”  …
• ድል ለዐማራ ፋኖ ‼
• ድል ለዐማራ ልዩ ኃይል ‼
• ድል ለዐማራ ሚኒሻ ‼
• ድል ለዐፋር ልዩ ኃይል ‼
• ድል ለአፋር ሚኒሻ ‼
• ድል የኦነጋዊያኑን ሴራ ተቋቁመው ሃገሬን ብለው ለሚዋደቁ ለመከላከያ ሠራዊት አባላት በሙሉ ‼
• ድል ለኢትዮጵያ ‼
Filed in: Amharic